ከማተቤ መለሰ ተሰማ እንደማነኛውም የሰውልጅ አማራውም የህግ የበላይነትን፣ እኩልነትና ነጻነትን፣ የሰባዊ መብት መከበርን፣ እድገትንና ብልጽግናን ወ.ዘ.ተ. አጥብቆ ይናፍቃል። እነዚህን ሰው ለመሆን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ለመቀዳጀትም ዋጋ ሲከፍል አመታትን አስቆጥሯል። እስካሁን ግን ልፋቱ ሁሉ አልተሳካም ብቻ ሳይሆን ከጊዜ ወደጊዜ እየከፋና እየመረረ፣እንቅስቃሴው ሽባ ውጤቱ ፍሬ አልባ። እየሆነና ኢትዮጵያዊ ነኝ በማለቱ በሌላው ወገኑ እንደጠላት እየታየ በመገደል ላይ ነው። እየደረሰበት ያለውን መፈናቀል፣ ንብረት መዘረፍ፣መደብደብ፣ መታሰር፣ መገለልና መገደል። ለመከላከል ቢዘገይም እንኳን መደራጀቱ በእኔ እምነት ተገቢነው ባይ ነኝ። ግን መደራጀት መሰባሰብ መሆኑ ቀርቶ እንደገና በበርካታ ድርጅት የመበታተን ሁኔታ በመታየት ላይ መሆኑ መዳክምን እንዳያስከትል ከምር እሰጋለሁ። አማራው በአማራነቱ ብቻ ከመደራጀት ይልቅ። እዚህ ግባ በማይባል ጥቃቅን ምክናያትና በስልጣን ፈላጊ ግለሰቦች ሰበብ። በተለያየ ድርጅት ከተበታተነ። ዘሩን ጨርሶ ከመጥፋት መከላከል ከማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ የማይቀር ነው። ስለዚህ አማራው ህልውናውን ለማቆየት ከፈለገ። የግል ፍላጎትን ገትቶና ቂምን አስወግዶ። በፍጹም ቅንነት ላይ በመመስረት እርስ በራስ መደማመጥን፣መቻቻልን፣ መተባበርን፣ መርሁ በማድረግ በአንድ አማራነት ዙሪያ መሰባሰብ መቻል አለበት እላለሁ።

አማራው በአማራነቱ መደራጀትና መተባበር ለምን አስፈለገ።
=====================================
1.ባለፍት 50 ዓመታት በኢትዩጵያ የተካሄደው ፀረ አማራ ዘመቻ ፍሬ በማፍራቱ። አማራው እንደ ናዚ ጦር ወንጀለኛ ተቆጥሮ። በሁሉም አካባቢ ከምር በመገፋቱና ከሁሉም ወገኑ በመገለሉ።
2.አማራው ዘሩን እንዳይተካ በጀት ተበጅቶ ተቋማት ተመስርተው መሬት በረገጠ ተግባራት እንዲመክን በመደረጉ።

3.አማራ ከተቻለ እንዲጠፋ ካልሆነ ደግሞ ይህነው የሚባል ሚና የሌለው ህዝብ እንዲሆን ከስነልቦና ጦርነት ጀምሮ በከፍትኛ ሁኔታ እየተጠቃ በመሆኑ። 4.አማራ ለዘመናት ከኖረበት ቀየ እንዲፈናቀልና እንዲሳደድ በመደርጉ።

5.በሁሉም የሃገሪቱ ክልሎች አማራው ተለይቶ በሁሉም ብሄረሰቦች እንዲጠላና በጭካኔ እንዲጨፈጨፍ፣ በመደረጉ።

6. ከእነህይወቱ በሳት መቃጠሉ፣ በገድል መጣሉ፣ከአካሉ የተቆረጠውን ስጋ እንዲበላ በመደረጉ፣ ሚስትና ሴት ልጆቹ ቁሞ እያየ እንዲደፈሩ በመደረጉ።

7. አማራው በየትኛውም መስሪያ ቤት ስራ እንዳይቀጠር በመደረጉና ባጋጣሚ ከተቀጠረም ከበታች ሰራተኛነት የዘለለ ቦታ ላይ እንዳይቀመጥ በመደረጉ። በአጠቃላይ በወያኔ አሰራር አማራ የበይ ተመልካች በመደረጉ።

8.በሚሊዬን የሚቆጠር አማራ ባለፉት 26 ዓመታት ብቻ በተሸረበው የዘር ፍጅት ሴራ ሰለባ መሆኑና ዛሪም በዚህ ህዝብ ላይ ያነጣጠረው የዘር ማጥፋት ዘመቻ መልኩንና ቅርፁን እየቀየረ በመቀጠል ላይ በመገኘቱ።

9.ወያኔ እስካሁን አማራውን ከፓለቲካው፣ ከኢኮኖሚው፣ ከወታደራዊ ና፣ ከማህበራዊ መስክ የማስወገድ ስራ ሲስራ በመኖሩና ባገኘው ዉጤት ሳይረካ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች በመኖራቸው።

10.የአማራ መሪትና ንብርቱ ተዘርፎ ድሃ እንዲሆን በመደረጉ። ልጆቹ መስራት እየፈለጉና መስራት እየቻሉ አማራ በመሆናቸው ብቻ በሃገራቸው ላይ ስራ ስለማይቀጠሩ። በስራ እጥነት እንዲቀመጡ መደረጉ። ይህንን ተከትሎም በአለማቀፍ ደረጃ በሚያስደነግጥ መልኩ
ስራ ፍለጋ በየ በርሃው የአውሪ በእየ እውቅያኖሱ ያሳንባሪ እራት እንዲሆኑ በመደረጉ።
11. በድህነት ወለድና መንግስት ሰራሽ በሆኑ ቸነፈር ህዝቡ እያለቀ ቁጥሩ እንዲቀንስ ወያኔ የቀየሰው በተግባር የተፈተነ እስትራቴጂ ማቆሚያ ስላጣ።

12.አማራው ያልሰራው ውንጀል ሲቆለልበትና፣ ከወገኑ ተለይቶ ሲገደል ዝም በማለቱ ውሽቱ እንደ እውነት እየተቆጠር በመሄዱ።

13. በኢትዩጽያ ውስጥ ያሉ የራሳቸውን ሀገርና መንግስት የመመስረት ግብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ሀይሎች አዝማሚያ ስለሚያስጋው ለእራሱም ለኢትጵያም ደህንነት ተደራጅቶ መገኚት አስፈላጊ በመሆኑ።

14.ትናንት አማራን ማጥፋትን የትግላቸው ግብ አድርገው የተነሱ ሀይሎች አስተምሮታቸው ሰምሮላቸው ሀይል አንቀሳቅሰው ባለፍት 50 ዓምታት አማራን እንደ ሁኔታዎች ሲያጠቁ የነበረ ከመሆኑ በላይ ዛሬም ቀላል የማይባል የሰው ሀይልና ፋይናንስ በማንቀሳቀስ በአማራ ህዝብ ላይ ሁለእንተናዊ የጥቃት ዘመቻ የከፈቱበት በመሆኑ።

15. የአማራ ህዝብ እንደህዝብ መብቱ ተከብሮ በአገሩላይ እንዲኖርና ያሉትን ሀብቶች አቀናጅቶ በመጠቀም ሌሎች ስልጡን ህዝቦች የደረሱበት ደረጃ መድረስ እንዳይችል በመደረጉ።
16.ይህ ሁሉ ግፍና ሰቆቃ ሲፈጽምበት ጉዳዩን በባለቤትነት ይዞ ጉዳቱን ከፍ ሲል ለዓለም ዝቅሲል ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያሳውቅለት ከፍል የግድ በማስፈለጉ።

17.ተደራጅቶ ዘሩን ጨርሶ ከመጥፋት መከላከል የግድ ስለሆነ።

18.በእሳቸው እንቅስቃሴ ግድያውና ማፈናቀሉ ቀንሶ የነበረው ከፕ/ር አስራት ሞትና ከመላወ አማራ ድርጅት ከመሃድ መፍረስ በኋላ ግድያውና ማፈናቀሉ እንደገና አገርሽቶ በደቡብና በቤንሻንጉል ከልሎች ሲቀጥል መታየቱ የመደራጀትን ጥቅም አመላካች መሆኑ።
19.ህብረብሄር ድርጅቶች ያተኮሩት በአጠቃላዩ ወያኔን በማስወገዱ ትግል ላይ እንጅ አማራው ጨቋኝ ነው የሚለውን ፕሮፓጋንዳ ሃሰትነት ለህዝብ ለማስረዳት የተለየ መርሃግብር ነድፈው ስለ አማራው ብቻ ሊሰሩ ስለማይችሉና አማራው ከወገኑ ተለይቶ በሁሉም ዘንድ እንደ ዱር እንስሳ እየታደነ እንዲገደል ያደረገው የውሽት ታሪክ በእውነት ላጲስ መፋቅ ስላለበት። ይህን ደግሞ መስራት ያለበት አማራው እራሱ በመሆኑ። የሚሉት ከብዙው በጥቂቱ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ተግዳሮቶች በቀጥታ በአማራ ህዝብ ህልውና ላይ የተጋረጡ ከባድ አደጋዎች በመሆናቸው ። የአማራው ህዝብ የሚያደርገው ትግል የህልውና እንጅ የቅንጦት እንዳይሆን አድርገውታል። የአማራው ትግል በመኖርና ባለመኖር መካከል የሚካሄድ ትግል እንጅ የፓለቲካ ስልጣን በመፈለግ ወይንም ሌላ አገር ለመመስርት አይደለም። ለአማራው ህዝብ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብስብ፣ የሃብትና የስልጣን ክፍፍል ዲሞክራሴያዊ መብቴ ይጠበቅልኝ። የሚሉ ጥያቄዎች ቅንጦቶች ናቸው። የአማራው ህዝብ አንገብጋቢው ጥያቄ እንደሰው በምድር ላይ በህይወት መኖር አለብን፣ ዘራችን እንደዳይኖስር ከዓለም መጥፋት የለበትም ነው። ለምንድን ነው የአማራው ነገድ እራሱን መካላከል ያልቻለው? ካልን መልሱ ሌላውን ትተን ያለንበትን ወቅት ብቻ በአይነ ህሌናችን ብንቃኝ። የፖለቲካ ሊቃን ያተኮሩት በሚያቀራርቡ አበይት ጉዳዮች ላይ ሳይሆን በሚያራርቁ ጥቃቅን ነገሮች ላይ ስለሆነ ነው። ይህ መለያየትን መሰረት ያደረገና አንዱን የአማራ ነገድ በመንደር የፖለቲካ ፍልስፍና ለመሽንሽን የሚደረገው እሩጫ በአጭር ካልተቀጨ ደግሞ ወያኔ የጀመረውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ያለምንም እንቅፋት እንዲያሳካ መፍቀድ ነው። እስኪ ከአማራው ነገድ ተወላጅ በርካታ ድክመቶቻችን መካከል 4ቱን ብቻ ለአብነት ልጥቀስ።

 

1.የግል ጥቅምን አስቀድመናል።
2.አኩራፊነትን ተላብሰናል።
3.በተቃዋሚ ተቃዋሚነት ተሰልፈናል።
4.ምንቸገረኝ ማለትን አዳብረናል።

ለወደፊቱ መፍትሄው ምንድን ነው።
======================

1.ልዩእነትን በማስወገድ ተባብሮ መቆም።

2.ከአለፉ ስህተቶቻችን መማር።
3.ግዴለሽነትንና ዝምታን ማስወገድ።

4.ወደጎን መራገጥን አስወግደን መላ ትኩረታችንን በወያኔ ላይ ማድረግ። የሚሉት ተጠቃሽ መሆን የሚችሉ ይመስለኛል።እነኝህን ነጥቦች ስራላይ ስናውል ብቻ ነው። አንድነታችንና ተብብራችን የሚጠናከረውና ዘራችንን ጨርሶ ከመጥፋት ልንታደገው የምንችለው። እነኝህን ስራላይ ስናውል እና ዝምታውን ስብረን ስንወጣ ነው የጥፋት መልዕክተኛውን የህዋሃትን ቡድን ብቻ ሳይሆን። እሱ በገፍ ያመረታቸውን እርሃብን፣ እርዛትን ስደትና ውርደትን ክፍሲል ከኢትዮጵያ ህዝብ ዝቅ ሲል ከአማራው ነገድ ትከሻ ላይ ማስወገድ የምንችለው።

ከበዛው ዝምታችን ጥቂቱን በመጥቀስ ላስታውሳችሁ።
================================

1.በደሙ ፍሳሽና በአጥንቱ ክስካሽ። ሉዓላዊ እነታችንን ሲያስከብር የኖረውን የኢትዮጵያን የመከላከያ ሰራዊት የደርግ ሰራዊት ነህ በማለትና በመበተን በእራብና በእርዛት እንዲያልቅ ሲያደርገው። በተለይም ከሶማሌው ወራሪ የሲያድባሬ ጦር ጋር ሲፋለም ግማሽ አካሉን ለሃገሩ ገብሮ ጀግኖች አምባ ይጦር የነበረውን አይኑ የፈረጠ እጅ እግሩ የተቆረጠ ወንድማችንን አውጥቶ በመበተን የአውሬ እራት ሲያደርገው ዝም አልነው።

2.በሃገሬቷ ላይ ተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮች ቢከሰቱ። መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ለ10 አመት ልብስና ቀለብ እንዲሆን ታስቦ ከቀደምትነገስታት ጀምሮ በጠቅላይ ግምጃ ቤት ሲጠራቀም የኖረውን ወርቅ፣ አልማዝ፣ እንቁ ወ.ዘ.ተ. የከበሩ ማህድናትን ወያኔ ወደ ትግራይ ሲጭን ዝም አልነው።

3.ሃገሬቷ በብዙ ወጭ ያስተማረችውን የሰው ሃይል ከስራ በማፈናቀል በደናቁርት ካዲሬዎቹ ሲተካው ዝም አልነው።

4.በመላው ኢትዮጵያ እንደ ጭድና ጭቃ ተዋህዶ በደምና በስጋ ተዛምዶ ይኖር በነበርው የአማራ ነገድ ላይ ይፋ የዘር ማጥፋት አዋጅ በማወጅ እንደዱር አውሪ በእያለንበት እያሳደነ ሲያስርሽን ዝም አልነው።

5.ሃገራችንን ዙሬያዋን እንደዳቦ እየቆረሰ ለጎረቤት ሃገራት ሲያድል ዝም አልነው።

6.አርሶ አደሩን ከቅየው በማፈናቀል መሬቱን ለውጭ ሃገር መንግስታትና ባላሃብቶች ሲሸጥ ዝም አልነው። እንዲያው ለአብነት ያክል እንጅ የእኛ ዝምታና የወያኔ ጥፋት ስንቱ ተቆጥሮ ያልቃል። እዚህ ላይ የአንድ እናትና ሌባ ልጃቸው አፈታሪክ ትዝ አለኝ።አንድ ወንድ ልጅ ያላቸው እናት ነበሩ አሉ። ልጃቸው በመጀመሬያ ከጎረቤታቸው እንቁላል እየሰረቀ ሲያመጣላቸው እሳቸው ተቀብለው በመቀቀል በጋራ ሲበሉ። ቆይቶ ደግሞ ዶሮ ሰርቆ ሲያመጣላቸው ወጥ በመስራት በጋራ ሲመገቡ። እንደገናም በግና ፍየል እየሰረቀ ሲያመጣ እናት ያለምንም ተግሳጽ እየተቀበሉ በማዘጋጀት ሲመገቡ ብዙ ከኖሩ በኋላ ከእለታት አንድ ቀን በሬ ሰርቆ ስለተያዘ ለፈርድ በቀረበበት ወቅት እናት ችሎት ላይ ምነው ልጄ ጉድ አደረግኸኝ ይሉታል አሉ። ልጅም ጉድ ያደረግሽኝ እማ አንች ነሽ። በመጀመሬያ እንቁላል፣ ከዚያ ዶሮ ከዚያ በግ እየሰረቅሁ ሳመጣልሽ ስቀሽ ከመቀበል ይልቅ ብትቆጭኝ ኖሮ ለዛሬው ፍርድ አልደርስም ነበር ብሏቸው አረፈ ይባላል። እኛም ሁሉንም በዝምታ ስለተቀበልነው ወደፊት የቀረው ነገር ቢኖር እንደበሬ ጠምዶ ማረስ ነው። ዝምታችን ካላበቃ ወያኔ ይህንንምከማድረግ ወደኋላ አይልም። ከዚህ ውርደትና የቁም ሞት ለመዳን መፍትሄው አማራው በክፍላተ ሃገር ሳይከፋፈል በአማራነቱ ብቻ ተባብሮና ተደራጅቶ መታገል ብቻ ነው። ተባብርን ባለመቆማችን አገራችንን ለአድጋ ህዝባችንን ለውርደት አጋልጠናቸዋል። የወጣቱን ትውልድ እራይም አጨልመንበታል፣ የአማራውን የነጻነት ትግልም ገድለነዋል። ዛሬ ይህንን የጥፋት መልዕክተኛ ቡድን ተባብረን ማስወገድ ካልቻልን ነገ የአማራው ነገድ ታሪክ በነበር ከመተካት አይድንም። የወያኔም የመጨረሻው መጨረሻ ልዕለ ግብ። ዝቅ ሲል አማራ የሚባል ነገድ ዘሩ ከምድረገጽ እንዲወገድ። ከፍ ሲል ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር እንደ ዩጎዝላቢያና ምስራቅ ጀርመን ከዓለም ካርታ እንድትፋቅና እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ በማለት አፍ ሞልቶ ደረት ነፍቶ የሚናገር ዜጋ እንዳይኖር ማድረግ ነው። እንተባበር ስል ግን ከ25 ሚሊየን እንደሚበልጥ የሚገመተው የአማራው ነገድ የአንድ አመለካክት አራማጅ እስከሚሆን እንጠብቅ እያልሁ አይደለም። እንዲያውም በእኔ እምነት ከታለመው ግብ ለመድረስ ወሳኙ ብዛት ሳይሆን ጥራት ነው። ወንጌልን ለዓለም ህዝብ ይሰብኩ ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ የመረጣቸው ደቀ መዛሙርቶቹ 12 ብቻ ነበሩ። ዘራችንን ከጥፋት ለመታደግም ግዴታ ሚሊዮኖች አንድ እስኪሆኑ መጠበቅ ተገቢ አይመስለኝም። ዋናው ቁም ነገሩ ያለው ግን በሌሎች መሷዕትነት ተጠቃሚ ለመሆን ሂሳብ የሚሰሩ ሰዎች ሳይሆኑ እራሳቸውን እንደሻማ አቅልጠው የአማራውን ነገድ ለመታደግ የወሰኑ የአማራው የቁርጥ ቀን ልጆች ከእያሉበት ተፈላልገው መተባበራቸው ላይ ነው። በአሳለፍነው እሩብ ምዕተ አመት። አማራው እንደበግ ታርዷል፣ ከቅየው ተፈናቅሎ ተሰድዷል። በዚህ የእልቂት ዘመን የአማራው የአብራኩ ክፋይ የሆነው በ3 ተከፍሎ ግማሹ ዘሩን ከጭርሶ ጥፋት ለማዳን ሲታትር ግማሹ በባንዳነት ተሰልፎ ለህዋሃት መሳሪያ በመሆን እልቂቱንበማፋጠን ላይ ሲሆን ግማሹ ደግሞ አርበኛውና ባንዳው ከሚተላለፍበት መሃል መንገድ ላይ ቆሞ ለሁለቱም ድንጋይ በማቀበል ላይ ነው። አሁን ባንዳውንና መሃል ሰፋሪውን በመተው እውነተኛው የአማራ የቁርጥ ቀን ልጆች በመተባበርና ሃይላችንን፣ ገንዘባችንን፣እውቀታችንን በማቀዳጀት ቀን ሳንቆርጥ ጊዜ ሳንመርጥ ድርጊትን መጀመር ነው የሚጠበቀው። ለዚህ እንዲረዳንም ቁጭ ብለን እስካሁን ምን ሰራን፣ ምንስ ጎደለን፣ ወደፊትስ ምን ማድረግ አለብን? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተን በመገምገምና ድክመቶቻችንን በማስወገድ ተባብረን ለተግባር መሰለፍ የወቅቱ አንኳር ጥያቄ ይመስለኛል።

የመተባበር ጠቀሜታው በአጭሩ።
===================

መተባበር ሃይልን ይገነባል፣ ደጋፊን ያበዛል፣ ታማኒነትን ያተርፋል። የሰው ሃይልን፣ የገንዘብ ሃቅምን፣ የመረጃና የኔት ወርክ ብክነትን ይቆጥባል።

የመተባበር እንቅፋቶች።
==============

1ኛ.እራስ ወዳድነት።

2ኛ. ስልጣን ፈላጊነት።

3ኛ. የቅንነት ጉድለት።

4ኛ.ግልፍተኝነት።

5ኛ.የራስን ስሜት ብቻ ማዳመጥ። የሚሉት ከብዙው በጥቂቱ ይጠቀሳሉ። የትብብር አይነቶች።

የትብብር አይነቶች
===========

በርካታዎች ቢሆኑም ለዛሪው ግን 3ቱን ብቻ ልጥቀስ። እነሱም።
1ኛ. ድጋፍ ሰጭእነት።

2ኛ. ተዛማጅእነት።

3ኛ. ሽርክና የሚሉት ሲሆኑ። አሁን ለአማራው ነገድ ትብብር የሚጠቅመን የትኛው ነው የሚል ጥያቄ ከተነሳ መልሱ ሁሉንም እንደእየ ሁኔታው መጠቀም ጉዳት የለውም የሚል ይሆናል። ዋናው ነገር ዘራችንን ከምድረግጽ ለማስወገድ የዘመተብን ትልቁ ጠላት ወያኔ እያለ እርስ በእርሳችን መነታረክንና በበርካታ ድርጅቶች መበታተንን ማቆም ከመቻሉ ላይ ነው። ከሌሎች ሃገራት ትብብር ምን እንማራለን። 1ኛ. በእንግሊዝ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጥር 1659 በተደረገው የተቃዋሚዎች ትብብር። 2ኛ. በኮሎቢያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጥር 1958 በተደረገው የተቃዋሚዎች ትብብር። 3ኛ. በቤንዙላ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጥር 1958 በተደረገው የተቃዋሚዎች ትብብር። 4ኛ. በፖላንድ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጥር 1989 በተካሄደው የተቃዋሚዎች ትብብር። 5ኛ. በሱይድን እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጥር 1909 በተካሄደው የተቃዋሚዎች ትብብር። 6ኛ. በደቡብ አፍሬካ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጥር 1994 በተካሄደው የተቃዋሚዎች ትብብር። እና በሌሎችም ሃገራት በእየጊዜው በተደረጉ ትብብሮች ከስድስት ወር እስከ አንድ አመት። በሚደርስ ጊዜ ውስጥ ህዝብን የድል ባለቤት አድርገውታል። ከእራሳችን የትብብር ሙከራዎችስ ምን እንማራለን። ሁላችንም እንደምናውቀው በሃገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ከዚያ በፊት ድርጅት መፍጠር ስለማይፈቀድ። ከሃይለስላሴ መውረድ በኋላ የተለያዩ ድርጅቶች ተመስርተው ብዙ የመተባበር ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን እነዚህን ሙከራዎች በሶስት ከፍለን ማየት እንችላለን።

1ኛ.በአንድ ተጽዕኖ በሚያደርግ ድርጅት ዙሬያ የተወሰነ ነጻነት ያላቸው ድርጅቶች የፈጠሩት ትብብር።

2ኛ. ተመጣጣኝ ሃቅም ያላቸው ድርጅቶች የፈጠሩት ትብብር።

3ኛ. ምንም አይነት ነጻነት የሌላቸው ድርጅቶች በአንድ ጠንካራ ድርጅት ዙሬያ በመሰባሰብ የሚፈጥሩት ትብብር ነው።

እያንዳንዳቸውን በምሳሌ እያስደገፍን እንይ።
==========================
ለመጀመሬያው ምሳሌ ሊሆነን የሚችለው በደርግ ዘመን 5 ድርጅቶች በጋራ የፈጠሩት ኢማሌድህ የተባለው ትብብር ነው። ይህ ትብብር በዙ ሳይቆይ በደርግ ቁልፍ ሰዎች የሚመራው ሰደድ ሁሉንም ዋጣቸው። ሁለተኛው ምሳሌ የሚሆነው። ወያኔን ለመጣል ተቋቁመው የነበሩ ትብብሮች ማለትም።

1. አማራጭ ሃይሎች።

2. የተቃዋሚዎች ህብረት።

3. የዲሞክራሴያዊ ሃይሎች።

4.ቅንጅት።

5. ኢፍዲን። የተባሉ ድርጅቶች በእየጊዜው ጀምረውት የነበረው ትብብር ነው። በእኔ ምነት በሁለተኛ ምሳሌእነት የጠቀስኳችው ድርጅቶች ቢቀጥሉ ኖሮ እውነተኛ ዲሞክራሴን ማምጣት ይችሉ ነበር። ለሶስተኛው ትብብር ምሳሌ የሚሆነን ወያኔ ነው። ለዚህ በአጭሩ ወያኔ ጠፍጥፎ የሰራቸውና ሲፈልግም በአንድ ቀን ሊያፈርሳቸው የሚችለው። ምንም አይነት ነጻነት የሌላቸውን ኦህዴድን፣ ብአዴንን፣ ዴህዴግን፣ ወ.ዘ.ተ. ያካተተውና ኢህአዴግ የሚል ስም የተስጠው ነው። ያለፍንበትን የፖለቲካ ሂደት በግርድፉም ቢሆን ከዚህ በላይ ለመነካካት የሞከርሁት ያለምክናያት አይደለም። ድርጅቶቹ እያንዳንዳቸው የተለያየ አመለካክትን የሚያራምዱ በመሆናቸው ለምሳሌ በመንግስት አደረጃጅት አንዱ ፌዴራል መንግስትን አዋቅራለሁ። ሌላው አሃዳዊ መንግስትን እመርጣለሁ። አንዱ ደግሞ ከእነ አካቴው እገነጠላለሁ። እየተባባሉ። በርዕዩታለም ፍልስፍናውም። አንዱ አብዮታዊ ዲሞክራሴን እከተላለሁ። ሌላው ሶሻል ዲሞክራሴን እመርጣለሁ። አንዱ ሌቨራል ዲሞክራሴን አሰፍናለሁ ወ.ዘ.ተ. በመባባል ልዩነታቸውን እያሰፉ
የኢትዮጵያን ህዝብ መከራና የወያኔን እዕድሜ ከሚገባው በላይ ሲያራዝሙት ኖረዋል። የአማራው ነገድ ትብብርና ትግል ግን ከላይ እንደተጠቀሱት ድርጅቶች ለፓለቲካ ስልጣን አይደለም። የአማራው ትግል የህልውና ትግል ነው። የአማራው ትግል በህይወት የመኖርና ያለመኖር ትግል ነው።ስለዚህ አማራው በርዕዮታለምም ሆነ በፖሊሲ የሚነጋገርበት ምክናያት ስለሌለው የሚደረገው ትብብር ስኬታማ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ።

የአማራው ትብብር ከብርት የጠነከር እንዲሆን መደረግ ያለበት።
=======================================

1.የትብብር እንከኖችን ጨርሶ የሚያስወግድና የሁሉንም ተባባሬዎች መብት የሚያስከብር ጠንካራና አሳሬ መመሬያ ማዘጋጀት።

2.የሚደረገውን ሁሉ እንቅስቃሴ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው ማድረግ።

3.የሚመረጠውን አመራር የስልጣን ጊዜ መገደብና ሁሉን አሳታፊ መርህን መዘርጋት።

4.ችግሮች ሲከሰቱ ፈጥኖ የሚፈታ የግልግል ቦርድ ማቋቋም የሚሉት ይሆናሉ ብየ አስባለሁ።

የአማራው ትብብር ቢከተል የሚሻለው መርህ።
============================

1.አማራነትና የኢትዮጵያዊነት አንዱ ካላንዱ የማይኖሩ ደምና ስጋ መሆናቸውን መቀበል።

2.የትግል አቅጣጫዎችን ወያኔ ላይ ብቻ ማድረግ።

3.ጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋና ወሎ ከሚል ከፋፋይ መንፈስ በመውጣትና። አማራ በሚል ድርጅት ጥላስር ተስባስቦ በአንድነት አብሮ መታገልና ማታገል።

4.ከሌሎች ብሄሮች ጋር የአማራን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ተባብሮ መስራት።

5.በሌሎች ድርጅቶች ላይ ችግር ቢኖር እንኳን .የአማራውን መብት እስካልነኩ ድርስ ባለመተቸና ባለማግለል ፍርዱን ለህዝብ በመተው የጎንዮሽ አለመናቆር።

6.በአማራ ክልል ህዝቡን በየደረጃው በሚስጥር ማደራጀትና ከተወካዮች ጋር በስውር መገናኘት::

7.ብሄረ-አማራ የሆኑ የመንግስት ባለስልጣናትና አባላትን በቤተሰቦቻቸውና በጓደኞቻቸው አማካኝነት የማሸሽ ሥራ መስራትና ምስጢር እንዲያሾልኩ ማድረግ።

8.በአማራው ላይ 50 አመት የተነዛበትን የውሽት ፕሮፓ ጋንዳ ለማጋለጥ።የተጠናከረ አጻፋዌ ፕሮፓጋንዳና የስነ ልቦና ጦርነት መክፈት።

9.በአማራ ህዝብ ላይ ስለደረሰው በደልና ግፍ ለሁሉም የሰው ልጅ ተጨባጭ በሆነ መንገድ በማቅረብ ማስረዳት።

10.ከሌሎች ብሄርም ሆነ ህብረ ብሄር ፓርቲዎች ጋር ሁሉን-አቅፍ ውይይት ለማድርግ ዝግጁ መሆን።

11.በአማራው ላይ የተፈጸሙ ዝግናኝ ድርጊቶች ከሚፈጥሩት የበቀል አስተሳሰብ በመውጣት ስለወደፊቱ ማሰብ::

12.ከሌሎች ጋር በመተባበር ማነኛውም ሰው በዘሩ፣ በሃይማኖቱና በአመለካክቱ የማይገለልባት። አንዲት የታፈረችና የተከበረች ዲሞክራሲያዌት ኢትዮጵያን መፍጠር። የሚሉት የማይታለፉ የትግሉ አንኳር መርሆች መሆን አለባቸው ብየ አምናለሁ።

የአማራን ዘር ጨርሶ ከመጥፋት እንታደግ!!!!
ኢትዩጵያዌ የአማራ ተጋድሎ ያሽንፋል!!!

ማተቤ መለሰ ተሰማ ኢሜል matebemelese@yahoo.com

Source    –   Zehabesha