መስፍን ወልደ ማርያም
ኅዳር 2009
በ2004 ዓ.ም. ‹‹አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ›› በሚል ርእስ አነስ ያለ መጽሐፍ አሳትሜ ነበር፤ መቼም የወያኔ መሪዎች ሁሉ አዋቂዎች ናቸውና አንብበውታል ብዬ አልገምትም፤ አወቂ የተባሉ አማካሪዎቻቸውም ለማንበብ ጊዜ ያገኙ አይመስለኝም፤ አንዳንድ ንዑሳን ሎሌዎች በፌስቡክ ላይ የዘላበዱ ይመስለኛል፤ በዚያን ጊዜ ያንዣበበው አደጋ ዛሬ ቀርቧል፤ የቀይ ባሕርን መሻገሩ እየተነገረ ነው፡፡
እንደምንሰማው ኤርትራ ከግብጽ ጋር ተቀራረበች፤ አንድ በሉ! ጂቡቲ ከሳኡዲ አረብያ ጋር ተቃቀፈች፤ ሁለት በሉ! ሱዳን በእርስ-በርስ ውጊያ ትተራመሳለች፤ ሦስት በሉ! አሜሪካ የእጅ-አዙር ዱላዎቿን አዘጋጀች፤ አራት በሉ! ኢትዮጵያ በውስጥ ትርምስ ከህልውናዋ ጋር ትታገላለች፤ አምስት በሉ! ሶማልያ በአልኢትሀድ ታፍናለች፤ ስድስት በሉ! ኬንያ በወላፈኑ እየተገረፈ ነው፡፡
አሜሪካ ‹‹ኮሚዩኒስት›› ደርግን ለመጣል ኤርትራን አስገነጠለ፤ ወያኔን አነገሠ! ፖል ሄንዜ ቢኖር ምስክር ያሆነኝ ነበር፤ በዚ መንገድ ሄዶ አሜሪካ እንደማያሸንፍ ነግሬው ነበር፤ ከዚያም በላይ ‹‹የፈለገው ቢሆን ወያኔ ኢትዮጵያዊ መሆኑን አትርሳ!›› ብዬው ነበር፤ አሁን ላይ ሆኜ ሳየው የተናገርሁት ስሕተት አለበት፤ ስሕተቱ ውጤቱ ላይ ሳይሆን ምክንያቱ ላይ ነው፤ ግን በሌላ የኢትዮጵያዊ ስሜት እካሣለሁ፤ እአአ በ1991 ከአንድ የአሜሪካ የደኅንነት አማካሪ ጋር ሰለኤርትራ ስንነጋገር ‹‹ኤርትራን ተዋት! በጣራ ላይ እንደተንጠለጠለች ድመት ናት፤›› ሲለኝ ተቆጥቼ አሁንም የምትቀልደው በኢትዮጵያ ነው፤ በዚህም ምክንያት ለኤርትራ በተመኘኸው መከራ እኔ አልደሰትም፤ ብዬው ነበር፤ ዛሬ ስጽፍ የማልወድደውን ነገር እየደጋገምሁ ነው፤ ሁለቱም አሜሪካውያን ምስክሮቼ በሕይወት የሉም፡፡
ለማናቸውም እኔ የተናገርሁትን መቀበልና አለመቀበል ዋጋ የለውም፤ ነገር ግን በዙሪያችን የሚካሄደውን ሁሉ እያዩ መስተካከል ያለበትን በጊዜ ማስተካከል ከባሰ አደጋና መከራ ያድነናል ብዬ አምናለሁ፤ በተውሶ ጉልበት መተማመን አያዋጣም፤ ዱሮም አላዋጣም፡፡
መስፍን ወልደ ማርያም