እኔ የኦሮሞን ሕዝብ ውዥምብር ለወያኔ ትልቁ ጉልበቱ ነው የሚል ጽኑ
እምነት አለኝ፡፡ ይንንም አስመልክቶ አስመልክቶ በርካታ አስተያየቶቼን
ለሕዝብ ለማጋራት ሞክሪያሁ፡፡ አስተያየት ብቻም ሳይሆን ተጨባጭ የሆኑ
ብዙ ሰዎች ሊያስተዉሏቹው በሚል መረጃዎችንም ለማካፈል ሞክሪያለሁ፡፡
አሁንም ከሁሉ በፊት የኦሮሞ ሕዝብ ጉዳይ እኔን ያሳስበኛል፡፡ የዚህ ሕዝብ
ነጻነት ከሌለ ሌላውም ነጻ ይወጣል ብዬ አላምንም፡፡ ይህ ሕዝብ እንደ ሌሎች
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሳይሆን አሁን ላይ ከሁሉም በላይ የአመለካከት ውዥንብር
ውስጥ የገባና ለጠላቶቹ የተመቸ መሆኑ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ሥጋት ነው፡፡
የዚህን ሕዝብ ነጻነት በሚል ዛሬ 70 ዓመት ሞላው የሚባል የተለያዩ ቡድኖች
በሥሙ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡ አሁንም እየተጠቀሙበት ነው፡፡ አሁን የኦሮሞ
ሕዝብ ነጻ መውጣት አለበት ከተባለ ከእነዚህ ቡድኖች ነው፡፡ እስኪ በነጥብ
በነጥብ አንዳንድ ነገሮችን ላንሳ
ወያኔና ኦነግ የፈጠሩት ቆቤው ትውልድ
ይህ ትውልድ ከምንም በላይ በአስተሳሰብ ባርነት ውስጥ የወደቀ እየሆነ
ያለውን ማስተዋል የተሳነው፣ በሌሎች ላይ ጥላቻን አርግዞ እንዲኖር የተደረገ
ብቻ ምን አለፋችሁ አዚም ተደርጎበታል፡፡ ልብ በሉ ለሚገድሉት እጁን አጣምሮ
እየተንበረከከ የኦሮሞን ሕዝብ በክብር ማማ ላይ ያዋሉትን አባቶቹን ይረግማል፡፡
እነተስፋዬ ገብረዓብ በጻፉለት ሴራዊ ልብ ወለድ ራሱን አሳምኖ ከማይወጣው
የአስተሳሰብ ዝቅጠት ገብቷል፡፡ ወያኔና ኦነግ ከተሳካላቸው ነገሮች አንዱ የኦሮሞን
ሕዝብ ልጆች ከማንነታቸው ማምከን ነው፡፡ አሁንም እየገደሉት ከአሉት ጋር
አደለም የዚህ ትውልድ ውጊያው፡፡ ወያኔ ሚኒሊክ እንዲህ አደረገህ፣ አማራ
እንዲህ ምናምን እያለች አፍዛ ያሻትን እያደረገችው ጠላት በፊታቸው መቆም
ከማይቻለው ጥንታውያን ጀግኖች በምናብ ይታገላል፡፡ ይህ ትውልድ የሚኒሊክንና
የጀግኖች አባቶቹን ታሪክ ያረከሰ ቀን መውደቁ አልገባውም፡፡ ይህ ትውልድ ለወያኔ
መሣሪያ እንጂ ወያኔን የሚዋጋ አደለም፡፡ የአባቶቹን እውነተኛ ታሪክ አንብቦ
የአባቶቹ መንፈስ ወኔ እንዳይሆነው ወያኔ አስደግማ እንደነ ተስፋዬ ገብረአብ
ባሉ የወያኔ ደብተራዎች አጽፋ ልብ ወለድ ታስነበበዋለች፡፡ የሚኒሊክም ታሪክ
ከሚኒሊክም ጋር የነበሩ የኦሮሞ ጀግኖች ታሪክ ወያኔን እጅግ ያስፈራታል፡፡
የእነዛን ጀግኖች መንፈስ የተላበሰ ትውልድ መጥፊያቸው እንደሆነ የወያኔ
ቡድን አባላት አሳምረው ያውቁታል፡፡ እና ሕዝቡን ከራሱ ታሪክ ማምከን
ብሎም ከራሱ ታሪክ እንዲጣላ ተቀዳሚ ሥራዋ ነበር፡፡ አስተውሉ እውን
ሚኒሊክ ከኦሮሞ ሕዝብ በላይ ለማን ክብር ሰጠ፡፡ ሰሞኑን አንድ ግርማ
ካሳ የተባለ ሰው የጻፈውን አንብቤ የቁቤው ትወልድ አስተሳሰብ ትዝ ብሎኝ
እጅግ አዘንኩ፡፡ ግርማ ካሳ የጨለንቆውን የሚኒሊክ ጦርነት ከእነጭርሱም
የሚኒሊክና በቱርክና ግብጾች ይታገዝ የነበረው የሐረሪው አሚር ጦርነት
እንጂ ከኦሮሞ ጋር ግንኙነት የለውም ይለናል፡፡ ምን ይሄ ብቻ የቁቤው
ትውልድ እኮ ግራኝ መሐመድም ኦሮሞ ነው ባይ ነው፡፡ የአኖሌውን ጦርነት
ከታሪክ ሳይሆን ያነበበው ከነተስፋዬ ገብረአብና መሰሎቹ ልብ ወለድ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሥም ውስጥ የተሰገሰጉ
ደብተራዎች ሴራ
ዛሬ ብዙው ኦሮሞ ነኝ የሚለው ከኢትዮጵያዊነት ማንነቱ እንዲወጣ ከተደረገባቸው
ወያኔና አጋሮቿም ከሚተቀሙባቸው አንዱና ዋነኛው ማለት ይቻላል በኢትዮጵያ
ኦሮቶዶክስ ቤትክርስቲያን አገልጋይ ነን በሚሉ ደብተሮች ምክነያት እንደሆነ ነው
የሚል እምነት አለኝ፡፡ ብዙ ብዙ ተብሏል ስለ ኦሮሞ ሕዝብ፡፡ ቤተክርስቲያኒቱም
በእነዚህ ሴረኞች ምክነያት ለብዙ ተግዳሮቶች ተጋልጣች፡፡ የኢትዮጵያ ኦረቶዶክስ
ቤተክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና ጠንቅቃችሁ የምታውቁ ትረዱኛላችሁ የሚል እምነት
አለኝ፡፡ እዚህ ጋር ጫጫታ መፍጠር ሳሆን ከተሳሳትሁ አርሙኝ፡፡ እኔ እንደሚገባኝ
የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እምነት የፍልስፍናና የጥበብ መሠረት ነበረች፡፡
ከ700-800 ዓመት ወዲህ ግን በዚህች ቤተክርስቲያን አደገኛ የሆነ ነገር እንደገባ
ይሰማኛል፡፡ ከዚህ ዘመን ወደዚህ ባሉት ጊዜያት እስከዛሬም ቤተክርስቲያኗ በአደገኛ
ሰዎች እየተበረዘች ዛሬ ላይ ከእነጭርሱ የለየላቸው በይፋ ተቆጣጥረዋታል፡፡ እንግዲህ
እንዲህ ያሉ አደገኛ ደብተሮች ተሰግስገውባት በነበረች ቤተክርስቲያን የኦሮሞ ሕዝብ
ብቻም ሳይሆን የብዙ ሌሎች ኢትዮጵያ ሕዝብን ብዙ ጊዜ ተገፍተዋል፡፡
ደብተሮች በቤተክርስቲያኗ ከእነሱ በቀር ሌላው መብት እንደሌለው ሌላውን
የሚንቁበት እነሱ ጻድቅ ሆነው የሚታዩባት መቅደስ ሆናለች፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ
ለእመነቱ ቅርብ ሆኖ ሳለ ደብተሮቹና ተከታዮቻቸው ራሳቸውን አግዝፈውባት
ባለችው በዚህች ቤትክርስቲያን በእምነቱ ጠንካራ የነበሩ ከኦሮሞው ሕዝብ
የወጡ አባቶች ሳይቀር ብዙ ተገፍተዋል፡፡
በተቃራኒው የጥንቆላና የድብትርና ሥራ የሚሰሩ ብዙ ሰሜንኞቹ ታላቅ ሆነውባት ኖረዋል፡፡
ዛሬም ይሄው ነው ያለው እውነት፡፡ እንኳንስ ተራውን ብዙም ስለእምነት ጠለቅ ያለ ዕውቀት
የሌለው ምዕመን ይቀርና ታላላቅ አባቶችንም ከቤተክርስቲያኗ ተገፍተው ወጥተዋል፡፡
ቤቴን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት ያለው ጌታ ዛሬ በእውን የምናየው የኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ራሷ ነች፡፡ እውነታው እምነት በሌላቸው ይልቁንም
የጥንቆላና ሌላ ርኩሰት በሚሰሩ ደብተሮችና በእምነታቸው እጅግ ጠንካራ በነበሩ
ከኦሮሞው ሕዝብ የወጡ አባቶች መካከል ያለው ልዩነት ሆኖ ሳለ ደብተሮቹ
በቅናት መንፈስ ሕሊናም ስለሌላቸው በጻፏቸው አስነዋሪ ነገሮች ብዙውን
የኦሮሞ ሕዝብ ከቤተክርስቲያኗ መሰደድ ብቻም ሳይሆን ቤተክርስቲያኒቱንም
በጠላትነት እንዲያይ አድርጎታል፡፡
ኦሮሞነት አማራነት ምናምን የቅርብ ጊዜያት ማንነቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ
ውስጥ ታላቅ ተበለው ጥንታዊ የእምነት አባቶች ዛሬ በአንድ ወገን አሮምኛ
በሌላ ወገን አማርኛ ሌላም ጋር ሌላ የሚያወራው ሕዝብ ዘሮች መሆናቸውን
አንርሳ፡፡ ኦሮሞነት አማራነት ምናም ደግሜ እናገራለሁ የቅርብ ጊዜ ማንነቶች ናቸው፡፡
ከእነዚህ ሽርፍራፊ ማንነቶች በፊት ለዘመናት የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህች አገር ኖሯል፡፡
ልብ በሉ ዛሬ ለምልክት በኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ መካከል የሚኖሩትን የዜይን
(ዝዋይ ሐይቅ ደሴቶች) ሕዝቦች፣ ዛሬ ላይ ኦሮምኛ የሚናገሩትን የወንጪ፣ አምቦና
አካባቢው ሕዝቦች፡፡ የሊሙና ኢናሪያ (ጂማ፣ ኢሉ አባቦራ)፣ ጋፋትና (ጌዶ፣ ወለጋ)
ዳሞት ሕዝቦች፣ ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ገሙ፣ ኮሬ፣ ከምባታ፣ ሀዲያ ሌሎች (ደቡብ)
ሕዝቦች የማን ልጆች ናቸው? ሰሜን ብቻ ነው በታሪካዊ አብያተ ክርስቲያን
የሚታወቀው? እዚሁ አዲስ አበባ ሥር አዳዲ ማሪያም፣ ዝቋላ አቦ በነበሩበት
አድሜ ኦሮሞም አማራም፣ ትግሬም አልነበሩም፡፡ ሕዝቡ ግን አለ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ባረከሱ ደብተሮች ምክነያት
ዛሬ ብዙ ልዩነቶች ተፈጥረዋል፡፡ ዛሬ ላይ ለይቶለት ይሄው ጎራ ለይተው
በሚናቆሩ ራሳቸውን የእምነት አባት ባደረጉ ግለሰቦች ቤተክርስቲያኗ ወድቃለች፡፡
ደብተሮቹ በካባ ተጀቡነው ብዙ ጥፋት አድርሰዋል፡፡
በእርግጥም የጥንቱን እንኳን ትተን የቅርብ ጌዜዎቹን እነ አቡነ ጴጥሮስንና
(ሰማዕቱ) በእኛውም እድሜ በታላቅ መንፈሳዊነታቸው የሚታወቁት አቡነ
ሰላማን (የባሌ ሊቀ ጳጳስ የነበሩ) ከየትኛው ሕዝብ የወጡ ናቸው? እርግጥ ነው
በእነሱ ደረጃ ያለን ሰው ዛሬ ለዘር ማንነት ማመሳከሪያ ማቀረቤ እኔም በድፍረት
እንጂ ትክክል አደለም፡፡
ደብተሮቹ ከሚኒሊክ ጋር የነበራቸው አንዱ ግብግብ ሚኒሊክ በይፋ የኦሮሞን
ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ለማደረግ በሄዱባቸው ሂደቶች ነበር፡፡ እንደ ደብተሮቹ
የኦሮሞ ሕዝብ አረመኔ እነሱ አማኞች ናቸውና፡፡ የሀይማኖት ነገር ብዙ ስለማይወራ
በሽፍንፍኑ ይታለፋል፡፡ ባንደባብቀው ግን የተሻለ ነው፡፡ ግን አሁን ላይ ትልቁ አደጋ
ሆኖ ያው በእንደዚህ ያሉ ሴራዎች ያደገ የቂመኝነት መንፈስ ነው፡፡ አንድ ቀን ይህች
ቤተክርስቲያን ትክክለኛ መሪዋን ስታገኝ በሥሟ ስለተፈጸመው ሁሉ ኢትዮጵያዊ
ሁሉ ልጇ ነውና ይቅርታ ትጠይቃለች ብዬ አምናለሁ፡፡ የቀደሙ ፈላስፋ
መሪዎቿንም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሰውን አረመኔ፣ ቅዱስ ብሎ የሚከፋፍል
ፍልስፍና የደብተሮች እንጂ የቤተክርስቲያኗ አደለምና፡፡ ይህን ፍልስፍና
ያስተማረቻቸው መሪዎች ነበሩ መካ ያሳደደቻቸውን የመጀመሪያዎቹን
ሙስሊሞች ለማስተናገድ የበቁትን የጥንቶቹ ነገስታት ያፈራችው፡፡ ዛሬም
ቢሆን እነዚያ የጥንት የቤትክርስቲያኒቱ መሪዎች ያቆዩት ፍልስፍናና ጥበብ
እውነተኛው የክርስትና መሠረት ለዓለም ሳያቀር እንደማመሳከሪያ እየቀረበ
ያለው ከዚችው ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ዛሬ የሐይማኖትና ማሕበራዊ ጉዳዮች
ተመራማሪዎች ከፈተኛ ትኩረት ሰጥተው ከሚመራመሩባቸው ሰነዶች በዋነኝነት
የዚህችው ቤተክርስቲያን መሆናቸውን ስንቶቻችን እንደምናውቅ አላውቅም፡፡
በደብተሮች ሴራ አገራችንንም፣ እምነታችንንም፣ በአጠቃላይ ማንነታችንንም
አጥተናል፡፡ ሁሉም ወደራሱ ተመልሶ እየሆነ ያለውን ያስተውል፡፡
የውሸት ታሪክ ሰለባ መሆን
በአንድ ወቅት የታሪክ ተመራማሪው ዶ/ር ታደሰ ታምራት ለቃለምልልስ
በቴሌቪዥን ቀርበው ጠያቂው አንድ ጥንታዊ ታሪካዊ ኩነት ያነሳላቸዋል፡፡
እሳቸው የቱንም ያህል የታሪክ ተመራማሪም ቢሆኑ ይልቁንም ለብዙ
መዛግብትም ዕድሉ ቢኖራቸው ጠያቂው ያቀረበላቸውን ጥያቄ በትክክል
ሊመልሱለት አልቻሉም፡፡ በእርግጥም ጠያቂው ቀደም ብሎ ስለሚጠይቀው
ጥያቄ መረጃውን በራሱ አጠናቅሮ ስለነበር አንድ የተጻፈ ጽሑፍ በቪዲዮ
በተቀዳ ንባብ ያቀርብላቸዋል፡፡ ይህ ዘመን ዛግዌዎቹ ሰሎሞናውያን ነን ለሚሉት
ሥልጣን የሰጡበት ዘምን ነበር፡፡ ሂደቱን አንድ በአንድ እየተከታተለ የሚመዘግብ
ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ አማራ የለም፣ ትግሬም የለም፣ ኦሮሞም ሌላውም ዛሬ አለሁ
የሚለው የለም፡፡ የሚነበበው መዝገብ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ታሪኩን የሚያነቡት
ሰው በግዕዝ እያነበቡ ወደ አማርኛ ይተረጉማሉ፡፡ ዶ/ር ታደሰ ይህን መዝገብ
አያውቁትም ታሪኩ ሲነበብ ግን ሊክዱት በማይችሉት ሁኔታ ክስተቶችን አንድ
በአንድ እየጠቀሰ የመዘገበ በመሆኑ በአጻጻፍ ስልቱም ተደምመው ተቀብለውታል፡፡
ያኔ ጸሐፊዎች ነበሩ፡፡ በቃ ከዛግዌዎቹ ወደ ሰሎሞናውያን ነን ወደሚሉት ስልጣን
ከተላለፈ ወዲህ ታሪክን መመዝገብ እየደበዘዘ መጥቶ መጨረሻም
መሳፍንት የተባለ የዱርዬዎች ማዕበል አገሪቱን ወረሳት፡፡ በእነዚህ ዘመናት ነው
እነ አማራ፣ ትግሬ፣ አሮሞ ምናምን የተባሉ ማንነቶች በቅለው ከዘመናት በኋላ
ሲታዩ አድገዋል፡፡ አመጣጣቸውም ስለማያውቁ ስለማይተዋወቁም ዛሬ ላይ
ትልልቅ ማንነቶች ሆነው ለአገር መፍረስ ምክነያት እየሆኑ ነው፡፡ የዛሬዎቹ
የታሪክ ዘጋቢዎች እንኳንስ ዘመናትን ርቀት ሄደው ማን ከየት መጣ የሚለውን
በመመራመር የተቋረጠውን የታሪክ ክፍተት ለመሙላት ዛሬም ድረስ በሕወት
የሚኖሩ የሽማግሌዎቻችንን ዕደሜ ታሪክ እንኳን አያውቁትም፡፡ በዛ ላይ
ታሪክን የሚጽፉት እውነታውን ከመመዝገብ አንጻር ሳይሆን የየራሳቸውን
ምኞት፣ የቀበሌያቸውን ሰው፣ የእኔ ያሉትን እያወደሱ የሌላ ብለው
የሚያምኑትን እያጥላሉ ነው፡፡ በቅርቡ አንድ ትግሬ ጸሐፊ ነኝ ባይ ሲጠየቅ
(መጻፍ ጽፎ ሲያብራራ) አደዋን ያሸነፉት ትግሬዎች ናቸው ሲል እንደው
ቢያንስ ማፈር የሚባለው እኔ ራሴ የደረስኩበት የሰዎች ስብዕና የት ገባ ነው
ያልኩት፡፡ ከዛም በላይ ታሪክ ጸሐፊ ነኝ ባዩ ይናገራል፡፡ እንግዲህ አደዋ በጣም
የቅርብ ጊዜ ታሪክ መሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ እውቅና ያለው
ብዙዎች የመዘገቡት መሆኑ ነው እንጂ ይሄም ሰው እንደ ተስፋዬ ገብረአብ
ብዙ የሚያምነው ባገኘ፡፡ ትግሬ በአደዋ ትግል ተሳትፏል ከተባለ አሉላ አባ ነጋ
አይረሳም፡፡ እሱም ትውልዱ ከተምቤን የሆነ ሰው ነበር፡፡ አደዋም አክሱምም
አደለም፡፡ በተቃራኒው ትግሬዎች የጣሊያን ባንዳ ሆነው ብዙ ያገለግሉ ነበር፡፡
ዛሬ ስልጣንላይ ያሉት ግለሰቦች ወደኋላ ታሪካቸውን ብታዩ የአሉላ ቤተሰቦች
ሳይሆኑ የባንዳዎቹ ቤተሰቦች ናቸው፡፡
ለዘመናትም በአሳፋሪ ስራቸው ተንቀው የቆዩ በመሆናቸው ዛሬ ላይ እያደረጉ
ያሉት ያንኑ ማንነታቸውን ነው፡፡ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ለመበቀል፡፡
ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የጠራ ማንነቱ ታሪክ ያልተመዘገበ መሆኑ ችግር ሆኖ
የኦሮሞ ሕዝብ ማንነት ደግሞ ጭራሽ በተዛባ መልኩ መዘገቡ ለዛሬው
ውዥንብር አንዱ አስተዋጽኦ ሆኖ እናየዋለን፡፡ አባ ባሕሬን ከባሕር የወጣ አሉት፡፡
አባ ባህሬን በዘመናቸው በአለ አነጋገር የሁኔታውን ግዝፈትና ፍጥነት ለማሳይት
የሚችል አገላለጽ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰው እንደ አሳ ከባሕር እንደማየወጣ መቼም
ጠፍቷቸው አልነበረም፡፡ ምን አልባትም የእስራኤላውያንን ታሪክ ትዝ ብሏቸው
ይሆናል፡፡ በእርግጥም አገላለጻቸው እንደዛ ነው፡፡ ልብ በሉ አባ ባሕሬን
የቤተክርስቲያን ሰው እንደመሆናቸው የእስራኤሎች ታሪክ ሊታሰባቸው እንደሚችል፡፡
ኦሪት ዘሕልቁ ላይ ያለውን በለዓምን እንዲረግምለት የጠየቀውን የአሞናውያን
ንጉስ ባላቅን አስታውሱት፡፡ እስራኤሎችን ከመፍራቱ የተነሳ ይህ ሕዝብ አገሩን ሁሉ
እየወረረ መጥቷል በዙሪያችን ሰፍሯል በፊቱ ሊቆም የሚችልም የለም እያለ በለአምን
እስራኤልን እንዲረግምለት ለመነው፡፡ እስራኤሎች በእርግጥም ከባሕር ነበር የወጡት፡፡
የአባ ባሕሬን አገላለጽ በወቅቱ የነበረውን የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ ከእስራኤሎቹ
ታሪክ ጋር ለማመሳሰል እንደሆነ እናያለን፡፡ እስራኤል በፊታቸው ሊየቆማቸው የሚችል
እንደጠፋ የኦሮሞም ሕዝብ እንቅስቃሴ ይህን ይመስል ነበርና፡፡ አመጣጡም ድገት
ሳይታሰብ መሆኑ ነው፡፡ ይህን ታሪክ በደንብ መርምረው እውነታውን ለሕዝብ
ከማሳወቅ ይልቅ ከባሕር እንደወጣ አሳ ተቆጠረ በሚል በግብታዊነት የሚናገሩ
የታሪክ ምሁራን ዛሬ ለሕዝቡ የተሳሳተ ግንዛቤ ፈጥረዋል፡፡ አባ ባሕሬን በአንጸሩ
በዛን ዘመን የተከሰተን ይህን ታሪክ መመዝገባቸው በራሱ ሊደነቁ በተገባው ነበር፡፡
ችግሩ የአባ ባሕሬንን ቃል ለየራሳቸው ወስደው ሁሉም የራሱን ዓላማ ማሳኪያ
አደረገው፡፡ ምን በሌለበት ሆነና እነ ተስፋዬ ገብረዓብም በአጋጣሚው እድል አገኙ፡፡
ዛሬ ለኦሮሞ ሕዝብ እየተነገረው ያለው የሚኒሊክ ዘመን ታሪክም የዚሁ አንድ
መገለጫ ነው፡፡ አሊያማ የሚኒሊክ ታሪክ እኮ በጣም የቅርብ ጊዜ በአካል ያሉ
ሰዎች ሳይቀሩ የሚጠየቁበት ነበር፡፡ ብዙው ታሪክም ተመዝግቦ ያለ ነበር፡፡ የታሪክ
ጸሀፊዎች ነን የሚሉት ያልተደረገ፣ ያልተጻፈና ያልታሰበ ነገር ለራሳቸው ሴራ
በሚመች ጽፈው ሕዝብን ከራሱ ማንነት አውጡት፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ለእንደነዚህ
ያሉ ሴራዊ ጸሐፍት ከየትኛውም ሕዝብ በላይ ኢላማም ሰለባም ሆነ፡፡ ከላይ
ያነሳሁት የቁቤው ትውልድ አእምሮው በእነዚህ መረዞች ተበከለ፡፡ ማንነቱን አጣ፡፡
ለሚገድሉት ጠላቶቹ እጁት አጣምሮ ክብሩ የሆነውን የአባቶቹን ታሪክ ይዋጋል፡፡
በተጨማሪም በደብተሮቹ አዚም የተደረገበት ይመስላል፡፡
በኦሮሞው ሕዝብና በሌላው ሕዝብ መካከል ያለ አለመተማመን
አሁን ሁሉም በየቀበሌው ስለሚያስብ እርስ በእርስ አለመተማመኑ የከፋ ነው፡፡
ከኦሮሞሕዝብ ጋር በተያያዘ ያለው አለመተማመን ግን ከሁሉም የከፋ ነው፡፡ ዛሬ
ላይ አንወሻሽ የኦሮሞ ሕዝብ ከሁሉም አጎራባቾቹ ሕዝቦች ጋር በወዳጅነት አይታይም፡፡
ሁሉም የሚያየው በጥርጣሬ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክነያቱ ሌሎችን እንዲጠላ
ተደርጎ የተሰራበት በመሆኑ ከብዙዎቹ በጦርነት ሳይቀር ተጋጭቷል፡፡ በአለፉት
25 ዓመታት የኦሮሞ ሕዝብ ያልተጋጫቸው አዋሳኞቹ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡
ስለራሱ የሆነውን እውነት ሳይሆን ሌሎች የሚሉትን እየሰማ ብዙ ተጎድቷል፡፡
በጎሰኝነትና በዘረኝነት ስለተመረዘ ከአዋሳኝ ሌሎች ሕዝቦች ጋር ብቻም አደለም
እርስ በእርስም ትልቅ መከፋፈል አለ፡፡ እንደወንድማማች የሚተያዩት ጉጂና ቦረና
ሳይቀር ደም ተቃብተዋል፡፡ አሁን ሴረኞቹ እንደሚያስቡት ኦሮምያ የምትባል
አገር ከኢትዮጵያ ተገንጥላ አንድ ቀን ብታድር ሶማሌን ማሰብ ቀላል ነው፡፡
እጅግ የከፋ ጥፋት እንደሚሆን አስተውሉ፡፡ በዚህ ላይ ኦሮምያን እንገነጥላለን
የሚሉት ዋናው አላማቸው የእስልምና አክራሪነትን ማስፋፋት ነው፡፡
በአጠቃላይ ከውስጥም ከውጭም በሚኖር ጦርነትና ሁከት የኦሮሞምም
በሉት ሌላው ሕዝብ የማይዘልቀው ቀውስና እልቂት ውስጥ እንደሚገባ አትጠራጠሩ፡፡
ዛሬ ለብዙው ይሄ አደጋ አልታይህ ብሎት ያፌዛል፡፡ ዛሬ የኦሮሞ ቁቤ ትውልድ
ሌሎችን መጥላት እንጂ ራሱን ማስተዋል አልወደደም፡፡ ይህ ሕዝብ ወደራሱ
ማንነት እስካልተመለሰ ራሱ መታመሙ ሳያንስ ለሌሎች ሕዝቦችም ችግር
ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ምን አልባትም የሴረኞቹ ምኞት ሆኖ ለዘለዓለም ቀውስ
ውስጥ ይገባል፡፡ያኔ በሩቅ የምንሰማው አይሲስ እኛው መካከል ይገባል፡፡
የሴረኞቹ እቅድ ይሄ ነው፡፡
አንሸዋወድ በሐረር፣ ባሌ አርሲ፣ ጅማ በክርስቲያኑና ሙሰሊሙ
ማህበረሰብ ከፍተኛ አለመተማመን አለ፡፡ ይህን ደግሞ እንዲኖር
ያደረጉት በአረብ አገር የሰለጠኑና ከአረብ አገር በሚሰጣቸው ዳረጎት እየኖሩ
ባሉ ኃላትና በወያኔ ቅንጅት ነው፡፡
ለአመት በዘለቀው የኦሮሞ ሕዝብ ዓመፅ በእነዚህ አካባቢዎች ከምንሰመው
የተለየ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ በሰሜን አሜረካና በተለያየ ቦታ ሴረኞቹ በሚዘውሩት
ዲያስፖራ ዘንደም የእነዚህ አካባቢዎች የሚኖረው ሌላው (እነሱ መጤ የሚሉት
አማራና ምናምን) ሕዝብ ለምን አመጹን ደግፎ አልተሳተፈም የሚል ውዝግብ ነበር፡፡
ይህ ዲያሰፖራ የሚባል የማይገባው ሕዝብ የሚያነሳው ጥያቄ ነው፡፡ እውነታው
ግን አማራ ሆነ ኦሮሞ ወይም ሌላው ክርስቲያን በእነዚህ አካባቢዎች በተደረጉ
የ”ሕዝብ” ተቃውሞዎች ለመሳተፍ የማያስችለው በቂ ምክነያት አለው፡፡
ሕዝቡ የሚያደርገውን ያውቅ ነበር፡፡ በአመጹ የተሳተፉበት ሙሲሊሞቹ ራሳቸው
በውል ያልገባቸው የሙስሊም አክራሪነትን የሚያስፋፉ ቡድኖች የሚመሩት
ነበርና፡፡ሕዝቡ ባላወቀው ነገር ነበር እየሞተ ያለው፡፡ ለጠዋትና ማታ ዜና
እንዲደርስላቸው ነበር ሴረኞቹ እንቅልፍ አጥተው ሕዝቡን እጁን እያጣመረ
አደባባይ ወጥቶ እንዲገደል የተደረገው፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ ዓመጹን በዋናነት
ይመራው የነበረው ቡድን ይህን እውነት አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ ሕዝቡም
በተለይ ክርስቲያኑ ገብቶታል፡፡ ከዚህ በፊት የሆነም ታሪካዊ ስህተትም ነበርና፡፡
ታሪካዊ የምለው ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት የ1960ዎቹ ጦርነት ማለቴ ነው፡፡
ይህን እውነት ብዙዎች ሊሸፋፍኑት ይሞክራሉ፡፡
ተማርኩ የሚለው የኦሮሞው ሕዝብ ልጆች
ይህ የሕዝቡ አካል ከየትኛው የማህበረሰብ ክፍል በላይ ጥላቻንና ቂመኝነትን
በሕዝብ መካከል የሚዘራ ሆኖ እናየዋለን፡፡ ለሕዝቡ ማንነትና ድህንነት ዋስትና
አርዓያ መሆን ሲገባው ተማርኩ በሚል ማንነቱ ተጀቡኖ ተሰሚነቱን ጥላቻንና
ክፋትን ለመንዛት ይጠቀምበታል፡፡ በቅርቡ በአውስትራሊያው ኤስቤኤስ ሬድዮ
ታዋቂው ጋዜጠኛ ካሳሁን ሰቦቃ ቃለምልልስ ሲደረግለት ኢትዮጵያዊ ማንነት
የሚባል ነገር የለም ያለው “ምሁር” ተማርኩ የሚሉ ብዙ የኦሮሞ ልጆች አንዱ
ማሳያ ነው፡፡ ግለሰቡ ኢትየጵያዊ ማንነት እንዳለ አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ ግን ራሱን
በጠላቻ እርግማን ውስጥ ከቶ ያንኑ ምሁር ነኝ በሚል አጋጣሚውን
ሌሎችንም በዚህ ጥላቻ መንፈስ ለመመረዝ ነው ሐሳቡ፡፡ ግን እሱ
ማንነት አላቸው ከሚላቸው ፈረንሳዊነትም፣ አውስተራላዊነትም ሌላ
ሊጠራ ከሚችል አገር ሁሉ በላይ ኢትዮጵያዊ ማንነት አለ፡፡ ኢትዮጵያዊ
ማንነት የዛሬ ሳይሆንም ጥንታዊ ነው፡፡ ይህ እኔ ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ አደለም፡፡
በቤታችሁ ያለ እናምንበታለን የምትሉት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚጠቅሳቸው ጥቂት
ዛሬም ድረስ ያሉ ማንነት ኢትዮጵያዊነት አንዱ እንደውም በልዩ ሁኔታ የተመዘገበ ነው፡፡
ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን የሚለው የታላቁ ነብይ አገላለጽ ብቻ
በቂ ነው፡፡ የኦሮሞ ምሁራን ለሕዝቡ ነጻነት ትግል ከመሳተፍ ይልቅ የወያኔ ዋና
አጋር ሆነው በሕዝብ ዘንድ ጥላቻ እንዲያድርና ከኢትዮጵያዊ ማንነት ወጥቶ ዛሬ
አቅመቢስ እንዲሆን ለሆነው የኦሮሞ ሕዝብ መሪ ተዋናይ ናቸው፡፡
አሁን አሁን የእነዚህን ምሁር ተብዬዎች አካሂድ የተገነዘቡ ብዙም በትምህርት
ያልገፉ የኦሮሞው ሕዝብ ልጆች በራሳቸው ጊዜ ፈንቅለው ወጥተው ሕዝቡን ወደራሱ
ማንነት እንዲመለስና በመሠረታዊ ጠላቶቹ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ጥረት ማድረግ
ጀምረዋል፡፡ በእርግጥም እየተሳካላቸው መጥቷል፡፡ ምሁር ነኝ ባዮቹ ያወደሙትን
የኦሮሞን ሕዝብ ማንነትና ወኔ ለመመለስ በቁርጠኝነት እየሰሩ ነው፡፡ ቀለም መቁጠር
ግማሹም የዕደል ጉዳይ ግማሹም የትኩረት ጉዳይ ነው፡፡ ጥበብና ፍልስፍና ግን
ተፈጥሮዋዊ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለበጎ አሳቢዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ
የሚሰጥ ልዩ በረከት ነው፡፡ የኦሮሞም ብቻ ሳይሆን ብዙው ተማርኩ የሚለው
ዛሬ ኢትዮጵያ ለገባችበት ውድቀት ምክነያት ነው፡፡ ከ60ዎቹ ጀምሮ አገሪቱን
ወደ ውድቀት እየመራት ያለው ይህ የሕብረተሰብ አካል ነው፡፡ ቀለም ያልቆጠሩት
ግን ታላላቅ ጠቢባንና ፈላስፎች የሆኑት አባቶች ከተበታተነችበት አንድ ያደረጓትን
አገር ዛሬ ጥበብ የነጠፈችባቸው “ምሁር” ተብዬዎች እያፈረሷት ነው፡፡ እርስ
በእርሳቸው ሲጫረሱ ኖረው ዛሬም አለቀቁንም፡፡ ሑሉም ቦታ አዋቂዎች እነሱ
ናቸው ግን ባዶ የመከኑ መሆናቸውን አያውቁትም፡፡ ማንም ሰው በቀለም ሥራዬ
ብሎ ከያዘው ያሰበው ይደርሳል፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ታላቅነት በጎ ሚና ሊኖረው ግን
መሠረታዊ ዕውቀት ያስፈልገዋል፡፡ የኦሮሞው ሕዝብ ልጆች ምሁራን ዝቅጠት በዛ
እንጂ ሁሉም ጋር ዝቅጠቱ በጉልህ ይታያል፡፡ ከሁሉም አደገኛው ነገር በክብር
የተሰጣቸውን የትምህርት ማዕረግ ለወራዳ ሥራቸው ማስፋፊያ ቲፎዞ እያስከተሉበት
የጥፋት ምክነያት መሆናቸው ነው፡፡
ጥቂት ሌሎች አስተውሎት ሊደረግባቸው የሚቡ ጉዳዮች
በመጨረሻም ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ እላለሁ፡፡ ሁሉም ሊያስብበት የሚገባ
ጉዳይ ነው፡፡ ለእኔ የኦሮሞ ሕዝብ ጉዳይ ከምንም በላይ ትኩረቴና ስኬት ከታሰበ
የዚህ ሕዝብ ወደማንነቱ መመለስ ወሳኝ ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ አሁን አሁን
ደግሞ አማራ ነን የሚሉ ሌሎች የወያኔ ሥራ አስፈጻሚዎች ተነስተዋል፡፡ ልብ በሉ
ወያኔ ደጋግማ ውሸት የሆነውን ነው በመናገር እውነት እንዲሆንላት የምትፈልገው፡፡
እላለሁ የአማራ ብሔረተኛ ነኝ የሚለው ቡድን የኦነግ ኮፒው ነው፡፡ እሱም ብቻ
አደለም፡፡ ዛሬ ላይ ተመልከቱ የአማራ ቡድን ነን የሚሉትን ቁጥር ብዛት፡፡ በኦሮሞው
ሕዝብ የተደረገው እንደዚሁ ነው፡፡ አእምሮ ያለው ያስተውል፡፡ ግንቦት ሰባት ሌላ
ምሁር ነኝ በሚል ግለሰብ የሚመራ ሌላው የወያኔ ቡድን ጉዳይ አስፈፃሚ እንደሆነ
ሥራዎቹ እያጋለጡት ይመስላል፡፡ ሰሞኑን ቡድኑ በሕዝብ ላይ ሲያሴር ነበረ ያለውን
አንድ ግለሰብ ገደልኩ ይለናል፡፡ ግንቦት ሰባት ምን እያለን ነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ
እንዲህ ያለውን ቁማር አሁን ገብቶታል፡፡ በግለሰብ ላይ እርምጃ ወሰድን ይሄ እኮ
የተለመደ ፋሽስታዊ የ60ዎቹ ትውልድ የመበላላት እርግማን እንጂ የሕዝብና አገር
ነጻነት ትግል ስልት አደለም፡፡ ግንቦት ሰባት ማንነቱ የተገለጠው አርባ ምንጭ ላይ
አደጋ አደረስኩ ያለ ዕለት ነው፡፡ እንደዚያ ያለው ክስተት ሆን ተብሎ ለወያኔ ፕሮፓጋንዳ
የሚደረግ ክስተት እንደነበር አስተውሉ፡፡ እንደሚለውም ያን ክስተት ግንቦት 7 ራሱ
የፈጸመው ሳይሆን ወያኔ ፈጸማው የግንቦት ሰባቱ መሪ እንዲናጋር የተደረገ ድራማ
ይመስላል፡፡ የአንዳርጋቸው ጽጌ መታሰር ሌላው የዚሁ ቡድን ለሕዝብ ሊመልሰው
ያልቻለው ጥያቄ ነው፡፡ ከአላጣው የትግል ስልትና ቦታ ኤርትራን የመረጠበት ሌላው
የማንነቱ ማሳያ ነው፡፡ ቀደም ሲል ከኤርትራ ውጭ ምን አማራጭ አለኝ ሲል ነበር፡፡
አሁን ያ ምክነያት አይሰራም፡፡ መላው ኢትዮጵያ እስከጠረፍ ድረስ ሥርዓቱን በቃን
ብለው እየተፋለሙ ያሉ ሕዝቦች እጅ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊ ነኝ የምትል
ሁሉ አስተውል፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ ካልክ ወያኔን በአንድ ሳምንት ባልሞላ
ጊዜ ውስጥ ከላይህ ላይ ታወርዳታለህ፡፡ ግን መጀመሪያ ሁሉም ትኩረት
ሰጥቶ በኢትዮጵያዊ ማንነቱ ሊታገል ይገባል፡፡ ወያኔ ጉልበቱ የሕዝብን ትግል
እንመራለን ብለው የሚነግዱ ብዙ ብድኖች ናቸው፡፡ ወሳኝ በሆነ ወቅት
ማንነታቸው የሚባርቀውን አስተውሉ፡፡
ሕዝብ ወሳኝ በሆነ ትግል ላይ በነበረበት ወቅት የለንደኑንና የአትላንታውን ስብሰባ
አዘጋጀተው አቅጣጫ የሚያስቀይር ንግግር ሲናገሩ የነበሩትን ቡድኖች አስተውሉ፡፡
ሁሉም ትኩረቱ አዲስ አበባ ላይ ያለውን የወያኔ ቡድን ላይ ያድርግ፡፡ ኤርትራና
ሌላው ጠረፍ አያስፈልግም፡፡ ትግሉን እዛው አዲስ አበባ ጀምሮ እዛው ማጠናቀቅ
ይቻላል፡፡ የወያኔ ደብተሮች አዚም ከልለቀቁብን በቀር ይህ በጣም ሊሆን የሚችል
የተሻለ ዕድል ነው፡፡
ልዑል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሁን! አገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ!
አሜን
ሰርጸ ደስታ
One Response