የአውሮፓ ፓርላማ ኅብረት ባቀረበላቸው ግብዣ ቤልጂየም ብራሰልስ ደርሰው እንደተመለሱ በተጠረጠሩበት የሽብር ተግባር ወንጀል ታስረው የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ለ40 ዓመታት ስለሽብርተኝነት መጥፎነት ሲያስተምሩ ኖረው በሽብር ተግባር ውስጥ ሊሳተፉ እንደማይችሉ መናገራቸውን ጠበቃቸው ገለጹ፡፡

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ታኅሳስ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ የቀረቡት፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበርና የመድረክ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር መረራ ላይ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ላለፉት 28 ቀናት ያደረጋቸውን ምርመራዎች ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

እንደ መርማሪ ቡድኑ ገለጻ ከራሳቸው ኢሜይል፣ ፌስቡክና ከተለያዩ መገናኛዎች ያገኘውን የሰነድ ማስረጃ ማስተርጎሙንና ለማስተርጎም ሰጥቶ በመጠባበቅ ላይ መሆኑንም ማስረዳቱን የዶ/ር መረራ ጠበቃ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር መረራ ፈርመው የራሳቸው ቃል መሆኑን ባያረጋግጡለትም፣ በተወሰነ መልኩ ቃላቸውን መቀበሉንም ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱንም ጠበቃው አክለዋል፡፡

በተጨማሪም የተጠርጣሪውን ቀሪ ቃል መቀበል፣ ሌሎች ቀሪ ማስረጃዎችን መሰብሰብና ማስተርጎም እንደሚቀረው በመግለጽ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 20(3) መሠረት ተጨማሪ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲቀፈድለት መርማሪ ቡድኑ መጠየቁን ጠበቃቸው ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር መረራ የሰላማዊ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ መሆናቸውንና ወደ አውሮፓ ቤልጂየም ብራሰልስ የሄዱት፣ የአውሮፓ ፓርላማ ኅብረት ባደረገላቸው ግብዣ መሆኑን ደጋግመው ማስረዳታቸውን ጠበቃቸው አቶ መሐመድ ኑሩ አብዱልከሪም ተናግረው፣  የኢትዮጵያን መንግሥት በሰላማዊ መንገድ ከመቃወማቸው በስተቀር የፈጸሙት ወንጀል እንደሌለ መናገራቸውን ጠበቃቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና መመርያውን እንዳልጣሱና ከማንም አሸባሪ ድርጅት ጋርም አለመወያየታቸውን እንደተናገሩ የጠቆሙት ጠበቃው፣ አዋጁን በመጣስ ከግንቦት ሰባት መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ብራሰልስ ላይ ተገናኝተው ‹‹ተወያይተዋል፣ ለሚዲያ መረጃ ሰጥተዋል›› የተባለው ስህተት መሆኑንና ምንም ዓይነት ውይይትም ሆነ መረጃ እንዳልሰጡ እንደነገሯቸው ጠበቃው ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር መረራ ለጠበቃው እንደገለጹላቸው የአውሮፓ ፓርላማ ኅብረት ለእሳቸው፣ ለዶ/ር ብርሃኑና ለአትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በተናጠል ባደረገላቸው ጥሪ ብራሰልስ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ብራሰልስ የሄዱትም በኮንፈረንሱ ላይ ለመሳተፍ ብቻ መሆኑንም እንዳስረዷቸው ጠበቃው አክለዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ ዓላማም እንዳልነበራቸው እንደነገሯቸው አቶ መሐመድ አስረድተዋል፡፡

ከቀድሞ ጓደኛ ጋር በአጋጣሚ ተገናኝቶ የእግዚአብሔር ሰላምታ መለዋወጥ ወይም ስላለፈ ታሪክ መነጋገር ወንጀል አለመሆኑንና መቼም ቢሆን ወንጀል ሊሆን እንደማይችል ዶ/ር መረራ እንደገለጹላቸውም አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ለዚህ አገር ሲያደርጉት ከቆዩትና ከዕድሜያቸው አንፃር ፍርድ ቤቱ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸውን እንዲፈቅድላቸው ጠይቀው እንደነበር ጠበቃው አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ የዋስትናውን ጥያቄ በማለፍ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን የ28 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዶ ለጥር 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡