መግቢያ

 ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳ

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ አጭር ነው። በማይረባ ጉዳይ ከመወዛገብ ቁም-ነገሩ ላይ በማተኮር ዘላቂና የሚበጅ መፍትሔ እንዲገኝ ለመጠቆም ነው። መሠረታዊ ጉዳዩም የሚያጠነጥነው በኢትዮጵያዊነት ላይ በመሆኑ፤ የኔን የዜግነት ማንነት፤ ከሁሉም በላይ የሚገልጸው፤ ኢትዮጵያዊነቴ መሆኑን በቅድሚያ ለማረጋገጥ እወዳለሁ። ቢሆንም፤ በራስ ቁዋንቁዋና ባሕል የተመሠረተ ማንነት በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ስር በሰላምና በዲሞክራሲ ሥርዓት እስከ ተገለጸ ድረስ አከብራለሁ። ነገር ግን በአክራሪነትና በዘረኛነት የተዘፈቀና የዘቀጠ፤ የመለያየትና የመገንጠል አዝማሚያ የሰፈነበትን ጎሰኛነት እቃወማለሁ። አደገኛም ነው እላለሁ።

ውዝግቡ

ሰሞኑን፤ ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳ፤ “የኦሮሞና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” በተሰኘ አርእስት ስለ ደረሰው መጽሐፍ ብዙ ውዝግብ ተፈጥሩዋል። መጽሐፉ ውስጥ ከተካተቱት ነጥቦች ውስጥ አማራውና ኦሮሞው ከአንድ ቤተ ሰብ (ከኢትዮጵ) የተገኘ መሆኑን ለመግለጽ የቀረበው ሐተታ ይገኝበታል። የኢትዮጵያ ነገሥታትም ኦሮሞዎች ነበሩ ይላል።

ታዲያ፤ እንደዚህ ያለ ከዚህ ቀደም ከተመዘገበው የኢትዮጵያ ታሪክ ለየት ያለ ዘገባ ሲቀርብ፤ ስለ ምንጩ ጥያቄ መነሳቱ የማይቀር ነው። ዶር. ፍቅሬ የተጠቀመበት ዋናው ምንጭ መሪራስ አማን በላይ ሱዳን፤ ከቀድሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ መሀል የድንጋይ ሳጥን ውስጥ የተገኘ የብራና ጽሑፍ እንደ ነበረ ገልጹዋል።

በመሪራስ አማን ተገኘ ስለ ተባለው ጽሑፍ ግን አስተማማኝነቱ ብቃቱ ባላቸው ባለሞያዎች ባለመረጋገጡ፤ ስለ ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ የተከሰተው ውዝግብ እየተሙዋሙዋቀ ነው። ባንድ በኩል፤ እንደ ዶር. ጌታቸው ኃይሌና ዶር. ጳውሎስ ሚልክያስ ያሉ የታሪክ ምሑራን ሰከንና ጠለቅ ያለ የምርመራና የመፍትሔ ሐሳብ ሲቀርብ፤ በሌላ በኩል የኦሮሞውንና የአማራውን ዝምድና በዓይነ-ጭፍን የሚደግፉ ወይም የሚቃወሙ ሰዎች ውርጅባቸውን እያዥጎደጎዱት ነው። አባዜያችን ይሆን?

የኔ ገጠመኝና አቅርቤው የነበረ የመፍትሔ ሐሳብ

እንዳጋጣሚ ሆኖ፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት፤ መሪራስ አማን፤ ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳና እኔ፤ መሪራስ አገኘሁት ስላሉት ሰነድ ቴሌኮንፈረንሶች አከናውነን ነበር። መሪራስ በጊዜው በቃል የነገሩኝን፤ በሁዋላም “መጽሐፈ ሱባኤ ዘበአማን ካልዕ፤ እየሱስ ክርስቶስ በኢትዬጵያ (1998 ዓ/ም)” (ገጽ 374)፤ መጽሐፋቸው ባነበብኩት መሠረት፤ ክርስቶስ ለ3 ዓመቶች በኢትዮጵያ ኖሮ ብዙ ተአምሮችን አከናውኑዋል ስለ ተባለ፤ በአጥጋቢ ማስረጃ የሚደገፍ ከሆነ የዓለም ታሪክንና መጽሐፍ ቅዱስንም እንደ ገና የሚያስመለክት እጅግ ከባድ ግኝት መሆኑ ተሰማኝ። ስለዚህ ለመሪራስና ለዶር. ፍቅሬ ሰነዶቹ እንደ ዶር. ጌታቸው ኃይሌ ባሉ ባለሞያዎች እንዲመረመር ሐሳብ አቀረብኩ። መሪራስም ለጊዜው መልካም ፈቃዳቸው መሆኑን ስለ ገለጹልኝ ዶር. ጌታቸውን አማክሬው፤ እሱም፤ እግዚአብሔር ያክብረውና፤ ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን ገልጾልኝ መልካሙን ዜና ለመሪራስ ስነግራቸው፤ ሐሳባቸውን ለውጠው፤ ሰነዱን ለራሳቸው ጽሑፍ እንደሚጠቀሙበትና አስተማማኘነቱንም የማረጋገጡን ዓላማ ያልተቀበሉት መሆኑን ስለ ገለጹልኝ ጉዳዩ ተኮላሽቶ ቀረ።

ዶር. ፍቅሬም በመሪራስ ግኝት ሰነድ ተጠቅሞ የራሱን መጽሐፍ በመድረሱ፤ ስለ ምንጩ አስተማማኝነት ባነሳበት፤ ትክክለኛነቱን በሱ በኩል የተቀበለው መሆኑንና ሌላ ማረጋገጫ የማያስፈልገው መሆኑን ስለ ገለጸልኝ፤ ጉዳዩን በዚያው ለመተው ተገደድኩ።

የመፍትሔ ሐሳብ

ዶር. ፍቅሬ በጻፈው መጽሐፍ የተጠቀመበት ምንጭ አስተማማኝነቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ አወዛጋቢና ጥርጣሬ የሰፈነበት ሆኖ እንደሚቆይ ግልጽ መሆን አለበት። ነገር ግን፤ እውነቱ እንዲታወቅ ካልተፈለገ በስተቀር መሪራስ አገኘሁ የሚሉትን ሰነድ አስተማማኝነት ለማረጋገጥ ባሁኑ ዘመን በጣም ቀላል ነው፡፤ ባለሞያ የሆነው፤ ዶር. ጌታቸው ኃይሌ፤ ባስረዳኝ መሠረት፤ ለዚህ ጉዳይ ማረጋገጫ የሚጠቅሙት የሚከተሉት ሶስት ዘዴዎች ናቸው፤

1ኛ/ የብራናውን እድሜ (carbon-dating) መለካት፤

2ኛ/ የፊደሉን አጣጣል መመርመር፤

3ኛ/ የቀለሙን ዓይነት መመርመር።

በቀላሉ ሊጣራ የሚችለውን ጉዳይ በማያስፈልግና አጉል ውዝግብ መናቆሩ ለማንም ስለማይበጅ፤ ሰነዱም በእርግጥ ታሪካዊና አስተማማኝ ከሆነ የሐገር ብቻ ሳይሆን የዓለምም ቅርስ ሊሆን ስለሚችል፤ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ መሪራስንና ዶር. ፍቅሬ ቶሎሳን ተገቢ የሆነውን የማረጋገጫ እርምጃ እንዲወስዱ እንደ ገና በማክበር አሳስባለሁ።

ለማንኛውም፤ የብዙ ወይም የልዩ ልዩ ጎሳዎች ዝርያዎች የሆንን ሁሉ ማንነታችንን በኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ስሜትና አንድነት እስከ ገለጽንና ለዘለቄታው ተግባራዊ እስካደረግን ድረስ ውድ ሐገራችን፤ ኢትዮጵያ፤ ሰላም፤ ልማትና ዲሞክራሲ የሰፈነባት እንደምትሆን ጥርጥር የለኝም።

የኢትዮጵያ አምላክ ሐገራችንን ይባርክ።