Wednesday, 28 December 2016 14:12
 የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ከመንግስት ባለስልጣኖች ጋር ለመወያየት የመጡት የአሜሪካው የሰብዓዊ መብቶች ረዳት ሚኒስትር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር የመተማመን ፖለቲካ ላይ እንዲደርሱ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ምክር መለገሳቸውን የሰንደቅ ምንጮች ገለፁ።

አሜሪካዊው የሰብዓዊ መብቶችና የሥራ ረዳት ሚኒስትር ቶም ማሊኖውስኪ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ካደረጓቸው ውይይቶች በተጨማሪ በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት ከመድረክ፣ ከመኢአድ፣ ከኢዴፓ እና ከሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ጋር የጎንዮሽ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል።

በውይይቱ ላይ ታሳታፊ ከነበሩ መካከል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ለሰንደቅ ጋዜጣ ውይይቱን አስመልክተው እንደተናገሩት፣ “በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል ገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ምህዳሩን እንዳጠበበው እና የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችም ጥሰቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አንስተዋል” ብለዋል።

እንዲሁም በውይይቱ ላይ ረዳት ሚኒስትሩ ቶም ማሊኖውስኪ በመድረኩ ላይ  ያንጸባረቁትን፣ “የኢትዮጵያ መንግስት አሁን ላይ የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት የሄደበትን ርቀት ተመልክተናል። ቁርጠኝነት እንዳላቸውም ገልጸውልናል። እኛም አበረታች ነገሮች ተመልክተናል። ተቃዋሚው ጎራውም ከክስና ከስሞታ ተላቆ መተማመን እና መቀራረብ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት አለበት” ማለታቸውን ነው።

ከዶክተር መራራ ጉዲና መታሰር ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ ረዳት ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ፣ “የዶክተሩ መታሰር ከፖለቲካ ጋር ሳይሆን ከሕግ ጋር እንደሚገናኝ ተነግሮናል። በዚህ የውስጥ ጉዳይ የምንለው ነገር አይኖርም። ከአውሮፓ መልስ የተያዙ በመሆናቸው የአውሮፓ ሕብረት የበለጠ ጉዳዩን ያውቀዋል ብለዋል።”

የአሜሪካን ልዑካን በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ አንገባም እያሉ፣ የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዝደነት ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ዶናልድ ጄ. ትራምፕ በማሸነፋቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ተቃዋሚዎች ተደስተዋል ብለው አስተያየት መስጠታቸው በዲፕሎማቶቹ እና በተቃዋሚ ፓርቲ አባሎች ዘንድ ትዝብት ላይ የጣላቸው መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ የመድረክ እና ሌሎች የፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች በአውሮፓ ሕብረት ጽ/ቤት ከአንዳንድ የአውሮፓ ሕብረት ተወካዮች ጋር መወያየታቸው ታውቋል። እንደሰንደቅ ምንጮ ገለፃ በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ከነበሩ አንዳንድ የተቃዋሚው ፓርቲዎች ተወካዮች “በዶክተር መራራ ጉዲና መታሰር የአውሮፓ ሕብረት ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ለሕብረቱ ተወካዮች” አስታውቀዋል። የአውሮፓ ሕብረት ተወካዮች በበኩላቸው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በቀላሉ የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ማሳረፍ ከባድ መሆኑን ገልጸዋል። ጉዳዩም የተያዘው ከሕግ ጋር መሆኑን መንግስት እየገለጸ ባለበት ሁኔታ ጫና ማሳደር በውስጥ ጉዳያቹ መግባት ሊሆን ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን መግለፃቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።

የአውሮፓ ሕብረት ተወካዮች ሰማያዊ ፓርቲ አለመገኘቱን ደጋግመው ማንሳታቸው ያበሳጫቸው ተሳታፊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሰጡት ምላሽ “አጠገባችሁ ላቀረብነው ችግር ትኩረት ሳትሰጡ ሰማያዊ፣ ሰማያዊ ማለታችሁ አግባብ አይደለም” ሲሉ ወቀሳ ማቅረባቸውን ታውቋል።

ስንደቅ