January 7, 2017

የ”ኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” የተሰኘ መዘዘኛ መፀሐፍ ሁለቱን ፕሮፌሰሮች በሰፊው እያወዛገባቸው ነው። ክርክሩ ወይም ንትርኩ ፀያፍ ከሆኑ ቃላቶች ፀድቶ እውቀት ላይ ብቻ ትኩረት ካደረገ አስተማሪነቱ ቀላል አይሆንምና ታዳሚዎቹ በጉጉት እየተከታተልን መኮምኮም ነው። እንደ መብረድ ሲል ቆስቆስ ቆስቆስ በማድረግ ድብድቡን ማስቀጠል ብቻ ነው ከኛ የሚጠበቀው። ? ።

ቀስ በቀስ ወደ ግል እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ቢዞርም የክርክሩ ዋና አጀንዳ ታሪክ ነው።አንደኛው የሀገራችንን ታሪክ ከመሰረቱ ውሸት ነው። አንድም የሀገራችን ታሪክ ብቃት በሚያጥራቸው ሀገር በቀል የታሪክ ሰዎች የተተረከ የ”ጠነዛ ታሪክ”ነው ይላል።አለያም ደግሞ ሀገራችንን በሚጠሉና ለማፍረስ በሚፈልጉ የውጪ ፀሐፍት የተፃፈ ነው ባይ ነው የስነፅሑፍ ሊቁ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ። ፕ/ር ጌታቸው ሀይሌ ደግሞ ታሪክ ብለህ የምታወራው አንድ ግለሰብ የደረሰውን ተረት ተረት ነውና አደብ ግዛ ነው የሚሉት።

ወደ ቁም ነገሩ ስንመለስ ታሪክ ላይ ክፍተት ከተገኘ ሙያው የሚጠይቀውን የጥናት ዘዴዎች በመጠቀምና ጥልቅ ምርምር በማድረግ እርምት ማድረግ አግባብ ነው። እዚህ ላይ ክርክር የሚያነሳ ሰው ያለ አይመስለኝም። እኔን እንደገባኝ ከሆነ የፕ/ር ጌታቸው ሀሳብ የማስተካከሉ ሂደት በአግባቡ መሆን አለበት የሚል ነው ።ባጭሩ ታሪክ አራሚው ታሪኩን ወደ ሕዝብ ይዞ ከመቅረቡ በፊት ቀደምት ታሪክ ፀሀፊዎች ማግኘት ያልቻሏቸውን አዳዲስና አሳማኝ የሰነድና የቁስ መረጃዎችን ማግኘቱን፣ ግኝቱን በሙያው ለተሰማሩ ዓለም አቀፉ ሙሁራን አቅርቦ ማስተቸቱን፣ ከዛም የግኝቱን እውነተኝነት አስመርምሮና ሞግቶ ተቀባይነት እንዲያገኙ ማድረጉን ማረጋገጥ ይገባል ነው የሚሉት።ይህ በሌለበት “እከሌ እንዲህ የሚባል መረጃ” አለው በማለት አለያም “አመናችሁትም አላመናችሁትም ፣ ጉዳዩ ተረት ቢመስልም እውነት ነው” አይነት ትርክት ይዞ እንደው በጨበጣ እኔን ስሙኝ የሚል አካሄድ አያስኬም። ሌላው እንግዳ ነገር ደግሞ በመስካቸው አንቱ የተሰኙ የአንድን ሀገር የታሪክ ጠበብቶችን በጅምላ ተሳስታችኾል፣ የጠነዛ ታሪክ ነው ያስተማራችሁን ብሎ መደፍጠጥ ግብዝነት ነው።ምሁራዊም ግብረ ገባዊም አካሄድ አይደለም ነው የሚሉት።

እኔ ታሪክ ከማንበብ ባለፈ የታሪክ ተመራማሪም፣ ተማሪም አይደለሁም።የምርምር ስራ እንዴት እንደሚሰራና ተመራማሪው የምርምር ውጤቶቹን ሲያቀርብ ማጣቀሻዎቹን እንዴት ማሳየት እንዳለበት ግን በሚገባ አውቃለሁ።በሙያዬ የምሰራው ይሄንኑ ነውና። በተለይ ደግሞ እንዲህ ለ ሺህ ዘመናት በሕዝብ ዘንድ የሰረፀን አመለካከት ለማስቀየርና በአዲስ አስተምሮ ለመለወጥ ስትነሳ የቀደመውን አስተምሮ ብልቱን የምትመታበትን ዋናውን ማጣቀሻህን በማያሻማና ግልፅ በሆነ መልኩ ማቅረብ የግድ ይልሀል። ይህንን ሳታሞላ ስራህን ሰው ፊት ይዘህ መቅረቡ አዳፋው ከባድ ነው። ትዋረዳለህ።

ፕ/ር ፍቅሬ ደፋር የስነፅሁፍ ሰው ነው። የታሪክ አላልኩም። ለዚህ እማኝ የሚሆነኝ ደግሞ ከሙያህ ውጪ የሆነውን ታሪክ መፀሐፍ የሚጀምረው የቀደሙ የታሪክ ዘጋቢዎችን ሙሉ ለሙሉ ስህተት ናቸው በማለት ፣ የባለፈውን የሀገራችንን ታሪክ የ”ጠነዛ” ብሎ መሆኑ ነው ።ሌላው ድፍረቱ ሕዝብን ያህል ነገር በተረት ለማሳመን መነሳቱ ነው። ሀሳባቸውን ለሞሞገት ይረዳል በማለት ለአዲሱ ታሪኩና ለመፀሐፉ ዋና አስኮል አድርጎ ያቀረበው ”የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” ማለትም የኦሮሞ አባት እና የአማራ አያት የሆነው ደሼት (ደሴት) አፈጣጠሩ እንዲህ ነው ይለናል …….

“ስለ ደሼት ስንናገር ምንም እንኮን ተረት ቢመስልም ሀቅ ስለሆነውና ለየት ስለሚለው ውልደቱ መናገር ጠቃሚ ነው።የቤላም (በልዓም) የልጅ ልጅ የሆነችው እናቱ ሼምሼል መነኩሲት ነበረች።ከወንድ እርቃ በግዮን አካባቢ በገዳም ውስጥ መንፈሳዊ ህይወት ትመራ ነበር።አንድ ቀን በግዮን ወንዝ ሳይሆን አይቀርም ገላዋን ስትታጠብ የወንድ ዘር በማሕፀኖ ዘልቆ ገባና ደሼት (ደሴት) ተፀነሰ”(ገፅ 60 ) ። “ይህ የሆነው ከሶስት ሺ አምስት መቶ አመት በፊት ስለሆነ ማስረጃው ሁሉ ቢጠፋም አያስገርምም” ይላል (ገፅ 61)።

እንግዲህ ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ እያነሱት ያለው ጭብጥ ይሄ ነው።መፀሐፉ ሙሉ ለሙሉ ተረት ነው ማለት ባይቻልም ፕ/ር ፍቅሬ አማራና ኦሮሞን ሊያስተሳስርበት ይዞት የቀረበው መረጃ ግን ተረት ነው። እሱም ይሄንን አልካደም።”ዘመኑ ስለራቀ ማስረጃ የለም” ብሎ ነው እንቅጩን የተናገረው። እራሱ ያመነውን ሀቅ ፕ/ር ጌታቸው ሲደግሙለት ለምን እንደተቆጣና ወደ እንካ ስላንትያ መዞሩ የሚገርም ነገር ነው።ለማንኛውም የአንድ ሀገርን ታሪክ ተረት ተረት ላይ ተመስርተህ ማረም አትችልም።ለዛውም ከአንተ ውጪ ሌላ ሰው ሰምቶት የማያውቀውን ተረት ተረትን እንደ ዋና ማስረጃ ጠቅሰህ።

ሌላውና የሚገርመው ጉዳይ የፕ/ር ፍቅሬ ደጋፊዎች የሚያነሱት ሀሳብ ነው። “ፕሮፌሰሩ ይዘውት የመጡት ሀሳብ ወቅቱን ያገናዘበና ኢትዮጵያ ከተጋረጠባት የመፍረስ አደጋ የሚታደግ ሀሳብ ስለሆነ መተቸት የለበትም፣ ውሸትም ቢሆንና ፕ/ር ፍቅሬ ዋሽቶ እያስታረቀን ከሆነም ዝም ብለን መቀበል አለብን” ነው የሚሉት።ይሄ አካሄድ ምንም ስሜት የማይሰጥ ከመሆኑም በላይ እጅግ አደገኛ የሆነ አካሄድ ነው። አንደኛ ሀገር በውሸት ሊገነባ አይችልም። ሁለተኛው አንድን ሀገር ጠንካራ የሚሆነው ከአንድ ዘር በሚቀዱ ጎሳዎች ስለተመሰረተም አይደለም።በደም ማስተሳሰሩ ሀገር የሚያድን ከሆነማ ሶስት ሺህ አመት ወደ ኋላ በመሄድ ተረት በመተረት ምን አደከመን። ኢትዮጵያን ሳናፈርስ እንቅልፍ አንተኛም በማለት እየተጉ ያሉት ጀዋር መሐመድ እና ዶ/ር ፀጋዮ አራርሶ እኮ ከአማራና ከኦሮሞ የሚቀዱ ግለሰቦች ናቸው።ደም መፍትሄ ከሆነ የችግሩ ሳሳይሆን የመፍትሄው አካል በሆኑ ነበር።

ለማንኛውም የአለማችን ሀያል ሀገር የሆነችው አሜሪካ 254 ከሚሆኑት የአለማችን ሀገራት ውስጥ 198 ከሚሆኑት ሀገራት ውስጥ ተውጣጥተው በተሰባሰቡ ሕዝቦች የተፈጠረች ሀገር ናት።በተቃራኒው ደግሞ ጎረቤታችን ሱማልያ ለባለፉት ሁለት አስርተ አመታት መንግስት አልባ የሆነችው ከአንድ ዘር ከወጡ ጎሳዎች ስላልተመሰረተች አይደለም። ስለዚህ ከአንድ ምንጭ መቀዳቱ በራሱ ለአንድ አገር ጥንካሬ ሊሆን አይችልም። ለድክመቱም ምክንያት ሊሆን አይችልም። ሀገር እንደ ሀገር ጠንካራ ሆኖ ሊጥል የሚችለው በውስጡ ያሉት ሕዝቦች በስምምነትና በፍቃደኝነት የሚያግባባቸውን የአስተዳደር ስርሀት መዘርጋት ከቻሉ ብቻ ነው።ባጠቃላይ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ሕዝቦችን በአንድነትና በፍቅር አብሮ እንዲኖሩ ለማድረግ ጠንክሮ መስራት የሚጠይቀው ታሪክ ላይ ሳይሆን ፖለቲካው ላይ ነው። መቀየርና ማስተካከል የሚቻለውና የሚቀለው ፖለቲካን እንጅ ታሪክማ ታሪክ ነው።ተስማማህም አልተስማማህም ፣ተቀበልከውም አልተቀበልከም ታሪክን ከበጎውም ሆነ ከክፉ ትምህርት ትቀስምበታለህ እንጂ ለጠብና ለልዩነት መሰረት አድርገህ መውሰድ ድንቁርና ነው።

ግዜነው ደም መላሽ

Source    –   Ethiopia Media Forum