ደረጀ ተፈራ

(ታህሳስ 23/2009 .)

……………………………………………….. 

በሚሊዮን የሚቆጠር እድሜ ያስቆጠሩ የሰው ልጅ ቅሪተ አካላት የተገኙባት የበርካታ ቋንቋዋች፣ ባህሎችና ታሪኮች ባለቤት የሆነችው ሃገራችን በአንድ ጀንበር ወይም ንጉስ ትእዛዝ በድንገት የተከሰተች ሳትሆን በርካታ ማህበራዊ፣ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ውጣ ውረዶች አልፋ፣ በብዙ እልልታና ኡኡታ መሃል ተረግዛና ተምጣ የተወለደች ናት። እኛ በምንገኝበት በዚህ ዘመን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ በከተማና በገጠር ባጠቃላይ በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከየት ተነስቶ አሁን ላለበት የአሰፋፈር፣ የእምነት፣ የባህልና የቋንቋ ሁኔታ እንደበቃ ለመረዳት ጥልቅ ጥናትንና ማስተዋልን ይጠይቃል። ከስነ ፍጥረት እስካሁን ሃገራችን ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው ታሪክ ተወርቶና ተጽፎ ባያልቅም ቢያንስ ቢያንስ ያለፉትን 500 ዓመታት በሃገራችን የተከናወኑ ዋና ዋና ክስተቶችን ቆንጥረን ብንመለከት የመጣንበትን የታሪክ መስመር በትንሹም ቢሆን ግንዛቤ ይሰጠናል።

 እንደሚታወቀው የሰው ልጅ በዚህች ዓለም ተፈጥሮ በሁለት እግሩ ቆሞ መራመድ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የእድገት ደረጃዎችንና ማህበራዊ ለውጦችን አሳልፏል። ለምሳሌ በድሮ ጊዜ ከተሞች ሳይመሰረቱ፣ ኢንዱስትሪዎች ሳይቋቋሙ የሰው ልጅ ህይወቱ (ኑሮው) ቀጥታ ከተፈጥሮ ጋር ግንኙነት በነበረበት ጊዜ በአንድ በተመሳሳይ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚገኝን የተፈጥሮ ሃብት በጋራ እየተጠቀሙ በጉርብትና የሚኖሩ የተለያዩ ማህበረሰቦች በውስጣቸውም ሆነ እርስ በርስ በሚያደርጉት ግንኙነት የሚከሰቱ ማህበራዊ ለውጦችና እድገቶች አሉ። በግብይት፣ በጋብቻና በመሳሰሉት መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ሁሉ በውሃ፣ በከብቶች ግጦሽ መሬት ጥበት እና በተለያዩ ምክንያቶች በመሃላቸው ግጭት ሊከሰት ይችላል። ለምሳሌ ከዛሬ 500 ዓመት አካባቢ ከሁኗ ሃረር ከድሮዋ አዳል የተነሳው አህመድ ግራኝ በቱርክ ቀጥተኛ ድጋፍ እየተደረገለት ሃገራችንን ከላይ እስከ ታች በጦርነት በማመስ ለበርካታ ሰዎች መፈናቀልና መሰደድ ምክንያት ሆነ።

 አህመድ ግራኝ ከቱርክ በርካታ የመድፍ፣ የነፍጥ እና የታጠቁ የአረብ ወታደሮች እርዳታ ያገኘበት ዋናው ምክንያት የኦቶማን ቱርክ ገዢዎች በሮማን ኢምፓየር ሞዴል ቀይ ባህርን፣ ግብጽንና ሱዳንን አካቶ የአረብ ሃገራትንና ምስራቅ አፍሪካን በአንድ ላይ በማድረግ የኦቶማን ቱርክ እስላማዊ ኢምፓየር ለመመስረት በነበራቸው እቅድ መሠረት ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ነበር። በመሆኑም የአማራ ነፍጠኞች በአፄ ልብነ ድንግል መሪነት ደማቸውን ያፈሰሱት በአህመድ ግራኝ ጀርባ ታኮ ኢትዮጵያን ቀኝ ለመግዛት የመጣን የኦቶማን ቱርክን ተስፋፊ ሃይልን በመመከት የሃገርን ነጻነት ለማስከበር ነበር። ከ14 ዓመታት በላይ የተደረገው ጦርነት የተጀመረው በ1522 .ም በናዝሬት አዳማ አካባቢ ሽንብራ ቆሬ በሚባል ቦታ ሲሆን የተጠናቀቀው ደግሞ በ1536 .ም በጎጃም ጣና አካባቢ ወይና ደጋ በሚባል ቦታ አህመድ ግራኝ ከተገደለ በኋላ ነው። አህመድ ግራኝ የተገደለው ከፓርቹጋሎች በተገኘ እገዛ ቢሆንም እነሱም ቢሆኑ ኢትዮጵያን ካቶሊክ ለማድረግ በመፈለጋቸው የዚህች ሃገር ፍዳ ተሸካሚ የሆነው “የፈረደበት” የአማራ ህዝብ በርስ በርስ ጦርነት ዳግም ደሙ እንደ ጎርፍ ፈሰሰ። ብዙዎች ሰማእትነት አያምልጥህ እያሉ በሽቅድድም ህይወታቸውን ገበሩ። በቱርክ አዝማችነት አህመድ ግራኝ በከፈተው የጀሃድ ጦርነትን ውልቅልቁ የወጣው ዘውዳዊው መንግስት ዳግም እንደ መንግስት ለመቆም በሚውተረተርበት ሰዓት የሰው ልጅ መገኛ፣ የተለያዩ ቋንቋዎችና ባህሎች መፈጠሪያ የሆነችው እማማ ኢትዮጵያ ታሪኳን የሚለውጥ ታላቅ ማህበራዊ ለውጥ አምጣ ለመውለድ ተንበረከከች።

 

ይህ ማህበራዊ ለውጥ (Social Change) እስኪበስል ድረስ ድምጹን አጥፍቶ ውስጥ ውስጡን ሲብላላና ሲዳብር ከቆየ በኋላ በቅድሚያ አካባቢውን እንደ ሚያወረዛ እርጥበት በጥቂት በጥቂቱ በመጨረሻም  የተጠመቀበትን ጋን ፈነቃቅሎ በመውጣት ሃገራችንን ከዳር እስከ ዳር እንደ ጎርፍ ያጥለቀልቃት ጀመር። ይህ ማህበራዊ ለውጥ ወይም ክስተት ከውጭ የመጣ ሳይሆን እዚሁ በኢትዮጵያ ምድር ተጠንስሶ፣ በአዝጋሚ ሂደት ዳብሮና ተሻሽሎ (Social Evolution) ለአሁኑ ማንነታችን ከፍተኛ ድርሻ ያለው ሲሆን የኢትዮጵያን ህዝብ በደምና በሥጋ እርስ በርሱ ያስተሳሰረ (የቀላቀለ) ነው። ለውጡ የተጠነሰሰበት የጋኑ መቀመጫ በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ በባሌ ተራራማ አካባቢዎች ነበር። ይህ ማህበራዊ ለውጥ (Social Change) የኢትዮጵያን ህዝብ አሰፋፈርና ስብጥር ሁኔታን ቀየረው። ለውጡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ በአካባቢው ህዝቦች ላይ በቋንቋ፣ በባህል እና በመሳሰለው ላይ ተጽእኖ አሳደረ። ይህ ማህበራዊ ለውጥ የኦሮሞ ጎሳዎች መስፋፋት፣ ፍልሰት፣ ስርጭትና ውህደት ነው።

 ምሁራኑ ለዚህ ማህበራዊ ለውጥ መነሻ ምክንያት ናቸው ብለው ከሚገልጹት ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፦ በወቅቱ በሃገራችን የነበረው የዝናብና የአየር ንብረት ባጠቃላይ የተፈጥሮ ሁኔታ ለኑሮ ተስማሚ ስለነበር ለሰውም ሆነ ለእንስሳት ቁጥር መጨመር ምክንያት በመሆኑ፣ በወቅቱ የነበረው የኦሮሞ ጎሳዎች የአኗኗር ሁኔታ ከብት ከማርባት ጋር የተገናኘ (Pastoral) ስለነበረና ከህዝብና ከከብት ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ ተጨማሪ የመኖሪያና የከብት ማሰማሪያ የግጦሽ መሬት (Grazing Land) በመስፈለጉ (Shortages of Land and Water Resources)፣ የገዳ ባህላዊ የኦሮሞ ህዝብ ሥርዓት የዳበረበትና በእድገቱ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት በህዝቡም ተቀባይነት አግኝቶ በከፍተኛ ሁኔታ ተግባራዊ የሆነበት ወቅት ስለነበረ፣ በተመሳሳይ ጊዜ እርስ በርሳቸው ተደጋጋፊ የሆኑ የባህል እና ሌሎች ማህበራዊ ለውጦች ሳቢያ (Cultural and Sociological Change) እና ሌሎችም ለለውጡ እንደ መነሻ ምክንያት ይጠቀሳሉ።

 ባጠቃላይ የኦሮሞ ጎሳዎች በፊት ከነበሩበት መኖሪያቸው ተነስተው በቡድን በቡድን በመሆን (በጎሳ) አዲስ ቦታዎችን ሲቆጣጠሩ የዛን ቦታ መጠሪያ በመቀየር በራሳቸው ጎሳ ስም ይጠሩታል። ለምሳሌ በጥንት ጊዜ አርሲ፣ ወለጋ፣ ኢሊባቦር፣ ወሎ ወዘተ የጎሳ ስሞች እንጂ የቦታ ስሞች አልነበሩም። በመሆኑም እነዚህ አካባቢዎች በኦሮሞ ጎሳዎች ከመያዛቸው በፊት የነበራቸው መጠሪያ ስም የተለየ ነበር ማለት ነው።

 በንጉስ ዘርዓ ያዕቆብ ፣ በአፄ በእደ ማርያም፣ በአፄ ገላውዲውስ እና በአፄ ሰርፀ ድንግል ዜና መዋዕሎች ውስጥ የተጠቀሱትንና ነገስታቱ በኢትዮጵያን የተዘዋወሩባቸውን የቦታ ስሞች ብንመለከት የብዙዎቹ መጠሪያቸው ተቀይሯል። ለምሳሌ፦

 በፊት ፈጥጋር ይባል የነበረው አሁን አርሲ ተብሎ ይጠራል።

በፊት ቢዛምና ዳሞት ይባል የነበረው አሁን ወለጋ ተብሎ

  ይጠራል

በፊት እናርያ የነበረው አሁን ኢሊባቦር ተብሎ ይጠራል።

በፊት ላኮመልዛ የነበረ አሁን ወሎ ተብሎ ይጠራል።

በፊት በፊት አንጎት የነበረው አሁን ራያ ተብሎ ይጠራል።

በፊት ሽምብራ ቆሬ የነበረ አሁን አዳማ (ናዝሬት) ተብሎ

  ይጠራል ወዘተ።

 ማስታዎሻ፦ የአካባቢ መጠሪያ ስሞች በኦሮሞ ጎሳዎች ፍልሰትና መስፋፋት ብቻ አልነበረም የሚቀየሩት ወይም የተቀየሩት። ለምሳሌ፡ ከጣልያን ወረራ በፊት ትግራይ እና ኤርትራ የሚባል የቦታ መጠሪያዎች አልነበሩም።

 *ትግራይ የሚለው መጠሪያ በአጼ ዮሐንስ iv ጊዜ እንኳን ያልነበረ የቅርብ ጊዜ ግኝት ነው። ከዛ በፊት “ትግሬ” በአውራጃ ደረጃ ነበር የሚታወቀው። በጠቅላይ ግዛት ስም “ትግሬ” ብለው መጥራት የጀመሩት ቀ//ሥላሴ ናቸው። በወቅቱ ትግሬ የሚባለው በአሁኑ ሰዓት ትግራይ ተብሎ የሚጠራው ሁሉም ሳይሆን ሽሬ እና አድዋ ብቻ ነበሩ። ዛላንበሳ፣ ይሮብ፣ ተምቤ፣ አክሱም፣ አጋሜ እራሳቸውን ችለው በተናጠል የሚተዳደሩ ሲሆን ዘራቸውም (ጎሳቸው) አንዳቸው ኩሸ ሌላቸው ሴማዊ ናቸው። ሁሉም ትግሬ አይባሉም ነበር። የትግርኛው ቋንቋ ተናጋሪው የቀሩትን በተለይየመንገድ አፍኖ ስለያዛቸው እንጂ በትግራይም ሆነ በኤርትራ ውስጥ ትግርኛ ብቻ ሳይሆን በርካታ ቋንቋዎች ይነገራሉ። ትግርኛ የሚናገር ሁሉ ትግሬ እንዳልሆነ ሁሉ ከአንድ በላይ ቋንቋዎችን ማለትም የኩናማ ቋንቋ፣ ትግርኛ፣ ትግረ ወይም የሳሆ ቋንቋዎችን መናገር ስለቻለ ያ ሰው ትግሬ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። አሁን ትግራይ በሚባለው ክልል የሚገኙት ኩናማ፣ ኢሮብ (ሳሆ)፣ ተምቤን፣ እንደርታ (አጋሜ) የሚባሉት አካካቢ የሚኖሩ ህዝቦች የአገው ወይም የኩሽ ህዝብ ዘሮች እንጂ ትግሬ (ሴሜቲክ) አይደሉም። ለምሳሌ ጀግናው ራስ አሉላ አባ ነጋ ዘራቸው (ጎሳቸው) ከአገው የሚመዘዝ እንጂ ከትግሬ አይደለም። ኤርትራ የሚለውን መጠሪያን ስንመለከት ደግሞ ከፋፋዩ ፋሽስት ጣሊያን ህዝቡን ለማደናገር የባህሩን ስም (Red Sea or Eritrea Sea) ለመሬቱ የሰጠው ነው። ማለትም ቀድሞ ባህረ ነጋሽ እየተባለ ለሚጠራው አካባቢ ጣሊያን ኤርትራ ብሎ አዲስ ስም አወጣለት ከጊዜ ወደ ጊዜ ህዝቡ የድሮውን እየረሳ አዲሱን እየለመደ ሄደ። ኤርትራ የባህር እንጂ የመሬቱ መጠሩያ አልነበረም። ሌላው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ኤርትራ የሚለው ቃል የቀይ ባህር (የውሃው) መጠሪያ እንጂ የሃገሩ ወይም የመሬቱ መጠሪያ አይደለም። ነብዩ ሙሴ እስራኤላውያንን ባህሩን ከፍሎ አላሻገራቸው እንጂ የተጓዙትማ በግብፅ መሬት ላይ ነበር።

 የደቡቡን የሃገራችንን ክፍል ስንመለከት ደግሞ የሚከተለውን እናገኛለን። ለምሳሌ ቀደም ባሉት ዘመናት በጅማና አካባቢው፣ በከፋ፣ እናርያ (ኢሊባቦር)፣ ከንባታ፣ ሃድያ፣ ሲዳማ፣ አርሲ (ፈጥጋር)፣ ወላጋ (ቢዛምና ዳሞት) እና የመሳሰሉት አካባቢዎች እንደ ዘመኑ ከአክሱም kingdom ጀምሮ፣ በላስታ፣ በጎንደር እና በሸዋ መቀመጫውን ላደረጉት የኢትዮጵያ ዘውዳዊ መንግስታት ስር የሚተዳደሩ ነበሩ። በተለይ ከኦሮሞ ምስፋፋትና ስደት በፊት የሸዋ ዘውዳዊ መንግስት፣ ከንባታ፣ ሃድያ፣ ፈጥጋር (አርሲ)፣ ዳወሮ፣ ሜቶሎሜ (ዳማት) ግዛቶች እርስ በርስ በቀጥታ የሚገናኙ ኩታ ገጠም ነበሩ።

 እዚህ ላይ ለማስታወስ ያህል በ14 ኛው ክፍለ ዘመን የሃገራችን ንጉስ የነበሩት የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ባለቤት ንግስት እሌኒ ከሙስሊም ቤተሰብ የሚወለዱና የዘር ሃረጋቸው ከደቡብ የኢትዮጵያ ከሃድያ ብሔረሰብ ነው። ግራኝ አህመድ ከኦቶማን ቱርክ ባገኘው እርዳታ ሃገራችንን ከላይ እስከ ታች ባመሰበት ጦርነት በርካታ የአማራ ሰራዊት በኢትዮጵያ ምድር ከጫፍ እስከ ጫፍ ደማቸውን ያላፈሰሱበት ቅንጣት መሬት አይገኝም። በዛ ወቅት የሃድያ ተወላጇ ንግስት እሌኒ አሊ ነበሩ  ከፓርቹጋሎች ጋር በመጻጻፍ ወታደራዊ እርዳታ እንዲገኝ ያደረጉት። ስለዚህ ከአህመድ ግራኝ ወረራም ሆነ ከኦሮሞ ጎሳዎች ወደ አካባቢው ከመስፋፋታቸው በፊት ጀምሮ ሃድያ በሸዋ ነገስታት ስር መሆኗን እዚህ ላይ ማስተዋል ተገቢ ይሆናል። አጼ ምኒሊክ ወደነዚህ አካባቢዎች ያደረጉት ዘመቻ የወያኔና የኦነግ ካድሬዎች እንደሚያስወሩት የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን የሸዋ ነገስታት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ከነዚህ አካባቢዎች ጋር ታሪካዊ ግንኙነት ስለነበራቸው፣ በተለያየ ጊዜ የደም መስዋእትነት የከፈሉበት የአባቶቻቸው ሃገር ስለሆነም ጭምር ነው። በታሪክ ተጽፎ እንደምናገኘው እነ አፄ ገላውዲዎስ፣ እነ ራስ ሐልመልማልና የመሳሰሉት የተሰውበት ነገር ግን በቀነ ጎደሎ ግዛቶቹ ከአማራው የተነጠቁበት (የተነጠሉበት) ስለነበር ታሪካዊ ያባቶቻቸውን ግዛቶች ለማስመለስ፣ ዘመዳሞችን ለማገናኘት፣ የተቃጠሉና የወደሙ ገዳማትና አብያተ ቤተ ክርስቱያናትን ዳግም ለማቆም፣ ባጠቃላይ ተበታትና የነበረች ሃገርን የማሰባሰብና የማቅናት ዘማቻ ነበር።

 አፄ ምኒልክ ወደ አንድ አካባቢ ሲዘምቱ “ሕዝብ በከንቱ እንዳያልቅና ሀገር እንዳይጠፋ አባቶችህ ለአባቶቼ እንደገበሩት አንተም በሰላም ለኔ ገብር፣ ይህንን ካደረክ ስልጣንህን እባርክልሃለሁ፣ በፍቅር እንኖራለን” የሚል ጥሪ አስቀድመው ለአካባቢው ገዢ/ ባላባት ይልኩ ነበር እንጂ በሰራዊታቸው ብዛት ታብየው በስሜትና በጀብደኝነት የሚነዱ አልነበሩም። የአካባቢው ገዢ ጥሪያቸውን በሰላም ከተቀበለ ስልጣኑን ባርከውለት አመታዊ ግብሩን ለመንግስት እንዲያስገባ አሳስበውት ሾመው ሸልመውት ይመለሱ ነበር። አጼ ምኒሊክ ወደ ጦርነት የሚሄዱት ሰላማዊው መንገድ ሲሟጠጥ ብቻ ነበር። እምቢ ባዩን ባላባት በመረጠው መንገድ በጦርነት ገጥመውት ከማረኩት በኋላ እንኳን ለሁለተኛ ጊዜ በሰላም እንዲኖር እድል ይሰጡት ነበር። ለምሳሌ የወላይታው ንጉስ ጦና እምቢ ብሎ ውጊያ ገጠመ። ተሸነፈ፣ በምኒልክ ተማረከ። ምህረት አደረጉለት። እሱም ዳግም እንደማይበድል ቃል ገባ፣ እሳቸውም ንግስናውን መለሱለት። ንጉስ ጦናም እስከ ህይወቱ ፍጻሜ ድረስ ከምኒልክ ጋር በፍቅር ኖሩ።

 እንደሚታወቀው ጸረ አንድነቶች መልካም መልካሙን ታሪካችንን እየደበቁ ክፉ ክፉውን እያጋነነኑና እየቀጣጠሉ ስለሚነግሩን ነው እንጂ፣ ሃገርን በፍቅርና በስምምነት መምራት ተቀዳሚ ስራቸው ያደረጉት አፄ ምኒልክ በመነጋገር (በዲፕሎማሲ) ያለ ጦርነት ወደ አንድነቱ ህብረት ዳግም ያመጧቸው የኢትዮጵያ ግዛቶችና የጎሳ መሪዎች እጅግ ብዙ – ብዙ ናቸው።

 ለምሳሌ ያህል በወለጋ፣ በጅማ፣ በአፋር፣ በምዕ/ምስ እና በደቡብ ሸዋ ይኖሩ የነበሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በየመንደሩና ጎጡ የሚገኙ በርካታ ባላባቶችን፣ የጎሳ መሪዎችን እና ገዢዎችን ያለምንም ጦርነት በሰላም የአጼ ምኒሊክን ንግስናን የተቀበሉና ወደ አንድነቱ ህብረት በፍቃዳቸው የተቀላቀሉ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ አብዛኛዎቹ የምኒሊክ ወታደሮች ኦሮሞዎች እንደነበሩ ማስታወስ ተገቢ ነው።

 የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ፣ የተለያየ ባህልና እምነት ያላቸውን ቁጥራቸው ከ80 በላይ የሆኑ የኢትዮጵያ ጎሳዎችን ያውም በዛ ኋላ ቀር በሆነበት ስልክም፣ ራዲዮም ሆነ ዘመናዊ መጓጓዣ በሌለበት ሁኔታ እነዚህን ህዝቦች አሰባስቦና አስማምቶ ሁሉንም የሚያካትት የጋራ ሀገር መገንባት እጅግ ውስብስብና ከባድ ነገር ነው። ከዚህ አንጻር አፄ ምኒሊክ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች  (ጎሳዎችን) አሰባስበው አንድ የጋራ ሀገር መገንባታቸው ሳያንስ እነዛኑ በየጎጥ ታጥረው በትንሹ እያሰቡ እርስ በርስ ሲተራመሱ የነበሩ የአካባቢ ገዢዎችንና የጎሳ መሪዎችን ለትልቅ ሃገራዊ ራዕይ እና ለአንድ አላማ አሳምነውና አስተባብረው የአውሮፓ ቀኝ ገዢ ወረራዎችን መመከታቸው እጅግ የሚያስመሰግናቸው አኩሪ ሥራ ነው።

 አፄ ምኒልክ ሀገር የማቅናትና የማደራጀት ከፍተኛ የሆነ ስራ በሚሰሩበት ጊዜ አውሮፓዉያን ሃገራችንን ጨምሮ መላው አፍሪካን በቀኝ ግዛት ለመቀራመት ያሰፈሰፉበት ወቅት መሆኑን ማስታወስ ይገባል። ስለሆነም ለአንድ አፍታ ያንን ጊዜ ለማሰብ ብንሞክር ንጉሱ ምን ያህል እጅግ ፈታኝ ጊዜ ውስጥ እንደነበሩና ያጋጠማቸውን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በጥበብና በትእግስት እንዳሸነፉ እንረዳለን። በጀግንነታቸው ብቻ ሳይሆን ባላቸው መልካም ስብእና እንኮራባቸዋለን።

 የወለጋ ባላባቶችና የጎሳ መሪዎች ያለጦርነትና ኮሽታ የምኒልክን ንግስናን በሰላም የተቀበሉና ወደ አንድነቱ ህብረት በስምምነት የተቀላቀሉ ናቸው። አጼ ምኒልክም ቢሆኑ አማርኛንና ኦሮምኛን አቀላጥፈው መናገር የሚችሉ፣ በምኒልክ የስልጣን እርከን ውስጥና በተዋጊነት እንዳልተሳተፉ ዛሬ ልጆቻቸው የኦሮሞ ህዝብ በምኒልክ እንደዚህ ተደርጓል በማለት በፈጠራ ታሪክ መጠመዳቸው፣ የንጉሱንና የኢትዮጵያን ታሪክ ጥላሸት መቀባታቸው እጅግ የሚያሳዝን ነው። በአርሲ፣ በሐረርጌ … በዚህ ወይም በዚያ አካባቢ በሚኖሩ ኦሮሞዎች ላይ አጼ ምኒልክ ይህንን ተፈጽመዋል በማለት ያለመረጃ በቅብብሌሽ ወሬ ከሳሽ የመሆናቸውን ሚስጥር ከሚጠቁሙን ውስጥ የመጀመሪያው የኦነግ፣ የወያኔና የሻቢያን ግንኙነት ምክንያትን ማጥናት ሲሆን ሌላው ደግሞ በወለጋና አካባቢው የነበሩ የጀርመን ፕሮቴስታንት ሚሽነሪዎችን ታሪክ መመርመር ስንችል ነው።

 ወለጋ አካባቢ ለረጅን ጊዜ በመኖሩ የኦሮምኛ ቋንቋ መናገር የሚችል ዮሐን ክራፍት የሚባል የጀርመን ፕሮቴስታንት ሚሽነሪና ሰላይ መጽሐፍ ቅዱስን ጀርመንኛን በሚጽፍበት በእንግሊዘኛ ፊደል (በላቲን ፊደል) በመጠቀም በኦሮምኛ ቋንቋ ተረጎመ (በነገራችን ላይ የቁቤ መነሻው ይህ ነው)። ይህ ዮሐን ክራፍት የተባለ ሚሽነሪ (ወንጌላዊ) ለተወሰነ ጊዜ ሸዋ ተቀምጦ በነበረበት ሰዓት ለአውሮፓ ቀኝ ገዢዎች ሲሰልል ተደርሶበት ከሃገር የተባረረ ቢሆንም ዳግም በኬንያ ሞምባሳ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገባ ነው። ከተወሰነ ጊዜ ሃገር ውስጥ ከቆየ በኋላ ተመልሶ ወጣ። የዮሐን ክራፍትን ዱካ ተከትለው የመጡ ሌሌች ሚሽነሪዎች (ወንጌላውያን) በእሱ መንገድ በመጓዝ በወለጋ ክርስትናን መስበክ እንደጀመሩ ህዝቡ ታቦት እያለ ቢያስቸግራቸው 10ቱን ህግጋት በእንጨት ላይ እየጻፋ ቤተ ክርስቲያን በማስቀመጥ ሰዎችን መሳብ ቻሉ። ት/ት ቤቶችን ከፈቱ። ት/ት ቤት መክፈቱ ባልከፋ ነገር ግን በርካታ የዘረኝነትና ጸረ ኢትዮጵያ መርዝ ተከሉ። የኦሮሞ ብሔረተኛ አስተሳሰብ ያላቸው ጽንፈኛ እንደ ኦነግ ዓይነት ያሉ ድርጅቶች መስራቾች አብዛኛዎቹ በወለጋ በዮሐን ክራፍት በተቋቋሙ የጀርመን የሚሽነሪ ት/ት ቤቶች ተኮትኩተው ያደጉ ናቸው።

 ሌላው ደግሞ ግራኝ መሃመድ በሰሜኑ የክርስቲያን መንግስት ላይ የጀሃድ ጦርነት በማወጅ ያካሂድ ለነበረው ጦርነት አብዛኛውን ተዋጊ ወታደሩን ይመለምል የነበረው በምእራብ ሐረርጌ፣ በአርሲና በሃድያ (ባሌ) አካባቢ ከሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ነበር። እንደ ወለጋው የዮሐን ክራፍት ዓይነት ሃገርን ከማፍረስ ጎን ለጎን ቤተ ክርስቲያንን ማቃጠል ይሰበክበት ከነበረው አካባቢ ነበር የዛሬው የኦሮሞ አክራሪ ብሔረተኛ የሆነው ጁሃር መሐመድና ጓደኞቹ ተወልደው ያደጉት እዚሁ አካባቢ ነው።

 የኦሮሞ ፍልሰት ወይም መስፋፋት ከመጀመሩ በፊት ባሌ፣ አርሲ፣ የሸዋና አካባቢዎቹ ድረስ ይኖሩ የነበሩት አማሮች፣ ሃዲያዎች፣ ከንባታዎች፣ ጉራጌውምችና ሌሎች ጎሳዎች ነበሩ። በገዳ ባህላዊ ሥርዓት የሰለጠኑ የኦሮሞ ተዋጊዎች በጎሳ በጎሳ እየተደራጁ  ወደዚሁ አካባቢ በመምጣት የቀድሞ ነባር (Native) ነዋሪዎችን በሃይል በማፈናቀል ወይም “ሞጋሳ” እና “ጉዲፈቻ” በተባሉ የኦሮሞ ባህል የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦችን ወደ ኦሮሞነት በመለወጥ (Oromization) መሰረት በርካቶች ኦሮሞ ሆኑ። ባጠቃላይ የሞጋሳና የጉዲፈቻ ባህል ኦሮሞነት ከዘር ጋር ግንኙነት እንደሌለው የሚያሳይ ሲሆን ይህም ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የአካባቢውን ህዝብ የአሰፋፈርና የቋንቋው ሁኔታ (Demography) እጅጉን ቀያየረው።

 ሌላው ደግሞ በወሎ የሚገኙ የየጁ ኦሮሞዎች ከአርሲ የመጡ ሙስሊም ኦሮሞዎች ናቸው። የአርሲ ኦሮሞዎች ታሪክ ወደ ኋላ ሄደን ከስር መሠረቱ ስንፈትሽ ደግሞ የሚከተለውን እናገኛለን። ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ከኦሮሞ መስፋፋት ቀደም ብሎ የአርሲ አካባቢ ቀደምት ነዋሪዎች የጉራጌና የከንባታ ህዝቦች ነበሩ። እነዚህ  የጉራጌና የከንባታ ህዝቦች በኦሮሞ መስፋፋት ወቅት ወደ ኦሮሞነት የተቀየሩ ናቸው። ከዛ ቀድሞ ብሎ እነዚህ የጉራጌና የከንባታ ህዝቦች በአህመድ ግራኝ ወረራ ወቅት ወደ እስልምና የተቀየሩ መሆናቸውንና፣ በኦሮሞ መስፋፋት ደግሞ ወደ ኦሮሞነት ተቀየሩ፣ በመጨረሻም ከአርሲ ወደ ሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ወደ ሆነው ወሎ በቀድሞ አጠራሩ ላኮሞንዛ በመሰደድ የጁ የሚባል ቦታ ሰፈሩ።

 

ወደ መካከለኛውና ምዕራባዊ የኢትዮጵያ አቅጣጫ ስንሄድ ደግሞ ወለጋን፣ ጎጃምን፣ ሰላሌንና ሸዋን ብንመለከት ተመሳሳይ የሆነ ታሪክ እናገኛለን። አሁን ወለጋ፣ ምዕራብ ሸዋ የሙገር ወንዝን ይዞ፣ ኖኖና አማያን አካቶ እስከ ጅማና ጊቤ በርሃ ድረስ ይኖሩ የነበሩ ጋፋትና ዳማት (ቤቶሎሚ) የሚባሉ ጎሳዎች (Kingdom) ይኖሩ ነበር። ይህ ሁሉ የሚያሳየን እኛ ኢትዮጵያውያን በሃይማኖት፣ በዘር፣ በባህል፣ በቋንቋና በመሳሰለው የተደበላለቅን መሆናችንን ነው።

 አሁን ካለው ወደ 35 ሚሊየን ከሚገመተው የኦሮሞ ህዝብ ውስጥ ከላይ ከዘር ማንዘሩ ማለትም ከኦሮሞ መስፋፋትና ስርጭት በፊት ጀምሮ “ቅልቅል የሌለው ንጹህ ኦሮሞ” ነው ተብሎ የሚገመተው 7ሚሊዮን ቢሆን ነው የሚል ግምት እንዳለ የታሪክ ምሁር የሆኑት ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ በቅርቡ ከSBS ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ ገልጸዋል። ለምሳሌ ለኦነግ ወይም ኦህዴድ ስብስባ ከተገኙ 100 የኦሮሞ ብሔር አባላት ተሰብሳቢዎች ውስጥ 20 ብቻ ናቸው “ቅልቅል የሌላቸው ንጹህ ኦሮሞዎች”  እንደማለት ነው። (5ሰው 1ሰው ወይም 20%)

 

አሁን ላለው የኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ድርሻ ስላለው ስለ ኦሮሞ ህዝብ ከኦሮሞ ውጭ ሌላው ኢትዮጵያዊ አይመለከተውም የሚል ካለ “አክሱም ለወላይታው ምኑ ነው” እንደማለት ያህል ነው። ስለ ኦሮሞ መናገርና መቆርቆር መብቴ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞና የአማራ አባቶች ዘመናዊት ኢትዮጵያን በጋራ አበጅተው የሰጡን የጋራ ውርሳችን ናት። ጽንፈኞቹ የፈለጉትን ቢቀባጥሩም የእኔ አቋም ግን ስለ ኦሮሞ ለመናገር መብት የሰጠኝ ኢትዮጵያዊነቴ ነው፣ አሁን ስላለችው ኢትዮጵያ ያለ ኦሮሞ ልገልጻት አልችልም። የኦሮሞ ህዝብ በአስተዳደሩ፣ በውትድርናው፣ በዘፈኑ፣ በስፓርቱ፣ በፓለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ ህይወቱ ባጠቃላይ በዘመናዊ ኢትዮጵያ ግንባታ ታሪክ ውስጥ ከአማራው ጎን ከፍተኛ ድርሻ አለው።

 ኢትዮጵያን የጠሉ ሁሉ ምኒሊክን እየጠሉ ተቸገሩ እንጂ አፄ ምኒልክ በወሬ ሳይሆን በተግባር ለሃገራቸን ኢትዮጵያ እድገት፣ ብልጽግና እና ነጻነት ብዙ የደከሙ፣ ለዘመናዊነት በር ከፋች በመሆን በርካታ ስልጣኔ ወደ ሃገራችን ያስገቡ ታላቅ ንጉስ ናቸው። ዓለም አልሰለጠነም በሚባልበት በዛ ጊዜ ከ80 በላይ የሆኑ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን በፍቅር አስማምተውና አስተባብረው የመሯትን ሃገር ዓለም በሰለጠነበት በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንደ ወያኔና ኦነግ ዓይነት ጽንፈኛ ድርጅቶች ነገር ሲያምሱና ህዝብን እርስ በርሱ ከማጋጨት ውጭ ለትውልድ የሚጠቅም ነገር ሲሰሩ አልታዩም። ወያኔ/ህወሃት አጼ ምኒልክ በገነቡት በ4ኪሎ ቤተ መንግስት ተጎልቶ ስማቸውን ከማጥፋት ውጭ በአግባቡ ህዝብና ሃገር መምራት አልቻለም። =======//======

 ደረጀ ተፈራ

(ውድ አንባቢያን፦ ይህ ጽሁፍ የግል ማስታወሻዬ ስለሆነ ስህተት ከተገኘበት ለማስተካከል ዝግጁ ነኝ)