ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ዶናልድ ትራምፕ

ታትሟልከ 9 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዶናልድ ትራምፕ በበርካታ አገራት ላይ የጣሉትን ታሪፍ የተቃወሙ 25 የአሜሪካ ግዛቶች በፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ላይ ክስ መሠረቱ።

የትራምፕ አስተዳደር ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት እንደ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ቻይና እና አውሮፓ ኅብረት ባሉ የአሜሪካ አጋሮች ላይ ከ10 እስከ 12.5 በመቶ የሚደርስ ቀረጥ ጥለዋል። ቀረጡ የተጣለው አገራቱ የጉልበዝ ብዝበዛን በአግባቡ አልተከላከሉም በሚል ነው።

በዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት የሚመሩት ግዛቶች ይህ ውሳኔ “የዘፈቀደ፣ ምክንያት የለሽ እና ከሕግ የተቃረነ” እንደሆነ በመግለጽ ክስ ማቅረባቸውን ቢቢሲ የተመለከተው ሰነድ ያስረዳል።

ለዚህ ክስ ምላሽ የሰጡት የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ኩሽ ዴሳይ፣ አሜሪካ በአገሪቱ በሚገኙ የንግድ ተቋማት ላይ ጫና ለሚያሳድሩ አሰራሮች መፍትሔ ለማበጀት “ሕጋዊ ሥልጣኗን እየተጠቀመች” መሆኑን ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ አክለውም፣ ጉልበት ብዝበዛ ተፈጽሞ የሚመረቱ ዕቃዎች ወደ አገሩ እንዳይገባ መከላከል ያልቻለ ማንኛውም አገር ” ምክንያታዊ እንዳልሆነ ” እና መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።

በአውሮፓውያኑ ሐምሌ ወር ተፈጻሚ መሆን የጀመረው አዲሱ ታሪፍ የተጣለው ጉልበት የሚበዘብዙ አገራትን ዒላማ ለማድረግ በ1974 በወጣ የንግድ ሕግ ላይ በመመስረት ነው።

ወደ አሜሪካ ከሚገቡ ሸቀጦች መካከል 99.4 በመቶ ይህ ቀረጥ እንደሚጣልባቸው የአሜሪካ የንግድ መሥሪያ ቤት ገልጿል።

ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት ይህንን ሕግ በመጠቀም ቻይና ላይ የጣሉት ታሪፍ ወደ ፍርድ ቤት ቢወሰድም ሳይሻር ቀርቷል።

ይህንን የጠቀሱት የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ሕጉን በመመስረት የተጣለው ታሪፍ “በፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን ሕጋዊ መሣሪያ ነበር፤ አሁንም መሆኑን ይቀጥላል” ብለዋል።

የአሜሪካ ግዛቶች የመሠረቱት ክስ፤ የትራምፕ አስተዳደር “ሕገ ወጥ የታሪፍ ሥርዓቱን ለማስቀጠል ሲል የጉልበት ብዝበዛን በምክንያትነት መጠቀም አይችልም” ይላል።

“የንግድ መሥሪያ ቤቱ የጣላቸው ታሪፎች በጣም ሠፊ ከመሆናቸው የተነሳ፤ ራሱ መሥሪያ ቤቱ ያስቀመጣቸውን ግቦች ይቃረናሉ፤ [እርምጃውን] አሳማኝ ለማድረግ ጥቅም ላይ የዋለውን ሕግም መሳለቂያ ያደርጉታል” ሲሉ በክሳቸው አስፍረዋል።

በተጨማሪም ክሱ፤ ከዚህ ቀደም ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2018 ቻይናን ብቻ ዒላማ በማድረግ ሕጉን የተጠቀሙት፣ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት በአገሪቱ ያለውን የጉልበት ብዝበዛ በተመለከተ ለስምንት ወራት ምርመራ ካደረጉ በኋላ መሆኑን ይጠቅሳል።

አሁን በ60 የአሜሪካ አጋሮች ላይ ታሪፍ ለመጣል የተደረገው የሁለት ወራት ምርመራ መሆኑንም በማነጻጸሪያነት አንስተዋል።

በዚህ ሕግ መሠረት “አንድ ኢኮኖሚ ላይ እንኳ ምርመራ አድርጎ ለማጠናቀቅ ከዚህ እጅግ የበለጠ ጊዜ ይወስዳል” ሲሉም ተከራክረዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በኋላ የወሰዷቸውን እርምጃዎች የሚቃወሙ የተለያዩ ክሶች ተከፍተውባቸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ የጣሉት ታሪፍ በአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጓል።