Wednesday, 07 December 2016 14:23

·        ኤርትራ ፖለቲካዊ ትርጉም ሰጥታዋለች

 የኳታር አየር መንገድ ካለፈው እሁድ ጀምሮ ከዶሃ አስመራ የነበረውን በረራ አቋርጧል። አየር መንገዱ በድረገፁ ባሰራጨው ዘገባ ደንበኞቹ ቀድመው የገዙትን ትኬት የሚመልስ መሆኑን አስታውቋል። ቀሪ ስራዎችንም  አጠቃሎ ለመፈፀም እስከ መጪው የካቲት ወር ድረስ የአስመራ ቢሮው ክፍት ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን አመልክቷል። አየር መንገዱ የመጨረሻ በረራውን ያደረገው ባለፈው እሁድ QR1444 በተባለው አውሮፕላን ከአስመራ ዶሃ ባደረገው ጉዞ ነው።

የኳታር አየር መንገድ ለምን የኤርትራ በረራውን እንዳቋረጠ የሰጠው ምክንያት ባይኖርም ኤርትራ ግን ፖለቲካዊ ትርጉም ሰጥታዋለች። መረጃውን ያሰራጨው ሱዳን ትሪብዩን ጉዳዩን አስመልክቶ ባሰራጨው ዘገባ ኳታር በድንበር ግጭት ውስጥ ያሉትን ኤርትራንና ጂቡቲን ስታደራድር የቆየች መሆኗን ገልጿል። የኳታር አየር መንገድ ከዶሃ አስመራ በረራ የጀመረው እ.ኤ.አ. በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም ነበር። ከዚያው ከዶሃ የጂቡቲ በረራውን የጀመረው ደግሞ በዚያው ዓመት መጋቢት ወር ነበር። እንደዘገባው “ኳታር የአስመራ ዶሃ በረራዋን ባቋረጠችበት ሁኔታ የዶሀ ጂቡቲው በረራዋን መቀጠሏ ሁለቱን አገሮች በማደራደር ሂደት ውስጥ  ወገንተኝነት እያሳየች መሆኗን የሚገልፅ ነው” ስትል አስመራ ቅሬታዋን አሰምታለች።  በረራው በድንገት ተቋርጦ በአፋጣኝ ትኬት እስከመመለስ መደረሱ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል።

ኤርትራ የአየር መንገድ በረራ መቋረጥ ሲገጥማት ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። በዓለማችን ግዙፍ ከሚባሉት አየር መንገዶች ውስጥ አንዱ የሆነው የሉፍታንዛ አየር መንገድ ከፍራንክፈርት በጂዳ በኩል ወደ አስመራ የነበረውን በረራ አትራፊ አይደለም በማለት እ.ኤ.አ በ2013 እንዲቆም አድርጓል። ከሰንዓ አስመራ ቀጥታ በረራ የነበረው የየመን አየር መንገድ ሀገሪቱ ከገባችበት የእርስ በእርስ ጦርነት ጋር በተያያዘ በረራውን ለማቋረጥ ተገዷል። ሱዳን በአሜሪካ ማዕቀብ ከተጣለባት ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን ሙሉ በሙሉ የቦይንግ ኩባንያ ጥገኛ የሆነው የሀገሪቱ አየር መንገድ መለዋወጫዎችን፣ አዳዲስ አውሮፕላኖችንና የጥገና ባለሙያዎችን ማግኘት ባለመቻሉ ከገበያ መውጣት ግድ ሆኖበታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከአስመራ ጋር የነበረው የቀጥታ በረራ በነበረበት መቀጠል ሳይችል ቀርቷል። በአሁኑ ሰዓት ከአስመራ የቀጥታ በረራ አገልግሎት የሚሰጡ ሶስት ዋና ዋና አየር መንገዶች ቀርተዋል። እነዚህም የግብፅ አየር መንገድ፣ፍላይ ዱባይ እና የቱርክ አየር መንገድ ናቸው።ኤርትራ የራሷን አየር መንገድ ለማቋቋም ያደረገቻቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች ስኬትን ሳያገኙ ቀርተዋል።

የኤርትራ መንግስት የውጭ ዜጎች ከአስመራ ከተማ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ የሚጓዙ ከሆነ አስቀድመው ከሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያቤት ፈቃድ ማግኘት ያለበት መሆኑን የሚደነግግ መመሪያ ካወጣ ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን ይህም በሀገሪቱ ያለውን የውጭ ዜጎች እንቅስቃሴ ገትቶታል። ይህ ብቻ ሳይሆን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችበት የድንበር ግጭት ከአስር ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም ምንም አይነት መፍትሄ አለማግኘቱ ከሁለቱ ሀገራት ድንበር አቅራቢያ ያሉትን ከተሞችና አካባቢዎች የስጋት ቀጠና ሆነው እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል። በዚህ በኩል ከኢትዮጵያ በብዙ እጥፍ አነስተኛ የቆዳ ስፋት ያላት ኤርትራ በብዙ ተጎጂ ሆናለች።