የሀገራችን የቱሪዝም (የጉብኝት) ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት የቆየውን የድርጅቱን መሪቃልና ምልክት ለመቀየር ሲንቀሳቀስ ቆይቶ በቅርቡ መቀየሩ ይታወሳል፡፡ ለነገሩ ተነሣሽነቱ ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) መሆኑና ሥራ መሥራት ትተው ሥያሜን መቀያየር ትልቅና ዋና ሥራ ማድረጋቸው ከፋ እንጂ የነበረው የድርጅቱ መሪቃልና ምልክት የሀገሪቱን የጉብኝት መስሕቦችን የመወከልና የመግለጽ በጣም ውስንነት ስለነበረበት መቀየሩ ባልከፋ ነበረ፡፡

መሥሪያ ቤቱ ባለሞያዎችን አወዳድሬ ምልክትና መሪቃል ሠየምኩ!” ካለ ወራት ማስቆጠሩ ይታወቃል፡፡ ድርጅቱ መሪቃሉን ሲሠይም ቅድሚያ በራሳችን ቋንቋ ወይም በአማርኛ መሠየምና ያንንም ቃል ወደ እንግሊዝኛ መመለስ ሲገባው በእንግሊዝኛ አስቦ በአማርኛ ለመሥራት የመሞከር አባዜ ጭራሹንም የአማርኛ መሪቃል መሠየም እንዳለበት እረስቶትLand of Origin የሚል እንግሊዝኛ መሪቃል ሠየመና ምልክቱንና መሪቃሉን ከወራት በፊት ይፋ አድርጎ ሥራየን ጨርሻለሁ!” ብሎ በተቀመጠበት ድርጅቱ ሀገርኛ መሪ ቃል አለመያዙ ራስን ሆኖ መቅረብን የግድ ከሚጠይቀው የጉብኝት (የቱሪዝም) መሠረታዊ አስተሳሰብ ጋር ተጋጨበትና በቀረበበት ትችት የመረጠውን መሪቃል አገርኛ ወይም አማርኛ ማድረግም እንዳለበት ተገነዘበና ቀጥተኛ ትርጉም ለመስጠት ተቸግሮ ሲዳክር ከቆየ በኋላ ትናንትና መጋቢት
13,2009.. የቱሪዝም (የጉብኝት) መሥሪያ ቤት 13 months of sunshine (የዐሥራ ሦስት ወር የፀሐይ ጸጋ!) የሚለውን የቆየ የመሥሪያ ቤቱን መሪ ቃል (Slogan) Ethiopia Land of Origin
በሚል ቃል ቀይሮ ለዚህ ለሠየመው የመሥሪያ ቤቱ መሪ ቃል “”የአማርኛ ቀጥተኛ ትርጉም በሀገሪቱ የቋንቋ ጠበብቶች ሳፈላልግ ቆይቸ ቀጥተኛ ትርጉምም ባይሆን የሀገሪቱን የቱሪዝም (የጉብኝት) ሀብቶችን ሊገልጽ የሚችል ቃል ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት!” የሚል ቃል ተገኝቶ ዛሬ የሀገሪቱ የቱሪዝም (የጉብኝት) መሪ ቃል እንዲሆን አጽድቄአለሁ!”” ሲል ትናንት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ምርዓየ ኩነት) የሁለት ሰዓት ምሽት ዜና ላይ የሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ ሚንስትር (የክፍለ ተግባረ መንግሥት ዋና ሹም) ቀርበው ገለጹ፡፡

እናም ሁኔታው በጣም ቢገርመኝ ነው ወደናንተ ያቀረብኩት፡፡ የሀገሪቱን የቋንቋ ሊቃውንት አስጠንተን ነው!” ነው ያሉት የክፍለ ተግባረ መንግሥቱ ዋና ሹም? ድንቄም ሊቃውንት አያ! እነማን ይሆኑ በሞቴ? እርግጠኛ ነኝ በዚህ Land of Origin ለሚለው ቃል ተስተካካይ የአማርኛ ቃል ትርጉም ፍለጋ ላይ አንድም የቋንቋ ሊቅ አልተሳተፈም፡፡ አንዱ ካድሬ ነው እንዲህ በሉት!” ብሎ ተስተካካይ ያልሆነ ቃል ሰጥቶ እንዲሠይሙት ያደረጋቸው፡፡ ምክንያቱም የቋንቋ ሊቃውንቱ ቢሳተፉ ኖሮ ሳይቸገሩ ቀጥተኛ የቃሉን ትርጉም ይሰጧቸው ነበር እንጅ የቋንቋ ሊቃውንት ሆነው ጭራሽ ቀጥተኛ ትርጉም መስጠት ተስኗቸው ወደ ተቀራራቢ ቃል መረጣ በመሔድ ተቀራራቢ ነው!” የተባለውን ነገር ግን ጨርሶ የማይገናኝ ቃል ሰጡ ባልተባለ ነበር፡፡

ሲጀመር አማርኛችን Land of Origin ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ቀጥተኛ ትርጉም መቸ አጣና ነው ስለታጣ ሌላ የዘርፉን ምንነት የሚገልጽ ቃል መረጥን!” የሚባለው? ችግሩ የአማርኛችን ሳይሆን አማርኛን ሳታውቁ እናውቃለን የምትሉት የእናንተ ነው፡፡ የእናንተን ደካማነት አላዋቂነት የአማርኛችን ለማድረግ ለማስመሰል መጣራቹህ ነው አሳዛኙና ነውረኛ ተግባራቹህ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ነውረኛ ተግባር ከመፈጸም እኛ አናውቅምና የምታውቁ ካላቹህ ተባበሩን?” ማለት ማንን ገደለ? እኔ ዘወትር የሚያናድደኝ ነገር ቢኖር ማንም በየ ብዙኃን መገናኛው እየተነሣ የባዕድ ቃል ይሰነቅርና አማርኛ ለዚህ ቃል ቀጥተኛ ትርጉም የሚሰጥ ቃል የለውም!” እያለ የራሱን አላዋቂነት ደካማነት የቋንቋ ድህነት የቋንቋችን ለማስመሰል መጣሩ ነው፡፡ እባካቹህ ለምትሰነቅሩት የባዕድ ቃል ተስተካካይ የአማርኛ ቃል ትርጉሙን ካላወቃቹህ እኔ አላውቀውም!” ነው የሚባለው፡፡ የራሳቹህን የቃል ድህነት የቋንቋው በማስመሰል በስሕተት ላይ ስሕተት አትፈጽሙብን፡፡

ቀጥተኛ የአማርኛ ቃል ትርጉም ወደሚለው ልሒድና Land of Origin ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ቀጥተኛ የአማርኛ ትርጉሙ የመፍለቂያ ምድር!” የሚለው ቃል ነው፡፡ መሠረተ ምድር!” ወይም ምድረ መነሻ!” ማለትም ይቻል ነበር ነገር ግን ለመንታ ትርጉም ስለሚጋብዙ ተስማሚ አይደሉም፡፡

ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት!” ወይም ኢትዮጵያ የቀዳሚዎች ምድር!” የሚለው የተመረጠው ቃል ቃሉ እንዲገልጽ የተፈለገውን ሀገሪቱ ያሏትን የቱሪዝም (የጉብኝት) መስሕቦችን አንዱንም አይገልጽም፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ቀዳሚነታችን በምንድን ነው? የትኛው የጉብኝት መስሕባችን ነው ቀዳሚነታችንን የሚያረጋግጠው? ሉሲ ተነሥታ ቀዳሚ ነን! ተከታይ ነን!” በሚል ፉክክር ተመዝና ትገለጻለች ወይ? እርግጥ ነው “… ዓይነቱን ሥልጣኔ፣ ባሕል፣ እሴት ወዘተርፈ. ለዓለም በማስተዋወቅ በማበርከት ቀደምት ነን!” ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ራሱ መሥሪያ ቤቱም ቢሆን የትኛው መስሕባችን ቀዳሚ እንደሚያደርገን ያምንበታልና ነው ኢትዮጵያ የቀዳሚዎች ምድር! ወይም ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት!” የሚል መሪ ቃል ሊሠይም የቻለው? በዚህ ጉዳይ ላይ መሥሪያ ቤቱ በጎብኝዎች ቢጠየቅ ይሄ ይሄ መስሕባችን በዚህ በዚህ ምክንያት በዚህ በዚህ መረጃ ቀደምት ስለሚያደርገን ነው!” ብሎ የሚለው ነገር አለው ወይ? እስከማውቀው ጊዜ ድረስ የለውም፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ባለሞያዎች የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቀደምትነታችንን
ለምትመሰክርባቸው ጉዳዮች እንኳን አፈ ታሪክ ነው! ፈጠራ ነው!” እያሉ የሚያስተባብሉ እንጅ እንደ ዜጋ እንኳ ተቆርቋሪነት ተሰምቷቸው ትንሽም ለመከራከር የሚሞክሩ አይደሉም፡፡ ይሄ በሆነበት ሁኔታና መሪ ቃሉም አመክንዮአዊ (Logical) ባለመሆኑ ተስማሚ አይመስለኝም፡፡

ኢትዮጵያ የመፍለቂያ ምድር!” የሚለው ቃል ግን Ethiopia Land of Origin ለሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉም ከመሆኑም በላይ የሉሲ የመሰሎቿና የዘመናዊ የሰው ዘር፣ የቡና፣ የጤፍና የበርካታ ዓለም ከእኛ ወስዶ የተጠቀመባቸውና እየተጠቀመባቸው ያሉ ነገር ግን በተንኮል በምቀኝነት ዕውቅና የነፈጋቸው የዕጽዋት ሀብቶቻችን መፍለቂያ፣ የምዕራባውያኑን ቤተ መዛግብትና ቤተ ቅርስ (ሙዚየም) ያጨናነቁ እንደ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት ያሉና የያዟቸው ዕውቀቶች መፍለቂያ፣ የሌሎቹም የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባሕላዊ ሥነ ጥበባዊና ሥነ ኪናዊ ቅርሶቻችን ወይም መስሕቦቻችን መፍለቂያ መሆኗን የሚገልጽ ቃል በመሆኑ የሀገሪቱ የቱሪዝም ወይም የጉብኝት መሥሪያ ቤቱ መሪ ቃል ሊሆን የሚገባው ኢትዮጵያ የመፍለቂያ ምድር!” የሚለው ቃል ነው፡፡ መፍለቂያነታችን እንደ ዜማና የዜማ ምልክት ባለ ሀብታችን ቀደምት ተከታይ ተብሎ ሊለይ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ቀደምትነታችንንም ይመሰክራል፡፡ እንደ ሉሲና ሥነ ምኅዳራዊ ሀብቶቻችን ባሉ ቀደምትና ተከታይ ሊባል በማይቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ መፍለቂያነታችንን በትክክል ይገልጸናል፡፡ ቀደምት የሰው ዘር ምንጭ ኢትዮጵያ ተከታይ የሰው ዘር ምንጭ ደግሞ እከሌ ስለማይባል፡፡ ምክንያቱም የሰው ዘር ምንጩ አንድ ብቻ ስለሆነ፡፡ ቀደምት ከተባለ ተከታዮች ስላሉ፡፡

ምልክቱን በተመለከተም ዛፉን የፈጠሩት በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ተመስለው የተጋመዱት ቅርንጫፎች (ብሔረሰቦች ወይም ጎሳዎች) ከወደ ስራቸው አካባቢ ሦስቱ ቀለማት ሲዋሐዱ የሚፈጥሩትን ቸኮሌት (ጠይም) ቀለም ተዋሕደው የፈጠሩ ቢሆንና ዛፉም ቅጠል ብቻ ሳይሆን ፍሬ ያፈራ ዛፍ ቢሆን ኖሮ ይህ አዲሱ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሥያሜም ሆነ ምልክቱ ተስማሚና ሀገሪቱን፣ የመስሕብ ሀብቷን፣ ጥበቧን፣ ሕዝቧን የሚገልጽ በሆነ ነበር፡፡ ምንጫችን አንድ ነውና፡፡ ተዋልደን ተዋሕደን ያለን ነንና፡፡

በዚህ አጋጣሚ ይህ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት አገልግሎት በባዕድ ቃል መጠራት የለበትምና የሚንስቴር (የክፍለ ተግባረ መንግሥት) መሥሪያ ቤቱ የቱሪዝም …” በባሉ ቀርቶ የጉብኝት …” መባል እንደሚኖርበት ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ tourism (ጉብኝት) የሚለው ቃል ግሱ tour (ጎበኘ) የሚለው ቃል ነው፡፡ ቃሉ ስም ሲሆን tourist (ጎብኚ) ይሆናል፡፡ በመሆኑም ሳያጡ ቀላዋጭነት ካልሆነ በስተቀር ከቅርብ ጉብኝትየሚለው ቃል እያለ እንደሌለን ተደርጎ ቱሪዝምእያልን የባዕድ ቃል የምንጠቀምበት ምንም ምክንያት የለምና ይህንን ቃል በሀገራዊ ቃል መተካት ይገባል፡፡

እዚህ ላይ ጎበኘ የሚለውን ቃል visit ለሚለው ቃል ትርጉም አድርገነዋልና ለዚህኛውም ቃል ልናደርገው አንችልም!” ከተባለ፡፡ እራሱ እንግሊዝኛውም tour የሚለውን ቃል ሲተረጉም a journey made for pleasure during which several different towns, countries, etc. are visited. በማለት ሁለቱም ቃል ተወራራሽ እንደሆኑ ይገልጻልና እንዲያ ልንል አንችልም፡፡

በዚያ ላይ አንድ ቃል በርካታ ትርጉሞችን መያዙ ወይም በርካታ ትርጉሞት በአንድ ቃል መተርጎማቸው በቋንቋዎች አጠቃቀም ውስጥ የተለመደ ነገርም ነው፡፡ ስለሆነም እዚህም ላይ ማስተካከያ ያስፈልጋል፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com