የዚህ ጽሁፍ መነሻ ፕሮፌሰር መሥፍን ወልደ ማርያም ስለ ዐማራ ሕዝብ «የክህደት ቁልቁለት» በተሰኘው
መጽሐፍ ገጽ 120-124 ያሰፈሩት አሳብ ነው። መረጃወቻቸውንም አንድ በአንድ እየጠቀሰ በሁሉም ላይ ማብራያ
በመስጠት «የዐማራ ሕዝብን» ህልውና የሚክድ መረጃ ማቅረብ አልመቻላቸውን ያሳል። ጸሐፊ ፕሮፌሰሩ የጠቀሱአቸውን
መረጃወች አልተረዱአቸውም ወይንም አዛብተው ጠቅሰዋቸዋል እያለ ይሞግታል። በአንፃሩም ታላቁን የዐማር ሕዝብ
ህልውና ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት መከጀል ከመልካም ህሊና የተፈጠረ ነውን? አመክንዮ ካሸነፈው ሊቅነት የተፈጠረ
አስተሳሰብስ ነውን? ያካልሆነ ለምን? ብሎ ይጠይቃል። መልካም ንባብ።
መግቢያ – የሀገራችን ሕዝቦች በኢትዮጵያዊነት የተሳሰሩ ስለ ሆኑ ሁሉም ማንነታቸውን ኢትዮጵያዊነት አድርገው ለብዙ
ዘመን በአንድነት መኖራቸው ይታወቃል። ከሕወሀትና ሻቢያ እንቅስቃሴ ወዲህ ግን በኢትዮጵያችን ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋና
በቅርብ በሚዛመዱት ኅብረተ ሰብእ ማንነት ተወስነው ራሳቸውን እንዲገልጡ ተገደዋል ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በሥጋና በደም
የተሳሰረ አንድ ሕዝብ ቢሆንም የትግራይ ነጻአውጭ ኃይል ግን ላለፉት 25 ዓመታት ኢትዮጵያውያን በዐማራነት ፣
በትግሬነት ፣ በኦሮሞነት ፣ በጉራጌነት ፣ ወዘተርፈ አተኩረው እንዲመለከቱ እና እንዲደራጁ ብዙ ስለ ሠራ ሁሉም ራሱን
በየነገዱ ለመግለጥ ተገዷል ። የሚገርመው ግን በዚህ ወቅት ከትልቅ እስከ ትንሽ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በቋንቋቸውና
በባህላቸው መሠረት «ትግሬ» «አሮሞ» «ጉራጌ» «ወላይታ» «ከምባታ» «ኮንሶ» «አፋር» ወዘተርፈ እየተባሉ ህልውናቸው
ሲለፈፍና ሲታወጅ ፣ የኢትዮጵያን ኅብረተ ሰብእ ወደ አንድነት አምጥቶ መሀል ላይ ተዘርግቶ ያገናኘውን ታላቁን የዐማራ
ሕዝብ በተመለከተ «ዐማራ አለ ወይስ የለም?» የሚል የህልውና ጥያቄ መነሣቱ ነው ። በሌላ አገላለጽ ለመሆኑ ዐማራ
የሚባል የሕዝብ ነገድ አለን ? ብለው የሚጠይቁና «የለም» ብለው የሚመልሱ ሰዎች መኖራቸውን መስማታችን ነው ።
እነዚህ ሰዎች ለሀገር አንድነት እናስባለን የሚሉ ናቸው ። ዐማራ የለም ለማለት ያስገደዳቸውም የሀገራችን ፖለቲከኞች
ላለፉት 25 ዓመታት ዐማራን ፀረ ኦረሞ ፀረ ትግሬ አድርገው ትልቅ የማስጠላት ሥራ ስለ ሠሩ፣ ሕዝቡንም በቋንቋ
ከመለያየታቸው የተነነሣ፣ የተለያየውን ሕዝብ ወደ አንድነት ለማማጣት የሚያስቡ ሰዎች፣ እንደ መፍትሔ አሳብ ያዩት
የዐማራን ህልውና መካድን ነው ። ምክንያቱም ሕወሀት ዐማራ ተነስቶ የቀድሞውን ሥርዐት ያመልስባችኋል እያለ እንደ
ማስፈራሪያ አድርጎ የሚጠቀምበትን ሕዝብ የለም ካሉ አገርን አንድ ለማድረግ ይቻላል ከሚል እሳቤ ይመስለኛል ። ይህ ግን
መስተዋል አይደለም ። በሀሰት አገር አይገነባምና ። ያለ ዐማራ ህልውና የምትኖር ኢትዮጵያም የለችምና ።
2
ይህም የዐማራን ህልውና የካዱ ሰዎች ብዕር ብዙዎቹን እያነጋገረ ይገኛል ። ዐማራ የለም ባዩም ሆነ ማንም ሰው
ዐማራ ካልሆነ ፣ ወይም ዐማራ ሁኖ በዐማራነቱ ካላመነበት ፣ ወይም ዐማራ መሆንና መባል ዋጋ ያስከፍለኛል ብሎ ካሰበ ፣
ራሱን ዐማራ አይደለሁም ብሎ መናገር ይችላል ፤ መብቱ ነው ። ዐማራ የለም ብሎ መናገር ግን አይቻልም ።
ዐማራ የሚባል ነገድ የለም ብሎ የሚናገረው ሰው የገዡ ሥርዐት ለ25 ዓመት ሙሉ በጠበንጃና በፕሮፓጋንዳ
ሊደመስሰው ያልቻለውን የዐማራ ማንነት በብዕር ደምስሶ ማጥፋት ከቻለ ፣ ይህ ክፍል በሕወሀት መሸለም ይገባዋል ባይ ነኝ!
አሁን አሁን በነፕሮፌሰር፣ በነዶክተር የሚጻፉ ጽሑፎች የዐማራ መኖር ለኢትዮጵያ አንድነት ዕንቅፋት የሆነ ይመስል «ዐማራ
የለም» በማለት የኢትዮጵያን አንድነት ለመስበክ ይሞክራሉ ። የዐማራ ህልውና ለኢትዮጵዮጵያ ሉዐላዊነት ምክንያት ይሆናል
እንጂ ለክፍፍል ምክናያት እንደማይሆን ታሪክ ምስክር ነው ። ለምሳሌ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው የፕሮፌሰር መስፍን
መጽሐፍ ፤ እዲሁም ሌሎችም ስለ ሀገር አንድነት በሚጽፉትና በዚህ አመለካከታቸውም የምናከብራቸው አንድ አንድ ሰወች
የጻፉትን ጽሑፍ በአስተውሎት ለተመለከተው ስለ ዐማራ ህልውና እና ታሪካዊ ሚና አስቂኝ አሉባልታ ነው የሚናገሩት ።
አንዳንድ ኦሮሞ ወንድሞቻችንም ያን ተቀብለው በፌስ ቡክ ስለ ሀገር አንድነት የተሳታፊዎችን ጥያቄ ሲመልሱ የነፕሮፌሰርን
ጽሑፍ በመጥቀስ «ዐማራ የሚባል ዕንቅፋት የለም» ሲሉ ሰማሁና አደነቀኝ። ይህም በሕወሀት ስብከት መሰረት ዐማራውን
እንደ ሕዝብ ጨቋኝ መደብ አድርገው ማየታቸውን አመልካች ነው ። ዐማራ የለም ባዮች ሰዎች የሚጠቅሱት ፕሮፌሰር
ጌታቸው፣ ፕሮፌሰር መስፍንም ዐማራ የለም ብለዋል እያሉ በመጥቀስ ይናገራሉ ። 1 በመሠረቱ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ
ዐማራ የለም አላሉም፤ በኋላ እንመለስበታለን። መሥፍን ግን ብለዋል አባባላቸውንና መረጃውቻቸውንም አንድ በአንድ
እንመለከተዋለን።
አሁን አሁን ዐማራ የለም ከማለት ጀምሮ የኢትዮጵያን ታሪክ የመበረዝ ሥራ በሰፊው እየተሠራ ይገኛል ።
ይልቁንም የሚያሳዝነው ይህን ሥራ የሚሠሩት ለሀገር አንድነት እናስባለን የሚሉ ምሁራን ነነ የሚባሉ ግለሰቦች የዐማራን
ህልውና መካድን የብዕራቸው ማሟሻ ማድረጋቸው ነው ።እውነት ለሀገር ከታሰበ ግን ሰዎቻችን የኢትዮጵያዊነትን አንድነት
ለመስበክ «ዐማራ የለም » ከሚል ርእስ መነሣት ያለባቸው አይመስለኝም ። የኢትዮጵያዊነት ዋነኛው ተዋናይ ዐማራ ነውና ።
የኢትዮጵያንም ሕዝብ የከፋፈለውና ከዚህ ያደረሰው የሕወሀት መፈጠር እንጂ የአማራ መኖር አይደለም። ስለዚህ
ዐማራውን ሕዝብ በጠላትነት መፈረጅ የተሳሳተ አመለካከት ነው ።
ሕወሐት እኮ ገደልኩት ፥ ቀበርኩት ፥ አከርካሪውን መታሁት የሚለው ይህንን የዐማራ ሕዝብ ነው ። በአሁኑ
ሰዓት ዐማራ የለም ማለት ትልቅ ዳህጸ -ብዕር /የጽሁፍ ግድፈት ነው ። በቃልም ለሚናገረው ትልቅ የቃል ግድፈት ነው ።
ይህ «ዐማራ የለም» የሚለው የጥላቻ አስተሳሰብ እንደ ባለጊዜዎቹ የሕወሀት ካድሬዎች ዐማራውም ሆነ ቤተ እምነቱ
የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አከርካሪውን ተመቶ ፥ ሙቶ ተቀብሯል ከሚሉት ያነሰ አባባል አይደለም ። እነሱ ነበረ
ገደል ነው ነው የሚሉት ፤ ይኸኛው አሳብ ግን ጭራሹንም የለም ነው የሚለው ።ዐማራ የለም የሚሉ ሰወች ለዐማራው
1
ነገር ግን ፕሮፌሰር ጌታቸው «ዐማራ የለም» አላሉም።ለምሳሌ እነ አቶ መኮነን የኦሮሞ ተወላጆችንም እንገንጠል አትበሉ ፤ ዐማራ የሚባል ሕዝብ
የለምና በሚል ሲናገሩ ይህ ጸሐፊ ሰምቷልይህንም ያሉት በፌስ ቡክ በቀጥታ በ10/15/16 ሲያስተላልፉ ነበር
https://www.facebook.com/melala.mesfin?pnref=story ቪድዮውን መከታተል ይቻላል ።
3
3
ሕዝብ ከሕወሀት የከፋ ሥራ እየሰሩ መሆኑንን ሊነገሩ ይገባል። ስለዚህ በዚህ ጽሑፍ ዐማራ… ዐማራነት …
ኢትዮጵያዊነት የሚሉትን ቁልፍ ቃላት በማብራራት ዐማራ የሚባል ነገድ አለ ? ወይስ የለም ? ለሚሉ የወቅቱ ጥያቄዎች
በአመክንዮ ላይ በተመሠረተ ማብራሪያና መልስ ለመስጠት ጥረት ተደርጓል ። ዐማራ የሚባል ነገድ /ጎሳ/ አልነበረም የለምም
የሚለው አሳብ በቂ አመክንዮ 2 የሌለው መሆኑንም በመረጃ ተመሥርቶ ይመልሳል ፤ የዐማራንም ህልውና በግልጽ ያሳያል ።
ዐማራ አለ የለም የሚል ጥያቄ መነሣቱ በራሱ የሚስደንቅ ነው !
-ዐማራ የለም ባዮች በሳይንሳዊ አመክንዮ ላይ ተመሥርተው ነው እንዳንል- ምንም ሳይንሳዊ መሠረት የላቸውም
። ከጥቂቶቹ በቀር በዚህ ጸሐፊ ግንዛቤ ይህን የሚሉ አካላት ዐማራ የሚባል ነገድ የለም የሚሉት ዐማራን ከመጥላት
በመነሣት አይመስልም ። ምን አልባትም አንድ አንድ ምሁራን ወደዚህ አሳብ ያጋደሉት፦
1ኛ አንዳንድ ያዐማርኛ አባባሎችን አዛብቶ ከመተርጎም ፤
2ኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሥጋና በደም የተሣሰረ ሕዝብ ስለ ሆነ ልዩ ልዩ ቋንቋ ከሚናገሩ ኢትዮጵያውን ጋራ
ያልተጋባ ዐማራ የለም በማለት ፤
3ኛ የአጼው ገዡ መደብ ሥርዓት በዐማራ ባህል ፥ ቋንቋ ፥ ሃይማት ላይ ተመሥርቶ ለብዙ ዘመን ስለ ኖረ ፣
በኢትዮጵያ ምድር ሁሉ ዐማራ ይኖር ስለ ነበረና ስለ አለ ፣ ኢትዮጵያ አገሬ ናት ብሎ ስለሚያምን ፣ ዐማራ ብሎ ከመጥራት
ይልቅ «ኢትዮጵያዊ» ብሎ መጥራት ይሻላል በማለት ይመስለኛል ። ከዚህ ውጭ ከሆነ ግን አጉል ፍልስፍና ነው የሚሆነው
። ሁኖም ከላይ የተጠቀሰው አባባልም ዐማራ የሚባል ነገድ በኢትዮጵ የለም ፣ አልነበረምም ፣ አያሰኝም ። ሁኔታው
የሚያሳየው ተጽዕኖ ፈጣሪ ፣ ባህሉን ሥርዓቱን ለሌሎች ማካፈል የቻለ ፣ ልዩ ልዩ ቋንቋ ከሚናገሩ ኢትዮጵያውያን ጋር
በሥጋ እና በደም የተሳሰረ ፣ ኢትዮጵያን የገነባ ፣ ሕዝብ መሆኑን ነው የሚያመለክተው ።
ዐማራ አለ የለም ከተባለ አይቀር ለጥያቄው መልስ መስጠት አስፈላጊነቱ አያጠራጥርም ። ዐማራን እያዩ
ለማያዩት ፣ እየተናገረ እየሰሙ ለማይሰሙት ፣ በደርግ ዘመን ፊውዳል እየተባለ ርስቱን ሲነጠቅ ፣ በሕወሀት ዘመን ደግሞ
በየክፍለ ሀገሩ ዐማራ በመሆኑ ብቻ እየተለቀመ ሲገደል ፥ ሲሰደድ እያዩት ላላዩት ፤ እኔ አማራ ነኝ የሚል በብዙ ሚሊዮኖች
የሚቆጠር ሕዝብ በኢትዮጵያችን መኖሩ እየታወቀ የለም ለሚሉ ፤ ካለውና ከነበረው ዐማራ ውስጥ ከ2 ሚሊዮን ተኩል
በላይ ዐማራ በሕወሐት ዘመን ጠፋ እየተባለ ቍጥሩ መቀነሱን በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሲለፈፍ ለመስማት ላልቻለ ሁሉ
አሁንም እንደ ገና መናገር ይኖርብናል ። ዐማራ ነበረ ፣ አለ ፣ ይኖራል ።
2 አመክንዮ ማለት ቃሉ የግእዝ ሲሆ አንድን ነገር ተቀባይነት እንዲያገኝ ያሚያደርግ በቂ ወይም አሳማኝ ምክንያት ፣ ምክንያታዊ ነጥብ ማለት ነው ።
4
ዐማራ የሚባል ነገድ ስለ መኖሩ
ሀ) “ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ” እንዲሉ የመጀመሪያውን ማስረጃዬን በምሳሌ ላቅርብ ፤ የዛሬ 20 ዓመት
አካባቢ በትርጓሜ ትምህርት ቤት ሳለሁ አንድ የዘጠና አምስት ዐመት ባለጸጋ የብሉይና የሐዲስ የቅኔ ሊቅ ቅዱስ ጳውሎስ
መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ያስተምሩ ነበር ። ስማቸው የኔታ ገብረ ሥላሴ (መልአከ ገነት) ይባሉ ነበር ። አዲስ ስለ መጣ
እምነት ተማሪዎች እንዲህ ብለን ጠየቅናቸው ። «የኔታ ማርጀት መሞት የሚባል ነገር የለም ፤ የሰው አምሮ የፈጠረው ነው ፤
ለእኛ መስሎ ስለሚታየን ነው እንጂ ፣ እርጅናና ሞት የሚባል ነገር የለም የሚል አዲስ እምነት ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል ፤
በጎተራና በነፋስ ስልክ አካባቢ ቤት ተከራይተው እያስተማሩ ነው ፤ ምን እንበላቸው» አልናቸው ። የኔታም መለሱና «ያን
ጅል ጥራና እኔን አሳየው ፣ እርጅና መኖሩን ያን ጊዜ ያውቃል … ሞት የለም የሚልህንም ወደ ቅዱስ ዮሴፍ ቤ/ክ አጠገብ
ወዳለው ፣ መካነ መቃብር ውሰድና የሕዝቡን መቃብር አሳየው ፤ ሞት መኖሩን ያውቃል» አሉን ። 3 እኔም ዐማራ የለም
የሚሉትን ሰዎች ኑ እና እኔን እኔን የመሰሉትን በሚሊዮን የሚቈጠሩ ዐማሮችን እዩና እመኑ ነው የምለው ። አሳባቸው
የዐማራው ሕዝብ በሥጋና በደም ከትግሬው ከጉራጌው ከአገው ከኦሮሞው ጋር ወዘተ ተሳስሯል ለማለት ከሆነ ? ምን ጥያቄ
አለው ፤ ቁም ነገሩ ግን ያስ ቢሆን ዐማራ የለም ያሰኘዋል ወይ ? አያሰኘውውም ። ኦሮሞውን ፥ ትግሬውን ፥ ጉራጌውን ፥
ከሌላ ሕዝብ ጋራ መዛመዱ የለም አላሰኘውምና ። ሰዎች ዐማሮች ነን በማለታቸው እየታሰሩ፣ እየተገደሉ ፣ ዐማራ የሚባል
ነገድ የለም አይባልም ።
ለ) ዐማራ የሚባል ዘመድ ወይም ነገድ አለ ወይስ የለም የሚለውን ጥያቄ «የሞኞች ጥያቄ ነው» ብለውታል
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ። ሲያብራሩም- «ሞኝ የሚባለው ዓይን እያለው ሰው ሁሉ የሚያየውን ግዙፍ ነገር የማያይ ፣ ሰው
ሁሉ የሚያውቀው የወልና የጋራ ዕውቀት እንግዳ የሚሆንበት ነው ። ሞኝ ዛሬ የተወለደ ይመስል የሚያጋጥመውን ነገር ሁሉ
ሰው ሳይጠይቅ በራሱ አይደርስበትም ። እንዲህ ያለ ሰው አለ ? «ዐማራ የሚባል ዘመድ አለ ወይስ የለም ?» ብሎ
የሚጠይቅ ሰው ካለ እሱ አንዱ ነው» በማለት ዐማራ የሚባል ነገድ የለም ማለት ትልቅ አለማወቅ መሆኑን ይናገራሉ ። 4
ኢትዮጵያዊነትን ለማሳየት የዐማራን ህልውና መካድ አያስፈልግም ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በሥጋ በደም ተሳስሯል ማለትና
ዐማራ የለም ማለት ልዩነት አለው ። እኔ የማውቀው ደግሞ ዐማራው ራሱን በሦስት መንገድ ነው የሚገልጠው
በኢትዮጵያዊነቱ ፣ በዐማራነቱ እና በሚኖርበት ክፍለ ሀገር ።
ስለዚህ ጥንታውያን ከሆኑት የኢትዮጵያ ኅብረተ ሰቦች አንዱ የሆነውን ታሪካዊ ሕዝብ የዐማራን መኖር ጥያቄ
ውስጥ የሚያስገባን ግለሰብ ኢትዮጵያን ያውቃል ከሚባል ሰው ሲሰነዘር ይደንቃል ፤ የሀገራችን ሰዎችም ትልቅ ትንሽ ሳይል
ባለፉት 25 ዓመታት ትልቅ የአስተሳሰብ እዳ ውስጥ እንደ ገቡ ተረድተን ልናስብላቸው ይገባል ። ዐማራ የለም መባሉ
እውነት ቢሆን ኑሮ (ይልቁንም በፕሮፌሰር አንደበት) ሕወሀትን «አማራ የሚባል የለም» ከማለት የተሻለ ደስ የሚያሰኘው
3 አዲስ አበባን ለማታውቁ ትልቅ መካነ መቃብር ያለበት ዮሴፍ የሚባል ቤተ ክርስቲያን አለ ፣ ለዚያ ነው እንዲህ ያሉት ።
4 ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አማራ የሚባል ዘመድ አለ ወይስ የለም ገጽ 1 ይመልከቱ ።
5
ነገር አልነበረም ። ነገር ግን የዐማራን ህልውና ለመካድ የሕወሀት ሕሊናው ስላልፈቀደለት ፣ እንደ ጦር የሚፈራውን ፣ ስሙና
ጥላው የሚከብደውን ሕዝብ ለአላፉት 25 ዓመታት አጠፋለሁ ብሎ ሲያስጨፈጭፍ ኑሮአል ። አሁንም በታጠቀ ሠራዊት
እጨፈጭፈው ይገኛል። ቤቱን ያቃጥልበታል፤ሀብቱን ይዘርፈዋል።
የፕሮፌሰሩ «የክህደት ቁልቁለት» ገጽ 120-124 በሚለው መጽሐፋቸው ዐማራን በተመለከተ እንደ መረጃ
የጠቀሱአቸውን መጻሕፍት አዛብተው እንደ ተረዱአቸው ነው እኔ የተረዳሁት ። ይህን አባባሌን ደረጃ በደረጃ አስረዳለሁ ።
ባለአእምሮ አንባቢ በእኔና በፕሮፌሰር መሥፍን አመለካከት ላይ የራሱን ፍርድ ይሰጣል።
መረጃ አንድ የደስታ ተክለ ወልድን ዐማርኛ መዝገበ ቃላት ፦ ይህን መጽሐፍ ፕሮፌሰር መስፍን ዐማራ የሚባል
ጎሳ /ነገድ ወይም ዘመደ ሰብእ አልነበረም ለማለት እንደ መረጃ መጥቀሳቸው ተገቢ አይደለም ። መጽሐፋቸውን አስተውሎ
ላየው ወይ ፕሮፌሰሩ የደስታ ተክለ ወልድን አሳብ አልተሩዱትም ፣ አለበለዚያም አዛብተው ተረጕመውታል ፤ ያም ካልሆነ
በአእምሮአቸው አንባብያን ያልተረዳነው የሆነ ሁኔታ አለ ። ፕሮፌሰር መስፍን ዐማራ የሚለውን ፍች በከፊል ወስደው ዐማራ
የለም የሚለውን አሳባቸውን ሊያንተርሱት ስለ ፈለጉ ብቻ ይመስላል ደስታ ተክለ ወልድን የጠቀሱት ። የደስታ ተክለ
ወልድን አሳብ ከዚህ እንደሚከተለው በማቅረብ ከፕሮፌሰር መስፍን አስተያየት አንጻር የመረጃ ጥቅሱን በማብራራት
አቀርባለሁ ።
1/ «ዐማራ (ዐም ፥ ሐራ) ፣ ዐም ፥ ሕዝብ ፣ ሐራ ፥ ነጻ ። በተገናኝ ነጻ ሕዝብ ፣ ገዢነት እንጂ ተገዥነት
የማይስማማው ማለት ነው» ብለው ደስታ ተክለ ወልድ ተርጎመዋል፤ በዚህም ትርጉማቸው የሕዝቡን ታላቅነት በስሙ
ገልጠው ተናገሩ እንጂ ዐማራ የሚባል ዘመድ ወይም ነገድ የለም አላሉም ። 5
2/ በተመሳሳይ ፍች የግእዝ መዝገበ ቃላትም ዐማራ የነገድ ስም መሆኑን አስረግጦ ይናገረዋል – «ዐም» ማለት
(በዕብራይስጥ) ሕዝብ ፣ ነገድ ፣ ብዙ ሰው ፣ ቋንቋውና ሕጉ ግዛቱ መንግሥቱ አንድ የሆነ ማኅበረ ሰብእ» ማለት ነው ።
«ዐምሐራ- ማለት ደግሞ «ዐማራ ፣ ጨዋ ሕዝብ ፣ ማለትም ነጻነት ያለው ሕዝብ ፣ ሌላውንም ነጻ የሚያወጣ ሕዝብ ማለት
ነው ይላል ። ከዚያም «ዐምሐራይ (ዊ) ያማራ ወገን ፥ ልሳን ፥ ቋንቋ ፥ ዐማርኛ ከዐረብ ከዕብራይስጥ ከግእዝ ከአራም
የወጣ» ተብሎ ተተርጕሟል ። 6 ይህም የሚያሳየው የራሱን ማንነት የሚገልጥበት ልሳን ያለው ሕዝብ መሆኑን ነው
የሚያመለክተው።
3/ «ዐማራነት»- የሚለውን ቃልም ደስታ ተክለ ወልድ ሲፈቱ «ዐማራ መሆን ፣ ተገዝሮ ተጠምቆ ማተብ አስሮ»
ብለውታል ። ይህን ማለታቸው የሚሳየው ዐማራው ሕዝብ ፣ ክርስቲያን ስለ ሆነ ፣ ክርስቲያን ያልነበረው ፣ ክርስቶስን
ያልተቀበለው ሕዝብ እንደ ዐማሮች ፣ ዐማሮች የሚያምኑትን እና የሚያመልኩትን ኢየሱስ ክርስቶስን አምኖ ሲጠመቅ
«ዐማራ ሆነ» መባሉን ነው የሚያሳየው ። ያም ማለት እንደ ዐማሮች በክርስቶስ አመነ ተጠመቀ ፣ ዐማሮችን በሃይማኖት
በባህል ተዘመዳቸው ፣ በሃማኖት ወንድም እኅት ሆነ ፣ ተባለ ፣ ማለትን ያሚያሳይ እንጂ ዐማራ የሚባል ነገድ ፣ ወይም ዘመደ
5
ደስታ ተክለ ወልድ የዐማርኛ መዝገበ ቃላት ገጽ 937
6 ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የግእዝ መዝገበ ቃላት ገጽ 1415
6
ሰብእ ወይም ጎሳ አልነበረም ፣ የለም ፣ ማለትን አያስተረጕምም ፤ ወይም አያሳይም ። ይልቁንም ይህ ቃል በሃይማኖት
አብርሃምን የመሰሉ ሁሉ «እስራኤል ዘነፍስ» የአብርሃም ልጆች እንደሚባሉ ፣ ዐማሮችም እንደ ተስፋው ቃል በክርስቶስ
ያመኑ ሕዝቦች በመሆናቸው ፣ ዐማራነታቸው የክርስትና መገለጫ መሆኑን ያመለክታል ።
4/ «ዐማሮች» የሚለውን ቃል ደስታ ተክለወል ሲፈቱት «ሺዎች ፣ ላስቶች፣ በጌምድሮች ፣ ጎዣሞች ፣ ወሎዎች»
7 ብለው የራሱ ጎሳ ነገድ ዘመድ ያለው ሕዝብ መሆኑን ከመግለጣቸውም በላይ በአሁኑ ሰዓት ዐማሮች በብዛት
በሚገኙባቸው አካባቢዎች ዐማሮችን ገልጠዋቸዋል ። ስለዚህ ዐማሮች በሚኖሩበት ሽዌ ፣ ጎጃሜ ፣ ጎንደሬ ፣ ላስቴ ፣ ወሎዬ
/ላኮመልዛ ፥ ወዘተ እየተባሉ መጠራታቸው በሰፈሩበት ቦታ መታወቃቸውን የሚያመልክት ሲሆን ፣ ዐማሮች መባላቸው
ደግሞ በማንነታቸው ነው ። መዝገበ ቃላቱ እዲህ እያለ ይህንን መጽሐፍ ጠቅሶ ዐማራ የለም ማለት የጥናት ውጤት
አይመስልም ፤ አንባብያን መዝገበ ቃላቱን በመመልከት የሕሊና ፍርድ ሊሰጡ ይችላሉ ። 8
5/ ዐማራ በቋንቋው ህልውናው ታውቋል ። ዐንድ ቋንቋ ያለ ተናጋሪ እንደማይፈጠርና እንደማይኖር ይታወቃል ፤
ቋንቋውን የሚናገረው ሁሉ የቋንቋው አስገኝ ባይሆንም ቋንቋውን በባለቤትነት ቋንቋው አድርጎ ያሳደገ ሕዝብ መኖሩን ግን
ቋንቋው ራሱ ይመሰክራል ። ለዚህም ሊቁ ደስታ ተክለ ወልድ «ዐማርኛ- ያማራ ቋንቋ ፣ ከግእዝ የሚወለድ ፣ ከሱርስትና
ከዕብራይስጥ ፥ ከዐረብ የሚዛመድ ሴማዊ ልሳን» በማለት ተርጕመውታል ። ዐማራ የሚባል ነገድ የለም ለማለት የተጠቀሱት
ሊቅ የራሱ ቋንቋ ያለው ዐማራ የሚባል ነገድ መኖሩን አስረግጠው ተናግረዋል ማለት ነው ። 9
6/ የሀገችን ቋንቋ እና ታሪክ ተመራማሪ ሊቁ አለቃ ታዬ ገብረ ማርያምም- ዐማርኛ ከአጼ ይኩኖ አምላክ በፊት
ከ1630 ዓመታት በላይ ሲነገር የነበረ ጥንታዊ ቋንቋ መሆኑን መናገራቸው ዐማራ ጥንታዊ ነገድ መሆኑን ያስረዳል ።
በአፄ ይኩኖ አምላክ ዘመን ዐማርኛ ቋንቋ ተጀመረ ማለት ፍጹም ተረታ ተረት ነገር ነው ። በአጤ ይኩኖ አምላክ
ጊዜስ ዐማርኛ ፈጽሞ ሠለጠነ ፤ ያማረ የተወደደ ፥ ጉሮሮ የማያንቅ ፥ ለንግግር የማያውክ ሁኖ ስለ ተገኘ ፣ የቤተ መንግሥት
ቋንቋ ሆነ እንጂ ንግግሩስ አስቀድሞ ከዚያ በፊት እጅግ ብዙ ዘመን የነበረ ነው ። አፄ ይኩኖ አምላክ የነበሩት እና የነገሡት
አሁን በቅርቡ በ6753 ዓመተ ዓለም በ1253 ዓ/ም ነው። … ያማርኛ ቋንቋ ከዚያ ዘመን ወዲህ ብቻ ተነገረ ማለት እንደ
ተረት ያለ የጨዋታ ታሪክ ነው ። ከዚህ አስቀድሞ ከ5200-6433 ዓመተ ዓለም ከአፄ ይኩኖ አምላክ በፊት ከ1630
ዓመት በላይ ዐማርኛ እንደ ነበረ ከፊተኛው ታሪከ ነገሥት ተጽፋል ። በዚህ ዘመን ውስጥ ከነገሡት አያሌ ነገሥታቱ ስም
በዐማርኛ ቋንቋ ነበረ ። ይህም ሊታወቅ ወረደ ነጋሽ አጎም ጉም አስጎምጉም ለትም ተላተም ዖደ ጎሸ አይዛር መራ ተክለ
ሃይማኖት ይገለጣል ይታያል ። ይኸ ሁሉ ስም ከምን መጣ ? ይህ ሁሉ ከግእዝ ከትግርኛ የማይገኝ ያማርኛ ስም ነው ። ነጋሽ
7
ደስታ ተክለ ወልድ ገጽ 938 ።
8
ዝኒ ከማሁ ደስታ ተክለ ወልድ አማርኛ መዝ ቃ ገጽ 939
9
ዝኒ ከማሁ
7
ጎሽ ይኸ የዓረብ ፊደል የዐማርኛ ቃል ነው እንጂ ግእዝ ሸ ኛ ጐ ጨ የሚል ቃል አንድ ስንኳ የለም ። በግእዝ ነጋሽ ነጋ ጎሽ
ሲል ጋሙስ ይላል ፤ ዓረቢ ፊደል ምንም የለበትም…። ብለዋል ። 10
7/ ሌላው በፕሮፌሰር መሥፍን የተጠቀሰው መጽሐፍ የአባ ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር የትግርኛ መዝገበ ቃላት
ነው ። በዚህ መጽሐፍ ዐምሐራ ለሚለው ቃል የተሰጠው ትርጕም «የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም» የሚል ነው ። ይህንን ትርጉም
ዐማራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ነው እንጂ ዐማራ የሚባል «አንድ ነገድ ወይም ጎሳ ወይም ዘመደ ሰብእ» የለም ለማለት
ፕሮፌሰር መስፍን ጠቅሰውታል ። በእኔ ግንዛቤ አባ ዮሐንስ አልተሳሳቱም ፤ ምክንያቱም ዐማራ የኢትዮጵ ሕዝብ ነውና ። ያ
ማለት ግን ትግሬ ዐማራ ነው ፤ ኦረሞ ዐማራ ነው ፤ ዐማራ የሚባል ሕዝብ በኢትዮጵያ የለም አልነበረም ለማለት አይደለም
። ለምሳሌ «ትግሬን» የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ብለው ቢተረጕሙት ፤ ኦሮሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ብለው ቢተረጕሙ
ትርጕሙን ማንም ሊቃወመው አይችልም ። ምክንያቱም እውነት ነውና ። ነገር ግን ኦረሞ የሚባል ነገድ የለም ፣ ትግሬ
የሚባል ነገድ የለም ካሉ ግን ሰው አይቀበላቸውም ። መዝገበ ቃላቱ የሚያሳየው ኢትዮጵያ የሁላችን መታወቂያ እና
መጠሪያ መሆኗን ነው ። የአባ ዮሐንስ መዝገበ ቃላት የሚያመለክተው አንደኛ ዐማራ በባህሉ በቋንቋው በኢትዮጵያ
መንግሥት ውስጥ በነበረው እና ባለው ተሳትፎ ሁሉን ለማስተሳሰር የቻለ ሕዝብ በመሆኑ ፤ ሁለተኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ
መሆኑን ነው የሚናገረው ። 11
8/ ሌላው በጵሮፌሠር መሥፍን እንደ መረጃ የቀረበው በ1901 የታተመው የአፈ ወርቅ ገብረ ኢየሱስ መጽሐፍ
ነው ። ጥቅሱን እንይ በመጀመሪያ «እስላሙን ታማራው ፣ ጉራጌውን ተሥልጤው ፣ጋላውን ከሻንቅላው አጋባው አዛመደው»
የሚለው ነው ። 12 ይህ ማለት ታዲያ ምን ማለት ነው ? በፕሮፌሰር ይህ ዐማራ የሚባል ነገድ ጎሳ የለም ለማለት
ይጠቀሳልን ? የኢትዮጵያን ሕዝብ ዝምድና ብቻ ነው የሚያመለክተው ፤ ምክንያቱም ክርስቲያን የሆነ ዐማራ ነገድ መኖሩን
ነው የሚጠቁመው ። በታሪክ እንደሚታወቀው ዐማራው ሁሉ ክርስቲያን ስለ ነበር ያንን ነው አጽንቶ የሚያሳየው።
9/ ሌላው መረጃ ዋሕድና ጦቢያ በሚል ርእስ በ1919 የታተመ በተባለው ልብ ወለድ ነው «እልፍ አእላፍ
አማራ ያሸብር የነበረ … አንበሳው ገርሞ በማተብ ታሰረ» የሚለው ኃይለ ቃል ነው ። 13
ይህም የሚያመለክተው የአንዱ ነገድ አርበኛ የዐማራውን እምነትና ባህል ተቀብሎ ፣ አምኖ ተጠምቆ ፣ ሥርወ
መንግሥቱ ክርስትና ለሆነው ለኢትዮጵያ መንግሥት ፣ ተገዥ መሆኑን ፤ ሽፍትነቱን ትቶ አማኝ መሆኑን ፣ የክርስና ትምህርት
የአንድ ነገድ ትምህርት ወይም ባህል ስላልሆነ ወደ ሁሉም መስፋፋቱን ነው የያመለክተው እንጂ ፥ አማራ የሚባል ነገድ
የለም የሚያሰኝ አይደለም ።
ብዙዎች እንደሚገምቱት ፥ እኔም ከፕሮፌሰር መጽሐፍ እንደ ተረዳሁት ፣ ዐማራ የሚባለው በኢትዮጵያዊነት
የሚያምን ሕዝብ ሁሉ ነው እንጂ አንድ የተለየ ነገድ ወይም ዐማራ የሚባል ሕዝብ የለም በሚል አገራዊ አንድነትን ለመስበክ
10 የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ 1914 ዓም ገጽ 51
11 መስፍን ወልደ ማርያም የክህደት ቁልቁለት 2003 ገጽ 121
12 ዝኒ ከማሁ ገጽ 122
13 ዝኒ ከማሁ
8
አስበው ይመስላል ። እኒህን ታላቅ ሰው ለአገር አንድነት በማሰባቸው እናከብራቸዋለን ። ነገር ግን ለአገር አንድነት እና ክብር
ጉልህ ተሳትፎ የነበረውን እና ያለውን ታላቅ ሕዝብ ህልውና መካድ መልካም አስተሳሰብ አይደለም ። ታሪክንም መፍራት
አይገባንም ። በኢትዮጵያ የለም አልነበረም መባል ያለበት ወያኔ የፈጠረው የዐማራ ክልል ፣ የትግራይ ክልል ፣ የዐሮሞ ክልል
፣ ወዘተ እንጂ ፣ ዐማራን ትግራይን ኦሮሞን ወያኔ አልፈጠራቸውም ። ኦሮሞ የለም ፣ ትግሬ የለም ፣ አፋር ፥ ሀድያ ፣ ከምባታ
፣ የለም ፣ ኩናማ ወዘተርፈ የለም ለማለት የማይቻል ከሆነ ፤ ዐማራ የለም ለማለት እንዴት ይቻላል ። እያዩ ያለማየትን ያህል
፥ እየሰሙ ያለመስማትን ያህል ይቈጠራል። አንድ አንድ ሰዎች ዐማራ የለም ካልን ሌሎች የዐማራን የበላይነት ታሪክ የሚፈሩ
ሰዎች የሕሊና ነጻነት ይሰማቸዋል ፣ ኢትዮጵያም አንድ ሁና ትኖራለች ብለው የሚያስቡ ይመስላል ። ነገር ግን መዋጋት
ያለብን ዐማራውን ሕዝብ ለማስጠላት የተዘራውን የጥላጫ ፕሮፓጋንዳ ነው።ዐማራ እንደ ሕዝብ ማንንም አለመበደሉን፣
የጸረ ዐማራ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሆነው ትውልድ ስለ ዐማራ ሕዝብ ውስጥ ስለላው ልበ ሰፊነት፣ የአብሮነት ስሜት
ማስተማር ነው የሚገባቸው ። ያለን ነገር ያለም ማለት ክህደት ነው። ክህደት ደግሞ መፍትሄ አይደለም።
ከነገድ ስምነት ባሻገር የዐማራ ግብር ፥ አኗኗር ና ማንነት የተገለጡባቸው መንገዶች ዐማራ የለም ለማለት መረጃ
አይሆኑም ።
=ዐማራ ማለት- «ክርስቲያን ማለት ነው» – ማለት ስሕተት አይደለም ። ሃይማኖታዊ ማንነቱን ያሳያል ፤ የዛሬውን
አያድርገውና ዐማራ ሁሉ ክርስቲያን ነበር ። እርስ በርሱ በአሳብ ሳይግባባ ሲቀር ይህን ካላደርግህ እንለያያለን ለማለት «እኔ
እና አንተ እስላምና ዐማራ» ይል ነበር። በሌላ አባባል ደግሞ ክርስቲያን ያልነበረ ሰው አምኖ ሲጠመቅ «እገሌ አማራ ሆነ»
ይባላል ። አባባሉ ክርስቲያን ሆነ ፣ የዐማሮችን ሃይማኖት ሃይማኖቱ አደረገ ለማለት ነው ። ይህም ከምንም በላይ ደስ
የሚያሰኘውን የዐማራውን ሕዝብ መንፈሳዊ ማንነት የሚያመለክት አገላለጥ ከመሆኑ ጋራ ፥ ዐማራ በእምነቱ በቋንቋው
የታወቀ ታላቅ ሕዝብ ወይም ነገድ እንደ ሆነ ነው የሚያመለክተው ። ክርስቲያን ያልነበሩት ሰዎች ክርስትናን መቀበላቸው
ከእነሱ ቀድመው የነበሩትን ክርስቲያኖች ክርስቲያን አይደሉም እንደማያሰኛቸው ፥ የዐማራውን ባህል ፥ ሃይማኖት ፥ ወግ ፥
ሥርዓት መገለጫቸው ያደረጉ ሰዎች መጨመራቸው እነሱን ዐማሮች ሆኑ ያሰኛቸዋል እንጂ ዐማራን የለም አያሰኝም ።
= ዐማራ ማለት «በደጋ የሚኖር ሕዝብ ማለት ነው»- ዐማራ በደጋ ብቻ ነው የሚኖር የነበረው የሚለውን
አባባል ለታሪክ ሰወች እንተወውና፤ ይህም አባባል አሰፋፈሩን የሚያመለክት ፣ የኑሮ ስልቱን ፣ የመኖሪያ አመራረጡን
አይተው ሰዎች ዐማራ በደጋ የዐየር ንብረት በከፍተኛ ቦታ የሚኖር ሕዝብ ነው ቢሉ፣ አሰፋፈሩን ያመለክታል ። ዐማራ የትና
እንዴት ይኖር እንደ ነበረ ቀደምት ባዩበት ቦታ የገለጡት የታወቀ ሕዝብ መሆኑን ያስረግጣል ያረጋጣል እንጂ ዐማራ የለም
አያሰኝም ። በእርግጥ ዐማራ የሚኖረው በደጋ ብቻ አልነበረም፤ በወይና ደጋ እና በቆላም ይኖር ነበር ። ይሁን እንጂ
ቤቱንም ሆነ ቤተ ክርስቲያኑን ከፍ ባለ ቦታ ላይ ይሠራና ይኖር ነበር ። ለዚህም አሁን ያለውን የዐማራ ሕዝብ አሰፋፈር
በመመልከት መረዳት ይቻላል ።
= «ዐማራ በማለት እና ኢትዮጵያዊ በማለት መካከል ልዩነት የለም» ለሚሉ 14 ይህ አባባል እውነት ነው ፣ ነገር
ግን ይህ ዐማራ የሚባል ታሪካዊ ሕዝብ የለም አልነበረም ወይም ከሌሎች ጋራ በመዳቀል ጠፍቷል የሚያሰኝ አይደለም ።
14 የጥፋት ዘመን 2008
9
ይህም የሚያሳየው ኢትዮጵያ የእኔ ናት ፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሕዝቤ ነው ብሎ የሚያምን ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ታሪክ የጎላ
ተሳትፎ ያለው ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ በማስተባበር እና በመተባበር ሉዓላዊት ኢትዮጵያን ለዚህ ትውልድ ከነክብሯ ያስረከበ
ሕዝብ መሆኑን ያመለክታል ። ባለታሪክ ሕዝብ መሆኑን ይገልጣል እንጂ ዐማራ የሚባል ሕዝብ የለም አያሰኝም ።
ለአገራችን ለሚያስቡና ለሚጽፉ ሁሉ የአንድን ሕዝብ ህልውና ክዶ የተለያየን ሕዝብ አንድ ለማድረግ ይቻላል
የሚል እምነት አይጠቅምም ። ይልቁንም ጎልቶ መነገር ያለበት ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሁሉም ኢትዮጵያውያን እጅ
ያለበት መንግሥት እንጂ የአንድ ነገድ መንግሥት አለመሆኑን ማሳየት ይበቃ ይመስለኛል ። ዐማራው ሕዝብ አሁን በሥላጣን
ላይ ያለው መንግሥትና የኦነግ ፕሮፓጋናዳ ሰለባ መሆኑን ታሪክ የሚረሳው አይመስለኝም ። መፍትሔው ብሔራዊ እርቅ
እንጂ መካካድ ስላልሆነ በመተማመን፣ እውነትን በመጻፍና በመናገር አራችንን ልንሠራ ይገባናል ።
ማጠቃለያ- ኢትዮጵያዊነት የሁሉም ማሰሪያ ልጥ ነው ። ኢትዮጵያዊነት ሕዝቦችን አንድ የሚያደርግ የተዋሕዶ
ባሕርይ ነው ። ዐማራ መቼም መች በኢትዮጵያዊነቱ አይደራደርም ። ከዚህ ጽኑ አቋሙ የተነሣ ዐማራነት ኢትዮጵያዊነት
ነው መባሉ ትክክል ቢሆንም ፥ ዐማራ የሚባል ነገድ የለም ማለት ግን በመረጃ የተደገፈ አባባል አይደለም ። ከቀረው
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋራ እየተባበረ እና እያስተባበረ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለዚህ ትውልድ አድርሷል ። ዐማራ
የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል ነው ። የራሱ የሆነ ቋንቋ ባህል ያለው ፣ ከራሱ ይልቅ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስቀድም
ማኅበረ ሰብእ ነው ። ከዚህ የተነሣ የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ የትግራይ ነጻ አውጭዎችና የኦሮሞ ነጻ አውጮች
(ኦነግ) እየተፈራረቁ ሲጨፈጭፉት ይኸው ሩብ መቶ ዓመት አለፈ ። ዐማራ በኢትዮጵያ ታሪክ ይኮራል ፣ በባህሉ ይኮራል ፣
የበታችነት ስሜት አይስማማውም ፤ ድሀም ቢሆን ሀብታም ነው ። አብሮነት ወጉ ፥ ሌላውን ማስቀደም መዐርጉ ፥ የሆነ
ሕዝብ ነው ። የክርስትና ሃይማኖቱ ፥ ኢትዮጵያዊነቱ ፥ ዐማራነቱ ማንነቱ ከሚገለጥባቸው ነገሮች ተቀዳሚወቹ ናቸው ።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ።
ይቆየን ።
መምህር ልዑለ ቃል አካሉ ዐለሙ (መጋቤ ሐዲስ)
Mhleulekal@gmail.com