ሰሞኑን የቀድሞ የአንድነት የፖለቲካ ፓርቲ (የእምነተ አሥተዳደር ቡድን) አመራርና ቀደም ሲል በወያኔ እስር
ቤቶች በታሰረበት ወቅት በነበረበት ኢሰብአዊ አያያዝ ለከባድ ሕመም በመዳረጉ አሁን ላይ ለከፍተኛ ሕክምና አሜሪካ
የሚገኘው አቶ ሀብታሙ አያሌው በቅርቡ ለአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው ዝግጅት ክፍል በሰጠው ቃለምልልስ ወያኔ
ሰብአዊና ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) መብታቸውን በጠየቁ፣ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ጥረት ባደረጉ
ንጹሐን ዜጎች ላይ እየፈጸመው ያለውን ሰቆቃ (ቶርቸር) መግለጹ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጅ በመዘንጋት ይመስለኛል
ሀብታሙ በቃለ ምልልሱ ላይ ያልገለጻቸው ተጨማሪ አስከፊ የሆኑ የሰቆቃ ዓይነቶች በመኖራቸው ከሁለት ዓመት
ከመንፈቅ በፊት ቅሊንጦ እስር ቤት በነበርኩበት ጊዜ ከታሰርኩበት ክፍል ውስጥ ባገኘኋቸው ሁለት አንበሶች ማለትም
ስለሚወዳት ሀገሩና ሕዝቡ ሲል ለመግለጽ የሚከብድ ሰቆቃ ስለተፈጸመበት አበበ ካሴ እና በወያኔ አጠራር የጋምቤላ
ክልል ርእሰ መሥተዳድር ስለነበሩትና በወገናቸው በአኙዋኮች ላይ በወያኔ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ምክንያት ወያኔን
ከድተው የፈጸመውን ጭፍጨፋ ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ስላጋለጡት አቶ ኦኬሎ አኳዬ ጀብድ “የቅሊንጦ አንበሶች!”
በሚል ርእስ ጽፌው ከነበረውን ጽፉፍ አሰቃቂ ሰቆቃ የተፈጸመበትን የአበበን ክፍል ነጥየ ባስነብባቹህ ያለውን
ሁኔታ በሚገባ ለመረዳት ያስችላቹሀልና በሚል አቀረብኩላቹህ፡፡
ታች አምና ከእስር ቤቱ እንደወጣሁ ይሄንን ጽሑፍ ለንባብ ላበቃው የቻልኩት በራሴ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን አበበ ካሴ
ማለትም ባለታሪኩ የተፈጸመበትን ኢሰብአዊ ግፍ ለሕዝብ እንዳደርስለት አደራ ብሎኝ ስለነበረም ነበር፡፡ ጽሑፉን
በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ እንደለቀኩት የኢሳት ጋዜጠኛ ካሳሁን ይልማ ቃለ መጠይቅ አድርጎልኝ ነበር፡፡ ነገር
ግን በወቅቱ ግልጽ ባልሆነልኝ አሁን ግን ግልጽ በሆነልኝ ዕኩይና ጠባብ ምክንያቱ ቃለመጠይቁን በጽሑፉ ላይ
ታሪኩን ስለዳሰስኩት ሁለተኛው ሰው ማለትም በአቶ ኦኬሎ አኳዬ ላይ ብቻ እንዲያተኩር በማድረግ ዋነኛ የሰቆቃ
ሰለባ ስለሆነውና አስደናቂ ታሪኩ ሊነገርለት ይገባ ስለነበረው አበበ ካሴ እንዳነሣ ሳይፈቅድልኝ ቃለምልልሳችንን
ቋጨው፡፡
ስለአበበ ለምን እንዳናወራ እንዳልፈለገ ስጠይቀው “ወያኔ ይሄንን ሰምቶ ጥቃት እንዳይፈጽምበት ነው!” አለኝ፡፡
አበበ በወያኔ ይታወቅብኛል ብሎ የሚፈራው ነገር እንደሌለና ጽሑፉ የተጻፈውም በእሱ ፍላጎት እንደሆነ ነግሬው
ወያኔ “በማንም ላይ ሰቆቃ ፈጽሜ አላውቅም!” በማለት የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እየዋሸ የሚፈጽመውን ሰቆቃ
ሸምጥጦ ስለሚክድ እኔ በእሱ ላይ የተፈጸመውን ግፍ ስላየሁ የዓይን ምስክር ሆኘ ይሄንን ለሕዝብ ብናቀርብ
የወያኔን ማንነት በማጋለጡ እረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልና ብናቀርበው ጥሩ እንደሆነ ብነግረውም ሊሰማኝ
ሳይፈልግ ቀረ፡፡ ለካ እሱ ነገሮችን ከኦነግ ጥቅም አንጻር ይለካ ስለነበረና የአበበ ካሴ አስደናቂ ተጋድሎ
መዘገቡ አማራን የሚያጀግን የሚያጸና እንደሆነ ስለተሰማውና ይህ እንዳይሆን በመፈለጉ ነበር ሊሠራው ያልፈለገው
የነበረው፡፡ ሰነባብቶ ግን ከአምስተርዳም ስቱዲዮ (መከወኛ ክፍል) የሚሠራው ሌላኛው የኢሳት ጋዜጠኛ ከማኅበራዊ
የብዙኃን መገናኛ የሚያገኟቸውን ጽሑፎች በሚያቀርቡበት ዝግጅታቸው ጽሑፉን አቅርቦታል፡፡ ለማንኛውም ያንን ጽሑፍ
እንድታነቡ ልጋብዛቹህ! መልካም ንባብ፦
ባለታሪካችን አበበ ካሴ ይባላል፡፡ ተወልዶ ያደገው ጎንደር ነው፡፡ አምና 2006ዓ.ም. ጥር 12 ቀን ነበር
የተያዘው፡፡ ወደ ቅሊንጦ ከመምጣቱ በፊት በተለያዩ ሀገሪቱ ውስጥ ባሉ የማሰቃያ ቦታዎች ሰቆቃ ሲፈጸምበት ቆይቶ
በመጨረሻ ነው እዚህ አምጥተው የጣሉት፡፡ አበበ ካሴ የግንቦት 7 ቆራጥ ታጋይ ነው፡፡ ከዚያ በፊት
ከ1981-1993ዓ.ም. ድረስ የቀድሞው ኢሕዴን የአሁኑ ብአዴን ታጋይ ሆኖ ለ12 ዓመታት አገልግሏል፡፡ ከዚያ
በኋላ እሱና ጓዶቹ ታግለው ለዚህ ያበቋቸው መሪዎቹ ከዚህ በስተቀር የማይባል ሁለንተናዊ ድጋፍ እየሰጠ ባበቃቸው
ሕዝብ ላይ የሚፈጽሙት ገደብ የለሽ ግፍና በደል አንጀቱን ሲቆርጥበት፣ አገዛዙ የኢትዮጵያን ሕዝብ የፍትሕ ጥያቄ
የመመለስ ብቃቱ ወኔው ፍላጎቱ ጽናቱ እንደሌለው ባረጋገጠ ጊዜ ጥሏቸው በረሀ ገባ፡፡ በረሀ ሆኖ ለሦስት ዓመታት
ያህል በግሉ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ በኋላ እንደሱ የከፋቸው ቢጤዎቹህ ተቀላቀለ ከዚያም ወደ ግንቦት 7 ተቀላቅሎ
ድርጅቱ ላዘዘው ተልእኮ አምና ጎንደር ላይ እስከተያዘበት ቀን ድረስ ለ9 ዓመታት ያህል ነፍጥ አንሥተው ከሚታገሉ
ወገኖች ጋራ ሲታገል ቆይቷል፡፡

ለአበበ ካሴ አምና ጥር 12 ገደኛ ቀን አልነበረችም፡፡ ያች ቀን የተሰጠውን ወታደራዊ ተልእኮ (mission)
እንደ አቶ በረከት ስምዖን ባሉ በዚህ አገዛዝ ባለሥልጣናት ላይ የሚፈጽምባት ቀን ነበረች፡፡ ለዚህ ከደቂቃዎች
በኋላ ለሚወስደው እርምጃ ከአጋሩ ጋራ ቦታውን ይዞ በሚጠባበቁበት ሰዓት በጥቆማ ተያዙ፡፡

አበበ ጎንደር ከመግባቱ በፊት ለዚህ ተልእኮ ከሁለት ጓዶቹ ጋራ ሆኖ ሙሉ ትጥቃቸውን እንደያዙ ከኤርትራ ተነሥተው
የሱዳንን በረሀ ለ13 ቀናት በእግራቸው ተጉዘዋል፡፡ ወደ ሀገራቸው ምድር ገብተው እየገሰገሱ እንዳሉ ከወያኔ
ካምፕ በቅርብ ርቀት ላይ በሆኑበት ሰዓት ከሁለቱ ጓዶቹ አንደኛው መሬት ላይ በመቀመጥ እንደደከመውና መንቀሳቀስ
እንደማይችል ተናገረ፡፡ አበበም እንደ አለቃነቱ ያሉበት ቦታ ከወያኔ ወታደሮች ካምፕ (የጦር ሰፈር) ቅርብ ርቀት
ላይ ያሉ በመሆኑ አደገኛ መሆኑን አስገንዝቦ እንደምንም ተጠናክሮ ቦታውን ከመልቀቅ ውጭ ምንም አማራጭ
እንደሌለውና እንዲነሣ አዘዘው፡፡ ጓዱ ግን ጨርሶ መንቀሳቀስ እንደማይችል ተናገረ፡፡ ይሄኔ ነበር አበበ ይህ
ባልደረባው በእርግጥም የወያኔ ሰላይ እንደነበረ አልነሣም ያለውም ስለደከመው ሳይሆን ሆን ብሎ እንደነበር
የገባው፡፡

አበበ በዚህ ልጅ ላይ ጥርጣሬ አድሮበት የነበረው ሱዳን በረሀ ላይ እንዳሉ ያሉበትን ሁሌታ ለአለቆቹ ለማስታወቅ
ከሁለቱም ነጠል ብሎ ስልክ ለመደወል በሚሞክርበት ሰዓት ድንገት ወደጓዶቹ ዞር ሲል ይህ አሁን ተቀምጦ
አልንቀሳቀስም ያለው ጓዱ መሣሪያውን የማቀባበል እንቅስቃሴ ሲያደርግ ያየው ይመስለውና ስልኩን አቋርጦ በመመለስ
መሣሪያውን ተቀብሎ ሲመለከተው በእርግጥም ተቀባብሎ አገኘው፡፡ ማን አዞት ለምን እንዳቀባበለው ሲጠይቀው “ሰው
ከርቀት ያየሁ መስሎኝ ነው!” ይለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ አበበ ይሄንን ልጅ በጥርጣሬና በጥንቃቄ ነበር
የሚመለከተው፡፡ ሁኔታውን ለአለቆቹ ለማሳወቅ ስልክ ለመደወል በተደጋጋሚ ሞክሮ ሊሳካለት አልቻለም በግሉ ወስኖም
ርምጃ መውሰድ አልፈለገም፡፡ ይህ ልጅ መሣሪያውን ያቀባበለው የነበረው እነ አበበን ለመግደል አስቦ ነበር፡፡

አበበ ይህ ጓዱ አልነሣም እንዳለው መሣሪያውን ይቀበለውና ሰላይነቱን እንዳወቀበትና ሊያደርግ የሚፈልገውንም ነገር
ማድረግ እንዲችል ወደፈለገበት ቦታ እንዲሄድ ይፈቅድለታል፡፡ ይሄኔ ልጁ ይደናገጥና እንዲገለው አበበን
ይጠይቀዋል፡፡ አበበም “እኔም ሆንኩ ድርጅቴ ሰው የመግደል ዓላማ የለንም፡፡ አንተን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ
ፍትሕና ነጻነት እራሳችንን መሥዋዕት ማድረግ እንጅ!” የሚል መልስ ይሰጠውና ልጁን እንዲሔድ ያዘዋል፡፡ ልጁ
ከአሁን አሁን ተኩሶ ገደለኝ በሚል ጥርጣሬ ዐሥሬ እየዞረ በመመልከት ወደ ካምፑ አቅጣጫ ተጓዘ፡፡ አበበ እነኝህ
አብረውት ያሉት ሁለቱ ጓዶቹ የተሰጣቸው ወታደራዊ ተልእኮና የትና ምን እንደሆነም ስለማያውቁ የዚህ ልጅ ከእነሱ
መለየትና ሔዶ ለወያኔ ስለነሱ መናገሩ አላሳሰበውም፡፡ አበበና አንዱ ጓዱም በተቻለ ፍጥነት አካባቢውን ከለቀቁ
በኋላ ሌሊት ሌሊት እየተጓዙ ጎንደር ከተማ ገቡ፡፡ ጎንደር እንደገቡም ሰዓቱ ሲደርስ ለጓዱ የሚወስዱት እርምጃ
ምን እንደሆነና በማን ላይ እንደሆነም ከነገረው በኋላ በቦታው ላይ ቅድመ ዝግጅት በሚያደርጉበት ሰዓት ይሄ
ከአበበ ጋር ያለው ጓዱ ቀደም ሲል ኤርትራ እያሉ አብሯቸው ለመታገል ግንቦት ሰባትን ተቀላቅሎ ከነበረ በኋላ ግን
ድንገት ከተሰወረ ሰው ጋር ፊት ለፊት ዐይን ለዐይን ይጋጠማሉ፡፡ ይህ ሰው የሬዲዮ መገናኛ ይዟል ልጁ ተደናገጠ
መለስ በማለት ቀጥ ብሎ አበበ ወዳለበት ቦታ ሔደ፡፡ ይሄንን ሁኔታ ለአበበ እየነገረ ባለበት ቅጽበት አካባቢው
በሦስት የጭነት ተሽከርካሪዎች ተጭኖ በመጣ የጸጥታ ኃይል ተወረረ፡፡ እነ አበበም በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

ይህ እነ አበበን በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሰው የወያኔ ደኅንነት ነው፡፡ ኤርትራ ሔዶ የአንድነት ፓርቲ አባል ነኝ
በማለት ስሙ ተስፋዬ እንደሚባል፣ ሁለት ዲግሪ እንዳለው አውርቶ የበረሀ ስሙን ታይሰን በሚል ሰይሞ እዚያ ታይሰን
በሚባል ስም እየተጠራ ታማኝነት አግኝቶ ከተማ ድረስ እየተላከ ድንገት ተሰውሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በድርጅቱ
ውስጥ የነበረ ሰው ነው፡፡

አበበ ከዚያች ቀን ጀምሮ ወደዚህ ወደ ቅሊንጦ እስከወረደበት ጊዜ ድረስ አስቀድሞ በጎንደር በኋላም እዚህ አዲስ
አበባ በማእከላዊ የግንቦት 7ን አንዳንድ ምስጢሮችና እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉ የግንቦት 7 የስለላ መዋቅር
ሰንሰለትና አባላትን፣ እጃቸው ላይ የተገኙትን ሊወስዱት አስበውት ለነበረው እርምጃ የሚያገለግሉ ሰነዶችን ማን
እንደሰጣቸው፣ እንዴት እንዳገኙት እንዲናገር ተጠይቆ ለመናገር ፈጽሞ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የሰው ልጅ የጭካኔ ደረጃ
የተለካበት ሰቆቃ (ቶርቸር) ሲፈጸምበት ነበር የቆየው፡፡ የመጀመሪያዋና ቀላሏ እራቁቱን እጅና እግሩን አስረው
የጉንዳን አሸን ላይ ነበር የጣሉት፡፡ በዚህ አልሆን ሲላቸው እያገላበጡ አንጠልጥለው ገረፉት፡፡ አሁንም
አልሆነላቸውን ሰቆቃውን እያከበዱት መጡ ውኃ የተሞላ የፕላስቲክ (የተለጥ) ኮዳ ብልቱ ላይ አንጠለጠሉበት፡፡
በዚህ ሁሉ መከራ ወይ ፍንክች ያለው አበበ ደረቱላይና ውስጥ እግሩ ላይ ኤሌክትሪክ አያይዘው አቃጠሉት፡፡ አበበ
“ግደሉኝ እንጅ ምንም ዓይነት ኢሰብአዊ የጭካኔ ድርጊት አይበግረኝም!” ብሎ እንቅጩን ነገራቸው፡፡ ርሕራሔ
ያልፈጠረባቸው አውሬዎቹ የአበበን የእጆቹንና የእግሮቹን ጣቶች ጥፍሮች እያንዳንዳቸውን በጉጠት እየገሸለጡ
እየቦጨቁ እየፈነቀሉ ጣሏቸው፡፡ ቆራጡ ጨካኙ ጀግናው አበበ ግን ጽናቱ ወደር አልነበረውምና ጨርሶ ሊፈታላቸው
አልቻለም፡፡ አውሬዎቹ ተስፋ ቆረጡ ከአበበ ምንም እንደማያገኙ ሲገባቸው ማእከላዊ ጨለማ ክፍል ውስጥ ወርውረው
ጥለውት ከቆዩ በኋላ ከዚያ አውጥተው እሱን ወዳገኘሁበት ቦታ ወደ ቅሊንጦ አመጡት፡፡ ከዚህ በኋላ የሚቀራቸው
እሱን ለመበቀል በሰቆቃ ብዛት እጅግ ከተጎዳው ሰውነቱ ነፍሱን በመግደል መለየት ብቻ ነው፡፡ እስከአሁን ይሄንን
አላደረጉም፡፡ ሲመስለኝ ይሄንን እንዳያደርጉ ያደረጋቸው ይህ ሥርዓት ሰቆቃ (ቶርቸር) በዜጎች ላይ
እንደማይፈጽም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ይደረግ የነበረው ሰቆቃ በደርግ ሥርዓት እንደቀረ ለሰብአዊ መብት ተሟጋች
ድርጅቶችና ለምዕራባዊያን መንግሥታት ሳያሰልስ ስለሚደሰኩር አበበ ደግሞ በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በወያኔ
እጅ እንዳለ መታወቁ ይኔንን የመጨረሻ እርምጃ እንዳይወስዱ አድርጓቸዋል፡፡

አሁን አበበ ከሌሎች ወንድሞችና እኅቶች ጋር የግንቦት ሰባት አመራር ተብሎ ክስ ተመሥርቶበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት
ተብየው እየታየ ነው፡፡ በዚህ አገዛዝ ሳንባ የሚተነፍሰውና የሀገርንና የሕዝብን ጥቅሞች ሳይሆን ከሀገርና ሕዝብ
ጥቅሞች ጋራ የማይጣጣመውን የሥርዓቱን ጥቅም ለማስጠበቅ ከሚሠራ “ፍርድ ቤት”፣ የሀገርና የሕዝብ ጥቅም ሳይሆን
የሀገርና የሕዝብ ጥቅም ተጎድቶ የቡድን ጥቅም በሚጠበቅበት በሚከበርበት በወያኔ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤
ሰላማዊ አማራጮች ፈጽሞ ስለተዘጋባቸውና የዜግነት ግዴታቸው የታሪክ አደራ አላሳርፍ ብሏቸው ለሀገርና ሕዝብ ፍትሕ
ነጻነትና እኩልነት በመታገላቸው፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከግፍ አገዛዝ ነጻ አውጥተው የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ ይህ
አገዛዝ የተወላቸውን ብቸኛ አማራጭ በመጠቀማቸው በዚሁ ምንም ዓይነት የሕዝብ ውክልና በሌላቸው በወያኔ ቡድን
ስብስብ የሕዝብ ተወካዮች ተብየ በወጣ ሰብአዊ መብቶችን ዓለማቀፋዊ ድንጋጌዎችንና የገዛ ሕገ መንግሥታቸውን
በቀጥታ በሚጻረር ሕግ አላግባብ “አሸባሪዎች!” ስለተባሉ ብቻ ግንቦት ሰባትንና የአርበኞች ግንባርን አሸባሪ
ናቸው ብሎ ከሚያምንና ከተቀበለ ፍርድ ቤት ፍትሕ ባይጠበቅም ፍርድ ቤት አቅርበዋቸዋል፡፡

አበበና ሌሎች ወገኖች ፍርድቤት በቀረቡ ጊዜ በተለይም በአበበ ካሴ ላይ የተፈጸመበትን ኢሰብአዊ የግፍ ዓይነቶች
ለፍርድ ቤቱ በሚያስረዱበት ጊዜ ዳኛው “እሱ ራሱ ይናገር እናንተ ምንድን ናቹህ?” በማለቱ በሰው ተደግፎ የቆመው
ቆፍጣናው ጎንደሬ አበበ ካሴ ዳኛው ያልጠበቀውን መብረቃዊ ቃላቶች በዳኛው ላይ አወረደበት፡፡ ዳኛው ደነገጠ
“ነገሩህ እኮ!” አለ አበበ “ምኑን ነው የምነግርህ?” ሲልም ጠየቀ “ለመሆኑ አንተ ዳኛ ነህ? ዳኛ ነኝ ብለህስ
ራስህን ትቆጥራለህ? ለዜጎች የፍትሕ ጥያቄ ፍትሕ የመስጠት ነጻነቱ ፍላጎቱና ብቃቱስ አለህ? ለመሆኑ በዚህች
ሀገር ፍርድ ቤት አለ? የማናውቅ መሰለህ? አንተ ዳኛ ሳትሆን ካድሬ ነህ፡፡ ቀን ቀን ዳኛ ነኝ ብለህ ካባ
ደርበህ ትውላለህ፡፡ ሌት ሌት ፋቲክ ለብሰህ ሕዝብ ስታሰቃይ ስትቀጠቅጥ የምታድር የሕዝብ ጠላት ነህ!” አለ
አበበ፡፡ አበበ ወኔውና ጽናቱ ዳርቻ የለውም!

ይሄንን የአበበን ታሪክ መጀመሪያ ከሌሎች በኋላም ከራሱ ስሰማ ትውስ ያለኝ የነ አቶ መለስ ጀግና አሞራው
ነበር፡፡ በእርግጥ አሞራው በአበበ ዐይን ሲታይ ትንኝ ነው፡፡ የሰማይና የምድር ርቀት አላቸው፡፡ ይሄም
ልዩነታቸው መሰለኝ እንዳስታውሰው ያደረገኝ፡፡ ለነአቶ መለስ ግን አሞራው የጀግናና የጽናት ምሳሌ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ምርዓየ ኩነት) ከአሞራው ጋራ ያደረገውን ቃለ ምልልስ ዐይታቹህታል፡፡ በቃለ ምልልሱ
አሞራው ምንም እንኳን ደርግ እንዲናገርለት የፈለገውን ነገር ባይናገርለትም አቀራረቡ ግን ምን ያህል የተለሳለሰና
ልምምጥ የተሞላ እንደነበር ታስታውሳላቹህ፡፡ “ሕወሀት ደርግ ከያዛቹህ እንዲህ እንዲህ ያደርጋቹሀል!” እያለ
እንደሚሰብኳቸው ቀባጥሯል፡፡ ያውም እንግዲህ ወያኔ ለሕዝብ ያቀረበው አሞራውን ለትዝብት ሊዳርጉ የሚችሉ ብዙ
ነገሮች ከመሀሉ ተቆራርጦ እንደቀረበ የቀረበው ቪዲዮ (ምስለ ትዕይንት) የሚያረጋግጥ በሆነበት ሁኔታ ነው፡፡

ቆፍጣናው አቤ ግን ቀድሞ ነገር መቸ ፊት ሰጣቸውና! እንኳን እንደ አሞራው እንዲህ ነው እንዲህ እያለ ሊቀበጣጥር
ይቅርና! ለምርመራ በመጡበት ቁጥር ተናግሮት የማያልቀውን እንደ መብረቅ የሚያነዱ ካላቶቹን ያዘንብባቸዋል፡፡
የምርመራ ሥራቸውን ለመሥራት ዕድል ባይሰጣቸው ከሱ ጋራ ስድብና ብሽሽቅ መግጠሙን ሥራ አድርገው ይዘውት ነበር፡፡

ከዚያ ሁሉ መከራው በኋላ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ምርዓየ ኩነት) ጋዜጠኞች የቪዲዮ ካሜራቸውን (መቅረጸ ምስለ
ትዕይንታቸውን) ተሸክመው አበበ እንደማያውቃቸው ሁሉ ልክ ነጻና ተቆርቋሪ ጋዜጠኛ በመሰለ አቀራረብ ቀርበው
ለማናገር ጥረት አድርገው ነበር አልተሳካላቸውም እንጅ፡፡ እነሱም ቅመሱ ብሏቸው አይደል! ሲያከለፈልፍ ያመጣቸው?
አጠጣቸዋ እስኪበቃቸው! ፀረ ኢትጵያነታቸውን፣ ፀረ ሕዝብነታቸውን እየዘከዘከ አንባረቀባቸው፡፡ ካልደመሰሱት ወያኔ
አሞራውን እንዳሳየ ሁሉ ነገ ሀገር ነጻ ስትወጣ አበበን ዕናይ ይሆናል፡፡ የዛ ሰው ይበለንና ፈጣሪ!

ዛሬ አበበ በዛ በተፈጸመበት ዘግናኝና አረመኔያዊ ጭካኔ የተሞላበት የግፍና ሰቆቃ ዓይነቶች የተነሣ ከጭንቅላቱ
እስከ እግሩ ድረስ የግራ ጎን ሰውነቱ በድን ሆኖ ደርቋል፡፡ ብልቱ ያዣል ፈሳሽ አለው፡፡ ጥፍሮቹ ግን እንደገና
በቅለዋል፡፡ በእነዚህ ህመሞች እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ ቀይ መስቀል መጥቶ በጎበኘው ሰዓት ድርጅቱ በራሱ ወጪ ሙሉ
ሕክምና እንዲያደርግለት አገዛዙን ፈቃድ ቢጠይቅም አገዛዙ ሊፈቀድለት አልቻለም፡፡

አቤ በውጭ ጋዜጠኞችም ተጎብኝቷል ቃለ መጠይቅም አድርገውለታል፡፡ ቆፍጣናው መብረቁ አቤ ለነሱስ ቢሆን መቸ
ተመለሰ! ለዚህች ሀገር ውድቀት፣ ለዚህ ሕዝብ ስቃይና መከራ መንግሥቶቻቸው ተጠያቂዎች መሆናቸውን እስኪደነግጡ
ድረስ ነግሯቸዋል፡፡ ወንድሜ አበበ ካሴ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ባለህበት ይጠብቅህ፡፡ አበበ አንዱ ምሳሌ ነው፡፡
ገድሎቻቸውን ሰው ሳያውቅላቸው ሳይሰማ ሳያይላቸው ከዓላማቸው ፈቀቅ አንልም እያሉ ከሀቃቸው ጋር በመጽናት፤ ግድል
አድርገው ሊገላግሏቸው እየቻሉ በሰቆቃ ብዛት ነፍሳቸው ሳይወጣ በወደቁበት ገምተው ተልተው ተጠራሙተው እንዲሞቱ
ያደረጓቸው በርካታ ዕንቁ ጀግና አንበሳ ዜጎች እንዳለፉ በእነዚህ የማሰቃያ የምድር ሲዖል ቦታዎች ለቶርቸር
(ለሰቆቃ) ገብተው ከወጡ ሰዎች የዐይን ምስክሮች ተረድቻለሁ፡፡

አንድ የገረመኝ ነገር ቢኖር እነኝህ ጀግኖች ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ከገበሬው ማኅበረሰባችን የወጡ መሆናቸው
ነው፡፡ በእርግጥ አንድ ግልጽ ነገር አለ የሀገር ፍቅር ስሜት ከከተማ ሰው ይልቅ በገጠር ሰው ይጠናል፡፡ የዚህም
ምክንያቱ የሚመስለኝ ሀገር ማለት በድንበር ተከልሎ ያለው መሬትና በውስጡ ያለው ነገር ሁሉ ማለት ነውና የገጠር
ሰው ደግሞ ሕይዎቱ የተመሠረተው በግብርና ስለሆነና ከአፈሯ፣ ከውኃዋ፣ ከዕጽዋቷ፣ ከአዕዋፋቷ፣ ከእንስሳቷ፣
ከሁለመናዋ ጋር ያለው ግኑኝነት ቅርብና ቀጥተኛ በመሆኑ የመሬቷ የውኃዋ የሌሎች ሀብቶቿ ዋጋ ስለሚገባው፣ ጋራ
ሸንተረሯን በእግሩ ስለሚወጣ ስለሚወርድባት ወዙ ከወዟ ላቡ ከላቧ ጋር ስለሚሞጋሞግ፣ ስለሚሻተት፣ ስለሚቀዳ
በክረምቱ በመኸሩ በበጋው በጸደዩ የተለያየ ዓይነት ማራኪ ውበት ገጽታዋ በዐይነ ሥጋውና በዐይነ ሕሊናው ላይ
ታትሞ ስለሚቀረጽበትና በእነዚህ ምክንያቶች ፍቅሯ የግዱን በልቡ እንዲያድርበት ስለሚያደርገው ይመስለኛል፡፡

የከተማ ሰው ግን ግፋ ቢል የበዓልና የበዓል ግርግሩ ካልሆነ በስተቀር እንደ ገጠሩ ሰው ስለሀገሩ በተለየ
እንዲያስታውስ እንዲናፍቅ የሚያደርገው ጠንካራ ትስስር ስለሌለው የሀገር ነገር ብዙም የሚደንቀው አይደለም፡፡
ይሄንን ነገር ምሁራን በሚባሉትና ባልተማሩት ወገኖች መሀከል ብናየውም ውጤቱ ከላይኛው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
ምሁራን የሚባሉት የፈለገ ነገር ቢሆን ግፋ ቢል “የተጠየቀውን በመጠኑ ለመቀነስ” ወይም “ሁሉንም ከማጣት ጥቂት
ለማግኘት” እንደራደር ይላሉ እንጅ ያልተማረው እንደሚለው “እሞታለሁ! እሠዋለሁ! እንጅ የሀገሬን ጥቅምማ አሳልፌ
አልሰጥም!” አይሉም፡፡ ምሁራን ነፍሳቸውን ይወዳሉ ጥቅመኛም ናቸው፡፡ ለሚጨበጠው ለቁሳዊ ነገሮች ያላቸው ግምትና
ዋጋ ከፍተኛ ነው፡፡ ለማይጨበጠው ለመንፈሳዊ ሀብቶች ግድ የላቸውም፡፡ እንደ መሥዋዕትነት የሚፈሩት ነገር የለም!
በተቻላቸው መጠን መሥዋዕትነትን በሚጠይቅ ጉዳይ ዙሪያ አይደርሱም፡፡ በዚህም ምክንያት ነው የዜግነት ግዴታቸውና
መማራቸው የጣለባቸው ኃላፊነት ሆኖ እያለ መሥዋዕትነት በሚጠይቅ ቦታ ሁሉ ላይ ምሁራኖቻችንን የማታዩዋቸው፡፡
በፖለቲካው(በእምነተ አሥተዳደሩ) ብቻ ሳይሆን በሰብአዊ መብቶች ጥበቃና ግንዛቤ ፈጠራ ዙሪያ በሚሠሩ ድርጅቶችም
በመሳተፍ ሲሠሩ የማታዩዋቸው፡፡

ሳይበላ፣ ሳይጠጣ፣ ሳይለብስ፣ ሳይጫማ፣ ሳይማር ግብሩን ከፍሎ ለዚህ ያበቃቸውን ወገንና ሀገር “ውለታቸው አለብኝ
ልከፍለው የሚገባ ዕዳ አለብኝ!” ብለው ቅንጣትም እንኳን የባለዕዳነት ስሜት ሳይሰማቸው የግል ቁሳዊ ጥቅማቸውን
ብቻ በማሰብ ሀገር አስተዋጽኦዎቻቸውን እጅግ እየፈለገች እያለች “ስትፈልጊ ለኔ ስትይ አራት እግርሽን ንቀይ!”
እያሉ እየጣሏት የሚሔዱት፡፡ “ያልተማረ ገበሬ!” ብለን የምንንቃቸው ወገኖች ግን በሀገር ጥቅምና ክብር በመጣ
ነገር ያለማወላወል ዐይናቸውን ሳያሹ አንዲት ነፍሳቸውን ለመስጠት ሲሰለፉ ነፍሳቸው መተኪያ የሌላት እንደሆነች
እንኳን አያስመስሏትም፡፡ ይህ ከሕዝባችን ቁጥር 85 በመቶውን ይይዛል የሚባለው የገጠር ሰው ባይኖር ኖሮ እኮ
እንደከተሜውና ምሁር ተብየው አስተሳሰብ ቢሆንማ ይህች ሀገር ዛሬ ላይ በታሪክ እንደሁ እንጅ በእውን ባልተገኘች
ነበር፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com