
እንደ መግቢያ
በታወቀ ምክንያት የኢትዮጵያ ታሪክ አወዛጋቢነት ቀጥሏል፡፡ “ታሪክ የሞተ ፖለቲካ ነው” የሚለው አባባል ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን አይሰራም፡፡ ይልቁንስ “ታሪክ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም ሊቀጥል የሚችል ፖለቲካ ነው” በስሜት በሚነዳ የዘውግ (የዘር፣ የጎሣ) ፖለቲካ ውስጥ ታሪክ ትልቅ ማገዶ ሆኖ ቀርቧል፡፡ እንዲህ ባሉ የታሪክ ውርክቦች ውስጥ ይበልጥ አትራፊው ገዥዉ ኃይል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ታሪክ የአሸናፊዎች ደንገ-ጡር በሆነችባት ኢትዮጵያ ገዥው ኃይል ለአገዛዙ በሚያመቸው መልኩ ታሪክን በርዞና ከልሶ ሲያቀርብ ታሪክን ሳያላምጡ የሚመጡ ደቃቅ “ፖለቲከኞች” በርክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ አተራረክ በአጥቂነትና በተከላካይነት የሚበየን የውዝግብ መድረክ ሆኗል፡፡ የአንድ ዘውግ ጉዳይን ሁልግዜ በተጠቂ ስሜት፤ ሌላኛውን ዘውግ በአጥቂነት የማየት ዝንባሌም በታሪክ ትንተና ውስጥ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ከታሪካችን የሚያግባባንን ማግኘት ተስኖናል፡፡ ጭራሹን ጉልህ የልዩነታችን መስክ ሆኖ ቀርቧል፡፡
ከሰሞኑ በምኒልክና በአድዋ ድል ዙሪያ ሶስት ጠርዞች፤ በሁለት ጐራ የተከፈለ ዱላ ቀረሽ “ክርክር” (እንደ እውነቱ “ዘለፋ” ማለት ይቀላል) በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲንፀባረቅ እየተስተዋለ ነው፡፡ የአገራዊ የጋራ ማንነታችንና የብሄራዊ እሴቶቻችን ንጣፍ መሰራት ሊሆን የሚችለው የዓድዋ ድል በዓል በዚህን ያህል መጠን የልዩነታችን ቀይ መስመር አስማሪ መሆኑ የሰከነ የውይይት ባህል እየራቀን ለመሄዱ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
ብዙዎቹን የአካዳሚውን መስመር ሰዎች እንደሚያስማማው “የኢትዮጵያ አገራዊ ታሪክ ዘመንና መቼትን ተሻግሮ የሚጠቀስ ሰፊ እና ረጅም ዕድሜ አለው” ከአናሳ ዘውግ በመምጣታቸው ሁሌም ቢሆን የበታችነት ስሜት በሚያሰቃያቸው የህወሓት ስዎች ሲገለፅ እንደኖረው የኢትዮጵያ ታሪክ በአንድ መቶ ዓመት ብቻ የሚቀነበብ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የተዋለደው ወጥ ይዘት ባጀበው ቀጣይ ተግባር ሳይሆን ውስጣዊና ውጫዊ በሆኑ የኃይል ግፊቶች የግዛት ወሰኑን በማጥበብና በማስፋት ሂደቶች መሀከል የተፈጠረ ነው፡፡ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ሲባልም የትላንቷ ኢትዮጵያ ቅጥያ እንጅ ከጠፈር የመጣች ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ የህወሓት “ኢትዮጵያ የአንድ መቶ ዓመት ታሪክ ነው ያላት” የሚለው የጉርምስና ሀተታ ከፖለቲካ ፍጆታነት የሚሻገር አይደለም፡፡
የታሪክ ሊቃውንቱ “ታሪክ የትውልዶች መገናኛ ድልድይ ነው” ሲሉ ቢደመጥም፤ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ታሪክ የትውልዱ የልዩነት ማስመሪያ ቀይ ቀለም ነው፡፡ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ለዘውግ ፖለቲካ ማፋፋሚያ አይነተኛ ማገዶ ነው፡፡ ታሪክ ለየዘውጉ (በ“ጨቋኝ” “ተጨቋኝ” ትርክት) ዘውጋዊ ንቃት መፍጠሪያነት አንጂ ከዚህ በተሻገረ መልኩ የአገራዊ ውህድ ህላዌ መጋቢና ደጋፊ ሆኖ ሲገለፅ አይስተዋልም፡፡
የማንነት ፖለቲካን የታከከ የታሪክ ትርጓሜ ጐልቶ በሚታይበት ኢትዮጵያ፤ በአገር ግንባታ ሂደቶች የታዩ ክስተቶችን በተመለከተ የሦስት ዘውጐች ሊሂቃንና ተከታዮቻቸው የበረታ ፉክክር ይስተዋልበታል፡፡
ባሳለፍነው ሩብ ክፍለ ዘመን ጉልህ የመገፋት ሂደት ውስጥ እየተዋለደ የመጣውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ራሱን ለማቅናት እየተውተረተረ የሚገኘው የአማራ ብሄርተኝነት፤ ግማሽ ክፍለ ዘመንን በሚሻገር መልኩ ተደክሞበት ዛሬም በውል ያልፀናው የኦሮሞ ብሄርተኝነት እና “የብቻ ሥልጣኔያችን ነው” የሚሉትን ሥልጣኔ ከአክሱም ሃውልት ፍርስራሽ ግርጌ መፈለግ የሚቀላቸው የአፄ ዮሐንስ ዘውድ አስመላሽ የትግራይ ብሄርተኞች በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ጫፍና ጫፍ የተወጠረውን የታሪክ ውርክብ በማጦዝ ወደረኛ የታሪክ ዘውግ ሙዚቃዊ ድርሰት /genre/ ፈጥረዋል፡፡
የምስራቅና የደቡብ ኢትዮጵያ የወል ማህበረሰቦች (Cultural communities) በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ አገር ግንባታ ሂደቶች የታዩ ውስን ማህበራዊ መለንቀጦችን እያስታወሱ ቢያኮርፉም፤ ከላይ እንደተጠቀሱት ሦስቱ (የኦሮሞ፣ አማራና የትግራይ) ዘውጐች በታሪክ ውርክቡ ውስጥ ሚዛኑን የሳተ የጉርምስና ሀተታ ሲያቀርቡ አይስተዋልም፡፡ አልፎ አልፎ ከሲዳማና ከወላይታ የሚመዘዙ ብሄረተኞች የሚኒልክን አገር ግንባታ ሂደት ሲነቅፉ መስተዋላቸውን ሳንዘነጋ፡፡ ከሚኒልክ የደቡብ ዘመቻዎች ተጠቃሹ የጉራጌ ዘመቻ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ ይሁንና የምኒልክን የአገር ግንባታ ሂደት የጉራጌ ልሂቃን እንደ ሌሎቹ ብሄረተኞች አግንነው ስብከት ሲያሰሙ አይስተዋልም፡፡
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ የንግሥና ዘመን ይጀምራል፡፡ የዳግማዊ ቴዎድሮስ የአንድነት ህሳቤ ባልተጠበቀ መልኩ የተቀጣጠለው አገራዊ ራዕይ (አንድነቷ የተጠበቀ፣ ማዕከላዊ መንግስቷ የተጠናከረ ዘመናዊት ኢትዮጵያ የመመስረት ህልሙ) በመሳፍንቱ እምቢተኝነት፣ በካህናት ልግመት፣ በቴዎድሮስ የበዛ የቅጣት በትር፣ . . . በመጨረሻም በናፒየር በተመራው የእንግሊዝ ወታደራዊ ዘመቻ ቢመክንም በቀጣይ በነገሡት ነገሥታት (የውስጥ ሽኩቻቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) ሊቀጥል ችሏል፡፡ በአፄ ዮሐንስ የዳር ድንበር ተከላካይነት ለጥቆም በንጉሰነገሥት ምኒሊክ የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ግንባታ ሂደት ከነሳንካዎቹ እውን መሆን ችሏል፡፡
ትውልድ የሚረግመው ጀግና!
ከምኒልክ የቀደሙት ሁለት ነገሥታት የተቻላቸውን ያህል ቢጥሩም ማዕከላዊ መንግስቱን በሚቆምና አገሪቷን ወደ ዘመናዊነት በማሻገር አፄ ምኒልክ የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች ነው፡፡ አፄው የግዛት አንድነትን ለማስጠበቅ ዘመኑ ያስገደደውን አማራጭ ሲወስደ የተጐዱ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ የማይካድ እውነት ነው፡፡
ይሁንና የአገር ግንባታ ሂደት ከደምና ከላብ ውጪ ከቶውንም ተከውኖ አያውቅም፡፡ ዛሬ ላይ እንደ ሰማይ ከዋክብት በሥልጣኔና በምርምር ስርጸት የራቁን የምዕራቡ ዓለም አገራት እንደ አገር ለመቆም የበዛ የደም ዋጋ ከፍለዋል፡፡
የዘመናዊት ኢትዮጵያ አፈጣጠርም አብርሃም ሊንከን ከደከመላት አሜሪካ፣ ኦቶማን ቢስማርክ “ነፍጥና መስዋዕትነት” በሚል ከተዋደቀላት ጀርመን አልያም ከጣልያን ወይም ፈረንሳይ . . . አፈጣጠር የተለየ ክስተት አላስተናገደም፡፡ የፈሰሰው የደም መጠን ይለያይ እንደሆን እንጂ አገራቱ በነፍጥና በመስዋዕትነት የመቆማቸው እውነት ለመካድ የማይመች ዓለምአቀፋዊ ጉዳይ ነው፡፡
እርግማን አንድ፤ “ምኒልክ ሂትለር ነው”
ከኦሮሞና አማራ ፊውዳል ቤተሰብ እንደተወለደ በህይወት ታሪኩ ዙሪያ የተሰናዱ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ አፄው የሸዋ ንጉሣዊያን የዘር ግንድ ውስጥ የተገኘ በመሆኑ በመሬት ማስፋት /land power/ የሚያምን፤ ይህን ተከትሎ በሚገኘው የሰውም ሆነ የተፈጥሮ ሐብት የተሻለ ሥርዓተ-መንግስት እንደሚያነብር የተረዳ መሪ ነበር፡፡
በአፄው የንግስና ዘመንም ሆነ የንጉሠ ነገሥትነት ጊዜ በአገር ማቅናቱም ሆነ የውጪ ወራሪ ኃይልን በመመከቱ ዘመቻ የድል ከፋች አውራ የጦር አበጋዞቹ ውስጥ የኦሮሞ ራሶች ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በብዙዎቹ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች የምኒልክን ጨካኝነት አጉልተው ለማውጣት የሚጠቀሙባቸው ዘመቻዎች ሁለት ናቸው፡፡ የአርሲና የጨለንቆ ዘመቻዎች፡፡ ቀሪ የኦሮሞ ግዛቶች (ወለጋ (ኩምሳ ሞረዳ)፣ ጅማ-ግቤ (አባ ጅፋር) . . . ) በተበጣጠሰ መልኩም ቢሆን በገዛ ፈቃዳቸው ለምኒልክ የገበሩ መሆናቸው ይሰመርበት፡፡
በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ከዘውግ ፖለቲካ የታሪክ አተረጓጎም አኳያ በአጨቃጫቂነቱ የሚነሳውን የአፄ ምኒልክ የግዛት ማስፋፋት እና ለስድስት ተከታታይ ዓመታት (1872-1878/79) የዘለቀው የአርሲ የመከላከል ፍልሚያ ነው፡፡ ከዓመታት ፍልሚያ በኋላ በራስ ዳርጌ እና በራስ ወልደ ገብርኤል የበረታ ዘመቻ አርሲዎች በራቸው ተሰበረ፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን ክስተት “የኢትዮጵያ ታሪክ የዘነጋው ነው” የሚሉን የኦሮሞ ብሄርተኛ ልሂቃን ፕሮፌሰር አባስ ገናሞ (The history of Arsi, 1880-1935) በሚል ሥራው ላይ “የአርሲ ህዝብ በራስ ዳርጌ ጦር አልቆ ኃይሉ ከተዳከመ በኋላ ዳግመኛ እንዳይነካና ለነፃነቱ እንዳይዋጋ ለመቀጣጫ ብለው ወንዶችና ሴቶችን ከአሰላ በስተ ሰሜን በሚገኝ አኖሌ በተባለ ሥፍራ ላይ እንዲሰባሰቡ በማድረግ ወንዶች በራስ ዳርጌ ትዕዛዝ የቀኝ እጃቸው እንዲቆረጥ ታዘዘ፡፡ ወራሪዎች የቆረጧቸውን እጅ በወንዶቹ አንገት ላይ እንዲንጠለጠል ተደረገ፡፡ በዚሁ መሰረት ሴቶችም ቀኝ ጡታቸውም እየተቆረጠ እንደወንዶቹ በአንገታቸው ላይ እንዲንጠለጠል ተደረገ፡፡ (ገጽ 45) ትርጉም” እያለ ይተርክልናል፡፡ ፕሮፌሰሩ ይህን ሲተርክልን አንድም የታሪክ ሰነድ በማስረጃነት አይጠቅስም፡፡ የታሪክ ማስረጃዬ የሚለውም ሥነ – ቃላዊ ትውፊትን ብቻ ነው፡፡ በታሪክ ሙያ መስፈርቶች ተቀባይነት የሚኖረው ታሪካዊ ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ የምኒልክ “የጡት ቆረጣ” ተረክ ዛሬ ላይ ሙሉ ድጋፍ አግኝቶ ከአዲስ አበባ 150 ኪ.ሜ ርቀት በምትገኘው ውሃና መብራት በሌለባት አኖሌ ሃያ ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሐውልት ተገንብቷል፡፡
“በአርሲ ዘመቻ ራስ ዳርጌ ቄጤማ እየበተነ መላ አርሲን ተቆጣጠረ” የሚል ትርከት (narrative) የለም፡፡ ምንም በማይካድ መልኩ በአርሲ ዘመቻ ራስ ዳርጌ እና ራስ ወልደ ገብርኤል የአርሲ ጀብደኛ ተዋጊዎችን ለመቅጣት በአንድ ቀን አራት መቶ የሚደርሱ አርሲዎችን ቀኝ እጃቸውን እንደቆረጡ በአያሌው ቀኖ ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጐመው የፋዘር ማርሻል ዲ.ሳልቫይች /The Oromo, an Ancient people, Great African Nation/ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ይህ መፅሐፍ አፍቃሪ ኦሮሞ የሆነው ፈረንሳዊው የኃይማኖት ሰው ከአርሲ ዘመቻ ጥቂት ዓመታት በኋላ አርሲ ደርሶ ከነዋሪዎቹ የሰበሰበውን መረጃ አካቶ የፃፈው መፅሐፍ ነው፡፡ በሰውየው መፅሐፍ ውስጥ “የሴቶች ቀኝ ጡት ተቆረጠ” የሚል መረጃ ፈፅሞ የለም፡፡ በጊዜው ይህ ድርጊት ተፈፅሞ ቢሆን ኖሮ ይህ የኃይማኖት ሰው ድርጊቱን ከመፃፍ ምን የሚያግደው ኃይል ነበር?
ሰውየው ጽፎት ተርጓሚው ዘለለው የሚል መከራከሪያ እንዳይቀርብ እንኳን ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ የትርጉም ሥራውን የሰራው አያሌው ቀኖ ኦሮሞ በመሆኑ ለክርክር አይመችም፡፡
የአርሲ ዘመቻ ከተፈፀመ ከሰማንያ አመታት በኋላ አርሲ ላይ የወለደው ፕሮፌሰር አባስ ገናሞ ግን ሥነ ቃላዊ ትውፊትን ብቻ መነሻ በማድረግ የምኒልክ ጦር በአርሲ ዘመቻ ጊዜ “የሴቶችን ጡት ቆርጧል” ይለናል፡፡ መቼም ለታሪክ ምርምር ዋና ወሳኝነት ያለው አስተማማኝ መረጃ ወይም የታሪክ ምንጭ ሰነዶች (በሙያው መስፈርቶች ተቀባይነት ያላቸው ታሪካዊ ማስረጃዎች) መሆናቸውን መካድ ያስተዛዝባል፡፡
በጊዜው የአገር ቤት ፀሐፍት የነበሩትን እነ ፀሐፊ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴንም ሆነ ዘግይተው የደረሱትን ህዝባዊ ታሪክ ፀሐፍትን “የተጉለት ደብተራ” ማለት የሚቀላቸው የዘውገ ብሔርተኞቹ “እውነት ከእኛ ዘንድ ብቻ ነች” በሚል “ለቅኝ ግዛት” ሃቲት በሚያመች መልኩ ዝግና የተመረጠ የታሪክ ግንዛቤ በመያዝ ትውልዱን መራር ትውስታዎችን ከብዜት (ፈጠራ) ታሪክ ጋር በመጋት የተነጠለ ምልከታ ማስረፅ እንደ ስትራቴጂ ተያይዘውታል፡፡ ውጤቱም ሐውልትን ያዋለደው ጥላቻና እልህ የተጫነው ፖለቲካዊ እርግማን በሚኒልክ ላይ ማዝነብ ሆኗል፡፡
የግማሽ ቀኑ የጨለንቆ ጦርነት …
“ከ1855 ጀምሮ ሐረርንና አካባቢዉን ይገዛ የነበረው ሼክ ሙሐመድ ኢብን ዓሊ ኢብን አብድል አል ሽኩር ይባል ነበር፡፡ እርሱም ለመጀመሪያ ጊዜ ራውፋ ፓሻ ከዘይላ መጥቶ ሐረርጌ ግዛት በገባ ጊዜ ተዋግቶ ነበር፡፡ ዳሩ ግን የግብፆቹ ትጥቅ ዘመናዊ ስለነበረ መመከት ባለመቻሉ ልጁን ሐጂ የሱፍን በቅድሚያ ልኮ ለግብፅ ከዲቭ ገባርነቱን መግለጽ ግዴታ ሆነበት፡፡ ነገር ግን የግብፅ ጦር ወደ ሐረር ከተማ ለመግባት ሲጓዝ በዙሪያው ያሉት ኦሮሞዎች የአላ፣ የጀርሲ፣ የባሊሌ፣ የአቡራ . . . ነገዶች ተሰብስበውና ጠንክረው በእግርም በፈረስም እየጋለቡ በጦርና በቀስት ሰባት ሰዓት ያህል ከግብፆች ጋር ተዋግተው በመጨረሻ ሲሸነፉ እነሱም እንደአገር ልማድ ሴቶቻቸውን ልከው መገበራቸውን አስታወቁ፡፡ ቀጥለውም መሪዎቹ በየተራ እየመጡ ለራውፋ ፓሻ እጃቸውን ሲሰጡ፤ የግብፅ ባንዲራ አሚሩ ቤት ላይ በገሃድ ተሰቅሎ ሐረር በግብፅ አገዛዝ ሥር መሆኑ ታወጀ” (ተክለ ፃዲቅ ፣ አፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት ገጽ 287)፡፡
ሐረር በዚህ መልኩ በግብፅ ከተያዘች በኋላ ለአስር አመታት ያህል በግብፆች ተገዝታለች፡፡ በዚህ ጊዜ ምኒልክ በወሎ በኩል የጀመረውን አገር የማቅናት ዘመቻ ወደ ደቡብ ፊቱን እያዞረ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆንም ምኒልክ የሸዋ ንጉስ እንጂ ንጉስ ነገስት አልነበረም፡፡
በተክለፃዲቅ አገላለፅ ፍሬያማ በሆነው አየሩ ለሰውነት ተስማሚ በሆነው ሰፊ የሐረር ግዛት ላይ ፈረንሳይም ጣሊያንም የቅኝ ግዛት ምኞታቸውን ዓይን ሳይወረውሩ አልቀረም፡፡ ምኒልክ ስትጠብና ስትሰፋ የኖረችውን ኢትዮጵያን እያሰበ፣ መሐመድ ኢብን አሊ ጋዝ አህመድ (ግራኝ አህመድ) ከምስራቅ እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ ለ15/16 ዓመታት ጠቅልሎ የገዛትን ኢትዮጵያ እያስታወሰ ፊቱን ወደ ሐረር ቢያዞር በምን መለኪያ እንደ ግብፆች “ቅኝ ግዛት” ሊባል ይችላል?
ግብፆች በሐረርም በዘይላም በሌላውም የኢትዮጵያ ዙሪያ ግዛታቸውን ለአስር ዓመታት ቢያስፋፉም በሱዳን የመሃዲስቶች አጥቂነትና በኩፊት የኢትዮጵያዊያዉን አሸናፊነት የተነሳ ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ውድቀት ስለገጠማቸው ያለ አስገዳጅ ጦርነት ሐረርን ለመልቀቅ ተገደዱ ፡፡ (ተክለፃዲቅን ያጤኗል)
በዚህ ጊዜ (ግንቦት 1878) የሐረር ተወላጅ ባላባቱ አሚር አብዱላሂ የሐረር ገዥ ሆነ፡፡ ጣሊያን ሐረር ላይ ዓይኗን ጥላ ነበርና ምኒልክ ጣሊያንን መቅደም ግድ አለው፡፡ አሚሩ ገዥ በሆነ በሰባተኛው ወር በወርሃ ታህሳስ 1879 የሚኒልክ አገር የማቅናት ዘመቻ ወደ ሐረር ፊቱን አዞረ፡፡
የአፄው የጦር ሜዳ ውሎ ዘጋቢ ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ የጨለንቆን ጦርነት እንዲህ ይተርከዋል “. . . አሚር አብዱላሂ ዛሬ (ታህሳስ 29) በዓለ ልደት (ገና) ነውና ክርስቲያኖች አይሰለፉም /አይዋጉም/ ብሎ መክሮ ጦሩን ጠቅልሎ ሰናድሩን /ባለጠመንጃውን/ ከፊት መድፎቹን ከመካከል፣ ቀስተኛውን ከኋላ ከዚያ ቀጥሎ ፈረሰኛውን ጋሻኛውን አሰልፎ በአምስት ሰዓት ወደ ሰፈር መጣ ንጉሡ መነጥራቸውን ከዙፋናቸው ፊት አቁመው ሲመለከቱት ከሰፈር ማዶ ያለውን ቁልቁለት ወርዶ ከደኑ ለጅሐድ /ለቅዱስ ጦርነት/ ሲመጣ አዩት፡፡
በዚህ ጊዜ በቁጣ . . . ሰራዊታቸውን “ሄደህ በለው” ብለው አሰልፈው ሰደዱት፡፡ . . . አሚር አብዱላሂም መድፎቹን ማስተኮስ ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ከመኳንንትም ከቤት አሽከሮችም ከሰራዊትም አጫሪው ፈረሰኛ ሄዶ ገጠመው በዚያ ጊዜ ፅኑ ውጊያ ሆነ፡፡ የንጉሱ ሰራዊት መድፎቹን እጅ አድርጐ /ማርኮ/ አዞረበት፡፡ የግንባሩም ሲዘልቅና ሲገጥመው አሚር አብዱላሂ ድል ሆነ (ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምንልክ፤ ገጽ 145)”
“የተደበቁ የግፍ ታሪኮችን ፈልፍለን አውጥተናል” የሚሉን እነ ገመቹ መልካ እና ወልደ ዮሐንስ ወርቅነህ በውጊያው “አጤ ምኒልክ በእጃቸው በገባው የአውሮፓ ነፍጥ እንደልባቸው ቢጠቀሙም የኦሮሞ ልጆች ለሐገራቸው ነፃነትና ለክብራቸው ሞትን ሳይፈሩ እየተፋለሙ የጀግና ሞት ሞተዋል፡፡ ቅኝ ገዥዎች የኦሮሞን ልጆች ደም ረግጠው በማለፍ በድዋንበር ፈረስ መጋላ በሚባለው አደባባይና በአምስቱም (የሐረር) በር የንጉሱን ባንዲራ (የአቢሲንያን ባንዲራ) ሰቀሉ” (ኦሮሚያ የተደበቀው የግፍ ታሪክ፤ ገጽ 82) ይሉናል፡፡ እዚህ ላይ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ሐረር ላይ የግብፅ ባንዲራ ለአስር ዓመታት መውለብለቡን በቁጭት ስሜት ቀርቶ በለዘብተኝነት እንኳ በመፅሐፋቸው ውስጥ ያልገለፁልን እነ ገመቹ መልካ የንጉሱ (የአቢሲንያ) ባንዲራ ሐረር ላይ መውለብለቡን እጅግ በቁጭት ስሜት ይተርኩልናል፡፡ ሐቁ ግን የምኒልክን የደቡብም ሆነ የምስራቁን ዘመቻ በድል ፋና ወጊነት የተወጡት የመንዝ ገበሬዎች ብቻ ሳይሆኑ ፈረሰኞቹ የሸዋ ኦሮሞዎችም ጭምር መሆናቸው ነው፡፡
ገመቹ መልካና ወልደ ዮሐንስ ወርቅነህ ከላይ በተጠቀሰ የጋራ መፅሐፋቸው የጨለንቆ ጦርነት ላይ 4000 (አራት ሺህ) ተዋጊ በአሚሩ በኩል እንደነበረ ይገልፃሉ፡፡ እውነት ነው፡፡ ሌሎች የታሪክ ፀሐፊዎችም የተሳታፊው ቁጥር ላይ ልዩነት አይስተዋልባቸውም፡፡ በጨለንቆ ጦርነት ላይ “አልቋል” የተባለው የሰው ህይወት መጠን ግን ዛሬም ድረስ አከራካሪ ነው፡፡ ኮብላዩ “ሚኒስተር” ጁነዲን ሳዶ “በጨለንቆ ጦርነት አንድ መቶ ሺህ የሀረር ሰዉ አልቋል” ይለናል፡፡ የሚጠቅሰዉ ታሪካዊ ሰነድ ግን የለም፡፡ ከርሱ የተሻለ የተቆርቋሪነት ስሜት ያላቸዉ እነ ገመቹ መልካ እንኳ ይህን በድፍረት አልጻፉም፡፡ ምኒልክ በድል አድራጊነት ሐረር እንደገባ አንድ አዋጅ አስነግሯል፡፡ “እስላሙና ኦሮሞው እንደ አባቱ ይደር” ይላል፡፡ ከዚህ አዋጅ ተነስተን በጦርነቱ ተሳታፊ ከነበሩት የአሚሩ ወታደሮች ባለፈ የከተማው ነዋሪ ላይ የደረሰ ውድመት ያለ አይመስልም፡፡ የከፋ ውድመት ቢደርስ በጊዜው ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ቦረሊ የተባለው የፈረንሳይ መንገደኛ ኢትዮጵያን በተመለከተ በፃፈው መፅሐፍ ውስጥ ጉዳዩን ለማካተት የሚቀድመው አልነበረም፡፡ ግማሽ ቀን ያልተሻገረው የጨለንቆ ጦርነት ወራትና አመታትን ከተሻገሩት የደቡብ (በተለይም የጉራጌ፣ የከፋ፣ የወላይታ፣ የሲዳማ . . .) ዘመቻዎች አኳያ (በንጽጽር ሲታይ) እዚህ ግባ የሚባል አይደለም (“የአንድ ሰው ሞት አሳዛኝ (ትራጄዲ) የብዙዎች ግን ቁጥር (ስታቲስቲክ)” ነውእያልን እንዳልሆነ ልብ ይሏል)፡፡ መቼም ኢትዮጵያ በጦርነት የተፈጠረች አገር ነችና ጦርነትን ከጦርነት ማነፃፀር ለኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ የመንግሥት ምስረታ (የስቴት ፎርሜሽንን) ባህርይን እዚህ ላይ ያጤኗል፡፡ ለዚህ ጦርነት መታሰቢያ በሚል ለነገ አገራዊ ዕዳ ሊያመጣ የሚችል “የመታሰቢያ ሐውልት” ሐረር ላይ በሃያ አምስት ሚሊዮን ብር ተገንብቷል፡፡ ያው የብሄርተኝነት መቀሰቻ ከሆነው አንዱ ከትላትን የሚጐተቱ መራር የጦርነት ታሪኮችን በብዜት መልኩ ለትውልዱ መጋት ነው፡፡ (እ)የተገነቡ ያሉ ሐውልቶችም ከዚህ የተሻገሩ አላማ የላቸውም፡፡
የነገሩ ምፀት ደግሞ ከምኒልክ አገር የማቅናት ዘመቻ በኋላ አድዋ ላይ ወራሪውን የጣሊያን ኃይል በተባበረ ክንድ ድል የነሱት ኢትዮጵያውያን ከአርሲና ከሐረር የተውጣጡ ፈረሰኞች ፣ ቀስተኞች እና ጋሻኛ የድሉ ባለቤት (ተሳታፊ) መሆናቸው ነው፡፡
የእነዚህ ከሐረር – ዓድዋ ፣ ከአርሲ – ዓድዋ. . . በባዶ እግራቸው ዘምተው ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው የተዋደቁ የኦሮሞ አባቶችን የዓድዋ ተጋድሎ በአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ ማወደስ አልሆንልህ ያላቸው የኦሮሞኛ ሙዚቃ አርቲስቶች (ቀመር የሱፍና ሹክሪ ጀማል) “ምኒልክ የአፍሪካ ሂትለር” ብሎ ለመዝፈን ግን አይሰንፉም፡፡ ነገሩ ግልፅ ነው! ዓድዋ ላይ ከአዋጊነት እስከ ጭፈራ ከፈረሰኛ እስከ እግረኛ ድረስ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በመዋደቅ ኮከብ ሆነው የዋሉትን የኦሮሞ አባቶች በኦሮምኛ ሙዚቃ ማወደስ ጠርዘኛው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ዋነኛ ማጠንጠኛ የኦሮሞን ጥያቄ በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ውስጥ የሚቀነብበው በመሆኑ ከ“ቅኝ ግዛት” ሃቲቱ ጋር በቀጥታ የሚላተም በመሆኑ ዓድዋን የሚያስታውሱ (የሚዘክሩ) የኦሮምኛ ሙዚቃዎችን ልናዳምጥ አልታደልንም፡፡
ለጠርዘኞቹ የኦሮሞ ብሄርተኞች ፕሮፌሰር ሬይሞንድ ጀናስ የኦሮሞዎች የዓድዋ ተሳትፎ ራሱን በቻለ ሬጅመንት የሚታይ እንደሆነ “The Battle of Adwa, African victory in the age of Empire” ሲል በሰየመው መፅሐፉ የሚገልፀው ነገር አይዋጥላቸውም፡፡ የኦሮሞ ፈረሰኞች በዓድዋ ጦርነት ጊዜ “ወደ ሸለቆው ሲወርዱ በድንገት የገነፈለ ጥቁር ባህር ይመስላሉ” በማለት ጀግንነታቸውን የገለጹበት መንገድ ለእነርሱ “የአቢሲንያ ተረት ተረት ነው”፡፡
አለመታደል ሆነና ለጠርዘኞቹ የኦሮሞ ብሄርተኞች ዓድዋ ላይ የዘመቱት የቀደሙት የኦሮሞ ተዋጊ አባቶች፤ ምኒልክ በርቀት መቆጣጠሪያ እያሽከረከረ የሚያፋልማቸው ሮቦት እንጂ ራሳቸውን ችለው፤ ማንነታቸውን ጠብቀው የተዋደቁ ብርቱዎች አይመስሏቸውም፡፡ በራሳቸው የቆሙ ብርቱዎች እንደነበሩ ቢያምኑማ የ“ቅኝ ግዛት” ሃቲትን ሲያነበንቡ ባልኖሩ ነበር፡፡ ይሄው ውድቅ አመለካከት አድዋን የመሰለ ወታደራዊ ድል ወደ ፖለቲካዊ ድል እንዳንቀይረው እንቅፋት ሆነብን!! ዛሬም በየጥጉ “የእኛስ የጉድ ነው” እያልን እናላዝናለን፡፡
የእርግማን አንድ፡ ማሳረጊያ
አርሲና ሐረር ሌሎችም የደቡብ አገር የማቅናት ዘመቻዎች በሁለቱም ወገን የደም ዋጋ ባስከፈሉ ውጊያዎች የተጠቃለሉ እንጂ በብላሽ ስጦታ (ወደው የገቡትን ሳንዘነጋ) ወይም በህዝብ ውሳኔ ወደ ምኒልክ ግዛት የተጠቃለሉ አይደሉም፡፡ በወቅቱም ሰብዓዊ ጥሰቶች በገባሪው ወገን አልደረሱም ብሎ መከራከር ትርፉ ጉንጭን ማልፋት ነው፡፡ ምኒልክ በደቡብ ዘመቻ እጅ/እግር አልቆረጠም ብሎ በጨበጣ መከራከር የትም አያደርስም፡፡ ቀርቶ የታሪክ መዛግብት ማገላበጥ፤ በትንሹም ቢሆን “ፍትሐ-ነገስት”ን ማስታወስ የአባት ነው፡፡
የወደረኛውንና ጭፍራውን እጅ/እግር መቁረጥ በምኒልክ ጊዜ የተጀመረ ድርጊት ሳይሆን የዘመናዊት ኢትዮጵያ የታሪክ አባት የሆኑትን ሁለቱን የቀደሙ ነገስታት (ቴዎድሮስና ዮሐንስ) ጨምሮ የፊት መሳፍንትም ሆኑ ነገሥታት ፈጽመውታል፡፡ ከቶም አንዳንዶች አፍንጫ እስከ መፎነን፣ ምላስ እስከ መቁረጥ ደርሰዋል፡፡ (መስለብማ በየትኛውም መሳፍንት “የወግ” ነበር)፡፡
በጉልበት ሌላውን ማስገበር በመፈራረቅ የተከወነ ድርጊት ነው፡፡ በመስመር መሐል በመካከለኛው ዘመን የተካሄደውን የኦሮሞ መስፋፋት የፈጠረውን እልቂት የአባ ባህሪን፣ የአለቃ አጸሜንና የአለቃ ታየን ሥራዎች እያጣቀሱ ሁኔታዎችን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ የታሪክ ሰነድ ባለሃብቱ ዶ/ር መርዕድ ወልደ አረጋይ ከዛሬ 45 ዓመት በፊት ለሦስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ) ማሟያው ያዘጋጀውን ጽሁፍ “Southern Ethiopia and the Christian kingdom 1508 – 1708, with special Reference to the Galla Migration and Their consequences” ላይ የተካተቱትን ወሳኝ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች መገምገሙ ለጋራ ቤታችን ይበጃል፡፡
“ሞጋሳ” እና “ጉዲፈቻ” በተሰኙ ማህበራዊ ሥርዓቶች የባህል ቅቤ ማቅለጫ ድስት (melting pot) ውስጥ የገቡትን የህብረተሰብ ክፍሎች ማሰብ ልንዘነጋው አይገባም፡፡ ኦሮሞ በመካከለኛዉ ዘመን ሲስፋፋ የተዋጡ የማህበረብ ክፍሎችን ክዶ መከራከር የሚያዋጣ አይደለም፡፡
በነዚህና መሰል ጉዳዮች ውስጥ ኦሮሞ ገዥም ተገዥም ነበር፡፡ አስገባሪም ገባሪም ነበር፡፡ ቀላጭም አቅላጭም ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ዛሬ ላይ ኦሮሞ መስፋፋቱን ተከትሎ ከሟሟበት የገዳ ሥርዓ ውጪ ሌሎች የዘውጉ ማንነቶች ከሞላ ጐደል ህያው ናቸው፡፡ ይልቁንስ ኢትዮጵያን ቀስቶ በማዋቀሩ ረገድ በማህበራዊውና በኢኮኖሚያዊው መስክ ይበልጥ አቃፊ ደጋፊ ሆኗል፡፡ ተጠቃሚነቱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ቢወድቅም ቅሉ፡፡ ፖለቲካዊ ተሳትፎው ግን ዛሬም ድረስ የዛለው ጠርዝ የታከከው የልሂቃኑ ጉዞ ውጤት ነው፡፡ መቼም በጥንቸሎች የታሰረው ዝሆኑ ኦህዴድን እንደ ወሳኝ የፖለቲካ ድርጅት የመቁጠር ግዴታ የለብንም፡፡
አሜሪካውያን ከሚያከብሯቸው መሪዎቻቸው መካከል አብርሃም ሊንከን አንደኛው ነው፡፡ ጭራሹኑ እስከ መመለክ የደረሰ መሪ ነው፡፡ ይሁንና የደቡብ ግዛቶች ከሰሜኑ ለመገንጠል ጦርነት በከፈቱበት ወቀት አብርሃም ሊንከን የአንድነቱ ጠበቃና መሪ በመሆን ከፍተኛ ጦርነት መርቷል፡፡ በዚህ ጦርነት ስፍር ቁጥር የሌለው ህዝብ አልቋል፡፡ አብርሃም ሊንከንን ግን አሜሪካዊያን በፀረ ህዝብነት አለያም በጨፍጫፊነት ሲያነሱት አይታይም፡፡
ለማናቸውም የኢትዮጵያ ዘመናዊ አገር ግንባት ሂደትና ፈተናዎች በዚያን ጊዜዋ ኢትዮጵያ መቼት ውስጥ ተቀምጣ መታየትና መመዘን ይኖርባታል፡፡ አባ ዳኘው-ምኒልክም የዛሬ ዘመን መሪ ሳይሆን የራሱ ዘመን መሪ ነው፡፡ የንግስና ዘመኑ የሚመዘነው በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች መመዘኛ ነጥቦችን በተንተራሰ ሳይሆን እንደ ጊዜው ማዕቀፍ መታየት ግድ ይለዋል፡፡
ቻርለስ ቲሊ “ጦርነት አገርን ይወልዳል፤ አገርም ጦርነት ይወልዳል” ሲል የተናገረውን ኃይለ ቃል መምዘዙ እንድንግባባ ዕድል ይሰጠን ይሆናል፡፡ ካልሆነም የጀርመን አባት ቢስማርክ (አገራት በብረትና በደም ይመሠረታሉ) “states are formed by iron and blood” በማለት በተግባር አገሩን ለማዋሃድ የተጓዘበትን መንገድ ማስታወሱ የምኒልክን አገር የማቅናት ዘመቻ ግልፅ ያደርግልናል፡፡
በዚህ አግባብ ምኒልክ ከአገር መሃንዲስነቱ አኳያ “ነፍጥና መስዋዕትነትን” የአገር ማዋሃጃ ስልት አድርጎ የተጠቀመበትን መንገድ በትይዩ አስቀምጠን ስናይ ምኒልክ ለ“ሂትለር” ሳይሆን ለቢስማርክና ለአብርሃም ሊንከን ይቀርባል፡፡ ቆራጥ ዘመቻዎቹን ስንመረምር ደግሞ “እምዬ” የሚለውን የቁልምጫ ሥሙን ለመቀበል ይቸግረን ይሆናል፡፡ ምኒልክ “እምዬ” ቢቀርበት እንኳ የአገር ምህንድስና ዉሉ በደንብ የገባው states Man ነው፡፡ በምኒልክ ሃውልት ላይ ተጽፎ እንደሚነበበው ጽሁፍ “ከትልቅ ወይም ከትንሽ ቢሆን መወለድ ሙያ አይደለም ራስን ለታላቅ ታሪክ መውለድ ግን ሙያ ነው”፡፡
እናም ሊንከን በአንድነት ጠበቃ ደግፎ ባቆያት አሜሪካን አገር ሚኒሶታ ግዛት አልያም ቢስማርክ በተዋደቀላት ጀርመን፤ በርሊን ውስጥ ሆት ዶግ እየበሉ፤ የካልዲስን ቡና እንደ ወረደ እያጣጣሙ ምኒልክ በነፍጥና በመስዋዕትነት ያቆማትን አገር ቢሳካ ለመግዛት ካልሆነም ለመገንጠል እየታገሉ “ምኒልክ ሂትለር ነው” ቢሉ አንድም ርባና ቢስ የትውልድ ፖለቲካዊ ርግማን ነው፤ ሌላም አላዋቂነትን በአደባባይ መግለጥ ነው፡፡
እርግማን ሁለት፡ “ምኒልክ ኤርትራን ሸጠ፤ ትግራይን በደለ”
በቀጣይ ዕትማችን የምንዳስሰው ጉዳይ ይሆናል!!
አድዋን ወደ ፖለቲካ ድል መቀየር ለምን ተሳነን? እርግማን ሁለት: “ምኒልክ ኤርትራን ሸጠ፤ ትግራይን በደለ”

ከዝግጅት ክፍሉ:- “አድዋን የሚያህል ወታደራዊ ድል ስለምን ወደ ፖለቲካዊ ድል መቀየር ተሳነን?“ በሚል ርዕስ የመጀመሪያውን ክፍል ማቅረባችን ይታወሳል፤ ሙሉው ጽሁፍ እዚህ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህኛው ክፍል ሁለት ዕትም እርግማን ሁለት “ሚኒልክ ኤርትራን ሸጠ፤ ትግራይን በደለ” የሚለው ርዕስ ዳሰናል፡፡
የኢትዮጵያ አገራዊነት ታሪክ ተፃሪሪ ትርጓሜና የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ምስረታ ሂደት የተመዘዙ መንታ ሰበዝ ናቸው፡፡ “ቅኝ ግዛት” vs “አገር ምስረታ፣ ማቅናት/ግንባታ” የሚሉ ተፃራኒ ትርጓሜዎች እንዳሉ ሁሉ፤ “አገር ሻጭ” እና “ባንዳ” የሚሉ የፖለቲካ እርግማኖች የዘመናዊት የኢትዮጵያ የታሪክ ገጽታ አካል ሆነው ቀርበዋል፡፡ ማንነትን የታከከ የታሪክ ትርጓሜ ባለበት ሁኔታ እነዚህ ብያኔዎች ሊጠፉ የማይችሉ የታሪክ ፍም እሳቶች ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ በገዥዉ ኃይል ፊት ታሪክ ትምህርት መሆኑ ቀርቶ ፍርድ ቤት ሆኗል፡፡
አፄ ዮሐንስ አራተኛ ከእርሱ በፊት እንደነበረው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስም ሆነ ከኋላው እንደተከተሉት ነገሥታት በሚያሟግት የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ያለፈ መሪ ነው፡፡ አፄ ዮሐንስ ወደ ስልጣን የመጣበት መንገድ ምኒልክ ወደስልጣን ለመውጣት ከተጓዘበት የዲፕሎማሲ መንገድ የሚለይ አደለም፡፡ ስልጣን የኃይል ሁሉ ማዕከል በሆነበት ቦታ ገባሪነትን መካድ ለኢትዮጵያ መሳፍንቶች የተለመደ ባህሪ ነበር፡፡ በውጭ ኃይሎች ድጋፍ የጦር መሳርያ አቅምን ማጠናከር፤ ጊዜና ወቅት ጠብቆ ወደ ንግሥና መንበር መውጣት፤ የዮሃንስ እና የምኒልክ መንታ ገፀ-ባህሪያት ናቸው፡፡
አፄ ሚኒሊክ “የጣልያን ተላላኪ ባንዳ ነበር” ማለት የሚቀናቸው የትግራይ ብሔረተኛ ልሂቃን የዮሐንስን የቀደመ የታሪክ እድፍ ተስቷቸው አይጠቅሱትም፡፡ የስዊዝ ሰው የሆነው ሙሲንጀር ፓሻ የጊዜው ያገር ጥናት ተጓዥ መንገደኛ ነበር፡፡ ይህ ሰው በምጽዋና በከረን አመታትን አሳልፈዋል፡፡ የወቅቱ ደጃች ካሳ (ዮሐንስ) እና የእንግሊዞችን ግንኙነት በማቃናት ቀዳሚ ሰው ነበር፡፡ በዚህ ሰው አገናኝነት ከእንግሊዞች ጋር የተወዳጀዉ ደጃች ካሳ ለናፒየር ጦር የመቅደላ መንገድ ሁነኛ ጠቋሚ ነበር፡፡ ያለ አንዳች ግነት ስለ ሥልጣን ለውጭ ኃይሎች በመታመን (ባንዳ፡- ለባዕድ ሥርዓት ታማኝነትን ማሳየት) አስገባሪውን (አፄ ቴዎድሮስን) በመክዳት ባገኘው የጦር መሳርያ ድጋፍ ታግዞ ወደ ስልጣን የወጣው ቀዳሚው ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ አራተኛ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ መሳፍንቶች ለአብነት በቴዎድሮስ ዘመን እንደ አገው ንጉሴ ያሉ መሳፍንቶች ከውጪ መንግስታት ጋር ቢፃፃፉም በውጭ ሀይሎች የጦር መሳሪያ ድጋፍ ወደ ሥልጣን ለመውጣት የተሳካለት መሳፍንት አልነበረም፡፡ ከዳጃች ካሳ (ዮሐንስ በስተቀር)!!
የአፄ ምኒልክ መንገድ ከዚህ ብዙ የራቀ መሆኑን መካድ ያስተዛዝባል፡፡ የአፄ ምኒልክ እና የጣልያኖች ግንኙነት ከአፄ ዮሐንስ የንግስና ዘመን ይጨምራል፡፡ ሚኒሊክ የዘር ሀረጉን የሚስበው ከአፄ ልብነ ድንግል ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የልጅ ልጅ የኃይለ መለኮት ልጅ በመሆኑ የመሀል ኢትዮጵያን ግዛት በመቆጣጠርና የደቡብ እና ምዕራብ ኋላም የምስራቅ ኢትጵያ ግዛቶችን በመጠቅለል ወደ ንጉሠ ነገሥትነቱ የመውጣት ምኞት ነበረው፡፡ ለዚህም ይመስላል አፄ ዮሐንስ ከነገሰበት 1964-1870 ዓ.ም ለተከታታይ ሰባት ዓመታት ለአፄ ዮሐንስ ሳይገብር የሥልጣን ተፎካካሪና የዙፋን ወደረኛ ሆኖ የተቀመጠ፡፡ በነገራችን ላይ በነዚህ ጊዜያት የአፄ ምኒልክ ማኅተም “ንጉሠ ነገሥት” ይል ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩም የአፄ ዮሐንስ ማኅተም “ንጉሠ ነገሥት” ይል ነበር፡፡ (ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ፣ ተክለ ፃዲቅን፣ ሀሎርድ ማክስን ያጤኗል)
በሁለቱ ወደረኞች ማሀከል የነበረውን የሥልጣን ሽኩቻ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ በውብ ብዕሩ “አንዲቷ ኢትዮጵያ በዮሐንስና በምኒልክ ተከፍላ የሁለት ነገሥታት ሀገር ሆነች፡፡ ሁለቱም በቤገ-ምድርና በጎጃም፣ በወሎ፣ በላስታ አውራጃ ላይ የውስጥ ፍልምያ ሲያሳዩ፤ እንደዚሁም የውጪ መንግስታትን ወዳጅነት አጥብቀው በደብዳቤና በየመልክቶቻቸው አማካኝነት ይሻሙ ነበር፡፡ ሁለቱም የውጭ ሀገር መንግሥታት ወዳጅነት የሚሻሙት አጠገባቸው ባሉት ሀገር ጎብኝና ነጋዴዎች ወይም ምጥዋ በሚቀመጡት ቆሲሎቻቸው ጎን ባላንጣን አስጠልቶ ራስን ለማስወደድ ነው (አፄዮሐንስ እና የኢትዮጵያ አንድነት ፤ ገፅ 57)” ሲል ይገልፀዋል፡፡
በሁለቱ ወደረኞች መሀል የነበረው የስልጣን ሽኩቻ መጋቢት 14 ቀን 1870 ዓ.ም ልቼ ላይ በምኒልክ ይቅርታ ጠያቂነት ዕርቅ ቢወርድም ተከታዮቹን አስራ አንድ ዓመታት (1871-1881) ምኒልክ የግዛት ወሰኑን ወደ ደቡብ ምዕራብ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍሎች በማስፋት የመሬት ይዞታውን (Land power) የግብር መሰብሰብ አቅሙን እና የጦር መሳሪያ ክምችት ሀይሉን በማጠናከር ስራ ተጠምዶ ነበር፡፡ ዓመታዊ ግብሩን በማስገባት ዮሐንስን የሚያዘናጋው ምኒልክ የጦር መሳሪያ ክምችቱና የሰራዊት ብዛት ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም፡፡
ጣሊያኖች በእንግሊዝ ችሮታ ምፅዋን በቁጥጥር ስር አድርገው ወደ አገር ውስጥ በሚገባ ማንኛውም አይነት እቃ ላይ ተፅኖ ሲያደርጉ አፄ ዮሐንስ የምኒልክ ከጣሊያን ጋር መቀራረብ አልወደደውም ነበር፡፡ የምኒልክ እና የጣልያኖች ወዳጅነት በውጫሌ ውል የወዲያው ግፊት (immediate cause) ሆኖ እስከተፈጠረው የአድዋ ጦርነት ጊዜ ድረስ ቆይቶል፡፡
ጣሊያኖች የወቅቱ ጠላታቸውን አፄ ዮሐንስ እንዲዳከምላቸው አፄ ምኒልክን ለማቅረብ መሞከራቸው የቀኝ ግዛት መሀንዲሶች ዘዴ ይመስላል፡፡ ይህም ሆኖ በርከት ያለ የጦር መሳሪያ ያስታጠኩትን ምኒልክ መጠርጠራቸው አልቀረም፡፡ ይህን ጉዳይ የታሪክ ጸሃፊዉ ፕሮቲ ክሪስ “Empress Taytu and Menilek II” በሚል መጽሀፉ የወቅቱ የጣሊያን መንግስት ወኪል የነበረው አንቶሎኒ በምኒልክ የበዛ መሳሪያ ክምችት ያደረበትን ስጋት ለምኒልክ አንስቶ እንደ ተማፀነው ጽፏል፡፡ ለምኒልክ፣ ለጣይቱ፣ ለራስ ዳርጌና ለአዛዥ ወልደ ፃዲቅ እንዲሁም ለሁለት አስተርጓሚዎች እንደየ ማዕረጋቸው ሥጦታዎችን ካጎረፈ በኋላ ምኒልክ ያገኘውን መሳሪያ ጣሊያኖችን ለመውጋት እንዳይጠቀምበት በክርስቲያናዊ ደንብ መሃላ ይፈፅምለት ዘንድ ተማፅኖ ነበረ (ገፅ 57-8 ይመልከቱ) የውጫሌው ውል ተደራዳሪ እና ፈራሚ የነበረው ጣሊያናዊው አንቶኖሊ እንደሚለው 1880 ዓ.ም ላይ (ከውጫሌ ውል አንድ ዓመት ቀደም ብሎ መሆኑ ልብ ይሏል) ምኒልክ የደቡብ፣ የምዕራብ እና የምስራቅ የኢትዮያ ግዛቶችን ጨምሮ 196,000 (አንድ መቶ ዘጠና ስድስት ሺህ) ሰራዊት እንደነበረው ሮቢስን “The Attempt to Establish a protectorate over Ethiopia” በሚለው መጽሃፍ (ገፅ 66) ይነግረናል፡፡
በነዚህ ጊዜያት ሁሉ አፄ ዮሐንስ በስም ደረጃ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በሰሜን ኢትዮጵያና አካባቢው (ብቻ) የተገደብ እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር፡፡ የአፄ ዮሐንስ የንግሥና ዘመን ፍፃሜ ሦስት አመታት ሲቀረው ሚኒሊክ (የሐር ላይ ባንዴራውን ሲያውለበልብ) በግዛት ወሰን፣ በግብር ማሰሰባሰብ፣ በጦር መሳሪያ ክምችትና በዲፕሎማሲ የበላይበት አፄ ዮሐንስን ይበልጠው ነበር፡፡ የአፄው የንግሥና ዘመን እየተሸረሸረ የመጣ ለመሆኑ ምኒልክ በተለየ ሁኔታ የአስራ አንድ አመታት (1871-1881 ዓ.ም) የሥልጣን ግስጋሴ ይነግረናል፡፡ በነዚህ ጊዜያት አፄ ዮሐንስ የውጭ ኃይሎች ፍልሚያ ቢኖርበትም ምኒልክን ለማስቆም ከቶውንም አልሞከረም፡፡ ይህ ሁኔታ ከማዘንና ከርህራሄ የመጣ ሳይሆን የአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት መመናመንና የማህበራዊ መሰረት መጥበብ ተከትሎ ከተፈጠረ የአቅም መዛል የመጣ ነበር፡፡
የዛሬዋ ኤርትራ ይህንን ስያሜ ከመያዝዋ በፊት “ባህረ ነጋሽ፣ ምድረ ሌማሴን፣ ከበሳ” በመባል ትጠራ ነበር፡፡ ኤርትራ የሚለው መጠሪያም ሆነ ፖለቲካዊ ቁመና ያገኘችው ጣልያን የቀይ ባህር ጠረፍን ታክካ ወደ አካባቢው መዝለቋ ኋላም መስፋፋቷ ከተመዘገበበት 1879 ዓ.ም ወዲህ ነው፡፡ (በተለይም የዘውዴ ረታን፤ የተከስተ ነጋሽን ሥራዎች ያጤኗል) በዚህም ጊዜ ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ነበር፡፡
ከ1864-1881 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረጉ ታላላቅ ጦርነቶች (ተድአሊ፣ ኩፊት፣ ጉራዕ፣ ጉንደት {ጉንዳጉዲ}) ኢትዮጵያ በድል የተወጣችው በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግስት ነበር፡፡ ወራሪው የግብፅ ኃይል በጉንደት እና በጉራዕ ተከታታይ ሽንፈት፤ ሌላ ጊዜ አውሳ ላይ በአፋሮች እጅ ወድቆ የግብፅ ጦር አፋር በረሃ ላይ የቀረው፤ በአፄ ዮሐንስ የንግስና ጊዜ ነበር፡፡ ጣልያን የአሉላን እጅ የቀመሠበት ውርድት በሮማ ፒያሳ ቺንኮ ቼንቶ (“የአምስት መቶዎች አደባባይ”) በሚል ያስታውሰዋል፡፡ ዮሐንስ በዚህና መሠል ድሎች የታደለ ቢሆንም አገር ውስጥ “የአቻዎች አውራ” በሚል ከያዘው የንጉሠ ነገሥትነት ማዕረግ የተሻገረ በራሱ አቅም የሚቆጣጠረው መሬት ከምኒልክ አንፃር የተዳከመ ነበር፡፡ የውጭ ኃይል ላይ ያስመዘገበው ድልም የግብፅን ጦር ከመጠራረግ ውጪ የጣልያንን ጦር ከምጽዋና ከአሰብ አካባቢ ማራቅ አልቻለም ነበር፡፡ በራስ አሉላ እንግዳ (አባ ነጋ) የተመራው ጦር ዶጋሊ ላይ የጣልያንን ጦር ከመታ በኋላ ሀያ ሦስት ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ማትርቀው ምፅዋ በመሻገር የጣልያንን ጦር ያልወጋበት ሁኔታ በቀጣይ ጊዜያት ጣልያን የዶጋሊን ቁጭቷን በሰሓጢ ላይ (መጋቢት 1880) ያለምንም ወሳኝ ውጊያ ምሽግ ላይ አድፍጦ በመተኮስ የአፄ ዮሐንስ ጦር አታክቶ በመመለሱ ረገድ ተሳከቶለታል፡፡ (ባህሩ ዘውዴን፣ ተክለፃዲቅን፣ ሮሊንስንን…ያጤኗል) ለዲፕሎማሲ ሽፋን ጥለውት የወጡትን ሰሓጢን በኃይል መልሰው ያዙት ዮሐንስ እጁ ላይ የነበሩትን ድሎች መልሰው እንደጉም ይተኑበት እንደነበር የዶጋሊው ጦርነት ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ምናልባት የዶጋሊው ድል በመቀጠል ጦሩ ወደ ምፅዋ የማዝመት ሁኔታ ቢኖር ድል ከኢትዮጵያ ጋር መሆን በቻለ ነበር፡፡
ሠላም ያልተገኘባቸው የአፄ ዮሐንስ ድሎች ኤርትራ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ለተስፋፊው የጣልያን ጦር ምቹ ጊዜ እየፈጠሩ እንደነበር ከዶጋሊ ድል በኋላ በአፄው መሪነት ሰማንያ ሺህ ጦር በማዝመት የተሞከረው የሰሓጢ ጦርነት የጣልያንን ይዞታ በማጠናከር የዮሐንስን የድል ተስፋ በማጨለም የተደመደመ መሆኑ ነው፡፡ ሰሓጢ ዮሐንስ ከጣልያኖች ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተያየባት የስንብት ቦታ ሆነች፡፡
ዮሐንስ እጅግ በሚያስቆጭ መልኩ መተማ ላይ ሲሰዋ፤ በምፅዋ፣ አሰብ፣ አስመራ፣ ሰሓጢና ቆላማው ክፍል ተወስኖ የነበረው የጣልያን ጦር ያለምንም ጊዜ ማባከን የደጋውን ክፍል ወረረው፡፡ (ዘውዴ ረታን፣ ተክለፃዲቅን፣ ባህሩን … ያጤኗል) ቀደም ሲል በወቅቱ የጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስተር ፍራንቺስኮ ክርስቲ “ኤርትራ” በሚል የተሰየሙና አካባቢዎችና የደጋውን ክፍል ጠቅልለው ከሰሜን ኢትዮጵያ ግዛት ነጠሉት፡፡ የዮሐንስ ያልታሰበ ሞት ለምኒልክ የስልጣን በር ሲከፍት ለጣሊያን ጦር “ኤርትራ” የሚል ግዛት እንዲረከብ ዕድል ፈጠረለት፡፡ በተደጋጋሚ ጦርነት የደቀቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦር ከዮሐንስ ሞት በኋላ መበታተን ዕጣ ክፍሉ ሆነ፡፡
እስከዚህ የታሪክ ሂደት ድረስ ምኒልክ በኤርትራ ጉዳይ አንዳች የሚያገባው ነገር አልነበረም፡፡ ጣልያን በቀይ ባህር ዳርቻ የምትቆናጠጥበት ዕድልን ያገኘችው በ1862 ዓ.ም በጣልያናዊው ጂሴፔ ሳፔቶና “ሩባቲኖ” የተባለ የመርከብ ኩባንያ ጋር ተቀናጅተው ከአፋሩ ሱልጣን መሀመድ ሃሰን አሰብን ገዝተው ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እንኳን ምኒልክ አፄ ዮሐንስም ንጉሠ ነገሥት አልሆነም፡፡ የያኔዋ ኢትዮጵያ በአፄ ተክለጊዮርጊስ ነበር የምትመራው፡፡ የኋላ ኋላ ይህ የግል ይዞታ የነበረው ወደብ ወደ ጣልያን መንግስት ሲጠቃለልም ሆነ እንግሊዝ ከአፄ ዮሐንስ ጋር አድዋ ላይ “የሂወት ውል” እየተባለ የሚጠራውን ስምምነት ስትፈራረም እና እንግሊዝ በሶስት ወራት ልዩነት ስምምነቱን አፍርሳ ነሃሴ 1876 ዓ.ም ምፅዋን ለጣሊያን ስታስረክብ ምኒልክ በደቡብ ዘመቻ እንደተጠመደ ነበር፡፡ አፄ ዮሐንስ 150 ኪ.ሜ በማይሞላ ርቀት መቀሌ ላይ ተቀምጦ ሁኔታውን በቁጭት ያስተውል ነበር፡፡
አፍቃሪ ኢትዮጵያ የሆነው የታሪክ ጸሐፊ ሩቤንስን ከላይ በጠቀስነው መጽሃፉ እንዳለው ዮሐንስ ከእንግሊዝ ጋር ያደረገው “የሂወት ውል” አንድ ደካማ ጠላት (ግብጽ) በሁለት ጠንካራ ባላጋራዎች (የጣልያና የሱዳኑን የማሃዲ ንቅናቄ) መተካት ሆነ፡፡ በሂደት የታየውም እንግሊዝ ውሉን ወደ ጎን ገፍታ ምጽዋን ለጣልያን በመስጠት፤ ለጣልያን ወረራ በር ስትከፍት እስላማዊ ተሃድሶንና የሱዳን ብሄርተኝነትን አዳብለው ለተነሱት መሃዲስቶች ደግሞ በኢትዮጵውያንና በኢትዮጵያ ግዛት ላይ በበቀል ስሜት እንዲዘመቱ አደረጋቸው፡፡
የአፄ ዮሐንስ መካር አልቦ የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ (የኃይማኖት ፖሊሲዉን ጨምሮ) እና ህብረት ያልታየበት የመተማ ጦርነት ዘመቻ የራሱን የኢትዮጵያን አንገት አስቆረጠ፡፡ የዮሐንስ የታሪክ ሽንፈቶች ለመከላከል ታጥቀው የተነሱ የትግራይ ዘዉጌ ብሄርተኛ ልሂቃን (ህወሓታዊያንና ዮሃንሳዊያን) የኤርትራን ጉዳይ ከምኒልክ ጋር ያዛምዱቱል፡፡ ህወሓት የበረሃ ማኒፌስቶውን ሳጋና ማገር በምኒልክና በአማራ ጥላቻ ላይ በማቆም፤ ሸዋን የስተቶች ሁሉ ቋት በማድረግ ትግራይን የምሉኼ በኩልሄዎች “አገር” (ልብ አድርጉ “አገር” ነው ያልነው!!) ያደርጋታል፡፡
ድህረ – ደርግን ተከትሎ የታሪክ ቅራኔዎችን በዞረ ድምር ሂሳብ ካላወራረድኩ የሚለዉ ህወሓት፤ በምኒልክ የደቡብ እና ምስራቅ ዘመቻዎች የደረሰውን ጥቃት እያስታወሱ ዛሬም ድረስ ቁጭታቸው ያልበረደላቸውን ዘውጌ ብሄርተኞች እያስተባበሩ በምኒልክ ላይ ፖለቲካዊ እርግማን ማውረድ ሥራቸው አድርገውታል፡፡ መንግስታዊ የመዋቅር ድጋፍ ያለው ይሄው ፖለቲካዊ እርግማን ምኒልክን “ኤርትራን የሸጠ” በሚል ከአድዋ ድል ለመነጠል እስከመሞከር የደረሰ የታሪክ ኑፋቄ ስብከት አደባባዩን ተቆጣጥሮታል፡፡
በወደብ አጠቃቀም፣ በንግድና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዙሪያ የሚያስተኩረውን የውጫሌን ውል ለኤርትራ መሸጥ እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡ የትግራይ ብሄርተኛ ልሂቃን የዮሐንስ “የሂወት ውል” ስምምነት በኢትዮጵያ ላይ ያስከተለውን ጉዳት ማስታወስ አይፈልጉም፡፡ ዛሬ ላይ ብርቅ የሆነው የህብረት ስሜት ትላንት በአባቶቻችን አብሮነት (ህብረት) የታየበትን የአድዋን ድል አሳንሶ በማቅረብ የመበሻሸቂያ መድረክ አድርገውታል፡፡
100ኛው የአድዋ ድል በዓል ሲከበር “ድሉ የትግራውያን እንጂ የሌሎች አይደለም” በሚል አይናቸውን በጨው አጥበው በአደባባይ ሲከራከሩ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ላይ ተገልብጠው “አድዋ ተቀጥላ ድል እንጂ ዋና ዋና ድሎች በአጼ ዮሃንስ ጊዜ የተገኙት ናቸዉ” በማለት (በዘንድሮዉ የአድዋ ድል በዓል አከባበር ላይ አድዋ ከተማ ተገኝቶ ንግግር ያደረገዉን የትግራይ ክልል ኃላፊ አባይ ወልዱን የንግግር ይዘት ያስታዉሷል) ከታሪክ ጋር መላተማቸዉን ቀጥለዋል፡፡ በአጼ ዮሃንስ የንግስና ጊዜ የተገኙ ድሎችን ከፍ አድርጎ ለማድረግ በምኒልክ መሪነት የተገኘዉን የአድዋን ድል ማሳነስ ምን የሚሉት የታሪክ ድህነት ነዉ? በመሀል ቤት በተለያዩ አመታት በሁሉም አዉደ ዉጊያዎች ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ህይወታቸዉ ያለፈ አባቶች ተረስተዋል፡፡ ሥም አልባ ጀግኖች አስታዋሽ የላቸዉም፡፡ ታሪክን በዜግነት ማዕቀፍ ሳይሆን በዘዉግ መነጽር ማየት የሚቀላቸዉ የህወሓት ሰዎች፤ ጊዜና ሁኔታዎች ፈቅደዉ የአድዋ ድል በአጼ ዮሃንስ መሪነት የተገኘ ቢሆን (ኑሮ) ይሄኔ ድሉ በአፍሪካ ደረጃ እንዲከበር የኢትዮጵያን ህዝብ ካዝና ከማራገፍ አልፎ ለክፉ ቀን ያስቀመጡትን የግዙፉን ኤፈርት ትልቅ በጀት ይዞ ለድል መታሰቢያዉ በድምቀት መከበር እንዲቀሳቀስ ባደረጉ ነበር፡፡
ምኒልክ ላይ ፖለቲካዊ እርግማን ማዉረድ የዮሃንስን የታሪክ ሽንፈቶች የሚያጠፋ ይመስል፤ ትዉልድና የታሪክ ትርጓሜ በተሳሳተ አቅጣጫ እንዲፈስ ማድረጉን ተያይዘዉታል፡፡ ይህ የኑፋቄ መንገድ የነገዋን ኢትዮጵያ በተለይም ትግራዋያንን በመነጠል የሚጎዳ እንጂ ምኒልክን የሚያረክስ አይደለም፡፡ ምኒልክ በስጋ ቢሞትም ኢትዮጵያ እስካልተበተነች ድረስ በመንፈስ ይኖራል፡፡ የምኒልክን የአንድነት ስሜት ጊዜና ወቅቱ በሚጠይቀዉ ማህበራዊ ዕድገት መሰረት በመግራት ኢትዮጵያን ወደከፍታዋ ለማዉጣት አቅሙም ፍላጎቱም የሌላቸዉ የህወሓት ሰዎች፤ ከሙት ሥርዓት ጋር ራሳቸዉን እያላተሙ በምኒልክና በዘመኑ ጀግኖች ተጋድሎ የቆመችዉን ኢትዮጵያ መበዝበዛቸዉን ተያይዘዉታል፡፡ የነገሩ ምጸትም ይሄዉ ነዉ፡፡ ምኒልክን እየረገሙ በረከቱን ለብቻ መብላት፡፡
ዶ/ር ዘዉዴ ገብረ ሥላሴ ኦክስፎርድ ዮኒቨርስቲ ባሳተመለት “Yohannes IV of Ethiopia; A political Biography” በሚል ሥራዉ፤ በ1879 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ አጼ ዮሃንስ ለምኒልክ በጻፈለት ደብዳቤ “… በእግዚአብሔር ቸርነት ጣሊያኖች ተዋርደዉና ተንቀዉ ይመለሳሉ” (ገጽ፤199 ላይ ይመልከቱ) ብሎት ነበር፡፡ አጼ ዮሃንስ በርግጥ ስለ ጣልያኖች በዓለም ፊት መዋረድና መሸነፍ በትንበያ መልክ የጻፈዉ ደብዳቤ ልክ ነበር፡፡ አጼዉ ባያሳካዉ እንኳ አባ ዳኘዉ መሪነት በዘመኑ የወንድ የሴት አርበኞች ብርታትና የተዋጣለት ቅንጅት ጣሊያንን ድል መንሳት ተችሏል፡፡ በትግረኛ ቋንቋ “ኢይጥዕሞ መዓር…” እንዲሉ የትግራይ ብሄርተኛ ልሂቃን በተለይም የህወሓት ሰዎች፤ የምኒልክና የዘመኑ ጀግኖች ድል አይጥማቸዉም፡፡ ነገሩ ጣማቸዉም አልጣማቸዉም ምኒልክ ከነሰብዓዊ ድክመቱ ዓምዳ ዉዳድ ለኢትዮጵያ (ለኢትዮጵያ መሰረትና ምሰሶ) ነዉ!!
ለመሆኑ አጼ ዮሃንስ ከምኒልክ የተሻለ መሪ ነበር? ታሪኩ ይህን አያረጋግጥም፡፡ የአጼ ዮሃንስ ለባዕድ ሥርዓት (ለእንግሊዝ) የማደግድግ ነገር ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነውና ይህን አንዘረዝርም፡፡ ከ1870-1875 ዓ.ም ድረስ በነበሩ ዓመታት አጼ ዮሃንስ በትግራይ፣ በወሎ፣ በዋጅራቱ፣ በራያና አዘቦ የሚኖሩትን ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች በሙሉ በግድ ኦርቶዶክስ ክርስትናን እንዲከቀበሉ “ሰማይ ዓምድ የለዉ፤ እስላም ሀገር የለዉ” የሚል አዋጅ አወጀ፡፡አዋጁ ግልጽ ነዉ፡፡ ክርስትናን ያልተቀበለ የመሬት ባለቤት ሊሆን አይገባም፤ በያኔዋ የኢትዮጵያ ግዛት ዉስጥም መኖር አይችልም ለማለት ነዉ፡፡ ቀሳዉስትን ከጦር ሠራዊቱ ጋር ይዞ የዘመተዉ አጼ ዮሃንስ፤ በጊዜዉ ያደረሰዉን አጠቃላይ ክስተት በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ የሚገኘዉ “ታሪከ ነገሥት” እንዲህ ይተርክልናል “መከራዉን የፈሩ እስላሞች በልባቸዉ ሳያምኑ ባፋቸዉ ብቻ ‹አምነናል› እያሉ ተጠመቁ፡፡ ሥጋ ወደሙ ከተቀበሉ በኋላ በስዉር ካፋቸዉ እያወጡ እስከ መጣል ደረሱ፡፡ መከራዉን ያልፈሩት እስላሞች ግን ‹ክርስቲያን ከመሆን ሞት ይሻለናል› እያሉ እኩሉ በሞተ፣ እኩሉም በእስራት፣ እኩሉም በመወረስ፣ እኩሉም ካገር እየወጡ በመሰደድ ተቀጡ (ታሪከ ነገሥት፤ገጽ 75 ላይ ይመልከቱ)”፡፡
ከዚህ የማይፋቅ የታሪክ ማስረጃ እንደምንረዳዉ አጼ ዮሃንስ በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ የከፋ ቅጣት ማድረሱን ነዉ፡፡ የአጼዉ የኃይማኖት ፖሊሲ ጸረ-እስልምና እንደነበር ለንግስት ቪክቶሪያ በላከላት ደብዳቤ ላይ በግልጽ አስቀምጦታል “ባገሬ አዘቦ የሚባል የኦሮሞ እስላም አገር አለ፡፡ ከርሱ ሽፍታ ተነሳብኝ፡፡ እርሱን ለማጥፋት ዘመትሁ፡፡እርሱንም በእግዚአብሔር ኃይል አጠፋሁት” ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ በተፈራረቁ ነገስታት እንደተበደሉ የማይካድ እዉነታ ነዉ፡፡ የአጼ ዮሃንስን ያህል ያስጨነቃቸዉ ንጉሥ ግን ከቶዉንም ያለ አይመስልም፡፡ በሀበሻ ምድር ሙስሊሞችን ብቻ እየለየ እንዲያሳድድ ተፈቶ የተለቀቀ እብድ ዉሻ ይመስል የወሎ ሙስሊሞችን እንዲህ አራቆቷቸዋል “(አጼ ዮሃንስ) አልጠመቅም ያለዉን እስላም ወሎ ከረሙ፡፡ ከእስላም ወገን በኃይማኖቱ የጸናዉና ጉልበት ያለዉ ወደ መተማ እየተሰደደ ከድርቡሽ ጋር ተደባለቀ፡፡ እኩሉም ወደ ሐረርና ቀቤና፣ ወደ ጅማ ተሰደደ፡፡ በዚሁም ምክንያት በያዉራጃዉ ሁሉ ሽፍታ ብቻ ሆነ፡፡ በየጅረቱም ሁሉ መጋደልና የሰዉ ደም መፍሰስ ሆነ (ታሪከ ነገሥት፤ ገጽ 60)”፡፡
የአጼ ዮሃንስ የከረረ የኃይማኖት ፖሊሲ መነሻዉ ግልጽ ይመስላል፡፡ የአጼዉ መሰረት ትግራይ ነዉ፡፡ በትግራይ ዉስን የሠራዊት ኃይል የጊዜዋን ኢትዮጵያ ማስከበር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ወዲህም ለአጼ ቴዎድሮስ የዉድቀት መፋጠን የካህናቱ እጅ እንዳለበት ተረድቷል፤ ኃይማኖታዊ ፖሊሲዉን ተከትሎ ከአዉሮፓ መንግሥታት የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደሚያገኝ አስቦ ነበር፡፡ (ለንግስት ቪክቶሪያና ለንጉሥ ዊልያም አራተኛ እንዲሁም ለፈረንሳይ መንግስት የላከቸውን የደብዳቤ ይዘቶች ያጤኗል) በዉጤቱ ግን ዛሬም ድረስ በዞረ ድምር የታሪክ ቅራኔ ቁስል ያልሻረ የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ቂምና መሃዲስቶችን በተቀላቀሉ ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች ትብብር መተማ ላይ በተካሄደዉ ጦርነት የንጉሠ ነገሥትነት ዘመኑን አሳጠረ፡፡ አልፎ ተርፎም የጎንደርና አካባቢዉ ህዝብና ታሪካዊ ቅርሶች ወደሙ፡፡
አጼ ዮሃንስ የጎጃሙን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከምኒልክ ጋር አደመብኝ በሚል ለራሱ እንኳን ኋላ ላይ ሲያስበዉ የዘገነነዉን እልቂት በጎጃም ገበሬዎች ላይ ፈጽሟል፡፡ አጼ ዮሃንስ የቅጣት ሰይፉን መዞ ፊቱን ወደ ጎጃም ሲያዞር የጎጃም ገበሬዎች፡-
“በላይኛዉ ጌታ በባልንጀራዎ
በቅዱስ ሚካኤል በባልንጀራዎ
በጽላተ ሙሴ በነጭ አበዛዎ
ጎጃምን ይማሩት ፈሪም አንልዎ”
የሚል ተማጽኖ ቢያሰሙም ከመዐቱ አልተረፉም፡፡ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ “አጤ ምኒልክ” በሚለዉ መጽሃፉ “የትግሬ ወታደር ቄሱን ተበተስኪያን፣ ገበሬዉን ከዱሩ፣ ነጋዴዉን ተመደብሩ እያወጣ ጨረሰዉ (ገጽ፣ 54)”፤ “ጎጃምን የመሰለ ደግ አገርም ሦስት ወር ሙሉ በትግሬ አንበጣ ተደመደመ” (ገጽ፣52) በሚል በወቅቱ የደረሰዉን እልቂትና ዉድመት ይገልጸዋል፡፡ አጼ ዮሃንስ ለራስ ዳርጌ በጻፈዉ ደብዳቤ “በእኔም በድሃዉም ኃጢአት እንደሆን አይታወቅም አገሩን (ጎጃምን) ሳጠፋ ከረምሁ” (ኀሩይ ወልደ ሥላሴ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ከሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል፤ ገጽ 179 ይመልከቱ) በማለት ጸጸቱን ይገልጻል፡፡
በኢትዮጵያ የነገሥታት ታሪክ በተለይም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ሂደት ወስጥ ብዙ ሰብዓዊ ጥፋት እንደደረሰ መካድ አይቻልም፡፡ ነገሥታቱ ከሰብዓዊነት አኳያ “አለማወቅ” የሚባል ሰብዓዊ ጉድለት እንደነበረባቸዉ “ፍትሐ ነገስት”ን በማስታወስ መረዳት አይከብድም፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የነገሥታቱ ሠራዊት ይህ ነዉ የሚባል ቋሚ ደመወዝ የሌለዉ በመሆኑ ዘመቻ በወጡ ቁጥር ቅጥ ካጣ ጭካኔቸዉ ጋር የገበሬዉን ንብረት መዝረፍና ማዉደም የሰርክ ተግባራቸዉ ነበር፡፡ በዚህ መሰል አሰቃቂ ሂደት የተጨፈለቁ የማህበረሰብ ክፍሎች፤ ጉዳት የደረሰባቸዉ ወገኖች መኖራቸዉ እሙን ነዉ፡፡ እንደዚህ ባሉ ዘመቻዎች የቀደሙትን ነገሥታት ገትተን የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራትች አባቶች የሆኑት የቴዎድሮስ፣ የዮሃንስ እና የምኒልክ ሠራዊት በተፈራራቂነት በገባራቸዉ ላይ ጥፋት አድርሰዋል፡፡ በጊዜ ሂደት መጠኑ እየቀነሰ ቢሄድም ገባሮቹ በባርነት ተፈንግለዋል፡፡ መሬታቸዉንም ተነጥቀዋል፡፡ ባህላዊና ሰብዓዊ ክብራቸዉ የተረገጡም አሉ፡፡ ትልቁ ቁም ነገር የዚህን ሁሉ ግፍ መደባዊ ይዘት መረዳቱ ላይ ነዉ፡፡
ታሪክን ገልብጦ ማንበብ የሚቀላቸዉ የህወሓት ሰዎች በዘመናዊት ኢትዮጵያ ዉስጥ የአገር ምስረታ ሂደት ዉስጥ የደረሱ ጥፋቶችን ከአንድ ቋንቋ ተናጋሪ በዳይነት (አማራ) ጋር ብቻ ለማያያዝና ቂምን ወደ ትዉልድ ለማሻገር ሥርዓተ-ትምህርት ከመቀየር ሐዉልት እስከ መስራት ድረስ የዘለቀ እኩይ ድርጊት ላይ ተጠምደዋል፡፡ በዉጤቱም አገራዊ የጋራ ማንነቶችን (የጋራ ጸጋና መከራዎቻችን፤ ድልና ሽንፈቶቻችን) እየጠፉ አካባቢያዊ ማንነት አለቅጥ ተወጥሯል፡፡ እንዲህ ያለዉ አዝማሚያ መጨረሻዉ አገር በመበተን የሚቆም ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ሁኔታችን ለርስ በርስ ጦርነት የቀረበ ሆኗል፡፡
በአገራችን የፖለቲካ ባህል በአሳዛኝ መልኩ እየበረታ የመጣ ክፉ በሽታ አለ፡፡ እርሱም ኃላፊነት መዉሰድ አለመቻል፡፡ ይህ ክፉ ልማድ ከ1960ዎቹ ትዉልድ የጀመረ ቢሆንም በድህረ-ደርግ በአደባባይ ዘዉጋዊ ልባስ አግኝቶ ማንነትን የታከከ ታሪክ ትርጓሜ ተንተርሶ አገሪቷን ወደ ብተናና እልቂት እየገፋት ይገኛል፡፡ ይህ ጉዳይ ዛሬ ላይ ከቁጥጥራቸዉ ቢወጣም የህወሓት ሰዎች በተጠና መልኩ ሲተገብሩት የኖሩት ጉዳይ ነዉ፡፡
ለህወሓት ሰዎች ታሪክ ትምህርት ሳይሆን ፍርድ ቤት ነዉ፤ አንዱን ንጉሥ ኮንነዉ ሌላዉን የሚያጸድቁበት፡፡ ከሦስት አመት በፊት የአጼ ምኒልክ 100ኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ ቀን የትኛዉም ዩኒቨርስቲም ሆነ እንደ ባህልና ቱሪዝም ያሉ መንግስታዊ ተቋማት በአገር አቀፍ ደረጃ ሳያከብሩት አልፏል፡፡ አሳፋሪዉ ነገር “የኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር”ም የገዥዎችን ቁጣ ፈርቶ ዝምታን መርጦ ማለፉ ነበር፡፡ በጊዜዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን (እንደ ሥርዓቷ) ሰማያዊ ፓርቲ በየግላቸዉ አቅማቸዉ በፈቀደ መጠን አክብረዉት ነበር፡፡ በአንጻሩ መጋቢት 2/2009ዓ.ም የትግራይ ክልል ደራሲያን ማህበርና መቀሌ ዩኒቨርስቲ በመተባበር የአጼ ዮሃንስን 128ኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ በደመቀ መልኩ አክብረዉታል፡፡ ዮሃንስ ከነሰብዓዊ ጉድለቶቹ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበር፡፡ በተለያዩ አዉደ ዉጊያዎች ከዉጭ ወራሪ ኃይሎች ጋር በጀግንነት ተፋልሟል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ደንበር ላይ የተዋደቀ ብቸኛዉ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነዉ!! በዚህና መሰል ጉዳዮች ታሪክ ከነድል-ሽንፈቶቹ ሲያሥታዉሰዉ ይኖራል፡፡ጥያቄው ለዮሃንስ የተሰጠዉ ክብር ለምኒልክ ሲሆን ለምን ይነፈጋል? የህወሓትና አክራሪ የትግራይ ብሄርተኞች ዮሐንስ የፈጸመዉን ሰብዓዊ ጥፋት ወደ ጎን ትተዉ በታሪክ ፍርዳቸዉ ነጻ ሊያወጡ ሲሞክሩ፤ ስለ ምኒልክ ለምን የብዜትና ፈጠራ ታሪኮችን በፖለቲካ ርግማን መልኩ ሲያዘንቡ ይታያል? ዮሃንስ በፈጸመዉ ጭፍጨፋ ታሪክ ነጻ ካወጣዉ ምኒልክንስ ታሪክ ስለምን ይኮንነዋል?
ለዚህ ነዉ ለህወሓት ሰዎች ታሪክ ትምህርት ሳይሆን ፍርድ ቤት ነዉ የምንለዉ፡፡ ዮሃንስን ከፍ አድርጎ ምኒልክ ላይ የፖለቲካ ርግማን የሚያወርድ የመቀሌ ችሎት!! በመስመር መሀል የትግራይ የአካዳሚያ ልሂቃን፣ ህዝባዊ የታሪክ ጸሃፍት፤ የ“አረና ፓርቲ አመራሮች” እና ብዙሃኑ የትግራይ ወጣቶች የመቀሌዉ የታሪክ ፍርድ ችሎት አጨብጫቢዎች መሆናቸዉን ስንታዘብ አድዋን የሚያህል ወታደራዊ ድል ስለምን ወደ ፖለቲካዊ ድል መቀየር እንደተሳነን ይገለጽልናል፡፡
የከረረ ዘዉጌ ብሄርተኝነት የክፉ ዉሾች ጉሮኖ ነዉ፡፡ ከታሪክ ዝንባሌ የመነጨ ሲሆን ደግሞ የአሳሞች ጋጥ ይሆናል (የጆርጅ ኦርዌል፤ Animal farm ላይ ያሉትን አሳማዎች ያስታዉሷል) አገራዊ ጅግኖቻችን እያወረድን ዘዉጋዊ ጀግና ማድረጋችንን ከቀጠልን የአድዋ ድል መንፈስ ፍጹም እየራቀን እንጅ እየቀረበን ሊመጣ አይችልም!!
(በቀጣይ ዕትማችን ከአድዋ ድል በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ ከአዲሱ የአማራ ዘዉጌ ብሄርተኛ ቡድን ላይ የታዘብናቸዉን እና የጽሁፉን ማጠቃለያ እናቀርባለን)
አድዋን ወደ ፖለቲካ ድል መቀየር ለምን ተሳነን? እርግማን ሦስት “ምኒልክ የእኛ ነው”

ከዝግጅት ክፍሉ:- “አድዋን የሚያህል ወታደራዊ ድል ስለምን ወደ ፖለቲካዊ ድል መቀየር ተሳነን?” በሚል ርዕስ ተከታታ ጽሁፎች ስናትም ሰንብተናል፡፡ የመጀመሪያው ክፍል ሙሉ ጽሁፍ እዚህ ላይ ይገኛል፡፡ እርግማን ሁለት “ሚኒልክ ኤርትራን ሸጠ፤ ትግራይን በደለ” የሚለው ሁለተኛው ክፍል ደግሞ እዚህ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ በሦስተኛው ክፍል የመጨረሻውንና ማጠቃለያውን ይዘን ቀርበናል፡፡
አፄ ምኒልክ ባልዋለበት ማዋል የዘመናችን “ፖለቲከኞች” ከታሪክ የሚያገኙት ግብር – አልባ ትርፍ ሆኗል፡፡ የአፄውን አገር የማቅናትና የግዛት አንድነትን የማስከበር ዘመቻ በ“ቅኝ ግዛት” የሚተረጉሙት እንዳሉ ሁሉ የማዕከላዊ መንግስት መቀመጫ ከትግራይ ወደ ሸዋ በመዞሩ ምኒልክን “ባንዳ” እና “አገር ሻጭ” እያሉ የአባቶቻቸውን ዝንፈት በአደባባይ ምኒልክ ላይ የሚለጥፉ ብልጣብልጥ “ፖለቲከኞች” ተበራክተዋል፡፡ በዚህ መሀል የእልህ – እልህ ፖለቲከኞች መገለጫ የሆነ አሳዛኝ ክስተት እየታየ ነው፡፡ እሱም “ምኒልክ የእኛ ነው” የሚሉ ደረቅ “ፖለቲከኞች” አደባባዩን ተቀላቅለዋል፡፡
በምኒልክ ላይ የሚወርደውን ፖለቲካዊ እርግማን “እንከላከላለን” የሚሉ ወገኖች “ምኒልክ የኛ ነው” ሲሉ እየተስተዋለ ነው፡፡ የአድዋ ድል በዘውግ ደረጃ ተቧድኖ ማክበር፤ ምኒልክንም ሆነ በርሱ ዘመን የተከወኑ ዘመን ተሻጋሪ ድሎች በተቧዳኙ ዘውጋዊ ማንነት ብቻ ለመቀንበብ በሚደረግ ጥረት ሊተረጎም ይችላል፡፡
ይበልጥ ግልጽ ለመሆን ያህል … “ምኒልክን” መርገም ዘውግ ተኮር የፖለቲካ ጥቅም አለው ብለው የሚያምኑ የኦሮሞና የትግራይ ጠርዘኛ ዘውጌ ብሄርተኞች አሉ፡፡ በአንፃሩ ምኒልክን እንደፍፁም መሲህ አድርጎ የሚያየው አዲሱ የአማራ ዘውግ ተኮር ስብስብ አለ፡፡ እነዚህ ጠርዝ የታከኩ አመለካከቶች የራሳቸውን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማሳካት የሚኳትኑ ቡድኖች ናቸው፡፡ አፄውን አብዝቶ በመርገም እና መሲህነቱን በማጎን ታሪክን የተንተራሰ ዘውጋዊ ንቃት መፍጠር የእንቅስቃሴዎቻቸው መገለጫዎች ናቸው፡፡
የአማራ ዘውጌ ብሄርተኝነት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ፍጹም አዲስ ክስተት ነው፡፡ መአህድ በህወሕት ጫና፣ ከኘ/ር አስራት በኋላ በነበሩ አመራሮች ድክመት፣ በዘውግ ማንነትና በአገራዊ ማንነት ግጭቶች የተነሳና በሌሎችም ምክንያቶች በፖለቲካው ሜዳ ላይ ከከሰመ በኋላ የአማራ ልሂቃን በህብረት ብሄራዊ ፓርቲዎች ዙሪያ በመስብሰብ ከእስር እስከ ህይወት ዋጋ የተፈራረቀ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ በነዚህ ጊዜያት ታሪክን የታከለ የዘውግ ውርክቦች ቢፈጠሩም “ምኒልክ የኛ ነው” በሚል በዘውግ ደረጃ በመቧደን የአድዋን ድል ያከበረ የፖለቲካ ኃይል ሲቪክ ማህበር፣ የኮሚኒቲ (ዘውጋዊ) ማህበር፣ … ጨርሶ አልነበረም፡፡
ዛሬ ላይ ፍፁም ባልተለመደ መልኩ የአማራ ዘውጌ ብሄርተኝነት አራማጆች፤ የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በዘውግ ደረጃ በመቧደን በመለስተኛ አዳራሽ (በስዊትዘርላንድ ሎዛን ከተማ)፣ በፓልቶክ፣ በፌስ ቡክ፣ መጠነኛ ስርጭት ሞገድ ባላቸው ሬዲዮ ኘሮግራሞች፣ … ሲያከብሩ ተስተውለዋል፡፡ የአድዋ ድል መታሰቢያ በአልንም ሆነ የምኒልክን ዘመን ተሻጋሪ ውርሶች ማክበር የሚያስመሰግንና ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡ ችግሩ ያለው እንዲህ ያለ አገራዊነትን ተሻግሮ የአፍሪካ ኩራት የሆነን በዓልና የድሉን መሪ አባ ዳኘው – ምኒሊክን በዘውግ ደረጃ ወርዶ ማክበሩ ላይ ነው፡፡ ስለ አፄ ምኒልክም ሆነ ስለ አድዋ ድል እንደ አገር አንጂ እንደዘውግ ተቧድኖ ማውራት በዓሉንም ማክበር የአባቶቻችንን የህብረት ድል በማፍረስ የሚበየን እልፍ ሲልም በክህደት የታጀበ የታሪክ ድኩማንነት ነው፡፡ አባቶቻችን ወደውና ፈቅደው አገራዊ ጀግና ሆነው አልፈዋል፡፡ እኛ ግን ከአገራዊ ጀግንነታቸው ጎተተን በማውረድ ዘውጋዊ ጀግና ለማድረግ ስንጣጣር እንገኛለን፡፡ ከዚህም በላይ የታሪክ ኑፋቄ ከቶ ከወዴት አለ? በታሪካችን ውስጥ ህብረትና በጎ መንፈስ እንዳናይ አገራዊ ዕጣ ፈንታችን ቀይዶ የያዘን ይመስል የታሪክ ገመድ ጉተታ ውስጥ መግባታችን አሳዛኝ ነገር ነው፡፡
አፄ ምኒልክ ከነጉድለቱ ዘመን ተሻጋሪ ውርሶች ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ጥሎ አልፏል፡፡ የዛሬዋ ኢትዮጵያ መልከዓ ምድራዊ ቅርጽ ከሞላ ጎደል የአፄው የንግሥና ዘመን ውጤት ናት፡፡ የአድዋ ድል የአባቶቻችን የመደማመጥና የመተባበር ውጤት ነው፡፡ ምኒልክን አልባ የአድዋን ድል ማስመዝገብ ይቻል (ይሆን) ነበር ብሎ ማመን ይቻላል፡፡ ይሁንና በታሪክ የምናውቀውን የአድዋን ድል ያለ ምኒልክ ማሰብ ክርስትናን ያለ ክርስቶስ፣ እስልምናን ያለ ነብዩ መሐመድ እንደማሰብ ያለ ቅዥት ነው፡፡ ይህ የታሪክ ሀቅ የማይዋጣላቸው ዝግና የተመረጠ የታሪክ ግንዛቤ ያላቸው ዘውጌ ብሔርተኞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አሁንም ቢሆን ማንነትን የታከከ የታሪክ ትርጓሜ እስካልቀረ ድረስ ይህ አይነት ምልከታ መቀጠሉ ጭራሹኑ እየሰፋ መሄዱ የት ይቀራል?
በምኒልክ የንግስና ዘመን ለተመዘገቡ ዘመን ተሻጋሪ ውርሶች፤ ዋልታና ማገር የነበሩ አባቶችን ውለታ መርሳት የሚቻል አይደለም፡፡ ራስ ጎበና ዳጬ፣ ደጃች ባልቻ ሳፎ፣ ፊትአውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ራስ መኮንን ወ/ሚካኤል ጉዲሳ፣ ራስ ዳርጌ፣ ራስ ወልደገብርኤል፣ ራስ መንገሻ አንቲከም … እያልን ከምንዘረዝራቸው ታላላቅ የጦር አበጋዞች ውስጥ ከኦሮሞና ከደቡብ የተዉጣጡ የአገር ምስረታ የፊት መስመር ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ እንደ ራስ ጎበና ዳጬ ያለ ጀግና የጦር አበጋዝ ሰባት ግዛቶችን (የደቡብና የምዕራቡን) የኢትዮጵያ አካል ማድረግ ችሏል፡፡
ዛሬ ላይ “ምኒልክ የእኛ ነው” የሚሉትን የአማራ ዘውጌ ብሔርተኞች የምኒልክ ብርቱ ቀኝ እጅ የነበሩት የጦር አበጋዞች ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት የደከሙትን ድካም፣ የከፈሉትን ዋጋ ከዚህ አንጻር በአደባባይ እየካዱ መሆኑን ይሰመርበት፡፡
አድዋ የአባቶቻችን የመደማመጥና የመከባበር ውጤት ነው ካልን በምን አግባብ በዘውግ ደረጃ ወርደን አድዋን በችርቻሮ እናከብረዋለን? ከእያንዳንዱ የአባ ዳኘው ምኒልክ ስኬታማ ተግባር ጀርባ የጦር አበጋዞች አሻራ አለበት፡፡ አፄው ያለ ጦር አበጋዞች ድጋፍ ኢትዮጵያን መመስረት አይሳካለትም ነበር፡፡
ለአፄ ዮሐንስ ውድቀት አንዱ ማሳያ የብርቱ ጦር አበጋዞች ድርቀት እንደሆነ ይስተዋል? አንድ ራስ አሉላ እንግዳ (አባ ነጋ) ከስንቱ ጦር አውድማ ይደርስለት? (ራስ መንገሻን ረስተን አይደለም በዮሐንስ ጊዜ እዚህ ግባ የሚባል መሪ አልነበረም፤ ኋላም ለባዕድ ስርዓት የማደግደግ ተደጋጋሚ ባህሪ የታየበት ሰዉ ነበር) የአፄ ዮሐንስ አቅመ ቢስነት የምኒልክ ጉልበታምነት ምስጢር ግልጽ ነው፡፡ ቀዳሚው አባ በዝብዝ የጦር አበጋዞች ድርቅ ነበረበት፤ ተከታዩ አባ ዳኘው ደግሞ ግራ ቀኙን ብርቱ ተፋላሚ ራሶች ነበሩት፡፡ ያዉም “ከአንተ በፊት እኛ እንወድቃለን” የሚሉት!!
በጠመዝማዛው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የምኒልክ እና የጦር አበጋዞች ድካም ለአገር አንድነትና ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ምስረታ የተከፈለ ዋጋ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ውህድ ህላዌ መሀንዲስ አባ ዳኝው በንግሥና ዘመኑ ራሱን እንደ አንድ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ንጉሠ ነገሥት እንጂ እንደ አንድ የ“አማራ” ንጉሠ ነገሥት አድርጎ አስቦ አያውቅም፡፡ የምኒልክን ኦርቶዶክስ ክርስቲያናዊ ንጉሠ ነገሥትነት ማብራራት አስፈላጊ አይደለም፡፡ አደባባይ ላይ የተሰጣ እውነት ነውና፡፡ ይሁንና ንጉሠ ነገሥቱ ሌሎችንም ሀይማኖቶች ባለመጋፋት “ባለህበት እደር” የሚል አዋጅ እንዳወጣ ይታወቃል፡፡
አፄ ምኒልክን በዘውግ ደረጃ ጎትቶ ማውረድና “ምኒልክ የእኛ ነው” በሚል ቃና፤ በተአብዮ ተሞልቶ በየፓልቶኩ መመጻደቅ የታሪክ ክህደት እንጂ አዋቂነት አይደለም፡፡ የነገሩ ምጸት እነዚህ ሰዎች በየማህበራዊ ሚዲያ “አላማችን በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ የአማራ መንግስት መመስረት ነው” ሲሉ የከረሙ መሆናቸው ነው፡፡ አባ ዳኘው ምኒልክና “አባት አገር አማራ” ምንና ምን ናቸው? ለየቅል!!
በመሰረቱ ከሆነ የምኒሊክ ቀዳሚ ማህበራዊ መሰረት ሸዋ ነው፡፡ ሸዋ ደግሞ የዘመናችን ሰዎች በዘውግ ተከል ፌዴራሊዝም ቀንብበው እንደሚነገሩን ሳይሆን፤ ሸዋ የኦርቶዶክ ክርስትና እና የቱለማ ኦሮሞ የማህበረ ኢኮኖሚያዊ ውህድ ውጤት የወለደዉ የወል ማንነት ነው፡፡ ይሄ የወል ማንነት በተለየ መልኩ በላይኛው መደብ ጋብቻን (በርግጥ ጭሰኛዉ መደብም አምቻ ጋብቻ ተፈጥሯል) መሰረት በማድረግ በጊዜ ሂደት ወደ ገዥ ኃይልነት እያደገ የመጣ የገዥ መደብ መሰረት ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል የሸዋ ኦሮሞ ዉስጥ በሂደት እንደ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ ጳጳሳት፣ ቀሳዉስትና ዲያቆናት የወጡት፡፡ የዉህዱ (የቱለማ ኦሮሞና የኦርቶዶክስ ክርስትና) ዉጤት ይመስላል ይህ ዘመናትን ያካለለ የውህድ ሂደት በምኒልክ ጊዜ ይበልጥ ጠንክሯል፡፡
ከብዙ ማሳያዎች አንድ ለመንገድ… የራስ ጐበና ዳጬ ልጅ ወዳጆ ጐበና የምኒልኳን ሸዋረገድን አገባ፤ በውጤቱም ወሰንሰገድ የተባለ ልጅ ተወለደ፡፡ ይህ ልጅ በአሥራ አራት አመቱ ባይቀጭ የምኒልክ አልጋ ወራሽ ይሆን ነበር፡፡ በዚህ አግባብ ምኒልክ ለጐጃም ሰው ሳይሆን ለቱለማ ኦሮሞ ይቀርባል፡፡ ከበጌምድር ሰው ይልቅ የሸዋ ኦሮሞ የምኒልክ የመጀመሪያ የንግስና ዘመናት የኃይል ምንጭ ሆኖ አገልግሏል፡፡ የመንዝም ሆነ የየጁ ገበሬ ለምኒልክ ገባር ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡
ስለ “አባት አገር አማራ” እያለሙ “ምኒሊክ የእኛ ነው” ማለት በዚያኛው ጽንፍ ምኒልክ ላይ የፖለቲካ እርግማን ከሚያዘንቡ የታሪክ ኑፋቄ ዘውጌ ብሄረተኞች ድርጊት በምን ይለያል? በምንም! ለአንድም ኃልዮታዊ ትንታኔ አልመች ብሎ ባለው የኢትዮጵያ ዘውጋዊ ክፍፍል የፖለቲካ ትርምስ ውስጥ ራሱን ለማቅናት የሚውተረተረው የአማራ ዘውጌ አኳያም እንደ “ወደረኞቹ” ሲፈጠፈጥ እየታዘብን ነው፡፡
ደግነቱ አማራ ክፍለሀገራዊ (አካባቢያዊ) ማንነቱን ጠብቆ ከኢትዮጵያዊነት ወርድና ቁመት የማይጠብ የማይሰፋ ክቡድ ህዝብ ነው፡፡ ፖለቲካዊ መብቃት ላይ ያልደረሱት የሳይበር አርበኞች እና ደቃቅ “ፖለቲከኞች” ግን ሳይነሱ መውደቅ የመጀመራቸውን ምስጢር ከአባዳኘውና ጓዶቹ የታሪክ ግርጌ ስር ቢፈልጉት መልሱን ያገኙት ነበር፡፡ ሌሎች የጉርምስና ሐተታ አነብናቢ ዘውጌ ብሄርተኞችም የአባቶቻቸውን አሻራ ያረፈበትን የምኒልክ ዘመን ተሻጋሪ ውርሶች ዝቅ ብለው ቢፈልጉ ለመፍትሔው (ለጋራ ነፃነት) ይቀርቡ ነበር፡፡
እንደ መውጫ
የትኛውም የታሪክ ትንተናና ፅሁፍ ዘላለማዊ እውነት የለውም፡፡ አዳዲስና አስተማማኝ መረጃዎች ሲገኙ በመረጃው መሰረት እንዲስተካከል ከቶውንም እንዲለወጥ ማድረግ ይቻላል፡፡ በታሪክ ያለቀለት ፍፁም እውነት የሚባል ነገር የለም፡፡ ታሪክ ሁልግዜም ቢሆን አንፃራዊ እውነት ነው፡፡ በዚህ አግባብ የኢትዮጵያ አገራዊነት ታሪክ ተፃራሪ ትርጓሜዎችን (“የብሄር ጭቆና” Vs “መደባዊ ጭቆና”) በሙያው (ታሪክ) መስፈርት ተቀባይነት ባላቸው (አፈ-ታሪክን በተሻገሩ) የታሪክ ማስረጃዎች እየተመዘኑ ወደ አደባባይ እንዲወጡ ማድረግ ይቻላል፡፡
ይህን አካዳሚያዊ ፅንሰ ሐሳብ በቅጡ በተጠና ሥርዓተ-ትምህርት በመደገፍ ታሪካችን የወደፊት እርምጃችን አካል እንዲሆን ማድረግ ኃላፊነት ከሚሰማው “መንግስት” የሚጠበቅ ተግባር ነበር፡፡ እንደአለመታደል ሆኖ የህወሃት አፈጣጠር እንዲህ ላለው ነፃ የአካዳሚ መስመር ተፃራሪ ኃይል ነው፡፡ በረኽኞች ጥልቅ በሆነ የትላንት ድምሰሳ የሚያምኑ በመሆኑ ታሪክን በጠባቡ በማየት ከፖለቲካ ሥልጣን ጋር ማቆራኘት ምርጫቸው አድርገውታል፡፡
የትላንት ድምሰሳቸውን ለማጠናከር ይረዳ ዘንድ የታሪክ ትምህርትን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ኮሌጆች ዩኒቨርሲቲዎች) በመርሐ-ግብር ደረጃ እያሰናበቱት ነው፡፡ በውጤቱም ታሪክን ከእውነታው ጋር ለአገራዊ ግንባታ ማዋል ቀርቶ፤ በሰነድ የተደገፈ ምክንያታዊነቱ መንምኖ ለዘውግ ፖለቲካ መቀሰቻ የሆነ መፈክራዊ ጩኽት የበዛበት የፕሮፓጋንዳ መድረክ ሆኗል፡፡
በአካባቢያዊ ማንነት የታጠረው (የተመረጠ) የታሪክ ግንዛቤያችን ዓለምአቀፋዊ ሰዎች እየተፈጠሩ ባለባት አለም ራሳችንን ነጥለን በአካባቢያዊ ማንነት በመታጠር ዘውጋዊ ትውልድ ለመፍጠር የሚደረገው መሯሯጥ ኢትዮጵያንና ትውልዷን በተረገመ የታሪክ ዘመን ውስጥ እንድታልፍ አስገድዷል፡፡ አድዋን የሚያህል ታላቅ የነፃነት መንፈስ ለማንቋሸሽ የተያዘው ሩጫ የዛሬዋንም ሆነ የነገዋን ኢትዮጵያ የትውልዶች መከራ ከማባባስ ያለፈ አንዳች ፋይዳ የለውም፡፡
አድዋን የሚዘክር አንድ ብሔራዊ ሙዚየም መስራት ያቃተው አገዛዝ ቂምን ለትውልድ እነሆ እያለ በየአካባቢው ለትውልድ ዕዳ የሚሆኑ ሐውልቶችን ይሰራል፡፡ የኃይማኖት አስተምህሮት ያህል ልዕልናን ተጐናፅፎ ያለው ዘውጌ ብሄርተኝነት ታሪክን ማገዶው በማድረግ ትውልዱን በተሳሳተ የታሪክ ወንዝ ጭልጥ ወዳለ ገደል እየመራው ይገኛል፡፡
ትውልዱ በታሪክ ትርጓሜ የሚቀርብለትን መረጃ ይዞ የፈለገውን አቋም መያዝ መብቱ ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ ግን ለፖለቲካ ግባቸው ሲሉ በታሪክ ፊት ጥቁር መጋረጃ ጋርደው ትውልዱን በተሳሳተ የታሪክ ወንዝ እንዲፈስ ማድረጋቸው የጋራ ቤታችንን መሰረት እንደመናድ ይቆጠራል፡፡ ፍፁም መስመሩን የሳተ የታሪክ አረዳድ፤ የጥላቻና የበቀል ስሜት ማነሳሳት ለአገሪቷና ለህዝቧ ደህንነት አደጋው የከፋነው፡፡
የታሪክ አረዳድ ለብሔራዊ መግባባት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለች ጠመዝማዛ የታሪክ ጉዞ ባሳለፈች አገር ብሔራዊ መግባባት የለም ሲባል ዘርፎቹ ብዙ ናቸው፡፡ ከዘርፎቹ ውስጥ ግን ታሪክ ቀዳሚው ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ አገር ከዘመናዊት ኢትዮጵያ ምስረታ፤ አገር የማቀናት ዘመቻዎች ጋር ተያይዞ ከተፈጠሩ ችግሮችና ተንከባላይ የትውልድ ዕዳዎች ታጋች (hostage) ከመሆን ይልቅ መታረቅ አለብን፡፡ ምዕራባዊያን በሥልጣኔ ወደፊት መጓዛቸውን ያላቆሙበት ምስጢር ከታሪካቸው ጋር ስለ ታረቁ ነው፡፡
የታሪክ መሰረቶች ላይ የሚቆሙ ልዩነቶችን መሻገሪያው ብቸኛ መፍትሔ ታሪክን ለታሪክ ባለሙያዎች መተው ብቻና ብቻ ነው፡፡ ታሪክን ለታሪክ ባለሙያዎች መተው ከታሪካችን ጋር እንድንታረቅ ድልድይ ይሆነናል፡፡ ያኔ የኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉንም ዘውጐች (በሰሜን በደቡብ በምስራቅና በምዕራብ ያሉትን) እንዲያካልል ማድረግ ይቻላል፡፡ ታሪካችንም የ“እኛ” እና የ“እነርሱ” በሚል ሳይሆን ዜግነታዊ መሰረት ባለው መልኩ አካቶነት ያለው የጋራ ታሪክ ማንበብ ንችላለን፡፡ ይህ መንገድ . . . በደም የተዋጀው ቆይታችን በእኩልነት ስሜት አንድነታችን በፅኑ መሰረት እንዲቆም ያደርገዋል፡፡
በኢትዮጵያችን ምድር ይህ እንዲሆን ከተፈለገ የኢትዮጵያ የታሪክ ካንሰር የሆነውን ህውሃት ከፖለቲካ መድረኩ ነቅሎ መጣል ግድ ይላል፡፡ የትግል ጠረጴዛው ላይ ያሉት ምርጫዎች ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ወይ አብሮ መውደቅ አልያም በአንድነት መነሳት፡፡ በእስካሁኑ ጉዟችን የመጀመሪያውን ምርጫ የያዝን ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው አድዋን የሚያህል ወታደራዊ ድል ከውስጥ ችግራችን አኳያ ወደ ፖለቲካዊ ድል መቀየር የተሳነን፡፡ ሁለተኛውን ምርጫ (በአንድነት መነሳት) የያዝን ቀን የአድዋን ድል ወደ ፖለቲካዊ ድል በመቀየር በፍትህና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት መፍጠር እንችላለን፡፡ በርግጠኝነት ያኔ ታሪክ ትምህርት እንጂ ፍርድ ቤት አይሆንም!!
Source – ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
