ያልተላከ ደብዳቤ

  “የከሸፈ ደብዳቤ!” ልለው ፈልጌ ተውኩት። ሳይቀባበል አይከሽፍምና ነው! “ከራስ ጋር             መነጋገርና ት ዝ ብ ት!” ብዬ ጽፌ የነበረውን አይታችኋል ብዬ እገምታለሁ። እዚያ ላይ           በነሐሴ ወር 2008 አንድ “ለመነሻ” የሚሆን ረቂቅ (Preliminary Draft) አዘጋጅቼ     ለዚህ ይመጥናሉ ለምላቸው አስራጭቼ ነበር። ሊኖርን ከሚችሉት አማራጮች አንዱ          አድርጌ ነበር ያየሁት። ከዚያ “ቄሱም ዝም! መጽሐፉም ዝም!” ሆነብኝ።          እንድታውቁት ያክል እንዳለ አሁን ይኸውና አውጣሁት

ግልጽ ደብዳቤ

ለአቶ አባዱላ ገመዳ  የኢትዮጵያ ፈደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሬፑብሊክ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ  ለአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ  የኢትዮጵያ ፈደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሬፑብሊክ ጠቅላይ ሚኒስቴር  አዲስ አበባ ፣ ኢትዮጵያ

መነሻችን

ይህ የፖለቲካ ደብዳቤ አይደለም! የዚህ ግልጽ ደብዳቤ ምክንያውቱም፤ ዓላማውም አንድና አንድ ብቻ ነው። “ኢትዮጵያን፣ የጋራ ቤታችንን”፣ ከዚህ ካጠለለባት የውድቀት ጽልመት እንዴትና በምን ዘዴ ልናድናት እንችላለን?” ብሎ ለመመካከር ብቻ ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ዋና ፖለቲካ “አገር ማዳን!” ነው ብለን በጥብቅ እናምናለን። ፖለቲካው፤ በኛ አስተያየት፤ “እዬዬ ሲዳላ ነው!” እንደሚባለው ነው። ኢትዮጵያን ከደርሰችበት ቋፍ ከመለስናት በኋላ እንደርስበታለን። አጉል አባባል ሆነና ነው እንጅ ዝንጅሮ “መጀመሪያ የመቀመጫዬን!” ብላለች እንደሚባለው መሆኑ ነው። መላው ሰውነቷ እሾህ ተስግሰጎባት ያለችው ነው። ከዚህ ሌላ ግብ እንደሌለን ልንረጋግጥላችሁ እንወዳለን

ምክንያታችን  እንደሚያውቁት፤መላው ዓለምም እንደሚያየውና እንደሚያውቀው፤ ኢትዮጵያ፤ “የጋራ ቤታችን”፣ በተለይም ላለፈው አንድ ዓመት ምጥ ላይ ነች። የምጡ፣ የጭንቁ ሁኔታ ከቀን ወደቀን እየባሰ መሔድ ብቻ ሳይሆን የብዙኃን ወገኖቻችን፣የሕጻናነት ሳይቀር መጥፊያ ሆነ። ከዛሬ ነገ ይቆማልየሚል አይነት ተስፋ እንዳናደርግም የመፍትሔ ጮራ፣ ጭላንጭሉ እንኳን አድማስ ላይ ቀርቶ ከአድማስ ባሻገርም አልታይ አለን። ይህ ጨልሞ መታየት ነው ይህንን ድብዳቤ እንድንጽፍላችህ የገፋፋን። ሰው የመሆንና የዜግነት ግዴታ ነው!

ከኛ የተሻለ እንደሚያውቁት ይህ ችግር እያደገ እየባሰበት ይመጣ እንጅ ድንገት ከሰማይ ዱብ ያለ አይደለም። ስሙ በግልጥ እንደሚያውጀው ኢትዮጵያ ዲሚክራሲያዊት ሬፑብሊክ ነች። ይህ ማለት ደሞክራሲ ያለባት አገር ማለት ነው። ሕገመንግሥቱም ይህንኑን ያረጋግጣል።ደሞክራሲ ማለት ደግሞ የተለያየና የተለየ ሀሳብና ዕምነት ያላቸው ለአገር ይህ ይበጃል የሚሉ፤ በግልም ፤ ድርጅትም መስረተው ተወዳድረው ያሸነፋሉ ወይም ይሸነፋሉ ማለት ነው።ጋዜጦችም ኖረው በነጻ የሚሰማቸውን ይጽፋሉ ማለት ነው።ይህ ማለት ደግሞ በአጭሩ ለኢትዮጵያ የሚበጃትን አንድ ብቸኛ ዕውነት ለብቻው በሞኖፖል የያዘ ወይም የተሰጠው ግለሰብም ሆነ ድርጅት የለም ማለት ነው።

Page 2 of 3

ከዚህ መሠረታዊ የደሞክራሲ ትርጉም የማይስማማ ሁሉ ደሞክራሲ በዋለችበት አምባ ዝርም አላለም እንደማለት ይሆናል። ተቃዋሚ የሚባሉድርጅቶችና መሪዎቻቸውተሸንፋችኋል መባል ብቻ ሳይሆን መሳተፋቸው ወንጅል ሆኖ ባቸው ወህኒወረዱ። የጋዜጠኞቻችን እጣ ፋንታ ይኸው ሆነ። መተንፈሻ መላዋሻ አጣን የሚሉ ጠበንጃ ወደማንሳት አመሩ። የእስልምና እምነትት ተከታዮችም ፈጠራ በሚመስል ምክንያት ወህኒ ወረዱ።ይህ ለማንኛችንም አይበጅም። አለመበጀት ብቻ ሳይሆን ጉዳቱን መመጠን እንኳን አይቻልም!

እንደሚያውቁት ላለፈው አንድ አመት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ አመፀ። ባለፈው አንድ አመት ማለታችን በኦሮምዎች ተጀምሮ አሁን መላውን የአማራ ብሔረሰብ የጨመረውን ለመጥቀስ ነው:: እንጅ በተለያየ ደረጃና መጠን አመፁ ላለፈው 25 አመት ተግና ጋብ ያለበት ጊዜ አልነበረም። መንግስትም ባለፈው 25 አመታት ያገኘው ብቸኛ መፍትሔ ቢኖር ጠመንጃ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ መፍትሔ አለመሆኑን መንግስትም የሚረዳው ይመስለናል። ያም ካልሆነደግሞን አልበርት አንስታትይን ብሏል ወደተባለው ይወስደናል። “እብደት ማለት ያንኑ አንድ ዘዴ ሽ ጊዜ መደጋገምና ግን ከዚያ ለየት የለ ውጤት አገኛለሁ ብሎ መጠበቅ ነው!” ብሏል (Insanity: Doing the same thing over and over again and expecting different results) ይህ ልናጤው የሚገባ መሠረታዊ ነጥብ ነው። እዚያ አለደረስንም! መድረስም የለብንም ብለን በፅኑ እናምናለን!

ተፈላጊው ነጥብ  በዚህ የጭንቅ ሰዐት ከእናነት የሚፈለገው “ቀና አስተሳሰብ!፤ መልካም ፈቃድና የአገር ፍቅር” ብቻ ነው። እነዚህ ካሉ፤ዛሬ ዓለማችን በደረሰበት ደርጃ ግጭትን ከግለሰብ ጀመሮ፤ በቤተሰብ፤ በመንደር፤ በመንግስትና ተቃዋሚ፤ በመንግስትና በሕዝብ፤ብሎም በመንግስታት መካከለል ለሚነሱ ችግሮች መፍትሔ ሰጭዎች (Conflict Resolution) ብዙ ግለስቦች ደርጅቶችና መንግስታት እንዲሁም ባለሙያዎች ሞልተው ተረፈዋል። አገልግሎታችውን ለመስጠትም ፈቃደኞች ናቸው። እንዳልነው ዋናው ነገር የሚጠበቅብን ቀና አስተሳሰብ፤ መልካም ፈቃድና የአገር ፍቅር ብቻ ነው። የማፈላለግ ጉዳይ እንጅ እንዚህን ትምህርትም፤የስራ ልምድም ተፈጥሮም ጭምር ለግሶናል!!

የምፍትሔው ችግር ምንጭ  የመንግስትዎን ችግርም የምንረዳ ይመስለናል። እንደሚያውቁት በዛሬዉ ዘመን የመንግስት ሚስጥር የሚባል ነገር የለም። በተለይም ይህ መንግሥት ምስጢር የለውም።ሁለንተናው የተሠራው በአደባባይነው! በዚህ ላይ መንግስት ከምስረታው ጀምሮ ለተወሰነ ግብ በ”ይድረስ ይደርስ!” የተመስረተ ስለነበር በውስጡ እኩለነትና አንድ አካል አንድ አምሳል የመሆን ነገር አልንበረውም።ፈታኝ ቀን ሲመጣ የተፍረከረከ ይመስለናል:: ከዚህ የተነሳ ጭምር ይመስለናል መንግስትዎ” በአንድ አፍ” አይናገረም። ይሕም የበለጠ የሚያባብስ ከመሆኑም ሌላ መፍትሔውን ያዘገየዋል። ዘገዬ አልዘገዬ እንደሚታየው አዝማሚያው መፍትሔ በግድም ያለውድ ወደማምጣት ያዘነበለ ነው!

ሌላው፣ የምንግስትዎን መሠርታዊ ፍርሐትም የምንረዳ ይመስለናናል። ፍርሐቱ “ነገን መፍራት!” ይመስለናል ። “ነገ” ደግሞ ፈሩም አልፈሩም መምጣቱ አይቀረም!። “ከአዳኙ ለመሰወር አንገቷን አሸዋ ውስጥ ቀበረች!” እንደሚባለው የሰጎን ተረት አይነት መሆኑ ይመስለናል። አንገቷን ትቅበር እንጅ ይህ የአዳኙን ፍጥነት ሆነ ፍላጎት የሚገታው አይደለም። “እንቅልፍ ተፍርቶ ሳይተኛ አይታደርም!”ም ይባላል።

የበለጠ መዘባበቻ እንዳንሆን

በድርቅና በድህነት ተመጽዋችነታችን የመላው ዓለም መዘባበቻ ሆነን ኖረን። በፖለቲካ አለመረጋጋት መናንወጥ ከጀመርን ይሔው ወደ 50 አመት እየተጠጋን ነው።

Page 3 of 3

ኢትዮጵያ ታሪካዊ አገር ነች። ዛሬ በዓለም ላይ በዲፕሎማቲክ መልእክተኞች ብዛት ከኒዮርክና ከዥነብ ለጥቆ ሶስተኛው አገር ኢትዮጵያ ነች። የ አፍርቃ አንድነትና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ዋና መስሪያ ቤት የሚገኘው አዲስ አበባ ነው። ያለምክንያት አልንበረም። ኢትዮጵያ ስለሆነች ነው። ይህ ሁሉ መንግስታት እያዩን እየተዘቡን ነው።

የውስጥ ችግራቸውን በጨዋ ደንብ ተነጋግረው መፍታት ያልቻሉ የት እንደደርሱ የምናውቀው ነው። ዩጎዝላቢያ ይባል የነበረው አገር ብጥቅጥቁ ወቷል። ሶማሌን እዚህ ጓሯችን የምናየው ነው። ሶሪያ በፍጥነት ወደዚያ እያመራች ነው። ይህ ሁሉ የሚሆነው ቁጭ ብሎ ለመነጋገር ባለመቻል ነው። “አንተም ተው!አንቺም ተይ!” ተው የሚል መጥፋትና ማጣት ነው። ሰሚም ማጣት ነው! የጋራ ቤታችን ይህ ዕጣ ፋንታው እንዲሆን አንፈልግም። የዚህ ደብዳቤ ዋና አላማ “አንተም ተው! አንችም ተይ!” ብሎ መነጋገር/ማነጋገር ለመፍጠር ነው።

መፍትሔው  መፍትሔው ክብ ጠረጴዛ ብቻ ነው! እንዳልነው ለተለያየ አይነት ወዝግብ መፍትሔ መፈለግ (Conflict Resolution) አዲስና ዛሬ እኛ ሀ ብለን የምንፈጥረው አይደለም።የታውቁ ፤ የተመሰከረላቸው የተረጋጋጡ መንግዶችና ዘዴዎች አሉ። ክቡ ጠረጴዛ የት ነው የሚዘረጋው? ልን ነጋገርበት እንችላለን!ክቡ ጠረጴዛ ዙሪያ ማንና እነማን ይቀመጣሉ? ያንንም ልንወያይበት እንችላለን!።መቼ? የሚለው ግን አጣዳፊ ነው።ከላይ እንደገለጽነው ዋናው ነገር በጎ ፈቃድ ማሳየት ብቻ ነው ።ያ ካልሆነ “ሳይሞከረ የቀረው አማራጭ!” ጸጸት ሆኖ እስከወዲያኛው ከኛም ከታሪካንም ጋር ተመዝግቦ አብሮን ይኖራል!!

ይህንን ማመቻቸት እንድንችል በሩን እንድትከፍቱ “በጋር ቤታችን!” በኢትዮጵያ ስም በብርቱ እንጠጥይቃለን!

ከአክብሮት ጋር

አሰፋ ጫቦ ነሐሴ 2008 ዓም

December 28, 2016

Source     –   Ethiomedia