25 Mar, 2017

በተከታታይ ዓመታት ከዕቅድ በታች እያስመዘገበና በተለያዩ መሰናክሎች እየተተበተበ የሚገኘውን የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ዘርፍ ለማስተካከል፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መጋቢት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ተሰብስቦ አማካሪ ምክር ቤት እንዲቋቋም ወሰነ፡፡

በተለይ በግብርና ኢኮኖሚ ዘርፍ ቡና፣ ሰሊጥ፣ አበባ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ የተለያዩ ጥራጥሬዎችና የቅባት እህሎች የወጪ ንግድ በበርካታ ችግሮች በመተብተባቸውና አገሪቱ ካላት ዕምቅ ሀብት አንፃር ዝቅተኛ የወጪ ንግድ አፈጻጸም እየተመዘገበ በመሆኑ፣ መንግሥት ችግሩን የሚፈታ ምክር ቤት እንዲያቋቁም አስገድዶታል፡፡

በዚህ መሠረት መጋቢት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተሰብስቦ የወጪ ንግድ ዘርፍ ላይ ያለውን ችግር የሚፈታና የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚያሻሽል ምክር ቤት እንዲቋቋም ወስኗል፡፡ ምክር ቤቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይመሩታል፡፡ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ እያሱ አብርሃ (ዶ/ር) የአማካሪ ምክር ቤት እንዲቋቋም መወሰኑን ለሪፖርተር አረጋግጠው፣ እሳቸውም የምክር ቤቱ አባል እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2009 ዓ.ም. የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከወጪ ንግድ ዘርፍ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የማግኘት ዕቅድ ነበራት፡፡ ነገር ግን ሊገኝ የቻለው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

ባለፈው በጀት ዓመትም ከወጪ ንግድ ዘርፍ ይገኛል ተብሎ የታቀደው 4.22 ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ ሊገኝ የቻለው ግን 2.856 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

ንግድ ሚኒስቴር ባወጣው የ2008 ዓ.ም. ሪፖርት፣ በ2008 ዓ.ም. የተገኘው 2.856 ቢሊዮን ዶላር ከ2007 ዓ.ም. ከተገኘው ጋር ሲነፃፀር በ139.321 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል፡፡

ንግድ ሚኒስቴር ለወጪ ንግድ ማሽቆልቆል በርካታ ምክንያቶችን አስቀምጧል፡፡ ንግድ ሚኒስቴር ያስቀመጣቸው ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው ላኪ ነጋዴዎች ለወጪ ንግድ ማሽልቆለል በምክንያትነት ከሚያቀርቧቸው መካከል፣ በሕገወጥ መንገድ በርካታ የግብርና ምርቶች ድንበር አቋርጠው የሚወጡ መሆኑንና ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት አለመኖር የቢሮክራሲ ውጣ ውረዶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ንግድ ሚኒስቴር ባወጣው ሪፖርት ለ2008 በጀት ዓመት የወጪ ንግድ አፈጻጸም መቀነስ ያስቀመጣቸው ምክንያቶች በምርት ዘመኑ በተፈጠረው የኤልኒኖ ክስተት ምክንያት የፍራፍሬ ምርት አቅርቦት መጠን መቀነስ፣ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የአገር ውስጥ ግዢ መፈጸም፣ በተለይ ለአኩሪ አተር፣ ለማሾና ለቦሎቄ ምርቶች የዓለም ገበያ ዋጋ ዝቅ ማለት፣ የኤክስፖርት ጫት አቅርቦት እጥረት፣ አንዳንድ አገሮች ጫት ወደ አገራቸው እንዳይገባ መከልከላቸውና የቡና፣ የሰሊጥና የጥራጥሬ ምርቶች ዋጋ መቀዛቀዝና ተወዳዳሪ መሆን አለመቻል የሚሉትን አስቀምጧል፡፡

የኢንዱስትሪ ምርቶች የወጪ ንግድም የቀነሰው በግብዓት አቅርቦት፣ በጥራት ችግር፣ በመንግሥት አገልግሎቶች የአሠራር ቅልጥፍና አለመኖር፣ ገዢ ኩባንያዎች በተለያዩ ምክንያቶች ውል በመሰረዛቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡

እነዚህ ችግሮች በዚህ ዓመትም ቀጥለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በበጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ወራት በርካታ የግብርና ምርቶች በሕገወጥ መንገድ ከአገር መውጣታቸው፣ ደረጃውን የጠበቀ ቡና ከወጪ ንግድ ይልቅ ለአገር ውስጥ ገበያ በሰፊው በመቅረቡ እንደሆነ የዘርፉ ተዋናዮች ይጠቁማሉ፡፡

መንግሥት በዚህ ዘርፍ ያለውን ችግር ከመሠረቱ ለመፍታት የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በተለይም የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ የንግድ ሚኒስቴር፣ የቡና፣ የሻይና የቅመማ ቅመም ባለሥልጣንና ዋና ዋና የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች የሚካተቱበት ምክር ቤት እንዲቋቋም ወስኗል፡፡

Source       –    Ethiopian Reporter