December 31, 2016 12:08

 

ዛሬ ላይ ወያኔና አጋሮቿ እውነተኛውን የሚኒሊክና ጎበናን ታሪክ አጠልሽታ ታሪኩንና ማንነቱን ከጀግኖች፣ ብልሕና አርቆ አሳቢ አባቶቹ ነጥላ የባዘነና ራሱን ያጣ ባደረገቸው ትውልድ እንዲህ ያለው እውነት እጅግ ያስበረግገዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የወያኔና አጋሮቿ ሴራ የገባቸው ከእንቅልፋቸው ባነው ወደማንነት ክብራቸው እየተመለሱ ያለ ይመስላል፡፡ እስኪ እኔም ስለጀግኖችና አስተዋይ አባቶቼ(ይህንኑ ብቻ ማለት ስለሚቻል እንጂ ከዚህ በላይ ቃል ቢኖር ባልኩዋቸው) የማንካካድባቸውን አንዳንድ ነጥቦች ላንሳ፡፡

ጎበና ዛሬ ማንም አፉን የሚያሟሽበት አድር ባይና ለሌሎች የሚያጎበድድ ሳይሆን በራሱ የሚተማመን በወደደውና በፈቀደው እንጂ ማንም አስገድዶት ወይም እፈራርቶት ወይም አታሎት ያደረገው ነገር የለም፡፡ ጎበና በዘመኑ ከነበሩ መሳፍንት እኩል የራሱን ክልል አስጠብቆ የራሱን ሕዝብ የሚመራ ጀግና ነበር፡፡ ይህን ጀግንነቱን የሚያውቁ የሚያውቁ ሊደፍሩት አልቻሉም፡፡ በጎበና ግዛት ማንም ሊገባ አልደፈረም፡፡ ጎበና ከማንም ጋር በወዳጅነት ካልሆነ ተገዶ ተባባሪ የሆነበት ሕይወት የለውም፡፡ ዛሬ ብዙዎች ለራሳቸው ሴራ እንዲመቻቸው ጎበናን ለአማራ ገዥዎች ያጎበደደ ሳይሆን በዘመኑ ቡዙ የአማራ መሳፍንትንና ዋነኞቹን ነገስታት ሳይቀር የተገዳደረ ጀግና ነው፡፡ የጎጃሙን ንጉስ ተክለኃይማኖትና ዋናውን አጼ ቴዎድሮስ  ጨምሮ በዘመኑ ከሚታወቁት ጎበና ከተገዳደራቸው መሪዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ጎበና ከሚኒሊክ ጋር ሕብረት ከመፍጠራቸው በፊትም ከአያሌ የዘመኑ መሳፍንት ጋር ተዋግቶ የራሱንና የሚያስተዳድረውን ድንበር ያሰከበረ ጀግና ነው፡፡ በኋላም ከሚኒሊክ ጋር በፈጠረው ሕብረት ዛሬ የምናውቃትን ኢትዮጵያን አንድ ያደረገ ልዩ ጀግና ነው፡፡ ከዛም ባለፈ አደዋን ድል ለማድረግ ወሳኝ ሚና የነበራቸው የኦሮሞ ጀግኖች የጎበና ልጆች እንደሆኑ እናስታውስ፡፡ በሥጋ የወለዳቸው ማለቴ ሳይሆን ጦርነትንና ጀግንነትን ከልጅነታቸው ጀምሮ ያስተማራቸው፡፡ ይህ ጎበና ከሚኒሊክ ጋር ሕብረት ከመፍጠሩ በፊት ካደረጋቸው በጣም ጥቂቱ ነው፡፡

ጎበና ከሚኒሊክ ጋር የነበረው ሕብረት፡

ጎበና ከሚኒሊክ ጋር ሕብረት የፈጠረው ለሚኒሊክ በማጎብደድ ሳይሆን ከልጅነታቸውም በነበር የታሪክ ተውውቅ በነበራቸው ወዳጅነት፣ በሚያመሳስላቸው የአስተዋይነትና የመሪነት ብቃት፣ አንዲሁም አርቆ አሳቢነትና ታላቅ አገር ኢትዮጵያን ለመመሥረት በተስማሙበት የጋራ ራዕይ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም የእነዚህን የሁለት አስተዋዮች ልብ ስላወቀ እውንም ማንም አንደ ሰው ዕድሜ ይሰራዋል ብሎ የማያስበውን ታላቅ ታሪክ ሠርተው እንዲያልፉ በአንድነት አሰማራቸው፡፡ የሚኒሊክና ጎበና ሕብረት የተመሠረተው እንዲህ ነው እንጂ ዛሬ የመከነው ትውልድ እንደሚመስለውና ኦፒዲዮ በሕወሐቶች ፍቃድ እንደሚዘወሩት አደለም፡፡ ጎበና ለሚኒሊክ ልዩ ጀግናቸው ናቸው ሰራዊቱንም ይመሩ ዘንድ የጦር አበጋዝ ሲያደርጉዋቸው የጎበናን ጀግንነት በመተማመን ነው፡፡ ዛሬ ግን ቀድሞ የምናውቃቸው የኦሮሞ ጀነራሎች ሳይቀሩ ከሰራዊቱ የአመራር ቦታ ታች ተጥለው በተላላኪነት የሚያገለግሉ ናቸው እንጂ ተራ ሥልጣን እንኳን የላቸውም፡፡ ሚኒሊክ ጎበናን ብቻ አደለም አያሌ የኦሮሞ ጀግኖችንና የአመራር በቃት ያላቸውን ኦሮሞዎች ያለምንም ስስትና ማመንታት ኃላፊነት ሲሰጡዋቸው የጎበና ሚና አብሮ ነበር፡፡  ብዙ ኦሮሞ ይህን አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ ግን አዚም ተደርጎበት ይሁን ሌላ አላውቅም ለልጆቹ የሚያወራው ያንኑ ወያኔና አጋሮቿ የሚናገሩትን ነው፡፡ ጎበናን ያዋረዱ መስሏቸው እራሳቸው እንደተዋረዱ ያልተረዱ ብዙዎች ናቸው፡፡

ጎበና የሌሎች ኦሮሞ ወንድሞቻቸውን ግዛት ከባዕዳን ወራሪ ኃይል ለመታደግ ያደረጉት ተሳትፎ

በአንድ ወቅት ሞረዳ በከሬ የተባሌ ሌላ የኦሮሞ መሪ ይመሩት የነበረው ዛሬ የምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍል ማለት ወለጋ ኢሉ አባቦራና አሶሳ በደረቡሾች ይወረራል፡፡ ሞረዳን ለመርዳትና ደርቡሾችን ለመመከት ጎበናና ሠራዊታቸው ወደዚያው ተልኮ ደርቡሾችን እስከ መጨረሻው መትቶ የሞረዳን ግዛት አስከብሯል፡፡ ከውስጥ በሚነሱ ወሳኝ የመሳፍንት ውጊያዎችም ጎበና ነበሩ የሚላኩት፡

የጎበናና ሚኒሊክ አገርን አንድ የማድረግና ሕዝቦችን ከባርነት ማላቀቅ

የጎበናና ሚኒሊክ ሕብረት እውንም ያሰቡትን ሁሉ ለማድረግ የሚያግደው አልነበረም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ብለን የምጠራትን አገር አንድ በማድረግ የሠሩት ታሪክ እንኳን እኛን አፍሪካን ሁሉ የሚያኮራ ታሪክ ነው፡፡ ዛሬ ያለው የመከነው ትውልድ ይህን ኩራት ነው ጥሎ ጠላቶቹ በነገሩት ታሪክ ባርነትን የመረጠው፡፡ ጎበናና ሚኒሊክ ይህን በማድረጋቸው አያሌ በባርነት ይኖሩ የነበር ሕዝቦች ነጻ እንደወጡ አስተውሉ፡፡ ኢትዮጵያ በጎበናና ሚኒሊክ አንድ ከመሆኗ በፊት እኮ ብዙ ሕዝብ በባርነት የሚሸጥና የሚለወጥ ዕቃ እንጂ ሰውም አደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ኋላም ከሚኒሊክ ጋር ሕብረት የነበራቸው የጅማው አባ ጀፋር በግዛታቸው የከፋ የባርነት ንግድ ሲካሄድ በሚኒሊክ ተግሳጽ ነበር የባሪያ ንግድ እንዲቆም የተደረገው፡፡ ይህ ታሪክ መዝግቦት ያለ እውነት ነው፡፡ ዛሬ ማንም እየተነሳ እንደሚዘላብደው ሳይሆን ኢትዮጵያ አንድ ከመሆኗ በፊት ብዙው ሕዝብ በአስከፊ የባርነት አገዛዝ ሥር ነበር፡፡ ዛሬ እንደሚደሰኮረው በዘመኑ የነበሩ የየአካባቢው ገዥዎች ለሕዝባቸው የሚቆረቆሩ ሳይሆን ለራሳቸው ምቾት ሕዝቡን ባሪያ አድርገውት ይኖሩ ነበር፡፡ ጎበናና ሚኒሊክ ከዚያ ዘመን የመጠቀና ዛሬም ያለው ትውልድ ያለደረሰበት ማስተዋል ነበራቸው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ብለን በምንጠራት ግዛት ውስጥ ከዘመናት በፊት ምን አይነት ሕዝቦች እነማን የኖሩባት እንደነበር ጎበናና ሚኒሊክ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር፡፡ ዛሬ ሊያምታቱ እንደሚሞክሩ የታሪክ ምሁራን ን ባዮች ሳይሆን ይህ ጎበናና ሚኒሊክ ወደ ኢትዮጵያ የጠቀለሉት ምድር ሁሉ ጥንትም የኢትዮጵያውያን (ሐበሾች) ምድር ነው፡፡ አስተውሉ፣ ጎበናና ሚኒሊክ የዚያን ያህል ርቀት ወደ ደቡብ ሲዘልቁ መጨረሻቸው ቦረና ነበር፡፡ ኬንያ አልገቡም፡፡ ይህ ምድር ዛሬ ሳይንስ እውንም የልዩ ሕዝቦች ዘር የሚኖሩበት እነድሆነ ይመሰክርልናል፡፡ በቅረቡ የወጣው የሰው ልጆች መለዘር(ሑመናን ጅነቲክስ) ጥናት የሚያረጋግጠው ይሄንኑ ነው፡፡ አስቀድሞ ነበር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን የተባለለት ሕዝብ ዛሬ ማንነቱን ሳይንስ አግኝቶት ታላቅ የጥናት ሚስጢር ሆኗል፡፡ ከሞሮኮና ግብጽ እስከ ሳንዳዌ ሕዝቦች(ታንዛንያ) የሐበሻ ዘር መሠረት የሆነው  ይነበባል፡፡

ዛሬ አድር ባዮችና ወሮበሎች እንደሚያወሩት ሳይሆን በኢትዮጵያ አንድነት ምስረታ ወቅት ሕዝቦች ነጻነታቸውን ነበር ያገኙት፡፡ ሚኒሊክና ጎበና የማንንም እምነት ባሕል ወይም ሌላ ማሕበረሰባዊ እሴት አላጠፉም፡፡ ሁሉም እንደእመነቱና ባሕሉ ነው ኢትዮጵያዊነትን እንዲቀላቀል ያደረጉት፡፡ ከነሙሉ ሰበዓዊና ኢትዮጵያዊ ዜግነት ክብሩ፡፡ ዛሬ ብዙዎች ሊያታቱት እንደሚሞክሩት ሳይሆን አንድም ሕዝብ ሐይማኖቱን፣ ባሕሉን በሚኒሊክ አስተዳደር የቀየረ የለም፡፡ ይልቁንም በወሎ በአጼ ዮሐንስ ሰዎች ያለውዴታቸው እምነት እንዲቀዩሩ መደረጉ ለዚህ ዘመን ትልቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ምክነያቱም ዩሐንስን ወያኔ የኔ በላ ስለምታምን ሌላውም ወያኔ የምትለውን እንጂ እውነትን መነጋር አልፈለገም አልደፈረም፡፡ ሚኒሊክን ግን ልክ ክርስትናን እንዳስፋፋ፣ እምነትታ ባሕልን እንዳጠፋ እጅግ በዝቶ ይነገራል፡፡ እውን አውነታው ይሄ ነው? ዛሬ ገዳ ምናምን እያለ የሚያነፋው ኦሮሞ ነኝ የሚለው ሁሉ ለመሆኑ የገዳ ሥርዓት እየተከበረ ያለው በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የት ነው? በሐርር ነው? ባሌ ነው? አርሲ ነው? ወይስ ጅማ? ከጅምሩም ጎበና በሚያስትዳድራቸው በሸዋ አደለምለምን እንወሻሻለን፡፡ የእስልምና እምነት በሚከተሉ የኦሮሞ ሕዝቦች ዘንድ እውን ገዳ ይከበራል? አውቃለሁ ከሸዋ ሌላ በቦረናና ጉጂ ይሄ ሥርዓት አለ፡፡ በአብዛኛው ቦረናና ጉጂ ደግሞ የእስልምና እምነት ተከታዮች አደሉም፡፡

ለመሆኑ ጎበናና ሚኒሊክ በኢትዮጵያ ሥር ባይጠቀልሉት ዛሬ አብዛኛው ነጻነት እያለ የሚደነፋው ለእነዚህ ጎበናና ሚኒሊክ ኢትዮጵያ ሥር ለአጠቃለሏቸው ሕዝቦች የተሻለ ዕድል ይኖራቸው ነበር? ሥብዕናን እኮ የአወጁት ሚኒሊክ ናቸው፡፡ ጅብ የማያውቁት አገር ሄዶ ሆነና ማንም ዛሬ አይታወቅም እያለ የራሱን ዲስኩር ይነዛል፡፡ እውነታውን እንናገር ከተባለ ይሄ ነው፡፡አገርን አንድ የማድረጉ ሂደት አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ጦርነቶች ነበሩ፡፡ አንዳነዶችም በትብብር አንደ ሆነዋል፡፡ ጦርነትን የመረጡት በባርነት የሚገዙትን ሕዝብ ነጻ ላለመልቀቅ እንጂ የሕዝብን ነጻነጽ ከመጠበቅ እንዳልሆነ አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ ሌላው ጦርነት ሁሌም ቢያንስ ክቡር የሰው ልጅ ሕወት የሚጠፋበት ክስተት መሆኑ ከአቅም በላይ ካልሆነ የሚመረጥ አደለም፡፡ የሚኒሊክና ጎበና አገርን አንድ በማድረግ የተጠቀሙትም እንደመጨረሻ አማራጭ እንጂ አቅሙና ችሎታው አለን በሚለ በግደለሽና በትቢት አደለም፡፡ ይህ በዘመኑ የነበረው የእነዚህ ሰዎችና ተከታዮቻቸው አስተዋይነት በእርግጥም በዘመናቸው ላከናወኑዋቸው ታላላቅ ታዓምራዊ የሚመስሉ ክስተቶች ስኬት ረድቷቸዋል፡፡ ከጦርነትም በኋላ ዓላማቸው ሰዎችን በግዞት ሥር ማዋል አልነበረም፡፡ ይልቁንም የተዋጓቸውን ሳይቀር በማስተማር በዛው በሥልጣናቸው እንዲቀጥሉ አድርገዋል፡፡ የወላይታው ጦና አንዱ ናቸው፡፡የአርሲው ጦርነት አስከፊነት የሚታወቅ ሲሆን ምኒሊክም በዚህ ጦርነት በአለቀው ሕዝብ ምክነያት እጅግ ስላዘኑ ሰራዊታቸው ቀሪውን ሕዝብ እንዳይበድልና ከመሬቱም አሸንፌሀለሁ በሚል እንዳያፈናቀለው አዋጅ አውጥተው ነበር፡፡ አዋጁም “የአሩሲ ሕዝብ ባላወቀው ነገር ከእኛ ጋር ጦርነት እገጥማለሁ ብሉ እጅግ ተጎዳ፣ አሁንም አሸንፌዋለሁ ብለህ መሬቱንና ንብረቱን እንዳትቀማው አዝዤሀለሁ” የሚል ነበር፡፡ እውነታው ይሄ ነው፡፡ እንግዲህ የዚያን ጦርነት አስከፊነት ሚኒሊክም አዝነውበታል፡፡ ግን አማራጭ በመጥፋቱ የሆነ ጦርነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው በአካባቢ መሪዎች በሆነው ግትርነት ነው፡፡ ይህ ባይሆን መሪዎቹም በነበሩበት በመሪነታቸው የሚቀጥሉ በሆነ ነበር፡፡ የጂማው አባ ጅፋር የተከተሉት ይሄንኑ ነበር፡፡ በሕዝብና አገር ሥፋትማ አባጅፋር ከሌሎች የተሸሉ ነበሩ፡፡ ጦርነትን የመረጡት መሪዎችም ራሳቸውን ለመከላከል እንጂ ሕዝብንም ለመከላከል አልነበረም፡፡ በሚኒሊክ ሕዝቦች ወደነጻነት እንጂ ወደ ባርነት አለተሸጋገሩም፡፡  መቼም ጅብ በቀደደው ነውና የአኖሌን ጦርነት አስመልክቶ ብዙ ብዙ ይባላል፡፡ ሐርማ ሙራ አርማ ሙራ ይሄ ሁሉ ከጦርነቱ አስከፊነት አንጻር ወታደሮች ሊፈጽሙት የሚችል ግፍ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ያለው ድርጊት ዛሬም ሰለጠንኩ በሚለው ዘምን ሊፈጸም ይችላል፡፡ በወያኔና ኦነግግም ከዚህ  ያልተናነሰ ድርጊት ተፈጽሟል፡፡ ያ ክስተት በአኖሌ ተፈጽሞ ከሆነም ግን በሚኒሊክ ትእዛዝ እንዳልሆነ  ቢያንስ ይታወቃል፡፡ ክስተቱ መፈጸም አለመፈጸሙ በራሱ አጠያያቂ ሆኖ በሚኒሊክ ትዕዛዝ እንደተፈጸመ የሚነገረው ሌላው የሴረኞቹ መረዝ እንደሆነ ሕዝብ አላስተውል አለ፡፡ ይልቁንም ይሄው ዛሬ አይናችን እያየ ጆሮአችን እየሰማ እናት ልጇን ገደለው የልጅሽ ሬሳ ላይ ተቀመጭ የሚል የወያኔና አጋሩ ሰራዊት እና መሪም ናቸው ያሉት፡፡  ሚኒሊክ ግን እንዲህ ከሰበዓዊነት የወረደ ባሕሪ ያላቸው ሰው አይደሉም፡፡ እርግጥ ጀግና ከምንም በላይ ሰብዓዊነትን ያከብራል፡፡ ሚኒሊክም ጎበናም ጀግና ተብሎ ከሚነገርው ከተራ ጀግንነትም ያለፈ ጀግኖች ናቸው፡፡ የታሪክ ጸሀፍት ነን የሚሉ ሳይቀሩ ራሳቸውን እንኳን ያስተዛዝበናል ያላሉትን ጽሑፍ ነው የሚጽፉት የሚያወሩት፡፡ በሚኒሊክ 5ሚሊየን ኦሮሞውች ትገደሉ፣ በአርሲ ቢቻ ይታገሉ የነበር ከ120000 ያላነሱ ኦሮሞዎች ተገደሉ የሚሉትም የዚሁ ታሪክ አንዱ አካል ሆነው እናነባቸዋለን፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አጠቃላይ ተደምሮ ስንት እንደነበር አላውቅም፡፡ እኔ ኤለመንተሪ እያለሁ በደርግ ጊዜ 30 ሚሊየን እንደነበርን ትዝ ይለኛል፡፡ በሚኒሊክ ዘመን ጦርነት 5ሚሊየን ከኦሮሞ ብቻ ከሞተ እንግዲህ…. ጸሐፊዎቹን በትክክል ስናይ ደግሞ ምን አላማ ይኖራቸው ይሆን ያስብላል፡፡  እንዲህ ያሉ ተራ ወሬዎች ሳይቀሩ ናቸው ዛሬ ዋና ታሪክ ሆነው እውነታውን እንዳንይዝ የተደረግንው፡፡ ለነገሩ የሻቢያው ሰላይ የወያኔ ቅጥረኛው ተስፋዬ ገብረዓብም የጻፈው ሴራዊ ልብ ወለድ እንደታሪክ ማመሳከሪያነት ይሰራበታል፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ግን ምን ነካው የሚያሰኘን ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡

ሚኒሊክ ለኦሮሞ ሕዝብ ያደረጉት ውለታና ራዕይ

ሚኒሊክ እንደንጉስ ሕዝብ እንጂ የሚያዙበት መሬት የላቸውም፡፡ ሚኒሊክ ለልጆቻቸው የሚያወረሱት ፍልስፍና እጂ ነብረት የላቸውም፡፡ ሚኒሊክ መሪ እንጂ ገዥ አልነበሩም፡፡   ከላይ ያነሳሑትን የታሪክ ጉድፍ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሚኒሊክ የሚፈጽሙ ሳይሆን በተቃራኒው አገሪቱን ከመሩት መሪዎች ሁሉ በብዙ ፈተናና ትግል ሥልጣንን ለኦሮሞው ሕዝብ ለመሥጠት ሚኒሊክ እጅግ ብዙ ለፍተዋል፡፡ በመጨረሻም ተሳክቶላቸው ይህንኑ ሕልማቸውን አሳክተዋል፡፡ ዛሬ ኦሮሞ ሁሉ እንደ ጠላት የሚያቸው ጎበናና ሚኒሊክ ነጻ ያወጡት እነሱ እንደሆኑ አይረዳም፡፡ ከሚኒሊክ በፊት ነጻ አስተዳደር እንደነበረው የሚደሰኩረው የኦነጋውያ ትውልድ ኦሮሞ ብቻም ሳይሆን አብዛኛው ሌላውም ሕዝብ ባሪያ እንደነበር ታሪኩን ወደ ኋላ ሄዶ ይይ፡፡ ከየትኛውም ሕዝብ በተለየ ግን ሚኒሊክ ለኦሮሞ ሕዝብ ያደላ አስተዳደር እንደነበራቸው በተግባር የምናየው ታሪካቸው እያለ የሌለ ታሪክ የተሰበከው ዛሬ ያለው የቁቤ ትውልድ ዳግም ባርነትን መርጧልና ምርጫውን እየኖረ ይገኛል፡፡ ሚኒሊክ በዘመኑ ካሉ መሳፍንትም ይሁኑ የቤተክነት ሰዎች አፈንግጠው የተከተሉት ፍልስፍና የኦሮሞን ሕዝብ ብቻ አልነበረም ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ ልዩ ምዕራፍ የከፈተ ነበር እንጂ፡፡ አስተውሉ በተለይ ለኦሮሞ ሕዝብ ሚኒሊክ ያደረጉትን፡፡ በሚኒሊክ አስተዳደር ከፍተኛውን ሥልጣን የያዙት የኦሮሞ ልጆች ከመሆናቸውም በላይ በመጨረሻም ንግስናቸውን ሚኒሊክ ሊሰጡ የወደዱት ለዚሁ ሕዝብ ልጆች ነበር፡፡ በመጀመሪያ ለወዳጃቸው ለጎበና የልጅ ልጅ ነበር እሱ ባለመሳካቱ በመጨረሻ ለራስ አሊ ልጅ ለልጅ ኢያሱ ሰጡት፡፡ ልብ በሉ እነዚህ ልጆች ያደጉት በወላጆቻቸው አልነበረም፡፡ ለንግስና የሚያበቃቸውን ትምህርት እየሰጡ ያሳደጓቸው ራሳቸው ሚኒሊክ ነበሩ፡፡ ኢያሱን በእርግጥም በፍልስፍናቸው አብቅተው ለንግስና ብቁ አድርገውት ነበር፡፡ እንዳሰቡትም ንግስናቸውን ሰጡት፡፡ ኢያሱም አያቱ ሚኒሊክ (የእናቱ አባት) የነገሩትን ስልጣኑን እንደያዘ ማከናወን ጀመረ፡፡ ቀድሞም ለሚኒሊክ አስቸጋሪ የነበሩት መሳፍንትና የቤተክህነት ሰዎች ግን የኢያሱን ልጅነት እንደ ድክመት ተጠቅመው ኢያሱን ለመጣል ሴራቸውን ቀጠሉበት፡፡ በመጨረሻም ኢያሱን ለግዞት ዳርገው ሌሎችን ሾሙ፡፡ እስኪ ይህ አልሆነም ብሎ የሚከራክር የታሪክ አዋቂ ነኝ የሚል ይናገር፡፡ በአንድ ወቅት በዩኒቨርሲቲ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ የሆነ የታሪክ መምህር ይህን እውነት እንደወረደ ተናግሮት ግን በሚኒሊክ መሆኑን ለመቀበል አልወደደውም፡፡ እሱ የኦነጋውያን ቤተሰብ አባል በመሆኑ ብቻ የሚያውቀውን እውነት አንኳን መቀበልን አልወደደም፡፡ አውቀቱ ግን አለው፡፡ ቢችል ሌላ የሌለ ታሪክ ቢጽፍ በወደደ፡፡ ዛሬ ያለው ኦሮሞ ይህን የታሪክ እውነታ አይናገርም፡፡ ክብሩንና ማንነቱን የጠበቁለትን ጎበናንና ሚኒሊክን ይረግማል ይሳደባል፡፡ ያዋረዱትን የመርቃል፡፡ ባሪያ ከአደረጉት ጋር ተባብሮ የክብሩን ተምሳሌቶች ይሳደባል፡፡ እና ነጻነትንና ባርነትን ያልለየ ትውልድ በባርነት ቢኖር ለምን ይደንቃል፡፡ ምን እየሆነ እንደሆነ ሁሉም ያስተውል፡፡

የኦሮሞም በሉት የሌሎች ሕዝቦች ከነጻነጽ ዳግመኛ ወደ ጭቆና የመለሳቸው ይልቁንም አስቀድሞም ለኢያሱ መጥፋት ሲያሴር የነበረው ኋላም ሥልጣንን በእጃቸው ያገቡት ኃለስላሴ ናቸው፡፡ ስለዚህ ዝርዝር አልገባም፡፡ ምን ሊረባ፡፡ ያለስማቸው ሥም ስለተሰጣቸው ሚኒሊክና ጎበና እንዲሁም የዘመኑ አጋሮቻቸው ግን ገና ብዙ የምንናገረው አለ፡፡ እያንዳንዱ የእነዚያን ብርቅዬ የአገር ጀግኖች ክብርና ማንነት እስኪገባው ድረስ ለጠላቶቹ ባሪያ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ ለአለፉት 25 ዓመታት የጎበና ሥም ስድብ የሆነባቸው የሸዋና ሌሎች የኦሮሞ ተወላጆች አሁን አሁን ከተቀበሩበት ወጥተው በይፋ ጀግናቸውን ጎበናንና ሌሎች የክብር ተምሳሌት የሆኖ የኦሮሞ ልጆችን ታሪክ በኩራት መናገር ጀምረዋል፡፡ ይህ አንድ ታላቅ እረምጃ ነው፡፡  ሁሉም ኢትዮጵያ ሕዝብ ሊክደው የማይችል ሁሉንም አንድ አድርጎ ወደ ክብር የሚመልሰው የዚያ ዘመን ጀግኖች ታሪክ ነው፡፡ በሐበሻ ምድር እነዚያ ሰዎች በታሪክ ማማ ላይ የሚታወሱበት ዘመን ይመጣል፡፡ ያኔ ዛሬ ጀግና የሆኑ ሁሉ ተራራ እንዳልሆኑብን አንነማ እንደነበሩም ላናያቸው ሸለቆ ይሆናሉ፡፡ ያኔ ኢትዮጵያ ለሕዝቦቿ ምቹ አገር ትሆናለች፡፡ ንጉሱ ሚኒሊክ ሕዝብ እንጂ መሬት እንኳን አልነበረውም፡፡ አገር አንጂ ለልጆ የሚያወረሰው ንብረት አልነበረውም፡፡ በኋላ በመጡ ቀድሞም በነበሩ ሕዝብን እንደ ዕቃ በሚቆጥሩ መሪዎች ምክነያት የሚኒሊክና ጎበና እንዲሁም ታላላቅ ጀግኖቻችን ሥም የሚጠፋበት ምክነያት የለም፡፡

ጉዳዩ የአስትዋይ መሪነት ጀግንነት እንጂ የኦሮሞ የአማራም አዳለም፡፡ ሆኖም ዛሬ ኢትዮጵያ በምንላት ምድር ላይ ልዩና ታላቅ ሥራ ሠርተው ያለፉት የአሮሞ ልጆች በዝተው መገኘታቸው የማንካካደው እውነት ነው፡፡  ዛሬ ኦሮሞ ባሕሪው ተለውጦ ማንም የሚዘውረው የባዘነ ግን በቁጥር ግዙፍ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ የተዋረደው ያንን ታሪክ አጥላልተው የአንተ አደለም ብለው የነገሩትን የጠላቶቹን ቃል ሰምቶ ስለክብሩ የሞቱለትንና ያስከበሩትን ጀግኖች ተሳድቦ ለተሳዳቢ የሰጠ እለት ነው፡፡ ወያኔ ይህን ሕዝብ እዚህ ደረጃ እንዳደረሰቸው ስለምታውቅ ዛሬ ዘና ብላ ትዘውረዋለች፡፡ ተባባሪዎቿን ኦነግነንና የእስልምና ፅንፈኝነትን ለማስፋፋት ሕልም የሚያልሙትን ዛሬም የኦሮሞን ሕዝብ ውዥምብር ውስጥ እንዲቆይ በከፍተኛ ድጋፍ አሰማርታቸዋለች፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ከእነዚህ ገዳዮቹና አስገዳዮቹ እስከሚላቀቅ ድረስ እራሱም ነጻ አይወጣም ሌሎችም በግዞት እንዲቆዩ ምክነያት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ወያኔ በሁኔታው ዛሬ ነቁብኝ ያለቻቸውን እያደነች ነው፡፡ መረራና ቡድናቸው ዛሬ በወያኔ ወጥመድ ውስጥ የገባበት ዋናው ሚስጢር ይሄ ነው፡፡ መረራን ከመጀመሪያውም ሚስጢሩን እንደሚያውቁ ብትረዳም ብቻውን ምን ያመጣል በሚል እንደመናቅም አድርጓት ነበር፡፡

ዛሬ መረራ ስብስባቸውን ውስጥ ውስጡን እያበዙ እንደሄ ስለተረዳች ነው ዋና ኢላማዋ የሆኑት፡፡ ስለመረራና ሌሎች እውነተኛ የኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት ታጋዮች ግን የሚናገርላቸው የኦሮሞ ሕዝብ ልሳን ጸጥ ነው ያለው፡፡ ሌላ ጊዜ ምደሩን ሁሉ የሚያጮኸው ኦሮሞ ነኝ የሚል አክቲቪስትና የወያኔ ልዩ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ስለ መረራ ትንፍሽ አላሉም፡፡ ይልቁንም እንኳን  ሆነ በሚል ሕዝብን ሌላ ትኩረት እንዲሰጥ ለጌታቸው ወያኔ እያገለገሉ ነው፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ

አሜን

ሰርጸ ደስታ