December 14, 2016
አባይ ሚዲያ ዜና
ናትናኤል ኃይለማርያም
የሕዉሐት አስተዳደር ሕጋዊነት በሌለዉ መልኩ የሶሻል ሚዲያዎችን እና የዜና ድሕረ ገጾችን ሆን ብሎ እገዳ ሚያደርገዉ በደህንነት አባሎቹና በወታደሩ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተዉ በግፍ የተገደሉትን ንፁህ ዜጎች ዘገባ እንዳይካሔድ እንዲሁም ገዳዮቹን ለፍርድ እንዳይቀርቡ ለማድረግ የታሰበ መሆኑን አዲስ የወጣዉ የአለም አቀፉ አምኔስቲ ሪፖርት አስታዉቋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ጥናት ያካሔደዉ አምኔስቲ ኢንተርናሽናል ከጁን እስከ ኦክቶምበር ባለዉ ጊዜ ዉስጥ በአገሪቷ ዉስጥ ከፍተኛ ዉጥረት የነገሰ መሆኑ ሲታወቅ በዚህ ጊዜ ዉስጥም ዋትስ አፕን ጨምሮ 16 የዜና አዉታሮች መታገዳቸዉን ሲገለጽ በኦሮምያ ሁኔታዉ የከፋ መሆኑንም አያይዞ ገልጿል።
ካልፈዉ ኖቬምበር ጀምሮ የአዲስ አበባዉን የማስተር ፕላን በመቃወም በአገሪቷ ዉስጥ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ተቃዉሞ መነሳቱን ያስታወሰዉ ይኸዉ ሪፖርት ይህን ተቃዉሞ ተከትሎም አገዛዙ ስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁንም አዉስቷል።
ጥናቱ የተካሔደዉ በኢትዮጵያ ያለዉን የሳንሱር (ቅድመ ምርመራ) ችግር፤ የኢንተርኔት አገልግሎት እጅግ በጣም ዝግ ያለ መሆኑና ሶሻል ሚዲያን ለመጠቀም ያለዉ አቅም እጅግ ዉስን መሆኑን ለአምኔስቲ ኢንተርናሽናል እና ለ Open Observatory of Network Interference ችግሩ ከተነገረ በኋላ መሆኑም አስታዉቋል።
ይህንንም በርካታ ሰዎችን በማነጋገር ምስክርነታቸዉን የሰበሰበዉ ሪፖርት ከኦሮምያ አካባቢ የተገኘ ሲሆን እንደ ፌስ ቡክ፤ ዋትስ አፕ፤ እና ትዊተር ለመጠቀም ማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን አምኔስቲ ያነጋገራቸዉ በሰጡት የምስክርነት ቃል ማረጋገጡን ሲገልጽ ባለፈዉ ኖቬምበር በኦሮምያ በተነሳዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ጋር የተያያዘ መሆኑንም በሪፖርቱ አስፍሯል።
የሕዉሐት አገዛዝም ፌስ ቡክ፤ ኢንስታግራም እና የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎቶችን የዘጋሁት ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና በሚካሔድበት ሳምንት ነዉ በማለት የገለጸ ሲሆን የዚህንም ምክንያት በማለት ሲያስረዳ ተማሪዎች በፈተና ጊዜ ሃሳባቸዉ ወደ ሌሎች ጉዳዮች እንዳይሰረቅ በማሰብ ነዉ ሲል የገለጸ መሆኑንም የአምኔስቲ ሪፖርት አያይዞ ገልጿል።
አምኔስቲ በኦሮምያ በአዲስ አበባ እና በአምሐራ አካባቢ ሙሉ በሙሉ የስልክ አገልግሎቶች ኦገስት 6 እና 7 ዝግ እንደነበረም በሪፖርቱ ሲገልጽ በጎግል ሪፖርትም ከጁላይ ወር እስከ ኖቬምበር ድረስ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ የተረጋገጠ መሆኑንም አክሎ በሪፖርቱ አስነብቧል። በዚህ ኢንተርኔት በተቋረጠበት ጊዜ ዉስጥም በትንሹ ተቃዉሞ ለማሰማት የወጡትን 100 ንፁሃን ዜጎች በአገዛዙ የደህንነት ሰዎች መገደላቸዉንም ጨምሮ ዘግቧል።
የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ እና የትልልቆቹ ሐይቆች የአምኔስቲ ኢንተርናሽናል ምክትል ኃላፊ የሆኑት ሚሼል ካጋሪ እንደገለፁት “ የተለየ ሃሳብን ለመቀብል ችግር ያለበት የሕዉሐት አገዛዝ ሶሻል ሚዲያዉን መዝጋቱን እንደ ጀብደኝነት የቆጠረዉ በመሆኑ የኢንተርኔት አግልግሎት መቋረጡን ፍትሃዊ ነዉ ብሎ እንድሚያምን ሲገልፁ አያይዘዉም ይኸዉ ኢንተርኔት አግልግሎትን መሰለልም ሆነ መዝጋት ምንም አይነት ሕጋዊ መሠረት የሌለዉ እና ተቃዉሞዉን ለማሰማት የወጣዉ ብሶተኛ ሕዝብ ላይ ሌላ ችግር በመጨመር ይባስ ብሎ በአስቸኳይ አዋጅ ሳቢያ የስለላ ሥራዉን አጠናክሮ መቀጠሉንም ገልፀዋል።
የሕዉሐት ባለስልጣናት ሁሉንም ነገር ክፍት በማድረግ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ ከማድረግ ይልቅ በችግሮች ላይ ቤንዚን በማርክፍክፍ ችግሩን ወደ ከፋ ደረጃ በማድረስ የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰት እየፈፀሙ ይገኛሉ ካለ በኋላ የሕዉሐትን ባለስልጣናት የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ከመዝጋት ይልቅ ሕዝብ የኢንተርኔት አገልግሎት ሊያገኝ የሚችልበትን እና ሃሳቡን በነጻነት የሚገልጽበትን አስፈላጊ የሆኑትን ቁሳቁሶች በተገቢዉ ሁኔታ ለሕዝብ ማቅረብ እንደሚገባቸዉ ለሕዉሐት ባለ ስልጣናት አሳስበዋል።”
የሕዉሐት ባለ ስልጣናት Deep Packet Inspection (DPI) የተባል ቴክኖሎጂ በመጠቀም ድሕረ ገጾችን እንደሚሰልሉም በሪፖርቱ ተገልጿል። DPI የሚባለዉ ቴክኖሎጂ የኢንተርኔት ትራፊክን መመልከት እና መሰለልም የሚያስችል እንደሆነም በሪፖርቱ ተካቷል።