በእውኑ ሰንደቃችን የማትወክለው ጎሳ ወይም ብሔረሰብ አለን?

ሰሞኑን ደግሞ በተራው ሀገር ሊያጠፋ እየቋመጠ ያለው “የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ” ነን ባዮቹ የጥፋት ኃይሎች ሊቃነመናብርት አቶ ሌንጮ ለታና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በአውሮፓ ሀገራት እየተዘዋወሩ ለደጋፊዎቻቸው ገለጻ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚሁ ገለጻቸው የሀገራዊ ንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ የኢትዮጵያን ሰንደቅ በተመለከተ ወደፊት እንደሚወሰን አስታውቀዋል፡፡ ይሄንን ሲሉም ታዳሚው በጭብጨባ ድጋፉን መግለጹ ተሰምቷል፡፡

ይሄም ድርጊት በየቦታው እየተሰበሰቡላቸው አንዲት ቃል በተነፈሱ ቁጥር በጭብጨባ የሚቀበሏቸው ታዳሚዎች እነማን እንደሆኑ በግልጽ የሚያስረዳ ጉዳይ ነው፡፡

አንዳንድ ወገኖች ይሄንን ሴራ ባለመረዳት ታዳሚውንና ጭብጨባውን በመመልከት ብቻ መላው በስደት ያለ ሕዝብ የተቀበላቸው መስሎ የታያቸው አሉ፡፡ ሀገራዊ ንቅናቄ ነን ባዮችም ይህ እሳቤ እንዲያዝ  ስለፈለጉ ነው ደጋፊዎቻቸው ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲገኙ ወይም እንዳይቀሩ ውስጥ ለውስጥ በጥብቅ በማሳሰብ እንዲገኙ እያደረጉ ያሉት፡፡
ሰንደቃችንን በተመለከተ ዶ/ር ብርሃኑም ከዚህ ቀደም አምና አውሮፓ በአንድ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ተሰብሳቢዎቹ በብዛት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ይዘው ስለነበረ “የነፍጠኛ ባንዲራ በዝቷል ቀንሱ!” ማለታቸው ተዘግቦ ነበር፡፡
“በሽግግር መንግሥቱ” ወቅትም የሰንደቃችን ጉዳይ መወያያ ሆኖ የተለያዩ ጎሳዎችና ብሔረሰቦች ተወካዮች ነን ባዮች ሰንደቃችንን የነፍጠኞች ሰንደቅ እንደሆነችና እነሱን እንደማትወክል አበክረው ይናገሩ እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡
በመሆኑም አሉና “ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች እንዲወክል መሀሉ ላይ ኮከብ ይጨመርበት!” ብለው የ666 አምላኪዎች መለያ ምልክት የሆነውን ኮከብ ጨመሩበት፡፡ ኮከቡ እንዴት ብሎ በምን ምክንያት አልተወከልንም ያሉትን ወይም አልተወከሉም የተባሉትን ጎሳዎችና ብሔረሰቦች እንደወከለ ግን እስከአሁንም ግልጽ አይደለም፡፡
እውን ግን ሰንደቃችን የምትወክለው አማራን ብቻ ነው? አማራስ ይህችን ሰንደቅ የኢትዮጵያ ሳትሆን የአማራ ናት፣ የምትወክለውም አማራን ብቻ ነው ብሎ ያውቃል? “አማራ ስላመጣው!” የሚለው ከሆነ የአስተሳሰብ መሠረታቸው ለዚህች ሀገር አማራ ያላመጣው እሴት ምን አለና ነው “አማራ ያመጣው ስለሆነ” ተብሎ ሊገለል የሚችለው? ምነውሳ ታዲያ ሌሎች እሴቶቻችንንም አልተዋቸው? “የአማራ የሆነ ነገር ሁሉ ሀገርን ሊወክል አይገባም!” የሚለው አስተሳሰብስ እንዴት ሆኖ፣ በምን ሚዛንስ ነው ትክክል ሊሆን የሚችለው?
ለመሆኑ የትኛው ሀገር ነው ጎሳዎችና ብሔረሰቦች ተስማምተው ያጸደቁትና የተቀበሉት ሰንደቅ? አሁን እነኝህ ናቸው የሀገርንና የሕዝብን ከባባድ ጉዳዎች መፍታት የሚችሉና አቅምም ያላቸው የሚባሉ? ችግር ሊፈቱ ወይስ ይባስ ሊያወሳስቡ?
የኦሮሞና የሌሎች ጎሳና ብሔረሰብ እሴት ኢትዮጵያን አይወክልም ወይ? ከወከለስ ለምንድነው እሱ የአማራስ ሊወክል የማይገባው? ለመሆኑ ሁሉንም ወይም ሀገርን ይወክል የተባለ አንድ ሀገራዊ እሴት በታሪካዊ አጋጣሚ ወይ የተፈለገው ነገር በወቅቱ ከአንዱ ብሔረሰብ ብቻ በመኖሩ በመገኘቱ ምክንያት በተፈለገበት ወቅት ተወስዶ ሀገርን የሚወክል እሴት ተደርጎ ይወሰዳል እንጅ በአንድ ሀገር ላይ ሁሉንም ጎሳና ብሔረሰብ የሚወክል እሴት በየት ሀገር ተገኝቶ ያውቃልና ነው “ሁሉንም የሚወክል መመረጥ አለበት!” የሚባለው? ከዓመታት በፊት ስለሰንደቃችን የት? እንዴት? መቸ? ለምን? መጣ የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ “ሰንደቅ ዓላማችን (ትእምርተ ኪዳናችን) ከየት መጣ ማንስ አጠፋው?” በሚል ርእስ የሰንደቃችንን ታሪካዊ ዳራ መጻፌ ይታወሳል፡፡
ስለሆነም ስለ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዝርዝር ጉዳይ ማወቅ የሚፈልግ ካለ ጎግል አድርጎ እንዲያነብ ልጠቁምና በርእስ ያነሣሁትን ጥያቄ መልሸ ጽሑፌን ልቋጭ፡፡
“በእውኑ ሰንደቃችን የማትወክለው ጎሳ ወይም ብሔረሰብ አለን?” የሚል ነው ጥያቄያችን፡፡ መልሱ ደግሞ የለም! የሚል ነው፡፡ እንዴት? ግልጽ ይሁን ከተባለም እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ከመሆኑ በፊት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ንዋዬ ቅድሳት ነበር፡፡ መንግሥት ከቤተክርስቲያን ወስዶ ነው የሀገሪቱ ሰንደቅ ያደረጋት፡፡ ቤተክርስቲያን ንዋዬ ቅድሳቷ ያውም የመጀመሪያው ያደረገችው በዘፍ. 9፥8-17 የተገለጸውን የእግዚአብሔር ቃል መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ጥቅሱ የሚያትተው እግዚአብሔር ምድርን ዳግመኛ በጥፋት ውኃ ላያጠፋ ምልክት ትሆን ዘንድ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ በጉልህ የሚታይበት ቀስተ ደመናው የምሕረት ቃል ኪዳን ምልክት አድርጎ ለሰው ልጆች ለፍጥረት ሁሉ መስጠቱን ነው፡፡ ልብ በሉ ለሰው ልጆች ሁሉ ነው እንጅ ለአማራ ብቻ አይደለም  የተባለው፡፡

አሁን በምድር ላይ ያሉ የሰው ልጆች ሁሉ በወቅቱ ቃል ኪዳኑ ከተሰጣቸው ከኖኅ ልጆች የተገኘ እንደመሆኑ በሰንደቋ የማይወክል የሰው ልጅ የለም ማለት ነው፡፡ አንዳንድ አላዋቂ “ይሄ የአይሁድና የክርስቲያን ሃይማኖት የሚለው ነገር ነው እስላምን አይመለከትም!” ይል ይሆናል፡፡ እንዲህ የምትል ብትኖር ተሳስተሀል! ይህ ቃልኪዳን እስልምናም ውስጥ ተውራት በሚለው የመጽሐፋቸው ክፍል ያለ ነውና፡፡ “እኔ እምነት የለኝም ወይም በእግዚአብሔር አላምንምና አልወከልም!” የሚል ቢኖርም እሱ ፈጣሪን ካደ እንጅ ፈጣሪ እሱን አልካደምና ይወከላል፡፡ በመሆኑም ይህች ሰንደቅ የማትወክለው ጎሳና የእምነት ዓይነት የለምና በሰንደቃችን “አልወከልም! ወይም አልተወከልኩም!” ሊል የሚችል አንድም አካል አይኖርም ማለት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህች ሰንደቅ ክብር አጥንቱን ከስክሶ ደሙን አፍስሶ የታሪኩ አካል፣ የማንነቱ መገለጫ አድርጓት ኖሯልና ይሄንን የጥፋት ኃይሎችንና የቅጥረኞችን “ሌላ ሰንደቅ ዓላማ እንፈጥራለን!” የሚልን ፉከራ መስማትም ሆነ እነሱን ማስተናገድም አንፈልግም!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com