ታኅሣሥ /2009

በየትም አገር፣ ሠለጠነም አልሠለጠነ፣ ሰው ሲያጠፋ በፖሊስ ተይዞ ፍርድ ቤት ይቀርባል፤ ፍርድ ቤቱ ክሱንና መከላከያውን ሰምቶና መርምሮ ፍርዱን ይሰጣል፤ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ መኖ ወደአለበት ማረፊያ ቤት ይወሰዳል፤ የወህኒ ቤት አዛዡ እስረኛውን ሲረከብ አግባብ ያላቸውን ሰነዶች በሙሉ አብሮ ይረከባል፤ ‹‹የሕግ እስረኛውን›› ለተወሰነበት ጊዜ በሕግ እየተንከባከበ ይጠብቀዋል፤ ያበላዋል፤ ያጠጣዋል፤ ለጤንነቱ የሚያስፍልገውን ሁሉ አቅሙ በፈቀደ መጠን ያደርግለታል፤ ከወዳጆቹና ከዘመዶቹ ጋር እየተገናኘ፣ ከሃይማኖት አባቶቹና ከጠበቆቹ ጋር እየተመካከረ ሕጋዊ ሰው ሆኖ ጠቃሚ የማኅበረሰሰቡ አባል እንዲሆን ጥረት ይደረጋል፡፡

‹‹ማረሚያ ቤት›› የሚለው ቃል ሌላ ትርጉም የለውም፤ እስር ቤቱን ወይም ወህኒ ቤቱን ስሙን በመለወጥ የአንድ አገርን ሕዝብ ለመደለል ወይም ለማታለል አይደለም፤ ጥፋተኛ ተብሎ የተፈረደበትን የሕግ እስረኛ ፍርድ ቤት ለወህኒ ቤት አዛዡ በአደራ የሚሰጠው እስረኛው ዕዳውን ከፍሎ፣ ተጸጽቶና ጸድቶ የማኅበረሰቡ አባል እንዲሆን ለማድረግ ነው፤ ማረሚያ ቤቱ ይህንን ሲፈጽም ለሕግ እስረኛውና ለማኅበረሰቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፤ ሰሞኑን የምንሰማው ይህንን የቆየና የተከበረ ሕጋዊ ሥርዓት የሚያፋልስና ማኅበረሰቡ ራሱን የሚያድስበትን መንገድ እየተዘጋ መሆኑን ነው፤ ተመስገን ደሳለኝ ፍርድ ቤቱ አደራ ከሰጠው መሥሪያ ቤት አለመኖሩንና ወዴት እንደተወሰደ ዘመዶቹ አያውቁም፤ አሮጊት እናቱና ወንድሞቹ በጭንቀት ላይ ናቸው፤ ይህ ከሕግ ውጭ በንጹሐን ሰዎች ላይ የተጣለ ንጹሕ ግፍ ነው፡፡

ማኅበረሰባችን ባሉት ተቋሞች ሁሉ — በፖሊሶች፣ በዓቃብያነ ሕጉ፣ በዳኞችና በማረሚያ ቤቱ አዛዦች — ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖረው ግዴታ ነው፤ አለዚያ መተማመንና መረዳዳት ከየት ይገኛል? የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሕግ እስረኞች ጋር ግንኙነት ያለው አይመስልም፡፡

ጊዜው ስሕተት እየታረመ መግባባት የሚፈጠርበት ነው እንጂ ስሕተት የሚፈለፈልበት አይደለም፤ ነገን እያሰቡ መሥራቱ ይበጃል፡፡

 

One Response