ግርማ ካሳ
አሁን ያለውን በዘር ላይ የተመሰረተ ፌዴራል አወቃቀር ሲነሳ ፣ የግለሰብ መብትን ያከበረ እንደ አሜሪካ ያለ ፌዴራሊዝም ይሁን ሲባሉ፣ ሕወሃቶች እና የኦሮሞ ብሄረተኖች ካናዳ/ኬቤክን፣ ስዊስ፣ ቤልጂየምና እና ህንድ ሲጠቅሱ ይሰማሉ፡፡ የነዚህ አገሮች የፌዴራል አወቃቀር በኢትዮጵያ ካለው አወቃቀር ጋር በምን እንደሚገናኝ ግልጽ ባይሆንም።
የኢትዮጵያ ፌዴራል አወቃቀር በመሰረቱ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም ነው ቢባልም፣ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ነው ለማለት ግን ያስቸግራል። በቋንቋ ላይ ቢመሰረት ኖሮ በአማራው ክልል ያለው የኦሮሚያ ልዩ ዞን በአማራው ክልል ዉስጥ፣ የአዳም፣ የጅማ ልዩ ዞኖች፣ የአዲስ አበባ ከተማ …በኦሮሚያ ዉስጥ አይጠቃለሉም ነበር። ከአንድ የጋምቤላ ክልል ይልቅ ሁለት የአኙዋክ እና የኑዌር ክልሎች ይኖሩ ነበር። ከአንድ የደቡብ ክልል ይልቅ ወደ አምሳ የሚሆኑ ክልሎች ይኖሩ ነበር። ከአንድ የቤነሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይልቅ ቢያንስ ስድስት ክልሎች (የበርታ፣ የጉሙዝ፣ የማኦ፣ የሸናሽ..) ይኖሩ ነበር።
የአገዛዙ ካድሬዎችና የኦሮሞ አንዳንድ ልሂቃን እነ ስዊስን እንደምሳሌ ሲጠቅሱ፣ ምን ያህል የሚጠቅሷቸውን አገሮች ፌዴራል አወቃቀርን እንደሚያወቁ አይገባኝም። ለምሳሌ ስዊስን እንዉሰድ። በስዊስ እንደዉም ኮንፌዴሬሽን ነው ያለው።
ስዊስ በጣም ትንሽ አገር ናት።የኢትዮጵያ አንድ 10ኛ ትሆናለች። በውስጧ ካንቶንስ ይሏቸዋል፣ 26 ከፍለ ሃገራት አሉ። እያንዳንዳቸው ካንቶኖች የተዋቀሩት በዋናነት ታሪክን እና ቋንቋ በመመርኮዝ ነው። በአሥራ ስምንቱ ካንቶኖች የስራ ቋንቋ ጀርመንኛ ነው። በነዚህ ካንቶኖች ፈረንሳይኛና ጣሊያንኛ ተናጋሪዎች ከ3 ወይም 2 በመቶ አይበልጡም። ስለዚህ ጀርመንኛ ብቻ የስራ ቋንቋ መሆኑ ችግር አልፈጠረም። በሶስት ካንቶኖች ፈረንሳይኛ ብቻ ነው የሥራ ቋንቋ። በአንድ ካንቶን ደግሞ ጣሊያንኛ። ይሄም የሆነበት ከቋንቋዎቹ ዉጭ የሚናገሩ እጅግ በጣም ትንሽ በመሆናቸው ነው። ከ5% በታች።
በሶስት ካንቶች ( በርን፣ ፍሪበርጋና ዋሊስ) ፈረንሳይኛና ጀርመንኛ የካንቶኖቹ የሥራ ቋንቋዎች ናቸው። በበርን፣ ጀርመንኛ ተናጋሪዎች 84% ሲሆኑ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች 8% ናቸው። 8% ትልቅ ማይኖሪቲ ስለሆነ ነው ፈርንሳይኛ የካንቶኑ የሥራ ቋንቋ የሆነው። በፍሪበርግና በዋሊስ ፈረንሳይኛ ተናጋሪው 68% በመቶ ነው። ጀርመን ተናገሪዎች ደግሞ ወደ 28% ናቸው። ጀርመኖች ማይኖሪቲ ቢሆኑም፣ ትልቅ ማይኖሪቲ ናቸው። በመሆኑ ጀርመንኛ ፈረንሳይኛ የካንቶኖቹ የሥራ ቋንቋ ሆኑ። ግራቡንደን በሚባለው ካንቶን፣ ጀርመን ተናጋሪዎች 75% ናቸው። ሆኖም ጣሊያኖች 12%፣ ሮማኒያን የሚባሉ 15% በመሆናቸው፣ በካንቶኑ ከጀርመንኛ ጋር ጣሊያንኛና ሮማንኛ የኦፊሴል ቋንቋዎች ናቸው።
በኦሮሚያ 9% አማርኛ ተናጋሪ ነው። በአዳማ ልዩ ዞን 59%፣ በጂማ ልዩ ዞን 40%፣ በቡራዮ ልዩ ዞን 31%፣በምስራቅ ሸዋ ዞን 24%፣ በአርሲ ዞን 18%፣ በሰሜን ሸዋ ዞን 17%፣ በሃራ ጉሩ ወለጋ 14%፣ በምስራቅ ወለጋ 11% ፣ በምእራብ ሐረርጌ 9% እና በደቡብ ምእራብ ዞን 8% የሚሆኑት ነዋሪዎች አማርኛ ተናጋሪዎች ናቸው።
እንግዲህ በስዊስ ፣ በበርን ካንቶን 8% የሆኑ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች በግራቡንዱን 12% የሆኑ ጣሊያንኛ ተናጋሪዎች ቋንቋዎቻቸው የካንቶኖቹ የሥራ ቋንቋ ከሆኑ ፣ የኦሮሞ ብሄረተኞች ስዊዘርላንድን እንደ ሞዴል ከወሰዱ፣ በኦሮሚያ አማርኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን መስማማት ነበረባቸው። ይሄ አንዱ ነጥብ ነው።
ሲዊዘርላንድ የኦሮሚያ 14% ወይም አንደ ሰባተኛ ብቻ አካባቢ ናት። በሕዝብ ብዛት ካየነው የሲዊስ ህዝብ በኦሮሚያ ከሚኖረው ህዝብ አንድ ሶስተኛ ብቻ ነው። ከዚህ የምንረዳው የሲውስ ካንቶኖች በጣም ትናንሾች መሆናቸውን ነው። በቋንቋ ብቻ ቢሆን ኖሮ ፣ ከላይ እንደጠቀስኩት ከ26 ካንቶቹ 18 ጀርመንኛ ተናጋሪ እንደመሆናቸው አንድ ክልል ይሆኑ ነበር። ይሄ ሁለተኛ ነጥብ ነው።
የሲዊስ አወቃቀር ከቋንቋ በተጨማሪ ታሪክን እና የአስተዳደር አመችነትንም ከግምት ያስገባ አወቃቀር ነው። ለምሳሌ የዙሪክ ካንቶን እንውሰድ። ሻርልማኝ የተባለው አንጋፋ ንጉስ የልጅ ልጅ ንጉስ ሉዊስ በ853 ዓ.ም Fraumünster abbey የተባለ ገዳም ለሴት ልጁ ሂልደጋርድ ይመሰርታል። ለገዳሙ የቤኔዲክቲን መነኩሴዎች የዙሪክና የዩሪ መሬቶችን እና የአልቢስ ጫካን ከግዛቱ ይሰጣቸዋል። በ1045 ንጉስ ሄንሪ 3ኛ ገዳሙ የራሱ አስተዳደር እንዲኖረው ይፈቅዳል። መነኩሴዎች ገዳሙን እና አካባቢውን ማስተዳደር ጀመሩ። በ1218 ዙሪክ የራሷ ነጻ ግዛት ሆነች።፡ ከዚህ ታሪክ የተነሳ ነው ዙሪክ የራሷ ካንቶን የሆነችው። ሌሎችም ካንቶኖች ተመሳሳይ ታሪክ ነው ያላቸው።
እንግዲህ ሕወሃቶች እና ኦሮሞ አንዳንድ ልሂቃን የሲዊስን ሞዴል እንደ ሞዴላቸው ከወሰዱ ለታሪክ ግምት ይሰጡ ነበር፡ ኦሮሚያ፣ አማራ ..የሚሉ ክልሎች ሳይሆን ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ወለጋ፣ ጂማ፣ ከፋ….የመሳሰሉ ክልሎች ይኖሩ ነበር።
እንደ እዉነቱ ከሆነ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ፌዴራል አወቃቀር መላ ቅጡ የጠፋበት ፌዴራል አወቃቀር ነው። እንደገና ቋንቋን፣ ታሪክን፣ የሕዝብን አሰፋፈር፣ ኢኮኖሚን፣ ጂዪግራፊን፣ የአስተዳደር አመችነትን፣ የሕዝብን ፍላጎትን ባካተተ መልኩ መዋቀር አለበት። ለእድገት በሚያመች መልኩ።