ይኼው መጽሐፍ በቅርቡ እ.ኤ.አ. ከዲሴምበር 3 እስከ 5 ቀን 2016 በሱዳን በዋድ መዳኒ በተካሄደ ዓውደ ጥናት በድጋሚ የተመረቀ ሲሆን፣ ለመጽሐፉ አስተዋጽኦ ያደረጉ በርካታ አጥኚዎች ዓውደ ጥናቱን ታድመዋል፡፡ ዓውደ ጥናቱ በስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የውኃ ኢንስቲትዩት (ሲዊ)፣ በዓለም አቀፍ የውኃ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት (ኢውሚ) እና በሱዳን ኃይድሮሊክ ጥናት ማዕከል (ኤችአርሲ) በጋራ የተዘጋጀ ነው፡፡ ተመሪማሪዎች፣ ኤክስፐርቶች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የግሉ ዘርፍና ሚዲያንም ያሰባሰበ ነበር፡፡ መጽሐፉም ሆነ ዓውደ ጥናቱ ዋነኛ ጭብጥ ያደረጉት በናይል ተፋሰስ በተለይም በምሥራቃዊ ናይል የሚካሄዱ ግዙፍ የውኃና የመሬት ኢንቨስትመንቶችን ነው፡፡

ኤሚል ሳንድስትሮም ከመጽሐፉ ሦስት አርታኢዎች አንዱ ሲሆኑ፣ በመጽሐፉ ከተካተቱ ምዕራፎች በአንዱ እየተስፋፉ የመጡ የመሬት ኢንቨስትመንቶች በናይል ኃይድሮ ፖለቲካ ላይ ስለሚኖራቸው ተፅዕኖ በስፋት ይተነትናሉ፡፡ እንደ ሳንድስትሮም ገለጻ፣ ለመሬትና ለሠራተኛ በአንፃራዊነት ርካሽ ዋጋ የሚጠይቁ አገሮች በግብርና ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ የውጭ ኢንቨስትመንቶች የሚስቡ መዳረሻዎች ሆነዋል፡፡ ምንም እንኳን በአካባቢው የሚከናወኑ የመሬት ኢንቨስትመንት ስምምነቶችና በድንበር ዘለል ውኃ ማኔጅመንትና የውኃ አቅርቦት ላይ ስለሚኖራቸው ተፅዕኖ ያለው ትክክለኛ መረጃ ውስንነት ያለበት ቢሆንም፣ የኢንቨስትመንቶቹ ቁጥር ግን በፍጥነት እየተመነደገ ስለመሆኑ ጥርጣሬ የለም ይላሉ፡፡

በእንግሊዝ በሚገኘው ሱሴክስ ዩኒቨርሲቲ በዴቨሎፕመንታል ስተዲስ ኢንስቲትዩት የዶክትሬት ተመራማሪ ራሚ ሎትፊ ሃና ከመሬትና ከውኃ ጋር የተያያዙ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶችን ለአራት ይከፍሏቸዋል፡፡ እነዚህም በቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት (በግል)፣ በቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት (በመንግሥት)፣ በሁለት መንግሥታት ድርድርና በአገሮቹ የግል ባለሀብቶች የሚካሄዱ ናቸው፡፡

ከእነዚህ መንገዶች በአንዱ ወይም በሌላው በናይል ተፋሰስ በቅርብ ዓመታት ግዙፍ የመሬት ኢንቨስትመንቶች ተከናውነዋል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን፣ ግብፅን፣ ሱዳንንና ደቡብ ሱዳንን ባቀፈው የምሥራቅ ዓባይ ተፋሰስ አገሮች ይህ ይበልጥ ተጧጡፎ ቀጥሏል፡፡ የስንድስትሮም ጥናት እንደሚጠቁመው፣ እ.ኤ.አ. ከ2008 እስከ 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በምሥራቅ ዓባይ ተፋሰስ አገሮችና በኡጋንዳ የተከናወኑት ግዙፍ የመሬት ኢንቨስትመንቶች 4.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ሸፍነዋል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ የግብፅ መንግሥት ብቻውን በላይኛው ተፋሰስ አገሮች የፈጸማቸው ግዙፍ የመሬት ኢንቨስትመንት ስምምነቶች 1.7 ሚሊዮን ሔክታር መሬት የሸፈኑ ናቸው፡፡

ለእነዚህ የግብርና ሥራዎች የውኃ አቅርቦት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ቢሆንም፣ በእነዚህ ኢንቨስትመንቶች ድርድር የውኃ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ችላ የተባለ እንደሆነ የሳንድስትሮም ጥናት ያሳያል፡፡ በውሎቹ ለመሬቶቹ ስለሚቀርበው ውኃ ምንም የተባለ ነገር እንደሌለ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ይኼ በናይል ዙሪያ ባለው የውኃ ሀብት ጥያቄ ላይ ተጨማሪ ውስብስብ የሚያክል ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በዋድ መዳኒው ዓውደ ጥናት የቀረቡት ጥናቶች በአሁኑ ወቅት በተፋሰሱ እየተከናወኑ ያሉ የውኃ፣ የመሬትና የኢነርጂ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶችና ዘላቂነታቸው ላይ ያለው አለመመጣጠን የናይል ጉዳይን ይበልጥ እንዳያወሳስበው ሥጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ የናይል ተፋሰስ አገሮችን እየፈተኗቸው ያሉ ችግሮች ላይ ተጨማሪ ፈተና ሆኖ እንዳይቀጥል፣ እነዚህ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች በከፍተኛ ጥንቃቄ መመራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ጥናቶቹ እንደ ደመደሙት፣ ከእነዚህ ኢንቨስትመንቶች አስቀድሞም ቢሆን የውኃው መጠንና ጥራት እየቀነሰ ነበር፡፡ በዚህ ላይ የአየር ንብረት ለውጥና የሕዝብ ብዛት መጨመር ሲታከልበት ፈተናውን ይበልጥ ያወሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል በአካባቢው ለሚገኙ ጥቂት አገሮች የምግብ ዋስትና ሌላ አንገብጋቢ አጀንዳ ነው፡፡ የቀጣናው ደሃ አገሮች ዜጎቻቸውን ለመመገብና በሕይወት ለማቆየት በግብርና ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ ናቸው፡፡ በተለይ የምሥራቅ ናይል ተፋሰስ አገሮች ሕዝብ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ግብርና፣ የመስኖ ግብርናና በኃይድሮ ፓወር ላይ ጥገኛ ነው፡፡ ከዘርፉ ብዙ የግብርና ጠቀሜታዎች መካከል የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወት መሆኑ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሥራ ዕድል የሚፈጥርና የመሬት ዋጋን የሚጨምር መሆኑ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የውጭ ንግድን ለማስፋፋትና ለአካባቢ ጥበቃ ምቹ የሆነ ቢዝነስ ለማከናወን ያለው ቁልፍ ሚናም ቀላል አይደለም፡፡

እነዚህን የግብርና ሥራዎች ለማከናወን የሚያስፈልገው ውኃ ሁሌም ከዝናብ አይገኝም፡፡ በመስኖ የሚከናወነው የግብርና ሥራ ቁጥሩ ከፍተኛ ነው፡፡ ከውኃ አቅርቦት ጥናቱ አንፃር ሥጋት የሆነው በመስኖ የሚካሄደው ግብርና ነው፡፡ ለመስኖ ግብርና የሚውለው የውኃ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ፣ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች የሚፈሰውን መጠን ይቀንሳል በሚል ነው ሥጋቱ የሚመነጨው፡፡ በዓባይ ተፋሰስ አገሮች መካከል ባለው ድርድር የውኃ መጠን መቀነስ ከዋነኛ አጀንዳዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ የናይል የማዕቀፍ ስምምነት እንዳይፈረም ያደናቀፈው ጉዳይ የውኃ ደኅንነት መሆኑ ለዚህ ምስክር ነው፡፡

እንዲሁም ተጨማሪ የውኃ አቅርቦት ጥያቄ እየጨመረ እንደሚመጣ ይጠበቃል፡፡ ስለወደፊቱ ጊዜ ያሉ ትንበያዎች ይህ ጥያቄ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚመጣ ያሳያሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውኃና የመሬት ሀብቶች ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ጌጤ ዘለቀ፣ ‹‹እ.ኤ.አ. በ2050 የተፋሰሱ አገሮች የሕዝብ ቁጥር አንድ ቢሊዮን እንደሚደርስ ትንበያ አለ፡፡ ከእዚህ ሕዝብ መሀል 70 በመቶ የሚሆነው በከተማ አካባቢ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ለውኃ፣ ለምግብና ለኢነርጂ አቅርቦት ጥያቄ እ.ኤ.አ. በ2035 ወደ 1,170,328 ጊጋ ዋት በሰዓት እንደሚያድግ ይጠበቃል፤›› ብለዋል፡፡

ከውኃ እጥረትና ከጥራት መቀነስ ጋር ለተያያዘው ችግር ከፊል መፍትሔ ተደርጎ የሚወሰደው የኢንቨስትመንቶቹ ዘላቂነት ነው፡፡ ዶ/ር ጌጤ በተፈጥሮ ሀብቶች ማኔጅመንት ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ዘላቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ባለፉት አራት አሠርት የተፈጥሮ ሀብቶች ዘላቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ከፍተኛ ወጪ ቢወጣም፣ የመሬት መሸርሸር አሁንም በምሥራቅ ናይል ከፍተኛ ተግዳሮት ነው፤›› ብለዋል፡፡ የተገኘው ውጤት ግን ከተደረጉ ጥረቶች ጋር የማይጣጣም እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ኢኖሰንት ንታካናና የኢንትሮ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ ግን፣ ተቋሞቻቸው የተፈጥሮ ሀብቶች በዘላቂነት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ጌጤ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች ዘላቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ሥራው መጀመር ያለበት በዕቅድ ዝግጅት ወቅት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብና ባለሥልጣናት የፕሮጀክቶቹ ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ ለዚህ ስኬት ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በኤክስፐርቶቹ ዕይታ የዘላቂነት ጉዳይ በአገሮቹ በተናጠል ከሚሠራ ይልቅ፣ በትብብር ቢሠራ ተመራጭ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ለአብነትም ያህል ዶ/ር ጌጤ የመሬት መራቆት ምርታማነትን ከመቀነስ ባሻገር፣ የተፋሰሱን ባዮ ፊዚካል ጤንነት ስለሚጎዳ አገሮቹ በትብብር ሊሠሩ ይገባል ይላሉ፡፡ ዶ/ር ጌጤ በአንድ የዓውደ ጥናቱ ተሳታፊ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የመሬት ዘላቂነት ለማረጋገጥ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተጠይቀው ነበር፡፡ ‹‹ለምሳሌ ሱዳን ንፁህ ውኃን ከደለል ለመለየት በሚሊዮን ዶላሮች እንደምታወጣ እናውቃለን፡፡ ለፅዳት ይህን ሁሉ ወጪ ከማውጣት ለመሬት ዘላቂነት ይህን ገንዘብ በኢትዮጵያ ከፍታማ ቦታዎች ላይ ማውጣት ይቻላል፡፡ ይህ ምርታማነትን ያሳድጋል፣ አፈሩንም እዚያው ያስቀራል፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የዋድ መዳኒ ዓውደ ጥናት ተሳታፊዎች በሱዳን የሚገኙ ሁለቱን ትልልቅ የመስኖ ግብርና ኢንቨስትመንቶች ማለትም ረሃድ የግብርና ኮርፖሬሽንንና ዳል የመስኖ እርሻን ሲጎበኙ እንደተነገራቸው፣ ኢንቨስትመንቶችን ለማንቀሳቀስ ከሚያውሉት ወጪ ውስጥ 60 በመቶ ያህሉ ለካናል ፅዳት የሚውል ነው፡፡ የሱዳን ሲናርና ሮሰሪስ ግድቦች የመያዝ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰው በመሬት መራቆትና በደለል ምክንያት ነው፡፡

ይህ ቢሆንም ሱዳን በመስኖ የሚካሄድ ግብርናን ለማስፋፋት ያላት አቅም ግዙፍ ነው፡፡ በሲዊ የወሰን ተሻጋሪ ውኃ ማኔጅመንት ክፍል ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አና ኤሊሳ ካስካዮ፣ እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ የመስኖ ግብርና በሱዳን ትኩረት ተነፍጎት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ነዳጅ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ ነበር፡፡ ነገር ግን ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ተነጥላ ራሷን ከቻለች በኋላ ከነዳጅ የሚገኘው ገቢ በመቀነሱ አሁን ደግሞ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

ዶ/ር አና ከዚሁ ጎን ለጎን በዓለም ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ላይ እ.ኤ.አ. ከ2008 በኋላ የተከሰተው ለውጥና በግብርና ዘርፍ መሰማራት የሚፈልጉ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቶች መበራከት፣ ሱዳንን ዋነኛ መዳረሻ ማድረጉን ይጠቁማሉ፡፡ አሁን በሱዳን በመስኖ የለማው መሬት ከ1.2 ሚሊዮን እስከ 2.2 ሚሊዮን ሔክታር የሚገመት ሲሆን፣ ከአጠቃላይ መታረስ ከሚችለው መሬቷ አንድ በመቶ አካባቢ ብቻ የሚሆን ነው፡፡

የሱዳን የውኃ ሀብቶች ቴክኒካል ክፍል ሊቀመንበርና የቀድሞው የውኃ ሀብት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሰይፈልዲን አብደላ፣ ሱዳን ገና ጥቅም ላይ ያልዋለ የውኃና የመሬት ሀብቶች ባለቤት እንደሆነች ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን የሀብቶች አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ በርካታ ክፍተት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ይቀበላሉ፡፡

ዶ/ር አናም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ሱዳን በመስኖ ለማልማት ያሰበችው የግብርና ሥራ ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ ቢውል ቢያንስ በዓመት ተጨማሪ አሥር ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶ/ር አና ገለጻ የሱዳን የመስኖ ግብርና የማስፋፋት ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ሊተገበር የሚችለው፣ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የውኃ ማጠራቀሚያ መሠረተ ልማት ሲሳካ ነው፡፡ ምናልባትም ሱዳን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የምትሰጠው ድጋፍ ከዚሁ ዓላማዋ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ጥቂት የማይባሉ የሱዳን ባለሥልጣናት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በሱዳን የሚከናወነውን የመስኖ እርሻ በእጥፍ ለማሳደግ እንደሚጠቅማቸው ያምናሉ፡፡ ግድቡ የውኃውን ፍሰት ለመቆጣጠርና ለመስኖ ግብርናው የውኃ አቅርቦት እንዲጨምር በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ሳይንሳዊ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

በተመሳሳይ ዶ/ር አና ግድቡ ሱዳን ውኃ ከመልቀቅና ከማከፋፈል አንፃር የምትወስዳቸው ውሳኔዎች የተሻሉ እንዲሆኑ በማስቻልም ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ጠቅሰዋል፡፡ ያልተጠበቀ እጥረት ቢፈጠር መፍትሔ የሚሰጥም እንደሆነ አክለዋል፡፡

ከሱዳን በተቃራኒ በኢትዮጵያ የመስኖ እርሻ በገበሬዎች የተወሰነ እንደሆነ፣ በኖርዲክ አፍሪካ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አታክልት በየነ ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና ከኢትዮጵያ መሬት ውስጥ 74.3 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነው ለግብርና የተመቸ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ አነስተኛ ገበሬዎች 14.6 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነውን ብቻ እንዳለሙም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የመንግሥት ይፋዊ መረጃ እንደሚያሳየው 4.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በመስኖ መልማት የሚችል ነው፡፡ አሁን የለማው አንድ ሚሊዮን ሔክታር ብቻ ነው፡፡ ዶ/ር አታክልት የመስኖ ማኔጅመንት ሽግግር የግብርና ፖሊሲው አካል የሆነውና ወደ ተግባር የገባው በቅርቡ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

አዲሱ ስትራቴጂ የሚበረታታባቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ዶ/ር አትክልት ያስረዳሉ፡፡ ለአብነትም ለድህነት ቅነሳ፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለአረንጓዴ ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ቁልፍ መሣሪያ በመሆን ሊያገለግል እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ የከተማ ነዋሪና የኢንዱስትሪ ፍላጎቶችን በአግባቡ የሚረዳ አምራች ለመፍጠርም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር አትክልት በጣና ሐይቅ ተፋሰስ የሚገኘው የቆጋ ግድብና ግዙፍ የመስኖ እርሻ 10,000 የሚጠጉ አነስተኛ አርሶ አደሮችን እንደሚያሳትፍ አመልክተዋል፡፡

ከዚህ በተቃራኒ በጋምቤላ ግዙፍ የእርሻ ኢንቨስትመንቶች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መዘፈቃቸው ይነገራል፡፡ በሊንድ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል የፒኤችዲ ተማሪ የሆኑት አቶ ወንድወሰን ሚጫጎ፣ ሁሉም ማለት በሚቻል ሁኔታ ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ በጋምቤላ 11 ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች፣ በርካታ የኢትዮጵያ ዜጎችና በውጭ አገር ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን የተሰማሩ ቢሆንም የአካባቢው ተወላጆች በባለሀብትነት እንዳልተመዘገቡ አቶ ወንድወሰን ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ወንደወሰን ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ምክክር አለመደረጉና በውሳኔ አሰጣጡ ተሳታፊ አለመሆናቸው፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲማሩና እንዲሠለጥኑ በቂ ዕድል አለመሰጠቱ፣ የተፈጠረው የሥራ ዕድል እጅግ አነስተኛ መሆን፣ የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸውን ከባንክ ብድር ለማግኘት ብቻ የተጠቀሙ ሐሰተኛ ባለሀብቶች መገኘት፣ ጣውላ በማምረትና በመሸጥ ሲሳተፉ የተገኙ ሕገወጥ ባለሀብቶች መገኘት በጋምቤላ ግዙፍ የግብርና ኢንቨስትመንቶችን ስኬት እንቆቅልሽ እንዳደረገው አቶ ወንድወሰን ዘርዝረዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የቀረቡ በርካታ ጥናቶች እንዳመለከቱት በምሥራቅ ናይል የሚገኙ የመሬት፣ የውኃና ኢነርጂ ኢንቨስትመንቶች መፃኢ ዕድል የተፋሰሱ አገሮች የትብብር አቅጣጫን የሚወስን ነው፡፡ የተሻለ ውሳኔ በመወሰን የአካባቢውን ሕዝቦች ኑሮ ለማሻሻል ሳይንሳዊ ዕውቀትና ጠንካራ ማስረጃ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነም አስምረውበታል፡፡ ይህን ለማሳካትም አገሮቹ ዕቅድ ሲያወጡም ሆነ ሲፈጽሙ ቀጣይነት ያለው ምክክር ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሰይፈልዲን አገሮቹ በተናጠል ፕሮጀክቶችን ማቀድና መፈጸም ከቀጠሉ፣ ያለው ውኃ በስኬት ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም እንደማያስችልም አስጠንቅቀዋል፡፡ እንደ እሳቸው እምነት ናይል በኃይድሮ ፓወር፣ በመስኖ፣ በትራንስፖርቴሽንና በቱሪዝም የአገሮቹን ራዕይ ማሳካት የሚችለው በትብብር ከተመራ ብቻ ነው፡፡

‹‹የናይል ውኃ በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ምን እንደሚሆን በአጠቃላይ መረዳት ካልቻልንና የትኛውም ዕርምጃ በናይል ላይ የማይቀለበስ ጉዳት እንደሚያስከትል ካልተረዳን ትልቅ ችግር ላይ እንወድቃለን፡፡ የናይል ወንዝ ሳይንስን በአግባቡ አልተረዳነውም፤›› ሲሉ ፕሮፌሰር ሰይፈልዲን በጋራ የመሥራት ጊዜው ለነገ የሚባል ሳይሆን አጣዳፊ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል፡፡