በኦሮሚያ ክልል አምቦ ከተማ ዳግም ህዝባዊ ተቃውሞ መቀስቀሱ ተሰማ፡፡ ቢቢኤን እንደዘገበው ትላንት ከረፋዱ ስድስት ሰዓት አከባቢ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ የስርዓቱ ሰዎች የመሰረቱት የሰላም ባስ አክሲዮን ማኅበር አውቶቡስ ጥቃት እንደተሰነዘረበት ታውቋል፡፡ እንደዚሁም የህወሃት ንብረት የሆኑ ሶስት ተሽከርካሪዎች ህዝባዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ተብሏል፡፡

እንደ ቢቢኤን ዘገባ በከተማው የተቀሰቀሰው ተቃውሞ መነሻውን ያደረገው በአምቦ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ሲሆን፣ ተቃውሞዉ ቀጥሎም ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች መዛመቱን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሰረት ጮሪ፣ አዋሩ እና አዲስ ከተማ በተባሉ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተቃውሞ ተስተጋብቶ እንደነበር ታውቋል፡፡ በአደባባይ በተደረገው ህዝባዊ ተቃውሞ ላይም ‹‹ዶ/ር መረራን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፤ ወታደራዊ አገዛዝ ይብቃ፡፡›› የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮች መስተጋባታቸውን እማኞች ገልጸዋል፡፡

በተማሪዎች ምክንያት ዳግም ያገረሸውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመበተን የአጋዚ ሠራዊት ኃይል የተጠቀመ ሲሆን፣ መንገዶችም ለተወሰኑ ሰዓታት ተዘጋግተው እንደነበር ከስፍራው የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡ ተቃውሞዉን ለመበተን የተሰማሩት አጋዚ ወታደሮች ያገኙትን ተማሪ እና አስተማሪ አፍነው መውሰዳቸውም ተነግሯል፡፡ የኦሮሚያ ህዝባዊ ተቃውሞ ለተወሰኑ ጊዜአት በረድ ብሎ መቆቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ ትላንት በአምቦ ከተማ ዳግም የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎም በስፍራው ውጥረት መንገሱን ለማወቅ ተችሏል ሲል ቢቢኤን ዘገባውን ቋጭቷል::