March 25, 2017

የድርጅቱ ህገ-ደንብ ጉባኤውን በየሁለት ዓመቱ ለማካሄድ የደነገገ ቢሆንም ፣ እከል ሲገጥም ለስድስት ወር ያህል ማስተላለፍ መቻሉንም ይደነግጋል ፣ ሆኖም በመለስ ሞት ምክንያት ከተላለፈበት ጊዜ ውጭ አስክ አሁን ድረስ ግን የተላለፈበት አጋጣሚ አልነበረም።

የጉባኤው መተላለፍም ዜና በቀጥታ ከኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ አካል የተነገረ ሳይሆን፤ ቅን ካድሬዎቻቸው ከታማኝ ምንጭ ያገኘነው ነው በሚል በየድረ ገጹ በሚያሰራጩት ወሬ በመሆኑ፣ ጉባኤውን ለማስተላለፍ የተፈጠረው አስገዳጅ ምክንያት ምንድነው ?የጉባኤውንስ መተላለፍ ዜና የምንሰማው ከኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ አካል ባለመሆኑም ውሳኔውን ያስተላለፈው ማነው? ምንስ ያመላክታል? የሚሉትን አንድንጠይቅ አንገደዳለን።

ባለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ’ የኮማንድ ፖስቱ ሴክሪታሪያት ‘ሲራጅ ፈጌሳ የሰጠው መግላጫ ላይ ባቀረብኩት አጭር መጣጥፍ ፣የመግለጫው መሰረታዊ መልአክት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘሙን ለማብሰር አንደነበር ገልጬ ነበር ። በተጓዳኝም ሃይለማርያም ደሳለኝ ‘ባደረግነው ጥናት 82% ሕዝብ አዋጁ አንዲቀጥል መፈለጉን ተገንዝበናል’ በሚል ፓርላማ ቀርቦ የወሽከተውም የአዋጁ መራዘምን ጉዳይ ለማጠናከር አንደነበር ገልጫለሁ ። ይሄንን የሰጠሁትን አስተያየት የሚያጠናከር ደግሞ በቅርቡ ዘአማን የሚባል አፍላ የህወሃት ካድሬ፣ የነሱ ገደል ማሚቶ የሆነ ድረ ገጽ ላይ ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መቼ ይነሳል? ለሚሉ መልሱ“አዋጁ የሚነሳው አዋጁ እንዲወጣ ምክንያት የሆኑት ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ሲቀሩ ብቻ መሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል”በሚልም መዘባበቱ አስተያየቴን ያጠናክራል ።

በኔ እይታ መከላከያ ምኒስትር ተብየው ሲራጅ ፈጌሳም ሆነ ሃይለማርያም ደሳለኝ በአሁኑ ጊዜ ቀጥተኛ ትአዛዝ የሚቀበሉት በስም አገሪቱን ከሚያስተዳድረው የሲቪል መንግስት ሳይሆን የዛሬ አምስት ወር ተኩል ከተቋቋመው “ኮማንድ ፖስት” ከሚባለው የወታደራዊና የደህንነት ጁንታ ነው።

ይሄ ኮማንድ ፖስት የሚባለው የወታደራዊና የደህንነት ጁንታ፤ ከሀይለ ማርያምና ከሲራጅ በስተቀር፤ እነማንን እንደሚያቅፍ ወይም እንደሚያካትት እስካሁን ለህዝብ ይፋ ባለመደረጉ፣ አዋጁ ከሰጠው ያልተወሰነ ስልጣንና፣ በተግባርም ባለፈው አምስት ተኩል ወራት በሃገሪቱ ከተካሄደውና አሁንም ካላቋረጠው፣ ዜጎችን ለመጠነ ሰፊ እስርና እንግልት የዳረገ መንግስታዊ ሽብር በመነሳት፣ “ፖስቱን”የወታደሩና የደህንነት የበላይ የሆኑት ሳሞራ የኑስና ጌታቼው አሰፋ በበላይነት እንደሚመሩት ለመገመት ይቻላል።

ከዚህ ቀደም መቀሌ ላይ በተካሄደ አንድ የህወሃት ስብሰባ ላይ (በሀገ መንግስቱ መሰረት ወታደር ጉባኤ ላይ መገኘት ባይገባውም) ሳሞራ የሲቪል መንግስቱን አብጠልጥሎ ወታደሩ ችግር እንድሌለበት ሲናገር ፣በተቃራኒ የድሮ ጓዱ አበበ ተ/ሃይማኖት “ደርግነት እያቆጠቆጠ – ዴሞክራሲው እየጨላለመ ነው – ህዝቦች ጠንቀቅ በሉ!” በሚል ያስነበበን ትንቢት መሰል ጽሁፍ ተግባራዊ እየሆነ ነው ያለውም ማለት ይቻላል።

አርግጥ ነው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመታውጁ ቀደም ብሎ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ የተካሄደው አገር አቀፍ ሊባል የሚችል ሕዝባዊ ትግል የአገዛዙን መሰረት አናግቶ አንደነበር ግልጽ ነው ። የአገዛዙን መሰረት ከማናጋት አልፎም ስርዓቱን ሊያፈርሰው ይችላል የሚል ፍራቻ በገዢው ቡድን ውስጥ በመከሰቱና፣ ቡድኑንም በሚመሩት መሃል ልዩነትና አለመተማመን ማቆጥቆጥ በመጀመሩ፣ ሁኔታው ከመባባሱ በፊት አርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው የሚለው፣ በመከላከያና በደህንነት መዋቅሩ በመወሰኑ ነው አዋጁ ተግባራዊ የተደረገው።

የአዋጁ ተግባራዊ መሆን ስርዓቱን ለመታደግ አማራጭ የሌለው መሆኑን የመከላከያና የደህንነት መዋቅሩ፣ አብዛኛውን የገዥውን ቡድን አባላት ለጊዜው ቢያሳምንም ፣ አዋጁ ለስርአቱ ሽንፈትን ያከናነበ አንደሆነና፣ የሚኩራሩበትንና ለ ሁገሪቷ አመጣንላት የሚሉትን ህገመንግስት በመሰረቱ ሰርዞ ‘ለተወሰነ ጊዜ’ ም ቢሆን፣ ወታደራዊ አገዛዝ መመስረቱ ያልተዋጠላቸው በመሀላቸው በመኖራቸው ከጅምሩ ሁሉንም ቡድን ያስማማ አንዳልነበር፣ በየድርጅቶቹ ውስጣዊ መወነጃጀልና አንዱ ድርጅት ሌላኛው ላይ ያካሂድ በነበረው ግልጽ ዘመቻ የተገነዘብነው ነው ።

ይሄም በመሆኑ ወደ ጀመርኩት ዋና ነጥብ ስመለስ ፤ ባልተለመደ መንገድ የኢህአዴግ ጉባኤ ላልተወሰነ ጊዜ ወይንም ቢያንስ ለአንድ ዓመት መተላለፉ በምን ምክንያት ነው? የሚለውን ለመመለስ ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች በይሆናል ማቅረብ ይቻላል።

አንደኛ፡ ኢህአዴግ የሚለውን ጭንብል ለብሶ ህወሃት ያለተቀናቃኝ ሲያሽከረክረው የነበረው የገዢ ቡድን በህዝባዊው ትግል ጥንካሬ ምክንያት የመፍረክረክ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል የሚለው እሳቤ ከህወሃት ውጭ ያሉትን ድርጅቶች፣ በተለይም ብአዴንና ኦህዴድ ውስጥ የሚገኙ የበላይና የበታች ሹሞችን ጥያቄዎችን አንዲያነሱ ከማስገደዱም በላይ፣ ህወሃትን አስመልክቶ የነበራቸውን የጌታና የሎሌ ግንኙነት አንዲመረምሩ ሁኔታውን በመፍጠሩ፣ የተወሰነ ማፈንገጥ በማሳየታቸው አለመግብባቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ፣ለጉባኤው መተላለፍ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ያለቅጥ ተራዝሞ የነበረው የድርጅቶቹ ውስጣዊ ግምገማ፣ ኦህዴድ ውስጥ የተካሄደው ሹምሽርና በቅርቡ ደግሞ ብአዴን ላይ በመካሄድ ያለው የአባላት ምንጠራና የአቋም መሸጋሽግ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ።

ሁለተኛ፡ ህዝባዊ ትግሉ በያዘው ስፋትና ፍጥነት ከቀጠለ ስርዓቱን ሊያፈርሰው ይችላል በሚል አዋጁ እንዲታወጅ የገፋፉትና ተግባራዊ ያደረጉት የወታደርና የደህንነት መሪዎች፣ ህዝባዊ ትግሉን ተከትሎ ብአዴንና ኦህዴድ ያሳዩት አንጻራዊ መነቃቃት፣ የህወሃትን የበላይነት ያሳጣል ብለው ካመኑ እናት ድርጅታቸውን ለመታደግ ያላቸው አማራጭ፣ (በዚህ አመቺ ባልሆነ ጊዜ ስብሰባውን ማካሄድ ሊያመጣ የሚችለው ስለማይታወቅ) “ነገሮች አሁንም አልተረጋጉም” በሚል የአዋጁን ጊዜ ማራዘም፣ ጉባኤውንም ማስተላለፍ የግድ ነው በሚል ያደረጉትም ሊሆን ይችላል።

ሁለቱም ይሆናሉዎች በገዢው ቡድን ውስጥ መንገራገጭና አለመተማመን እየሰፈነ መምጣቱን አመላካች ናቸው። በቀጣይም አዋጁ ለተራዘመ ጊዜ ቆይቶ ከመሃል አንድ አምባገነን ይዞ ይወጣል ወይንስ ህወሃት በወታደሩና በደህንነት ውስጥ ያለውን የበላይነትተጠቅሞ ዳግም የኢህአዴግ አድራጊና ፈጣሪነቱን የሚቀጥል ይሆናል የሚለው በሂደት የሚታይ ይሆናል።

የህዝባዊ ትግልም ድሎች የሚለኩት የተነሱበትን አላማ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ብቻ ሳይሆን የጠላትንም ጎራ በማዳከምና በመሃሉም መተማመንን እንዲያጣ በማድረግም ጭምር ስለሆነ፣ በኢህአዴግ ጎራ አሁን የሚታየው ድክመት ባለፈው ሁለት አመት የተካሄደው ህዝባዊ ትግል ውጤት መሆኑን መገንዘብም ይኖርብናል።

አበጋዝ ወንድሙ