በተረጂዎች ስም የተሰበሰበው እንዲሁም ወደፊት የሚሰበሰበው ገንዘብ በተመለከት ግልጽ አሰራር ሊበጅለት ይገባል።

March 22, 2017 – 

የገንዘብ እርዳታና አሰባሰብ!

በተረጂዎች ስም የተሰበሰበው እንዲሁም ወደፊት የሚሰበሰበው ገንዘብ በተመለከት ግልጽ አሰራር ሊበጅለት ይገባል። ”
ይህ 1000199240971 ?! በቆሼ በሰው ሰራሽ በተለይ በመንግስት ቸልተኝነት ለደረሰው አደጋ ፣ ለወገኖቻችን በስማቸው የተከፈተ የገንዘብ ማስቀመጫ ቋት ነው። እንደሚገመተው ከሆነ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የማያንስ፣ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደተሰበሰበ እየተነገረ ነው።ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከለጋሾች ምን ያህል ገንዝብ እንደተሰበሰበ እስካሁን ኦፊሴላዊ ገለፃ አላደረገም ። በመሰረቱ በወገኖቻችን ላይ ለደረሰው ሰው ሰራሽ አደጋ ፣ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ የሚሆነው ፣ የእርከን ደረጃውን ታሳቢ በማድረግ ፤የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ተጠያቂ ነው የሚሆነው ። በዚሁም መሰረት በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ላጡ፣ ህይወታቸውን መመለስ ባይቻልም ለቤተሰቦቻቸው የህይወት ካሳ መክፈል ፣ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ተገቢውን ምትክ ካሳ የመክፈል ሙሉ ለሙሉ የህግ ግዴታ አለበት።
ወደተነሳውበት ዋና ጉዳይ ስገባ፤ በተረጂዎች ስም ስለተከፈተው 1000199240971 የገንዘብ ማሳባሰቢያ የተመለከተ ነው። ይህ ገንዘብ የሚሰበሰብበት የሂሳብ ቋት፣ በማን እንደሚንቀሳቀስ ? በምን መልኩ ለተረጂዎች እንደሚደርስ እስካሁን ግልጽ የሆነ አሰራር ሰለመኖሩ ከአስተዳደሩ ለህዝቡ በይፋ የተሰጠ መረጃ የለም። በተለይ በተጎጂዎች ስም በአይነት እና በገንዘብ እየተሰበሰበ ስላለው ነገር ተረጂዎችን ያሳተፈ መሆን አለበት ። ነገሩን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ከሁለት ቀን በፊት ለንባብ የበቁ ጋዜጣች ይዘውት የወጡት መረጃ በመመልከት ፣ በተረጂዎች ስም ገንዘብ እየተሰበሰበ ፣ ተረጂዎች ግን ጾማቸውን እንደሚያድሩ የሚያመላክት ነው።

ለምሳሌ ያህል እነዚህን ማሳያዎች እንመልከት ፦ “እኛ ዕኮ የምንኖረው ቆሻሻ ውስጥ ነው። ወይ ከዚህ ቦታ አንሱን ወይ ቆሼን አንሱልን እያልን ስንጮህ ኖረናል። ዛሬ ግን ስናልቅ መጣችሁ አይደል? ~ ( አስራ አንድ ቤተሰቦቿን በቆሼ አደጋ አጥታ ብቻዋን የቀረችው ወጣት ለወረዳው ባለስልጣናት የተናገረችው – ሪፖርተር ጋዜጣ መጋቢት 10/2009)። በተጨማሪ፣”ቤተሠብ ከሚያመጣልን ሻይና ዳቦ በስተቀር መንግስት ምንም እየረዳን አይደለም፣ ቤተሰቦቻችንን የለሊት ልብስና ብርድ ልብስ እንዲያመጡልን ስንነግራቸው ‘መንግስት እየረዳችሁ ነው እየተባለ አይደለም እንዴ?’ ይሉናል ፤ ግን ማንም የረዳን የለም።” ~(አንድ የቆሼ አደጋ ተጠቂ እናትአዲስ አድማስ ጋዜጣ መጋቢት 9/2009) ። እነዚህን እውነታወች ብዙ ነገር የሚያመላክቱ ናቸው። በመሆኑም ፣ ከላይ በተገለጸው የሂሳብ ቁጥር ማለትም (1000199240971) በተጎጂዎች ስም የተሰበሰበው እንዲሁም ወደፊት የሚሰበሰበው ገንዘብ በተመለከት ግልጽ አሰራር ሊበጅለት ይገባል። በኦፊሴላዊ ደረጃ ለሚሰበሰብ ገንዘብ ፣ገንዘብ እንዴት እና በነማን መንቀሳቀስ እንዳለበት በግልጽ መታወቅ አለበት። ተጎጂዎችን መነሻ በማድረግ ለሚከናወኑ ማናቸውም ነገር ፣ የተጎጂ ቤተሰብ ተወካዮች ፣ በህብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ግለሰቦች፣ እና ሌሎችን የማዕከል ልዩ ኮሚቴ ሊቋቋም ይገባል። ጉዳት የደረሰባቸውን መልሱ ለማቋቋም ግልጽነት ያለው ፣አሳታፊ የሆነ ሥራ ሲሰራ ብቻ ነው ችግሩን ለማቃለል የሚቻለው ።

ከአገር ቤት ውጪ ፣ በተለያየ ሃገር የሚገኙ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ! ለወገኖቻቸው ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት እጀግ በጣም የሚደነቅ ነው። የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እነሱም ባሉበት ቦታ ሆነው፣ ለወገኖቻቸው ለመድረስ ገንዘብ በተለያየ መንገድ እያሰባሰቡ ነው። እንዲህ አይነቱ መልካም ተግባር የሚደነቅ ነው። አስተዳደሩ በከፈተው የሂሳብ ቁጥር የሰበሰባቹትን ገንዘብ ለማስገባት ያላችውን ስጋት ወይም ጥርጣሬ በደንብ ነው የምረዳው፣ ይህም ስለሆነ ገንዘብን በተከፈተው የሂሳብ ቁጥር አስገብ ብዬ የምሰጠው ምን አይነት አሰተያየት የለኝም። ሆኖም ግን በተረጂዎች ስም የሚሰበሰበው ገንዘብ ለተረጂዎች በትክክል መድረስ አለበት፤በዚህም መሠረት የተሰበሰበው ገንዘብ ወደፊትም ለመሰብሰብ የታሰበ ገንዘብ ካላ፣ እንዴት እና በምን መልኩ መሆን አለበት ለሚለው ጥያቄ በቂ ዝግጅትና መልስ ሊኖራችሁ እንደሚገባ በአክብሮት ለመግለፅ እወዳለሁ ።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!

(ይድነቃቸው ከበደ)