Wednesday, 29 March 2017 11:54

      ኢዴፓና ሰማያዊ የኢህአዴግን ውሳኔ እየተጠባበቁ ነው

በይርጋ አበበ

ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና 21 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያካሂዱት የቅድመ ድርድር ዝግጅት እክል እየገጠመው ይመስላል። መድረክ ራሱን ማግለሉን ሲገልጽ ኢዴፓና ሰማያዊ ፓርቲ በበኩላቸው ኢህአዴግ የሚያመጣውን የመጨረሻ ውሳኔ እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል።

ከድርድሩ ቅድመ ዝግጅት ራሱን ያገለለው የመድረክ ሰራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጥላሁን እንደሻው የፓርቲያቸውን አቋም ለሰንደቅ ጋዜጣ ሲገልጹ “መድረክ ራሱን ያገለለው የ22 ፓርቲዎች ስብሰባ ድርድር ነው ብሎ ስለማያምን ነው” ያሉ ሲሆን “የድርድር መልክ እንዲይዝ ጠይቀን ነበር። እስካሁን ባየነው ሂደት ግን የድርድር ይዘት ያለው ሆኖ አላገኘነውም። ምክንያቱም 22 ፓርቲዎች በአንድ ጉዳይ ላይ የየራሳቸውም አቋም እያነሱ መናገር የተለመደ የድርድር አካሄድ ሰላልሆነና ድርድር ሊሆንም አይችልም” በማለት ፓርቲያቸው ከድርድሩ ቅድመ ዝግጅት ማግለሉን ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል።

አቶ ጥላሁን አያይዘውም “ኢህአዴግ ከቀሪዎቹ ፓርቲዎች ጋር ከሚያደርገው ድርድር በተጓዳኝ በአስቸኳይ ከመድረክ ጋር ቀጥተኛ ድርድር መጀመር አለበት ብለን ጠይቀናል። ለዚህ አዎንታዊ ምላሽ እስከምናገኝ ደረስ እዚያ መቀመጡ (21 ፓርቲዎች ጋር አብሮ መደራደር) አስፈላጊ ሆኖ ስላላገኘነው ለመውጣት ወስነናል” ብለዋል። ኢህአዴግ የመድረክን ጥያቄ ተቀብሎ ለመደራደር ፈቃደኛ ከሆነ መድረክ መተማመን የሚፈጥሩ እርምጃዎች እንዲሟሉለት እንደሚፈልግ ያስታወቁት አቶ ጥላሁን የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በተለይም እንደ ዶክተር መረራ ጉዲና እና አቶ በቀለ ገርባ ያሉ የመድረክ አመራሮች እና ጋጠኞች እንዲፈቱ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የሚሉት ነጥቦች እንደሚገኙባቸው ተናግረዋል።

የኢዴፓው ሊመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው “እስካሁን ደረስ ባደረግናቸው የቅድመ ድርድር ውይይቶች ድርድር የሚፈቅደውን ስታንዳርዶች ባማከለ መልኩ እንዲሆን ነው። በመርህ መሰረት እንደራደር ብለን ስንነሳ አደራዳሪ እንዲኖር እንፈልጋለን ብለን ነው በእኛ በኩል እየጠየቅን ያለነው። ነገር ግን አደራዳሪ ከሌለ ውይይት ነው ሊሆን የሚችለው። ውይይት ደግሞ በእኛ እቅድ ውስጥ የለም” ብለዋል። “በአደራዳሪ ምርጫ የኢህአዴግ አቋም ለውጥ ካላመጣ እናንተ ከድርድሩ ትወጣላችሁ ወይ?” ተብለው የተጠየቁት ዶክተር ጫኔ “ኢህአዴግ በአቋሙ ጸንቶ አደራዳሪ አልፈልግም ካለ ከድርድሩ የሚወጣው ኢህአዴግ እንጂ እኛ (ተቃዋሚዎች) አይደለንም። የእኛ ድርሻ ተሰባስበን በኢህአዴግ አማካኝነት ድርድሩ መቋረጡን ጋዜጣዊ መግጫ እንሰጣለን” በማለት ተናግረዋል።

የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ በበኩላቸው “እስካሁን ድረስ ባደረግናቸው ውይይቶች በታዛቢና በተሳታፊ እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን ሂደቱን እንዲከታተሉ ስምምነት ላይ ደርሰናል። ነገር ግን በአደራዳሪ ላይ ኢህአዴግ በአቋሙ ጸንቶ አደራዳሪ ላይ ካልተስማማን ሰማያዊ ፓርቲ ከድርድሩ ይወጣል” ብለዋል።ፓርቲዎቹ ማን ያደራድር በሚለው አጀንዳ ላይ የኢህአዴግን የመጨረሻ አቋም በዛሬው ዕለት (መጋቢት 20 ቀን 2009 .) በሚያደርጉት ስብሰባ ያውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።  

ስንደቅ