December 5, 2016 
አቶ አሰፋ ጫቦ
በገዛ ዳቦዬ…
አስፋ ጫቦ Dallas Texas USA
ዛሬ በሌላ ሰበብ በጨረፍታም ቢሆን ለማየትና ለማሳየት የምሞክረው አሜሪካ ኗሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በንግዱ ዘረፍ ተሳታፊነት ነው።ዲያስፖራ አላልኩም!ቃሉን ስለማልወደው ነው! ሌላ ቀን እንወያይበታለን!
ገና አሜሪካ እንደመጣሁ 1984(1992) ፣በፊት የሚያውቁኝና አዲስ ያወቁኝም አሜሪካኖች ዋሺንግቶን ዲ ሲ ፤ጆርጅ ታዎን(Goergetown) በሚባለው የሀብታሞች መንደር፤አበሻ ምግብ ቤት ምሳ ጋበዙኝ።በጫወታችን መካከል በእንግድነቴ በዞርኩበት ስለኢትዮጵያውያን የታዘብኩትንና ያለኝን አስተያየት ሰጠህ። ወረዱብኝ! በተለይም ዲን ጀምስ ፖል(James Paul) ወረዱብኝ።”አንደኛ እንደህግ ባለሙያ አልተናገርክም! በቂ መስረጃ ሳትይዝ ወደድምዳሜ ተሸጋገርክ! ሁለተኛምና እዚህ ያሉትን ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያውያን ባህርይ ልብ አላልክም።ኢትዮጵያዊው በተፈጥሮ ልታይ ልታይ የማይል (Low Profile)ሕዝብ ነው። እንጅ ለመሆኑ ከአፍሪቃ የትኛው አገር ነው ቤተክርስቲያናት፤ መስጊዶች፤ የባህል ማእከሎች(Community Centers) ፤የምግብና ሌሎች አገራቸውን ነክ የሆነ ነገር ያዘጋጄና ያደራጀ በከፍተኛ ሥልጣንና በየዪኒቨርስቲዎቹ …”ይቅርታ ብጤ ጠይቄ ተለያየን። ከዚያ ወዲህ የበለጠ ልብ እንድል ረድቶኛል
የዛሬ ወር ገደማ ይመስለኛል የትራምፕን የአሜሪካንን ፕሬዚደንት ምርጫ ማሸነፍ ሰበብ ሆኖ “በማግስቱ!” የሚል ጽፌ ነበር። ማሕበራዊ ገጽ (Facebook)ና ድህረገጻት (Online) ሁሉ ለጥፌው ነበር። አዲሳባ አዲስ አድማስም ላይ ወቷል።እንዳሉኝ ከሆነ ቁጥር ስፍር ያሌለው ሰው ማንበበ፣ አስተያየት መስጠት ብቻ ሳይሆን አዳርስውታልም (Share)።ደስ አለኝ!” የውለዱትን ሲስሙለት የደገሱትን ሲበሉለት!” እንደሚባለው መሆኑ ነው።፣”በማግስቱ!” መዝጊያው ላይ አንዳንድ ስለ አሜሪካን የምታዘባቸውን አልፎ አልፎ ማቅረብ እሞክራለህ ብዬ ነበር። ይኸ ያ መሆኑ ነው! የትራምፕን መመረጥ ጥቁር አሜሪካውያን Afirican Americans) እንዴት እንዳዩት በጨረፍታ ለማየትና ለማሳየት ሙከራ መሆኑ ነው ።
የዛሬ አመት ይሁን እንዲያ ሌላ የጻፍኩትም ነበረኝ። ሙሉ ለሙሉ አላስታውሰውም። የማስታውሰውን ያክል ካለሁበት ከዳላስ ወደዋሽንግቶን ዲ.ስ ለመብረር ዳላስ Love Field Airport አውሮላን ማረፊያ ሄደኩ። ፈታሹ የያዝኩትን ቡና “ድፋው!” አለኝና ደፋሁት። የሚጠጣ ነገር የታሸገም ቢሆን አውሮፕላን ይዞ መውጣት ከተከለከለ ቆይቷል። ለወዳጆቼ ይሆናል ብዬ የገዛሁትን ዊስኪና የወይን ጠጅ “ወይ ጠጣው ወይድፋው!”አለኝ።ሰጠሁት እንጅ አልደፋትም! የጸጥታው ጉዳይ ነው። በዛሬው ዘመን ፈንጂ ምን ማን መስሎ እንደሚመጣ አይታውቅምና! “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ!” የሚሉት አይነት መሆኑ ነው።
እኔ አውሮላን መብረርረ ይስለቸኛል! ረዥም ሰአታት ቁጭ የሚያሰኝም በረራ አውቃለሁ። ከዳላስ ዋሽንግቶን ዲ.ሲ 3 ሰአት ከሩብ ነው። ቢሆንም የሰለቸኛልና ጋዜጦች፤መጽሐፍት ቡና ይዤ ተሳፍሬ አባብለዋለሁ። አውሮላንኑ ላይ የሚሰጠውን ነጻ ቡናና ቁራሳ- ቁርስ(Snack) አለወደውም።የለበጣና የይስሙላ ይመስለኛልና!የአሁኑን አላውቅም እንጅ ለአለም አቀፍ በረራ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የጀርመን አየር መንገድ የመስለ የለም።የአገር ውስጥ በረራ ሁሌም፤የትም የማስተናገዱ ደረጃው ዝቅ ይላል።
ስለዚህም ቡናና ቁርሳ- ቁርስ(Snack) ለመግዛት አውሮፕላን ማረፈፊያ አዳርሽ(Terminal) ውስጥ ወዲያ ወዲህ ስል ብዙ ኢትዮጵያዊያንን አየሁ።አሁን አቡነ ባርናባስ የሆኑት አባ ወለደትናሳኤ አንዴ ሎስ አንጀለስ (Los Angeles) ጫዋታ ላይ “አቶ አስፋ እባክዎ ይተውኝ! አበሻን እንኳንስ ፊቱን አይቼ ከማጅራቱም ቢሆን እለየላሁ!” ያሉኝ አስታወሰኝ። አንዳንድ ኢትዮጵያውያ እንግሊዚኛውን በቅጡ የማይችሉ በአማርኛ ሲያናግሯቸው በእንግሊዚኛ የሚመልሱትን አንስተን ስንጫወት ነበር። አሁን ይህንን የነሳሁት ኢትዮጵያዊውንና ብዛቱን ለመለየት ችግር አልነበረብኝም ለማለት ነው።
ቡና ፍለጋ የገባሁበት አንዲት ወደወጣትነት የምታደላ ልጅ አገኘሁና “አንቺ ይህንን አየር ማረፊያ ተቆጣጠርነው አይደለም እንዴ!” አልኳት። ይህንን እዚህ አሜሪካኖቹ “ትንሽ ጫዋታ”(Small Talk) ብለው የሚጠሩት አይነት መሆኑ ነው። በአብዛኛው ፈርንጆቹ ዘው ብለው ወደፍሬ ሐሳብና ወደሚያከራክርና ወደሚያወያይ ጉዳይ አይገቡም። ገራ ገሩንና የማያሻማው ላይ ያተኩራሉ። ብዙ ጊዜ የ አየር ጠባይ ተዘውትሮ የዚህ ደንበኛና መደበኛ ርእስ ወይም ስፖርት ነው። አየሩ ባለቤት የሌለው የሁሉም ንብረት ነውና!
ኢትዮጵያዊው፤በአብዛኛው፤ከሰላምታ በኋላ፣” ምን የአገራችን ነገርኮ…!” ብሎ ይጀመራል። ቢያውቅህም! በቅጡ ባያውቅህም!ዛሬ ጥዋት ተገናኝታችህ ከሆነም! “የአገር ፍቅር!” መሆኑ መስለኝ። ቢሆንም ይህን የመሰለ ጉዳይ ቦታ ቦታና ወቅትም የሚፈልግ ይመስለኛል። “ከምንና ስለምን፣ ከማንስ ጋር!” የሚለው አስቀድሞ የሚታወቅና ካደረው ከሰነበተው ቢጀመር የሚሻል ይመስለኛል። ያለበለዚያ የሚገባውን ክብደት ያጣና የለበጣ ያሰመለዋል ብዬ እፈራለህ።የሚያወሩትን ማጣትም ሳይሆን ይቀራል? “ዝም አይነቅዝም !”ጥሩ አማራጭ ይመሰለኛል።መስመር የለቀቅህ መሰለኝ!የኔነገር!
ታዲያ“አንቺ ይህንን አየር ማረፊያ ተቆጣጠርነው አይደለም እንዴ፦” ያልኳት ልጅ “አይ! ገና ነው! ገና ነው!” አለችኝ። ኮስተርና ፍርጥም ብላ!ጥያቄየን እንደዋዛና ለስላምታ በር መከፍቻ እንዳቀርብኩት አልቆጠርችውም። የምታየውንና የሚታያትን እውነት የተናገረች መስለኝ። ከዚህ ተነሰቼ አንድ ለማስረጃነት የሚሆን አቀርባለሁ።