Wednesday, 14 December 2016 13:53
 በሀገሪቱ ከተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ አስመጪዎች በቂ የውጭ ምንዛሪን ማግኘት ባለመቻላቸውና ምንዛሪውንም ለማግኘት ረዘም ያሉ ጊዜያትን ለመጠበቅ በመገደዳቸው በሸቀጦች ዋጋ ማሳወቅ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑ ታወቀ። ማክሰኞ ታህሳስ 4 ቀን 2009 ዓ.ም ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር ውይይት በተደረገበት ወቅት አንድ እቃ ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ በአስመጪዎች በኩል እቃው ከተገዛበት ዋጋ በላይ (Over Invoice) እና  ከዋጋ በታች(Under Invoice) የማሳወቅ ሁኔታ በስፋት እየታየ መሆኑ ተመልክቷል። የችግሮቹ ምንጮች በርካታ ቢሆኑም፤ አንዱና ዋነኛው ችግር ግን ሀገሪቱ ካለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ አስመጪዎች በአንድ መልኩ ከብሄራዊ ባንክ ኤልሲ ከፍተው በቂ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻላቸውና የሚያገኙትም ረዥም ጊዜን ጠብቀው ከመሆኑ ጋር የተያያዘ መሆኑን በውይይቱ ላይ ተመልክቷል።

አስመጪዎቹ ከብሄራዊ ባንክ ኤልሲ በመክፈት በቂ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር በአንድ መልኩ ውጪ ካሉ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው የውጭ ምንዛሪን በመውሰድ እንደዚሁም ከጥቁር ገበያው ዶላርን በመግዛት ሸቀጦችን የሚያስመጡበት ሁኔታ መኖሩ ተመልክቷል። አስመጪዎቹ ከብሄራዊ ባንክ የተፈቀደላቸው የውጭ ምንዛሪ መጠንና ሀገር ውስጥ በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ ካስገቡት ሸቀጥ ጋር ሲደመር ከፍተኛ ሆኖ ስለሚገኝ ልዩነቱን ለማስወገድ ሲሉ የሸቀጦችን ዋጋ ከገዙበት ዋጋ በታች አድርገው የሚያቀርቡ መሆኑ ተመልክቷል።

በዚህ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡን በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የሀገር ውስጥ ታክስ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደስታ በዛብህ አስር ሺህ ዶላር የሚሸጥ መኪና የአምስት ሺህ ዶላር ኤል ሲ የሚከፈትበት ሁኔታ የተከሰተ መሆኑን ገልፀዋል።

በእለቱ ማብራሪያ የሰጡት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጫኔ ቀደም ባሉት አመታት የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እስከ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የነበረ መሆኑን ገልፀው ፤ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ግን ይህ የኤክስፖርት የውጭ ምንዛሪ መጠን ወደ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የወረደ መሆኑን ገልፀዋል። የሀገሪቱ  90 በመቶ የኤክስፖርት ገቢ ከግብርናው ዘርፍ የሚገኝ መሆኑን ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በአለም አቀፉ ገበያ የግብርና ምርቶች ዋጋ እየወረደ መሄድ በኢትዮጵያ የኤክስፖርት ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረ መሆኑን አመልክተዋል።  “በሀገሪቱ በቂ የውጭ ምንዛሪ ቢኖር ኖሮ የንግዱ ማህበረሰብ ተራ ሳይጠብቅ ከብሄራዊ ባንክ በቀላሉ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይችል ነበር” ያሉት አቶ ከበደ፤  አሁን እየታዩ ያሉት የገቢ እቃዎች  ትክክለኛ ዋጋ የማሳወቅ ችግር ጉዳይ ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን አስታውቀዋል። ችግሩንም ለመፍታት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን መፍታት ዋነኛው መፍትሄ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው አመልክተዋል።

ስንደቅ