ቅጽ 45፤ ቁ.1 ታህሣስ፤ 2009
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰላም አይገዛም!
በተለያዩ ዘመናት አገራችን ኢትዮጵያ በሯን ጥርቅም አድርጋ ዘግታ ከዓለም ተለይታ የኖረችበት ዘመን ሲሰላ ከዓለም ሥልጣኔ ተቋዳሽ ሳትሆን ወደኋላ እንድትቀር ምክንያት ሆኗታል የሚል የታሪክ ዕውነታ ተመዝግቧል። ለምሳሌ በ8ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን የአክሱም ሥልጣኔ መውደቂያና የዛጔ ሥርወ-መንግሥት መሸጋገሪያ ላይ፣ ለአምስት መቶ ዘመን ያህል ከዓለም ተለይታ በሯን ዘግታ የኖረችበትን ዘመን የታሪክ ፀሐፊዎች የጨለማው ዘመን ብለው ይጠሩታል። ከዚያም በኋላ አፄ ሱስንዮስን ከሥልጣን አስወግደው ዙፋኑን የወረሱት ልጃቸው አፄ ፋሲል፣ በአገራችን ውስጥ ለካቶሊክ ሃይማኖት መስፋፋት ምክንያት የሆኑት የውጭ አገር ስዎች ስለሆኑ ከእንግዲህ አንድም የውጭ ዜጋ በአገሬ መሬት ላይ እንዳላይ በማለት ጠራርገው ከኢትዮጵያ በማስወጣታቸው፣ አገራችን ኢትዮጵያ ከውጭው ዓለም ጋር ለብዙ ዓመታት ሳትገናኝ ኖራለች። በእነዚህ ሁለት የታሪክ ዘመናት ውስጥ በዓለም ላይ ብዙ ኅብረተሰብን የሚጠቅሙ አዳዲስ የሳይንስ ግኝቶች ቢፈጠሩም፣ አገራችን የዓለም ኅብረተሰብ ያገኘውን የሳይንስና የማኅበራዊ ኑሮ ውጤቶች ሳታገኝ መቅረቷ የማያጠራጥር ዕውነታ ነው።