Wednesday, 14 December 2016 13:51
– መንግስት በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት አላሰርኩም ብሏል
በይርጋ አበበ
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሳማንታ ፓወር በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የታሰሩት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ እንዲፈቱ ጠየቁ። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ “አቶ በቀለ ገርባ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት አልታሰሩም” ሲል መልሷል።አምባሳደር ሳማንታ ፓወር በትዊተር አካውንታቸው ላይ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የታሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እንዲፈቱ ከጠየቁባቸው አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን የኦፌኮውን ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ እንዲፈቱ በጠየቁበት መግለጫቸው የሩሲያ፣ የኢራን፣ የቻይና፣ የኩባ እና ሌሎች አገራት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ይገኙባቸዋል። “በአዲሱ ዓመት (በፈረንጆች ማለታቸው ነው) ቤተሰብ ሲሰባሰብ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ለእስር የተዳረጉ ግለሰቦች ግን በዓሉን በብቸኝነት ለማሳለፍ ይገደዳሉ ቤተሰቦቻቸውም በደስታ ማሳለፍ አይችሉም” ያሉት አምባሳደር ሳማንታ ይህ የትዊተር ቅስቀሳቸውም ለአስር ቀናት እንደሚቆይ ገልጸዋል።
በኢፌዴሪ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መሀመድ ሰይድ በአሜሪካዋ አምባሳደር መግለጫ ዙሪያ አስተያየታቸውን ከሰንደቅ ጋዜጣ ተጠይቀው “ማንኛውም ግለሰብ የፈለገውን አመለካከት መያዝ ይችላል። አመለካከቱንም ከሌሎች ጋር በፈለገው መልኩ መለዋወጥ ይችላል። ከዚያ ውጭ ግለሰቦች የፈለጉትን አመለካከት በመያዛቸው ተጠያቂ የሚሆኑበት መሰረት የለም። ምክንያቱም ይህ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ነው። ከዚህ ባሻገር ግን ባጠፉት ልክ በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር ነው ያለው” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል። አቶ መሀመድ አያይዘውም በፖለቲካ አመለካከቱ ብቻ የታሰረ ግለሰብ እንደሌለ ተናግረዋል። አቶ በቀለ ገርባም ለእስር የታደረጉት በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳይሆን ህግን ተላልፈው ስለተገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ መሀመድ “ህግ ለሁሉም እኩል ነው። ለአንዱ የሚሰራ ህግ ለሌላው የማይሰራበት ምክንያት የለም። በዚህ መሰረት ህግን እና ህግን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው ሊሰራ የሚገባው። የአቶ በቀለ ገርባ ጉዳይ በህግ የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ የመጨረሻ እልባት የሚያገኘው በፍርድ ቤት ነው። ፍርድ ቤት የሚወስነውን ሁላችንም እሱን ተግባራዊ ለማድረግ የምንጠብቅበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ ይህ በህግ የተያዘ ጉዳይ በመሆኑ እና የህግን የበላይነት የማስከበር ጉዳይ ስለሆነ እሱ ነው ተግባራዊ የሚሆነው” በማለት ተናግረዋል።
አቶ በቀለ ገርባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግን) ዓላማ ለማስፈጸም ተንቀሳቅሰዋል ተብለው ተከሰው በእስር ላይ ይገኛሉ።
በተያየዘ ዜና የአሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበሩ ዶክተር መረራ ጉዲና በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው የታሰሩ ሲሆን በጠበቃቸውና በወዳጆቻቸው እንዳይጠየቁ ተደርገዋል ሲል ፓርቲው ተናግሯል። በተጠየቀባቸው የ28 ቀን ቀጠሮ መሰረትም ታህሳስ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ይሆናል።
ስንደቅ