January 4, 2017
ነጻነት አብዜማ                                                                                                                                                                                     

ከጥቂት ወራት በፊት በሀገር ቤት ገዢውን ቡድን ያስጨነቀ ፤ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ደግሞ መነቃቃትና የለውጥ ተስፋን ያጫረ ተቃዉሞ ተከስቶ ነበር። የእኩልነት ፣ የፍትህና ፣ የነጻነት ጥማት በአንድ በኩል ፤ የኑሮ ወድነት ፣ በልቶ ማደር ያለመቻልና ፣ ተስፋ ማጣት በሌላ በኩል ያንገፈገፈው ኢትዮጵያዊ በተለይም በኦሮሞና በአማራ አካባቢዎች ያለአደራጅ አንድነን ብሎ ተነስቶ ነበር። መያዣ መጨበጫ ያጣው ገዢው ቡድንም የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅ እንደደረሰ ይታወቃል። አዋጁ ፥ በተለይም ደግሞ ኢንተርኔትና ማህበራዊ ሚዲያን ማፈኑ ፥ በተወሰነ ደረጃ መቀዛቀዝ መፍጠሩ አይካድም፨
ይህ አየሩን የተቆጣጠረው የጽንፈኛ ብሄርተኞች ጩኸት ልብ ብሎ ላስተዋለው ግን በብዥታና በአፈታሪክ የታጀበ ነው። እነዚህ ዘርን ወይም ብሄርን መሰረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎችና ጫጫታዎች ከሚያጭሩት ጥያቄዎችና ብዥታዎች ወይም ስህተቶች 5ቱን ለአብነት ማንሳት ወደድኩ፨ነገር ግን ትግሉን ክፉኛ የጎዳውና እየጎዳው ያለው በውጭ ሀገር የሚኖሩ ጽንፈኛ ብሄርተኞች ያካሄዱትና እያካሄዱ ያሉት ጠባብና ዘረኛ እንቅስቃሴ ነው ብዬ አምናለሁ። በተለይም ጃዋርና ተከታዮቹ የኦሮሞ ትግል የሚመራው በነሱ እንደሆነ ከመግለጽ አልፎም ፤ አላማው ኦሮሚያ የምትባል አዲስ ሀገር መመስረት በሚመስል መልኩ እንቅስቅሴ መጀመራቸው እየተጋጋለ የነበረውን ሀገር አቀፍ ተቃውሞ ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሶበታል። በዚህ የደነበሩና በእስከዛረው ሂደት የተሰላቹ አንዳንድ አማራዎችም ወደ ጎሳ ስልቻቸው ገብተው መጮህ ጀምረዋል፨

  1. እንወክለዋለን ብለው የሚያስቡት ብሄር ከሌላው ብሄር የበለጠ እንደተጨቆነና እንደተበደለ አድርጎ ለማሳየት መሞከር።በታሪካችን ሰዎች በብሄራቸው ምክንያት የተለያየ ጫና ሰለባ እንደነበሩ ብዙ አያከራክርም። ያንን በአግባቡ መግለጽና ማስተማር ተገቢ ነው። ማጋነንና ተረት የሚመስሉ አፈታሪኮችን እየፈጠሩ ማሰረጫት ግን ችግር ነው። አንዳንዶቹ በሌሎች አገሮች እንዳየነው አይነት ቅኝግዛትና የዘር መድሎ ጋር ለማመሳሰል ሲተጉ ሁሉ ታዝበናል፨እንደ ጃዋር አይነቶቹ ደግሞ የተለየ ጭቆና ደርሶብናል ብሎ በጣም በመጮህ ያልነበረ ጎሳዊ ስሜትን መፍጠርና ቅርጽ መስጠት ይቻላል በሚል እኩይ ግላዊ ስሌት ሲንቀሳቀሱ ይስተወላሉ፨መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ቢያንስ ላለፉት 40 አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተበደለና መብቱ ያልተረገጠ የህብረተስብ ክፍል የለም። ሌላው ቀርቶ የትግራይ ህዝብም ጭምር ተጨቁኗል ሲሉ ራሳቸው ጽንፈኞቹ ይመስክራሉ። ታድያ ይህ ከሆነ የማን ብሄር ነው ከማን ጭቆና ነጻ የሚወጣው?
  2. የሚቃወሙትንና የሚታገሉትን የወያኔን ሃስብ የብሄር ልብስ ብቻ ቀይሮ መጫወት።
    ወያኔ 17 አመት በትግል 25 አመት በስልጣን ፥ ሙሉ በሙሉ አልሳካ ብሎት ነው እንጂ ፥ ሊያስረጽ የሚሞክረው ዘረኝነትና ጎሰኝነትን ነው። ታዲያ ጃዋርና ተከታዮች በኦሮሞ ስም ከመምጣታቸው ውጪ ከምንታገለው ህዋሃትና አስተሳሰቡ ጋር ምን ይለያቸዋል? ይህ ካልሆነ ፥ አንድን ዘረኛ ታግሎ ጥሎ በሌላ ዘረኛ መተካት ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን ይፈይድለታል?በአንጻሩ በዘር ተደራጅቶ ወያኔን መጣል ፤ በሰለጠነበትና በራሱ መንገድ መግጠም ስለሚሆን ይከብዳል። ቢቻልም እንኳን ወያኔ ከተፈጠረ ጀምሮ ያልተለየው ተቃውሞና ትግል ከሌላው ህዝብ ጋር ይጠብቃቸዋል። ይልቁንም በኦሮሞም ይሁን በአማራ ወይም ሌላ ብሄር እንታገላለን የሚሉ ሰዎች ፥ ስልጣን ላያቀምሳቸው ይችላል እንጂ ፥ እዛው ገብተው ምኞታቸውን እውን ለማድረግ ቢሞክሩ ይቀላል፨
  3. ራሳቸውን ለሚናገሩት ቋንቋ ወይም ለመጡበት ጎሳ ህጋዊ ተወካይ አድርጎ ማሰብ።
    የአንድ ማህበረሰብ ልሂቅ የህዝቡን ድምጽ ከማስተጋባት አልፎ የተሻሉ ሃሳቦችን ወደህዝብ የማስረጽ ሚና እንዳለውይታወቃል። የፈለገ ሰውም በብሄሩ ተደራጅቶ መታገል ይችላል፨

ነገር ግን የዛ ብሄር ተወላጅ ነኝ ለሱም እታገለላለሁ ስላለ ብቻ ያ ህዝብ ውክልና ሰጥቶታል ማለት አይደለም። የሱ ፍላጎትና እታገልለታለሁ የሚለውም ህዝብ ፍላጎት አንድ ነው ማለትም አይደለም፨

በአንድ በኩል ስለ ዲሞክራሲ ልእልና ያወራሉ በሌላ በኩል ያለዉክልናና ያለምርጫ የአንድ ጎሳ ብጹዕ ተወካይ መስለው ይቀርባሉ። አንዳዶቹ ሪፈረንደም አካሂደው ያዩት ይመስል ያ ብሄር መገንጠል እንደሚፈልግ ሁሉ እርግጠኛ ናቸው። ይሄ ብዥታ ነው!

  1. ወደ አንድነትና እኩልነት ለመምጣት ፤ ወያኔንም ለመጣል በዘር መደራጀትን እንደ ብቸኛና ብቸኛ አማራጭ አስመስሎ ማቅረብ።በተጨባጭ በ97 ምርጫና በቅርቡም እንዳየነው ወያኔ መስቀል እንዳየ ሰይጣን የሚረበሸው ህዝብ በአንድነት ሲነሳ ነው፨ ዘረኝነት ችግራችን ነው እያሉ በዘር መደራጀት መፍትሄ የሚሆነው እንዴት ነው?በዘር ተቧድኖ ሲታኮሱና ሲጠዛጠዙ ከቆዩ በኋላመለያየት ነው እንጂ እንዴት አንድነት ሊመጣ ይችላል? ተጨቆንኩ ብሎ የተነሳ ብሄር አሁን እንደሚታየው ተራው ቢደርሰው ጭቆናውን ከማካካስና ጨቋኝ ከመሆን ውጪ ሌላ አማራጭም የለውም፨በሌላ በኩል የትግራይ ህዝብ በወያኔ ስርአት አልተጠቀመም ካልን ፤ በዘር መደራጀት በአንዱ ብሄር ስም ጥቂቶችን ወደ ስልጣን አምጥቶ ይጠቅም እንደሆነ እንጂ ቆምንለት ለሚሉት ብሄር ምንም አይፈይድም፨

    አንዳንዶች አንድ ብሄር አቅም ከገነባ በኋላ ነው ከሌሎች ብሄሮች ጋር መደራደር የሚችለውም ይላሉ። ለመሆኑ የትኛው ብሄር ነው ከሌላው የበለጠ አቅም ያለው? መለኪያውስ ምንድነው?

    የአማራ ታጋይ ነን ባዮቹ ደግሞ ሌሎቹ ስለገፉበት ለነሱም የሚገባ የመሰላቸው ይመስላል። የብሄር ጭቆናና ትግል ተላላፊም አይደለም። አንድ ብሄር ችግር ስለደረሰበትና በዛ ተድራጅቶ ረጅም መንገድ ስለሄደ ይሄ ለሁሉም ብሄር ተገቢና አዋጭ መንገድ ነው ማለት አይደለም፨

  2. የቁጥር መብዛት ወይም ማነሰን እንደ የተለየ መብት ማግኛ መቁጠር።
    አንድ ብሄር በህዝቡ ቁጥር ከሌላው ስለበለጠ ወይም ስላነሰ ብቻ የዛ ብሄር ተወላጆች ከሌላው ዜጋ የበለጠ መብትና ጥቅም የሚጠይቁት በየትኛው አመክንዮ ነው? ኢትዮጵያውስጥ ሁሉም ዜጋ ተጨቁኗል ካልን ፤ ኦሮሞ ወይም አማራ በቁጥር ብዙ ስለሆኑ ልዩ መብት ለማግኘት የሚያስቡት ለምንድን ነው? እንኳን ብዙ ነን ባዮቹ ፤ በቁጥር አናሳ የሁኑትም በአሁን ሰአት ልዩ ድጋፍና ድጎማ ቢጠይቁ አያምርም። ዜጋ በችሎታው እንጂ በብሄሩ ቁጥር ብዛትና ማነስ ተጠለሎ እንዴት ልዩ ጥቅም ይጠይቃል?የዚህ አስተሳሰብ ትልቁ ድክመት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥርት ያለ በቀላሉ ሊሰመርና ሊለይ የሚችል የብሄር ስብጥር እንዳለ ታሳቢ ማድረጉ ነው። እውነታው ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የዘር ሀርግ ሳይቆጥር ከወደደው ጋር ሲጋብ ሲዋለድና ሲዛመድ ነው የኖረው። ግልጽ የሆነ የካርታም ሆነ የደም መስመር ማስመር ፈጽሞ አይቻልም። ሌላው ቀርቶ ኦሮምኛ ተናጋሪ ሁሉ ወጥ የሆነ ወይም አማራ የሆነ ሁሉ ተመሳሳይ አድርጎ ማየትም አይቻልም። ትልቅ ዘር ነኝ እያለ የሚፎክረው ሁሉ የተለያዩ ትናንሽ ዘሮችና ባህሎች ስብስብ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ድምጻቸው የሚሰማው የ3 ወይም 4 ብሄሮች ብቻ ሳይሆን ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሄሮች የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን መዘንጋትም ብዥታ ነው፨

በአጠቃላይ አንዳንድ ግለሰቦች ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅማቸውን በጠባብ የብሄር መነጽር አጨንቁረው ማስላታቸው አይደንቅም። ትልቁን ስእልና ከራስ ይልቅ የህዝብን ህልውናና ጥቅም ማሰብ የሚፈልግ ግን ከላይ የተጠቀሱትን አይነት ብዥታዎች ልብ ሊል ይገባል። ይልቁንም ሁሉንም እኩል ለሚያደርግ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ፤ ለግለሰብ ነጻነትና ለሀገር አንድነት መታገል አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፨

ለዲሞክራሲና አንድነት መታገል ያለጥርጥር ሁሉንም አሸናፊ ያደርጋል!