22 Mar, 2017

ቃለየሱስ በቀለ

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት

የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር

በአዲስ አበባ የሚገኙ አሽከርካሪዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተከሰተ የነዳጅ እጥረት ምክንያት በየማደያው ረዥም የተሽከርካሪ ሠልፎች በመፈጠራቸው፣ ነዳጅ ለማግኘት መንገላታታቸውን ገለጹ፡፡

በመዲናዋ የሚገኙ ባለአውቶሞቢሎች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ቤንዚን ለመቅዳት የሥራ ሰዓታቸውን እያቃጠሉ በየማደያው ረዥም ሰዓት እያጠፉ ነው፡፡ ባለታክሲዎችም ሥራ ፈተው ቤንዚን ፍለጋ እንደሚንከራተቱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በነዳጅ አቅርቦት ላይ የተፈጠረ ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለ አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጀት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የድርጅቱ ኃላፊነት በየዓመቱ ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት ለአገሪቱ ነዳጅ ፍጆታ የሚውል የተለያዩ የነዳጅ ውጤቶች ገዝቶ ማስገባት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከውጭ በሚገባው ነዳጅ ላይ የተፈጠረ ምንም ዓይነት ችግር የለም፡፡ ‹‹ከጂቡቲና ከሱዳን ነዳጅ በአግባቡ እየገባ ነው፡፡ በዚህ በኩል ምንም የተፈጠረ ችግር የለም፤›› ብለዋል አቶ ታደሰ፡፡

የንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ የሚመለከተው የነዳጅ መሸጫ ታሪፍ ማውጣት ብቻ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

የነዳጅ ሥርጭት ቁጥጥር ሥልጣንና ኃላፊነት የተረከበው የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ችግሩ የተፈጠረው ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ የነበረውን ቤንዚን ከኤታኖል ጋር የማደባለቅ ሥራ እንደገና በመጀመሩ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የነዳጅ ተቋማት ደረጃ ማስጠበቅ ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ተክለ አብ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ተቋርጦ የነበረው 95 በመቶ ቤንዚን ከአምስት በመቶ ኤታኖል ጋር የማደባለቅ ሒደት መጋቢት 7 ቀን 2009 .. ተጀምሯል፡፡ የኤታኖል ማደባለቂያ ጣቢያ ያላቸው ኦይል ሊቢያ፣ ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) እና ናይል ፔትሮሊየም ሲሆኑ፣ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት ኦይል ሊቢያና ኖክ ናቸው፡፡ በተለይ የኦይል ሊቢያ ማደባለቂያ ጣቢያ ግዙፍ በመሆኑ ለቶታል ኢትዮጵያ፣ ለተባበሩት ፔትሮሊየምና ለሌሎችም ኩባንያዎች የተደባለቀ ቤንዚን ያቀርባል፡፡

‹‹በፊት ቤንዚን ከሱዳንና ከጂቡቲ በቦቴ ተጭኖ ከገባ በኋላ በቀጥታ ወደ ነዳጅ ማደያዎች ወይም የነዳጅ ኩባንያዎች ዴፖ ነበር የሚገባው፡፡ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ከኤታኖል ጋር ማደባለቅ ከተጀመረ በኋላ፣ ከጂቡቲና ከሱዳን የገባው ቤንዚን ቦቴዎች ወደ ማደባለቂያ ጣቢያ ገብተው አራግፈው ከኤታኖል ጋር ተደባልቆ እንደገና ጭነው ይወጣሉ፡፡ በዚህ መሀል የትራንስፖርት ማኔጅመንት የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው፤›› ብለዋል አቶ ኃይሉ፡፡

አቶ ኃይሉ እንደሚሉት ቤንዚን ከኤታኖል ጋር ማደባለቅ ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ ባለፈው ሳምንት እንደ አዲስ ሲጀመር በተፈጠረ የትራንስፖርት ቅንጀት ችግር፣ በነዳጅ ሥርጭቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ከዚህ ውጪ ከውጭ ተገዝቶ በሚገቡ የነዳጅ ውጤቶች ላይ የተፈጠረ እጥረት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

የተከሰተው ጊዜያዊ የትራንስፖርት ቅንጅት ችግር እንደሆነ የገለጹት አቶ ኃይሉ፣ ችግሩን ለመፍታት ከትራንስፖርተሮችና ከኤታኖል ማደባለቂያ ጣቢያ ባለቤት ኩባንያዎች ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከነዳጅ ኩባንያ ኃላፊዎች ጋር በቅርበት እየሠራን ነው፡፡ ትራንስፖርተሮችንም ስብሰባ ጠርተናል፤›› ያሉት አቶ ኃይሉ፣ ጉዳዩን ያባባሰው የተጠቃሚዎች የዋጋ ግምት (Speculation) እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገሯቸው የአንድ የነዳጅ ኩባንያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ችግሩ የተፈጠረው ባለፈው ሳምንት ኤታኖል ማደባለቅ ከተጀመረ በኋላ እንደሆነ ገልጸው፣ ኩባንያቸው ከበፊቱ የተሻለ መጠን ነዳጅ በየማደያው ቢያቀርብም ባልተለመደ ፍጥነት ነዳጁ እያለቀ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

      ‹‹ኩባንያችን ቤንዚን ለማደያዎች ቢያከፋፍልም አሁን ገልብጠን ወዲያው አለቀ እንባላለን፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አላወቅንም፡፡ ለእኛ ግን ሥራ አብዝቶብናል፤›› ብለዋል ኃላፊው፡፡

አቶ ኃይሉ ችግሩን ያባባሰው ተጠቃሚዎች ‹ነዳጅ ከነአካቴው ሊጠፋ ነው› በሚል ሥጋት ከሚያስፈልጋቸው በላይ በመቅዳት ላይ በመሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የነዳጅ እጥረት አለ የሚል ወሬ ሲሰማና አነስተኛ የመኪኖች ሠልፍ በየማደያው ሲታይ ሁሉም አሽከርካሪ ተሽቀዳድሞ ለከርሞ የሚሆነኝ በሚል አሥር ሊትር የሚቀዳው 30 ሊትር ይቀዳል፡፡ ሁሉም መኪናውን ሞልቶ ነው የሚወጣው፡፡ ይኼ ደግሞ የተራገፈው ነዳጅ በቶሎ እንዲያልቅ ያደርጋል፤›› ያሉት አቶ ኃይሉ፣ ሁኔታው በአጭር ጊዜ ውስጥ ይስተካከላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የሚደባልቁት ኩባንያዎች ሦስት ብቻ በመሆናቸው የአቅም ውስንነት እንዳለ የተጠየቁት አቶ ኃይሉ፣ በተለይ ኦይል ሊቢያ ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ የአቅም ችግር እንደሌለ ገልጸው ችግሩ የትራንስፖርት ቅንጅት እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡

በነዳጅ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ሌላው ያነሱት ችግር የነዳጅ ማደያዎች ቁጥር ማነስ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ710,000 በላይ ተሽከርካሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 70 በመቶ ወይም 400,000 ያህሉ አዲስ አበባ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለ400,000 ተሽከርካሪዎች አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙት የነዳጅ ማደያዎች ብዛት 100 ብቻ መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያዎች፣ አንድ ማደያ በአማካይ 4,000 ተሽከርካሪዎች እንደሚያስተናግድ ገልጸው የነዳጅ ማደያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰሞኑን ለተከሰተው ችግር መንስዔ ባይሆንም የነዳጅ ማደያዎች ቁጥር ማነስ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገሯቸው የነዳጅ ኩባንያዎች ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ አዳዲስ የነዳጅ ማደያዎች ለመገንባት ፍላጎት ቢኖራቸውም መሬት ማግኘት ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በመሬት ጉዳይ ከአዲስ አበባ መስተዳደር ጋር ብዙ ጊዜ የተነጋገርን ቢሆንም አሁንም መፍትሔ አልተበጀለትም፤›› ያሉ የአንድ የነዳጅ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ኩባንያዎች ከነዳጅ ሽያጭ የሚያገኙት የትርፍ ህዳግም አነስተኛ መሆን የነዳጅ ማደያዎች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ እንደማያበረታታ ገልጸዋል፡፡ 

የመሬት ዕጦትና የነዳጅ ሽያጭ የትርፍ ህዳግ ዝቅተኛ መሆን ለነዳጅ ማደያዎች ቁጥር ማነስ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ የኩባንያው ኃላፊ ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደርና የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡  

ዜና

ቃለየሱስ በቀለ‘s blog 

Author

anon

ቃለ