ሸንቁጥ አየለ
———————————————————————
1ኛ- ወያኔዎች ለ25 አመታት በዬሚዲያዉ: በዬመጠጥ ቤቱ: በዬጓዳቸዉ እና በዬ ስርቻዉ የሚለፈልፉት አንድ የምቀኝነት ንግግር አለ::”እኛ ታግለን: እኛ ሞትን ለማን ብለን ነዉ ስልጣኑን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለተቃዋሚ የምናስረክበዉ?” የሚል ነዉ::ይሄም ሲፈታ ምን ማለት ነዉ? በኛ ደም ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ከምትገነባ ኢትዮጵያ በመከራ ለዘመናት እየተሰቃዬች ትኑር ማለት ነዉ::
2ኛ- ቅንጅት በ1997 ዓም ምድር አንቀጥቅጥ ምርጫ አድርጎ ከወያኔ ከ180 ወንበር በላይ (ቁጥሩን አንዳንዶች ከ250 በላይ ነዉ ይላሉ) ማሸነፍ ችሎ ነበር::ያኔም ህብረት የሚባለዉ ድርጅትም ደህና ዉጤት አስመስግቦ ነበር::ህበረት እና ቅንጅት በጋራ ተባብረዉ ፓርላማ ቢገቡ ወያኔን ብዙ ነገር ያለማምዷታል::በሂደትም የስልጣን ሽግሽግ እና የስልጣን ቅብብሎሽ ባህል በኢትዮጵያ እንዲፈጠር መንገዱን ይቀይሳሉ ብሎ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ተስፋ አድርጎ ነበር::የሆነዉ ግን አጀብ የሚያስብል ነበር:: የህብረቱ መሪዎች ተሯሩጠዉ ወደ ሚዲያ ወጥተዉ “የቀኝ ሀይሎች ክንፍ እያንሰራራ ነዉ::የቅንጅት በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የቀኝ ሀይሎች እንደገና በኢትዮጵያ ምድር ስልጣን ሊቆጣጠሩ መዘጋጀታቸዉን ያሳያል::ይሄም ለብሄረሰቦች እኩልነት መልካም ሂደት አይደለም” ብለዉ ቁጭ::
ያኔ የሀገሪቱን የምርጫ እንቅስቃሴ ከመከታተልም በላይ የግል ጋዜጣ ላይ ሀሳቤን አካፍል ስለነበረ “አሁን ከመነቃቀፍ በሂደት የምትገነባዉ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በመተባበር ላይ ቢተኮር ጥሩ ነዉ::ወያኔም በሂደት የሰላማዊ ስልጣን ሽግግር ሂደቱ አስፈሪ እንዳልሆነ እየገባዉ ሲመጣ ስልጣን ለማካፈል ብሎም በሂደት ሀገሪቱን ወደ ዲሞክራሲ ለማሸጋገር ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል:: ስለሆነም የቀኝ የግራ የሚለዉ ከንቱ መካሰስ ቀርቶ የጋራ ትብብር የሚፈጠርበት ቢታሰብበት” የሚል ምክር ብጤ ሰንዝሬ ነበር::ሆኖም የህብረት እና የቅንጅት ጎራ ባልተጨበጠ ስልጣን ላይ መነቋቆር ላይ በጣም ተጠምዶ ነበር::ጽልመታዊ ሀገራዊ የምቀኝነት መንፈስ መሆኑ ነዉ::
3ኛ-አቶ ገብረ ክርስቶስ የተባሉ ጸሀፊ ቅንጅት ከዬት ወዴት የሚል መጽሀፍ ጽፈዋል::በጽሁፉ ዉስጥ እጅግ ብዙ ቀልብ የሚስቡ ታሪኮች አሉ::ከዚሁ ከምቀኝነት ጋር የሚሄድ አንድ ታሪክ ግን ልምዘዝ::ቀስተ ደመና የሚባለዉ ፓርቲ እራሱን የምሁራን ስብስብ አድርጎ የፈረጀ ነበር ይሉናል አቶ ገብረ ክርስቶስ::እናም መኢአድ የሚባለዉ ፓርቲ የነበረዉ ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ያበሳጨዉ ነበር::እንዲሁም ቀስተ ደመና መኢአድን እንደ መሀይሞች ስብስብ ይመለከተዉም ነበር::ስለሆነም የቀስተ ደመና ሰዎች ሁሌም ሲገናኙ መኢአድ የሚባለዉን ድርጅት እንዴት እንደሚዉጡት ይመካከሩ ነበር::
መኢአዶችም ይሄን እዉነት ሲረዱ ገና ቅንጅቱ በግሩ ዳዴ ሳይል በመኢአድ እና በቀስተ ዳመና መሃከል ከፍተኛ ፍጥጫ ነበር ይላሉ::አቶ ገብረ ክርስቶስ::ይታያችሁ በመዋሃድ ላይ ያሉ ፓርቲዎች ገና ምንም ሳይሰሩ እንትናን እንዋጠዉ በሚል መርህ በምቀኝነት ፍልስፍና ሲዳክሩ:: ተዋህደዉ ሊከስሙ እየሰሩ ያሉ ድርጅቶች መሀከል እንዲህ አይነት መንፈስ እንደ ማንበብ ያለ ጽልመታዊ ምቀኘት ከቶም አስገራሚ ነገር ያለ አይመስለኝም::
4ኛ-ይባስ ብሎ ቅንጅቱ እራሱ ጉድ መዞ : ጉድ አንግቦ መጣ::ከቅንጅቱ መሪዎች ዉስጥ “ቅንጅት ከዘጠና ፐርሰንት በላይ አማራ ነዉ::ስለዚህ ቅንጅት መፍረስ አለበት::” የሚል ስንጸ ሀሳብ ይዘዉ የመጡ መሪዎች ተገኙ:: እናም ከሀገር ቤት እስከ ዉጭ ሀገር እንዲሁም ታዋቂ ጋዜጣ ነን የሚሉ የወቅቱ የጥላቻ አርገብጋቢ ጋዜጦችም ይህችኑ መፈክር ትንታኔ መሳይ ነገር ሰሩባት::አንዱ ታዋቂ ነኝ ባይ ጋዜጣ እማ በታዋቂ ጋዘጠኞቹ በኩል አምስት ገጽ ሙሉ ትንታኔ ለቅልቆ ይዞ መጣ::እናም ትንታኔዉ ሲጨመቅ ለቅንጅቱ መፍረስ ዋንዉ ምክንያት በዉጭ ሀገር የዲያስፖራ አማሮች በቅንጅቱ ደጋፊነት መብዛታቸዉ ነዉ ብሎ ቁጭ:: ላልተጨበጠ ስልጣን ልታገል ወይም ላግዘህ ያለን ወገን ለመንቀፍ ጥቂትም ቅር ያለዉ ወገን አልነበረም::ከዚህ ክስ ጀርባ ግን ያዉ የምቀኝነት መፈስ ነዉ የሚቦካዉ::
5ኛ-የኦሮሞ ጽንፈኛ አክራሪ እና እንገነጠላለን ባይ ፖለቲከኞች “ለምንድን ነዉ የምትገነጠሉት? ከምትገነጠሉ የኦሮሞ ህዝብም :ሌላዉ ኢትዮጵያዊም የሚስማማበት እና የሚመቸዉ ዲሞክራሲ የሰፈነበት: የህግ የበላይነት የሚረጋገጥበት ሀገር እንዲገነባ የመሪነቱን ሚና ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችሁ ጋር ለምን አትወስዱም? በተለይም ትልልቅ ቁጥር ያላችሁ የኦሮሞ እና የአማራ ብሄረሰብ አባላት በመነጋገር አንድ የሆነ የሚያግባባ ነገር ብዙ ተጨቃጭቃችሁ እና መክራችሁ ለምን አታመጡም?” ተብለዉ ሲጠዬቁ የሚመልሱት መልስ “ኦሮሚያ ሀብታም ነች::ሰፊ እና ለም መሬት አላት::ሌላዉ ብሄር ከዚህ ለም ነገር ሊጠቀም አይገባዉም::በዚህ መሬት መጠቀም ያለበት ኦሮሞዉ ብቻ ነዉ::” ብለዉ ይመልሳሉ::እነዚህ ኦሮሞ ይገንጠል የሚሉ ፖለቲከኞች የት ነዉ የመሸጉት::ደጉ አሜሪካ::ደጉ አዉሮፓ ነዉ::ደጉ አሜሪካ እና አዉሮፓ አንተ ከኛ ሀብት አትጠቀምም አላላቸዉም::እንዲኖሩ እና ሀብት እንዲያፈሩ መብታቸዉ እንዲጠበቅ እድል ሰጥቷቸዋል::
እነሱ ግን ከኦሮሞ መሬት ሌላዉ እንዳይጠቀም በሚል ምቀኝነት ይባክናሉ::ለዚያዉም ጦርነት የሚወስነዉ የመሬት ስፋት ጉዳይን እንደ ቁምነገር አንግበዉ ለም ለሙን ሁሉ በካርታ ላይ አስፍረዉ በጠባብ ህልም ይዳክራሉ::ታዲያ ሌላ የሚያስደምም ታሪክ አብሮ ተጎትትቶ መጥቶላቸዋል:: አማራን እገነጥላልሁ ያለዉ ሀይልም እነሱ ለም ለም ብለዉ ያሰቧትን መሬት ጥቅልል አድርጎ የአማራ ካርታ ብሎ ሰርቶላቸዋል:: ዉጤቱን የሚወስነዉ ጦርነት ብቻ ይሆናል ማለት ነዉ:: የሶማሌ ተገንጣዮችም ባሌ እና አርሲን ሲብስም እስከ መሃል ሸዋ የህልማቸዉ መተንተኛ አድርገዉ ያቀርቧታል::ሲዳማዉስ ሀገር ሲፈራርስ ምን የማይጠይቀዉ ለም መሬት ይኖረዋልም? ሲዳማዎችም በልባቸዉ የሚቀምሩት ለም መሬት ቀላል አይደለም::አንዱ የምቀኘት መንፈስ የሚወልደዉ መንፈስ የጠነከረ እና የበረታ ነዉ::ምቀኘት ምቀኝነትን ይወልዳል::ቅዱስ ዳዊት ያለምክንያት እንዲህ አላላም ” ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ። መዝ 18:25″
6ኛ-አሁን ደግሞ አማራ መገንጠል አለበት የሚሉ ቡድኖች ተነስተዋል:: ቡድኖች ያልኳቸዉ የተሰባሰቡበት ድርጅት እሁለት ቦታ ተለያይቷል የሚል መረጃ ለህዝብ ስለተለቀቀ ነዉ::አንደኛዉ ቡድን በመግለጫዉ የመገንጠል ሀሳባችንን አንስተናል ብሎ ስላለ ነዉ::ሆኖም የመገንጠል ህሳቤ የሚያራምዱት ቡድኖች አሁንም ያችኑ መጀመሪያ ጀምሮ ሲሏት የነበረችዉን ሀሳባቸዉን አልለቀቋትም:: “ለምን አማራ ይገነጠላል? አማራ መገንጠል አያስፈልገዉም:: አማራ ማድረግ ያለበት እራሱን አጠንክሮ ወያኔን ከሌሎች ጋር በመተባበር በሀይል ከኢትዮጵያ አስወግዶ ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ነዉ::” ተብለዉ ሲመከሩ የሚመልሱት መልስ ያስገርማል::”አማራ ለማንም አይሞትም::አማራ የሚሞተዉ ለራሱ ብቻ ነዉ::አማራ ምን በወጣዉ ነዉ ለቀሪዉ ኢትዮጵያዊ ህዝብ ዲሞክራሲ የሚታገለዉ?” ብለዉ ቁጭ::ይሄም መራራ ምቀኘት ነዉ::
አማራ ታግሎ ለራሱም ለኢትዮጵዉያን የምትመች ሀገር ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ቢፈጥር ያኮራል እንጅ አያበሳጭም:;ግን የምቀኝነት መንፈስ ማለቂያ የለዉም እና እንደ ወያኔዎቹ አማራ ታግሎ ምን በወጣዉ ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊት ያደርጋል ብለዉ ይሞግታሉ:: ወያኔ ምን አለ? ትግሬ ታግሎ ኢትዮጵያን ምን በወጣዉ ዲሞክራሲያዊ ያደርጋል ብሎ ነዉ የሚሞግተዉ::ትግሬ ታግሎ ትግሬ ብቻዉን ኢትዮጵያን ግጦ ይጨርሳት ብሎ ነዉ ወያኔ በጥጋብ እስኪፈነዳ በእብሪት ተወጥሮ ሀገር የሚያምሰዉ::ይሄም መራራ ምቀኝነት ነዉ::
7ኛ-ባለፈዉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ ሲመሰረት ኮሌኔል ዳዊት ወልደጊዮርጊስ የተናገሩት ንግግርም ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብሮ የሚሄድ ነዉ:: “ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ የታፈሩ እና የተከበሩ በድርጅቶች መሃከል የጋራ ንቅናቄ እንዲፈጠር ብዙ የጣሩ” ብዬ በልቤ አወድሼ ሳልጨርስ ያችዉ የምቀኝነት መንፈስ ተመዛ እዚያዉ አደባባይ ላይ ዱብ አለች::”አማራ የተደራጀ እና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለዉ ድርጅት ስለሌለዉ ለጊዜዉ በአንድ ሰዉ እንዲወከል አድርገናል:: አሁን ባለዉ ተጨባጭ ሁኔታ የአማራ ህዝብ አደራጅቶ ይወክለናል ብሎ ወደዚህ የላከልን ድርጅት ስለሌለ አማራዉ በአንድ ሰዉ እንዲወከል ግድ ሆኗል:: እንግዲህ እኛ ወደፊት ለአማራዉ ድርጅት እንፈጥርለታለን::” ብለዉ የቀድሞ የመላዉ አማራ ህዝብ ድርጅት ወጣቶች መሪ የነበረዉን ሰዉ ለህዝቡ አስተዋወቁ::አጀብ ሸዋ ! አልኩ በልቤ:: እዚያ የተደረደሩትን ድርጅቶች ህዝብ መርጦ እና ወክሎ ነዉ ማለት ነዉ የላካቸዉ? ለራሴ ጥያቄ አነሳሁ:: ይሄ መልሱ ሀሰት መሆኑን ሁሉም ያዉቃል:: እናም በልቤ እንዲህ አልኩ” አይ የሀበሻ ክፋት እና ተንኮል? መቼ ነዉ ማለቂያሽ?”::እንዲህ ብዬ የጠዬቅሁት ያለ ምክንያት አይደለም::
የአማራ ድርጅት ነን ብለዉ ከአምስት በላይ ድርጅቶች እያሉ ሁሉንም የሉም ብሎ በመደምሰስ የአማራ ድርጅት ስለሌለ ብሎ ማወጅ ክፋት እና ምቀኝት ብሎም ሀሰት እና ሸፍጥ መሆኑ ወዲያዉ ፍንትዉ ስላለልኝ ነዉ:: ቢያንስ በሀሳብ “ለጊዜዉ ስላልተስማማን ነዉ : ድርድር አድርገን የአማራ ድርጅቶችንም እናቅፋለን” ብሎ በአክብሮት መግለጽ ሲገባ እየታገልን ነዉ ያሚሉ ድርጅቶችን አንድም የሉ ብሎ መደምሰስ አስደናቂ ሸፍጥ ነዉ:: በዚያችዉ ቅጽበትም በአማራ ድርጅቶች እና በግንቦት ሰባት መሃከል መራራ ጥላቻ እንደሚወለድ ገምቼ ነበር:: እና ዉጤቱ ምን ሆነ? አሁን በግንቦት ሰባት እና የላችሁም በተባሉት የአማራ ድርጅቶች መሃከል መራራ የመጠላለፍ ፍልሚያ እየተደረገ ነዉ::ሆኖም ቁጭ ብለዉ ይሄን ነገር ለመነጋገር እና ለመፍታት የሚደረግ ጥረት አይታይም::የኢትዮጵያ ህዝብም በዚህ መሰሉ የመጠላለፍ እና የመነቋቆር ሂደት ልቡ በየቀኑ ዝቅ ይላል::ህዝቡ አንድ ነገር ይፈልጋል::ወያኔ ወድቃ ማዬት:: አንዲት ዲሞክራሲያዊት የበለጸገች ኢትዮጵያ ተፈጥራ ማዬት::
የኢትዮጵያ ፖለቲካ የክፋት ጽልመት ሂደቱ ግን ይቀጥላል::እንዲህ አይነት ጽልመታዊ የክፋት መንፈሶች ግን ፈሪ እና አድር ባይ ናቸዉ እና አንድ አንባ ገነን ሰባብሮ ይጥላቸዋል::ኢትዮጵያ ግን ወደ ዲሞክራሲ እንዳትሸጋገር ብዙ መጓተት እና መጎተት እየደረሰባት ነዉ:: ምናልባትም ሀገሪቱ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ሳይሆን ወደ ሌላ ወደ ክፉ አንባ ገነን እጅ ልትወድቅ ትችላላች:: ወይም ወደ ክፋ ሁኔታ ዉስጥ ገብታ ልትቀረቀር ትችላለች:: በፖለቲከኞች ጥልመታዊ የምቀኘት መንፈስ የተነሳ:: ምክንያቱም ፖለቲከኞች በስራቸዉ ጥመት እና ክፋት ሲበዛበት እግዚአብሄርም ስራቸዉን አያከናዉንላቸዉም:: እግዚአብሄር ቅንነቱ ከቅኖች ጋር ብቻ ነዉ::ጠማሞች ላይ ግን ያዉ መጽሀፍ እንዳለዉ ነዉ:: ነገሮች የሚከናወኑት ” እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ:: ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ። መዝ 18:25″ እንዳለዉ ነዉና::
ፖለቲከኞች ሆይ እባካችሁ ሌላዉን ጉሳንጉስ እና ኩሳንኩስ ተንኮል እና ምቀኝነት ተዉት::እግዚአብሄር ስራችሁን እንዲያቀናዉ : ይህችን መከረኛ ሀገርም እንድትታደጓት ለአንድ እዉነት ብቻ በቅንነት ስሩ::አንዲት ዲሞክራሲያዊት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የምቀኝነት መንፈስ ካጸለመዉ ህሊናችሁ ወደ ብርሃናማዉ ሀገራዊ የፍቅር መንፈስ ዞር በሉ::
Source – Ethiopian Media Forum (EMF)