ዶ/ር ተክሉ አባተ

YeAmara tegadelo

ከጥቂት ወራት ወዲህ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረ ከሳቡ ወሳኝ ጉዳዮች ውስጥ የአማራ መደራጀት ዋናው ሳይሆን አልቀረም። ይህን ጉዳይ በተመለከተ በርካታ ጽሑፎችና ንግግሮች ተደርገዋል። አማራው እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነገድ መደራጀትና ራሱን ከተቀነባበረ ጥፋት ማዳን እንዳለበት የሚሞግቱ በርካቶች ናቸው። አሳማኝ የመከራከሪያ ነጥቦችንም አንስተዋል። በአንጻሩ ደግሞ አማራው በኢትዮጵያዊነት እንጅ በነገዱ መታገል መዘዙ ብዙ እንደሆነ ያስጠነቀቁ አሉ። ከሁለቱም ወገኖች አንዳንዶች ነጥቦቻቸውን በምክንያት ወይም በመረጃና በማስረጃ መደገፍ ሲሳናቸው አፍ አውጥተው ሌሎች ጸሐፍትን ሲሳደቡና ”ወያኔ ነህ”፣ ”ፀረ አማራ ነህ” እያሉ ሲያሸማቅቁ ታይተዋል። ከነዚህ ከተሳዳቢዎችና ከአሸማቃቂዎች በስተቀር ለሌሎች ጸሐፍት ከፍ ያለ አክብሮትና ምሥጋና አቀርባለሁ። መሠረት ያላቸው ውይይቶችና ክርክሮች ለሚደረገው ትግል ግልጽነትንና መናበብን ይፈጥራሉና!

እኔም በበኩሌ ኢትዮጵያዊነትን መርሁና የስብዕናው አካል እስካደረገ ድረስ አማራው በነገዱ መደራጀት መብቱ እንደሆነ ለአማራውም ለሌላውም ኢትዮጵያዊ እንደሚጠቅምም ”የወቅቱ ፖለቲካዊ አሰላለፍና ፋይዳው” በሚል ርዕስ ሞግቻለሁ (ጽሑፉ Ethiomedia, Zehabesha, እና ESADF ላይ ወጥቶ ነበር)። ውድ አንባቢዎቼም ገንቢና መካሪ አስተያየቶችን ልከውልኛል። ዳሩ ግን በጽሑፌ ውስጥ ያልተካተቱ ግን ብዥታ የፈጠሩ ነጥቦች ተነስተዋል። እነዚህን ጉዳዮች ለማጥራትና ከፍ ያለ መናበብ ለመፍጠር ይህችን ጽሑፍ ሳበረክት በደስታ ነው። የአማራውን ተጋድሎ ለመደገፍ እንደ መስፈርት ሊያገለግሉ የሚችሉ ነጥቦችን አንስቻለሁ። በዚች ጽሑፍ የተነሱትና የተብራሩት ጉዳዮች የወቅቱን የአማራውን ተጋድሎ ለሚመሩና ለሚደግፉ እንዲሁም ለሌላውም ውድ ኢትዮጵያዊ ወገኔ እንደሚበጁ አምናለሁ። ጽሑፉ የተንዛዛና አሰልቺ እንዳይሆን በጥያቄና መልስ መልኩ ተዘጋጅቷ።

አማራ ከኢትዮጵያ ሊገነጠል ይችላል?

ለአማራው ማኅበረሰብ አማራነትና ኢትዮጵያዊነት የስብዕናው ምሰሶዎችና መሠረቶች ናቸው። አንዱ ከሌላው ተለይቶ አይታይም። አማራ ተገንጥሎ የራሱን መንግሥት መመስረት ለአንድ ሰከንድ እንኳ የሚታሰብ አይደለም። በመሆኑም አማራነትን ከኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያዊነትን ከአማራነት ለመለየት መሞከር ጸጉር ስንጠቃ ነው።

በርግጥ ቁጥራቸው የማይታወቁ ግን ጥቂት የሚባሉ ወገኖቻችን አማራው እስከ መገንጠል የሚያደርስ ትግል ውስጥ እንዲገባ የሚያምኑ አሉ። ምናልባት ከዚህ አቋም ያደረሳቸው አማራው ላይ የደረሰውና በመድረስ ላይ ያለው የግፍ ብዛት ሊሆን ይችላል። ይህ እንኳን ባይሆን ሃሳባቸውን በነጻነት የማንሸራሸር መብታቸው ግን መከበር አለበት።

ባጠቃላይ ሲታይ አማራው ኢትዮጵያዊነትን እንዲረሳ ማሳመን ማለት ህወሓትን ኢትዮጵያዊነትን በሙሉ ልብ እንዲቀበል ማሳመንን ያህል የከበደ ነው። ይህ መረጃም ማስረጃም ከማያስፈልጋቸው እውነታዎች ውስጥ አንዱ ነው። የሚታይ የሚነበብ የሚዳሰስ ነው። በመሆኑም የአማራውን ትግል የሚደግፍ ወይም ለመደገፍ ያሰበ ሁሉ ኢትዮጵያዊነት መነሻም መድረሻም መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።

ትግል በአማራነት እስከ መቼ ይቀጥላል?

ይህም ሆኖ የአማራው ተደራጅቶ መታገል የሚደገፈው ወይም የሚያስፈልገው ኢትዮጵያ ውስጥ አስተማማኝ፣ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊና ከሕግ በታች የሆነ መንግሥት ተቋቁሞ ሁሉንም ነገዶች በእኩልነትና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ማስተናገድ እስኪጀምር ድረስ ቢሆን የተመረጠ ነው። በአማራነት መደራጀት በራሱ ችግር ከሆነ ችግሩን የፈጠረው ያለው መንግሥት ነው። አማራው ከደረሰበት ብርቱ ችግር በመነሳት በፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ከተሞከረው ፈር ቀዳጅ እንቅስቃሴ ውጭ ያደረገው መደራጀት የለም። 25 ዓመት ሙሉ በአማራነት ላለመደራጀት ወስኖ የኖረ ማኅበረሰብ ነው። አሁን ግን ምርጫው የመኖርና ያለመኖር ስለሆነ እየተደራጀ ነው። ሆኖም ግን ይህ ሁሉ ችግር ከተፈታና አማራውና ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ‘ቀና ብለው መሄድ’ ከቻሉ በነገድ መደራጀት አያስፈልግም። ያን ጊዜ ሁሌም እንደተለመደው በአስተሳሰብ ላይ ብቻ የተመሠረት ፖለቲካዊ ሱታፌ በቂ ይሆናል። ሌሎችም በነገድ የተደራጁ ድርጅቶች ተመሳሳይ አቋም መያዝ ያስፈልጋቸዋል። ፕሮፌሰር አሥራት እንዳሰመሩበት የአማራ ተጋድሎ ለሁሉም ወገን እኩል የሆነ አርቆ አሳቢ መንግሥት እስኪመሰረት ድረስ ነው።

የአማራው ተጋድሎና የሌሎች ኢትዮጵያዊ ነገዶች ተጋድሎ እንዴት ይዛመዳሉ?

የአማራው ተጋድሎ ያስፈለገው የራሱን ከዚያም የሌሎችን ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ መብትና ነጻነት እውን ለማድረግ ነው። የሌሎችንም ኢትዮጵያዊያን ነገዶች መብትና ታሪካዊ ተሳትፎ ወይም ድርሻ እውቅናን ይሰጣል። እጅግ ተባብሮም ይሠራል። መገንጠልም ይሁን አንድነት የሚወሰነው በአማራው ወይም በተወሰኑ አካላት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በመሆኑም የሌሎችን ነገዶች ትግል የአማራው ተጋድሎ ማበረታታት መደገፍ ያስፈልገዋል። መሬት ላይ ያለው ነባራዊው ሁኔታ የሚያሳየውም ይህን ነው። አማራው፣ ኦሮሞውና ደቡቡ በትግላቸው አንዱ ሌላውን ሲያበረታቱ ሲመሰጋገኑ እያየን ነው። ይህ መንፈስ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ግን ወሳኝነት አለው።

የአማራው ተጋድሎ ከአንድነት ኃይሉ ጋር እንዴት ይዛመዳል?

በመጀመሪያ ደረጃ አንድነት ወይም ኢትዮጵያዊነት የሚል ስም ለተወሰኑ አካላት ብቻ መስጠት ተንኮል ነው። ሌሎች በነገድ የተደራጁት ሁሉ አንድነትን ወይም ኢትዮጵያዊነትን እንደማይቀበሉ የሚያመለክት ነውና! አማራነትና አንድነት ወይም ኢትዮጵያዊነት መለያየት የማይችሉ የስብዕና ክፍሎች እንደሆኑ ከላይ ተጠቁሟል። በአፋር፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ፣ በኦሮሞ ወዘተ ነገዶች ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችም አንድነትን ወይም ኢትዮጵያዊነትን መዳረሻቸው ያደረጉ አሉ። በርግጥ ጥቂቶች የመገንጠል እሳቤ ሊኖራቸው ይችል ይሆናል።

ለማንኛውም የአማራው ተጋድሎ ከሌሎች ነጻነት ከሚናፍቃቸው ወገኖች ሁሉ ጋር ተናቦ መሥራት ይኖርበታል። የአማራውን ተጋድሎ አስፈላጊነት ለማሳየት በኢትዮጵያዊነት ወይም በአንድነት ስም የሚንቀሳቀሱ አካላትን መሞገት፣ ማሳጣት፣ መታገል፣ አይጠበቅበትም። የአንድነት ኃይሉም በምንም መልኩ የአማራውን ተጋድሎ ማሳነስ፣ ማኮሰስ፣ ማፈን፣ መግታት ወዘተ አይጠበቅበትም። አንዱ ለሌላው እጅግ አስፈላጊ ወገኑ እንደሆነ ማመንና በሚገርም መናበብና መተባበር መሥራት አለባቸው።

ሥልጣንንና የግል ጥቅምን በመጠየፍ አንዱ የሌላው ግብዓትና ደጀን እየሆነ ትግሉን ማፋፋም ያዋጣዋል። አንዱ ሌላውን እንደ ተፎካካሪ ተቀናቃኝ መመልከት የለበትም። የአንድነት ኃይሉን የሚመሩ ወይም የሚደግፉ አማራ ኢትዮጵያዊያን አሉ። ያሉበትን ድርጅት እየተው የግድ የአማራውን ተጋድሎ መቀላቀል አይጠበቅባቸውም። በያሉበት ሆነው አቅም የፈቀደላቸውን ማበርከት ይችላሉ። ይህ አልሆን ብሎ በሁለቱ ወገኖች መካከል ክርክር ጭቅጭቅ ከቀጠለ ግን ሕዝቡ የራሱን እርምጃ ይወስዳል እየወሰደም ነው።

የአማራው ጠላት ማን ነው?

በመሠረቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ድህነት፣ ዘረኝነት፣ አምባገነንነት እና የመሳሰለው ሁሉ ነው። ይህን ደግሞ በአካል የገለጠው የተረጎመውም አሁን ያለው መንግሥት ነው። በመሆኑም መንግሥትን እንደ ጠላት መቁጠር ከተጀመረ ከርሟል። ለአማራውም ጠላቱ ይህው ነው። የህወሓት ከፍተኛ አመራር ከመመስረቻ ማኒፌስቶው ጀምሮ በበራሪ ወረቀቶች፣ በንግግሮች፣ በሽለላዎች፣ በሥርዓተ ትምህርት ሳይቀር አማራን ጭራቅ አድርጎ አስቀምጧል። በተግባርም ለቁጥር ያዳገተ ግፍ መከራ በተቀነባበረ መልኩ አድርሶበታል። ይህ ነው የአማራው ጠላት እንጅ ሰፊው ውድ የትግራይ ሕዝብ አይደለም።

በመሆኑም የአማራው ተጋድሎ በጽሑፎችም ይሁን በንግግሮች እስካሁን ድረስ እያደረገ እንዳለው ወያኔን ከትግሬ በግልጽ መለየት ይጠበቅባቸዋል። አማራ ሆኖ አማራውን የሚያሳድድ እንዳለ ሁሉ ትግሬ ሆኖ ትግሬንም አማራንም የሚያሳድድ አለ። ፍረጃ በነገድ ሳይሆን በድርጅት ይልቁንም በግለሰብ ደረጃ ብቻ መሆን አለበት። ትኩረትን ከህወሓት ከፍተኛ አመራርና ከዋና ዋና ባንዳዎች ላይ ብቻ ማድረግ እጅግ ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ ነው ሰፊ ሕዝባዊ ድጋፍና ብሄራዊ አንድነት ሊገኝና ለጸና የሚችለው!

ከአማራው ተጋድሎ አመራር ምን ይጠበቃል?

የአማራው ተጋድሎ እና አመራር ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ወሬውና ሽለላው ደግሞ በውጭው ዓለም ተናኝቶ ይገኛል። አገር ቤት ያለው በጎበዝ አለቃነት የሚመራው አካል ንግግሩ ቋንቋው ሥራ ብቻ ነው። ስለሠራውና እየሠራው ስላለው ጀብዱ የሚያወራበት ጊዜም እቅድም የለውም። እስከአፍንጫው የታጠቀን ሠራዊት በአሮጌ ክላሽ ያርበደብዳል። ለህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የራስ ምታት ሆኗል። በውጭው ዓለም ያለው ሁሉ ግን ደጋፊ ቢሆን ነው። ደጋፊ ደግሞ ማውራት ያለበት ከደጋፊ እንጅ ከአመራር በሚጠበቅ ቋንቋ መሆን የለበትም። የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ስንገመግም ግን የምናገኘው እውነታ የተለየ ነው። ትግሉ ያለው ኢንተርኔት ላይ ወይም ከኢትዮጵያ ውጭ በሚመስል መልኩ ይወራል። አመራሩ ”እኔ ነኝ” የሚሉም ድምጾች እየተሰሙ ነው።

ለነጻነት የሚደረገው ትግል መራራና እልህ አስጨራሽ ነው። ለድል ለመብቃት ሕዝብን ደጀን አድርጎ መነሳት እጅግ አስፈላጊ ነው። የሕዝብን ድጋፍና አመኔታ ለማግኘት ደግሞ ትግሉን የሚመሩም የሚያስተባብሩም፣ በይፋ የሚደግፉም አካላት ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ባህላቸው ማድረግ አለባቸው።

ለምሳሌ በውጭው ዓለም አማራ ተኮር ድርጅቶች ወይም እንቅስቃሴዎች ስንት እንደሆኑ፣ እነማን እንደመሰረቷቸውና እንደሚመሯቸው፣ ግባቸውና ዓላማቸው ምን እንደሆነ፣ የትግል ስልታቸው ወዘተ በግልጽ አይታወቅም። ይህም የድርጅቶችን አቋም በደንብ መርምሮ ድጋፍ እና ወይም ተቃውሞ ለመስጠት አስቸጋሪ አድርጎታል። በርግጥ የአባላትን ማንነት ይፋ ማድረግ ከደህንነት አኳያ አይጠቅምም። የአመራር አባላት ግን በደንብ መታወቅ አለባቸው። ሕዝብ የማወቅ መብትና ፍላጎት አለው። ከዚህ በኋላ በህቡእ ለመምራት መሞከር የትግሉን ዘመን ማራዘም መከራንም ማብዛት ነው። ”የፈራ ይመለስ!” እንደተባለው የፍርሃት ቆፈን ያለቀቀው ተራ አባል እንጅ አመራር መሆን የለበትም።

ሌላው ትግሉ ከአመራር አባላት ኢትዮጵያዊ ጨዋነትንና ጀግንነትን ይፈልጋል። ከስሜትና ከአሉባልቶ የጸዳና በመረጃና በማስረጃ ትንታኔ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ አብዝቶ ይፈለጋል። የሥራ ባልደረባን በማጭበርበርና በማታለል በመምታትና በማስመታት ከፍ ለማለት የሚሞክር ካለ ዝቅ እንዲል መደረግ አለበት። የኢትዮጵያ ሕዝብ በፖለቲካው መስክ የነቃ ተሳትፎ ከማያደርግባቸው ምክንያቶች አንዱ ምናልባትም ዋናው ይህው የግል ሕይወትና ገጽ ግንባታ ላይ ያተኮረ የፖለቲካ አመራሮች ችግር ሳይሆን አይቀርም። ”ወጣቶች ናችሁ ልምድ የላችሁም” በሚል ሰበብ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን መሸፋፈን ለማንም የሚበጅ አልሆነም። ይህ ትውልድ ግን የጨለማ ጉዞ እንደማይፈልግ በግልጽ እያሳየ ነውና የአመራር አባላት የላቀ ሞራል ይዘው ይገኙ ዘንድ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Source       –        Ethiopia Zare.   ኢትዮጵያ ዛሬ

 

 

One Response