ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አመራር የሆኑት ፖለቲከኞቹ አበባ አካሉ እና ይሳቅ ወልዳይ እንዲሁም ጠበቃ አበራ ንጉስ
የምስሉ መግለጫ,የኢሕአፓ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይሳቅ ወልዳይ (ግራ)፣ ፖለቲከኛ አበበ አካሉ (መሃል) እና ጠበቃ አበራ ንጉስ (ቀኝ)

ታትሟል4 ነሐሴ 2026, 15:48 EAT

ተሻሽሏል ከ 7 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ፖለቲከኞቹ አበበ አካሉ እና ይሳቅ ወልዳይ እንዲሁም ለቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ታዬ ደንደአ ጠበቃ የሆኑት አበራ ንጉስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ሁለቱ ፖለቲከኞች እና የሕግ ባለሙያው “በፌደራል ፖሊስ” አባላት የተያዙት ትናንት ሰኞ ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም. ከጠዋት ጀምሮ በተለያየ ሰዓት እንደሆነ የቤተሰብ ምንጮች፣ ጠበቃ እና የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።

በቅድሚያ የተያዙት ለተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጠበቃ በመሆኑ የሚታወቁት አበራ ንጉስ ናቸው። የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የፌደራል መንግሥት ባቋቋመው በዶ/ር ሙሉ ነጋ የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አበራ፤ ሲታሰሩ የመጀመሪያቸው አይደለም።

በ2016 ዓ.ም. “ጦርነት ይብቃ” በሚል ሊካሄድ ታቅዶ ከነበረው ሠልፍ ጋር በተያያዘም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

“የፌደራል ፖሊስ” አባላት ወደ ጠበቃ አበራ ቤት የመጡት ትናንት ጠዋት አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የቤተሰብ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሰዓቱ አበራ ወደ ሥራ ለመሄድ ዝግጅት ላይ እንደነበሩ የሚናገሩት ምንጩ፤ “በድንገት ነው የመጡት፤ እሱም ለራሱ ተደናግጦ ነበር” ብለዋል። የፌደራል ፖሊስ አባላቱ አበራ “ለምርመራ እንደሚፈለጉ” መናገራቸውንም አስታውሰዋል። እንደ ምንጩ ገለጻ፣ ጉዳዩ ምን እንደሆነ ግን ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።

የሁለት ልጆች አባት የሆነው አበራ የት እንደሚገኝ እስካሁን በትክክል አለመታወቁንም አክለዋል። ዛሬ ማክሰኞ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ለብርበራ ወደ ቤት መጥቶ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል።

የጠበቃ አበራን መታሰር ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቅድሚያ ካጋሩ ሰዎች አንዱ የኢሕአፓ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ይሳቅ ወልዳይ ናቸው።

ይሳቅ፤ ግንቦት ላይ በተካሄደው ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ኢሕአፓን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእጩነት ከቀረቡ በኋላ ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው ይታወሳል። ይሳቅም ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርገዋል።

የጠበቃው አበራ ወዳጅ የሆኑት ይሳቅ ቀን 8 ሰዓት ተኩል በመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት አብርሃም ሃይማኖት በላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይሳቅም የተያዙት በፌደራል ፖሊስ አባላት እንደሆነ የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ምንጭ፤ ትናንት ከሰዓት ይሳቅ ከፖሊስ መኪና ወርደው ሜክሲኮ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሲገቡ መመልከታቸውን አስረድተዋል።

የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት አብርሃም እንደሚናገሩት በአንድ ቀን የታሰሩ ሦስተኛ ሰው የሆኑት የፓርቲው አባል ታዋቂው ፖለቲከኛ አበባ አካሉ ናቸው። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ዋና ጸሐፊ የነበሩት አበበ አካሉ ሐምሌ 2016 ዓ.ም. አንስቶ ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ኢሕአፓን ተቀላቅለዋል።

አበበ “ከመኖሪያ ቤታቸው ውጪ” በሆነ ስፍራ የተያዙት ምሸት ላይ መሆኑን የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት አብርሃም ለቢቢሲ ተናግረዋል። ፖለቲከኛው ከትናንት ምሽት እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ ያሉበት ሳይታወቅ መቆየት ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ስጋት ፈጥሮ እንደነበር ገልጸዋል።

“እስከ ጠዋት ድረስ ቤተሰቡ ከፍተኛ ስጋት ላይ ነበር፤ አሁን ነው በቅርብ [ሰዓት] ወደ ሜክሲኮ ታስሮ እንዳለ ማረጋገጥ የተቻለው” ሲሉ ስደስት ሰዓት ገደማ ላይ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። አበበ ያሉበት ቢታወቅም እስካሁን ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳልተገናኙ አክለዋል።

ጠበቃ አበራም ከቤተሰብ ጋር አለመገናኘታቸውን አንድ ምንጭ ተናግረዋል። ሁለቱ ፖለቲከኞች እና የሕግ ባለሙያው እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ሌላ ምንጭ ገልጸዋል።

ቢቢሲ የሦስቱን ግለሰቦች እስር በተመለከተ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምላሽ ለማግኘት ጥረት አልተሳካም። የፌደራል ፖሊስ ሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ጄይላን አብዲ በአሁኑ ሰዓት አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።