Wednesday, 29 March 2017 12:15

በይርጋ አበበ

በኢትዮጵያ ቆላማው ክፍል የሚኖሩ ከ12 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዕለት ጉርሳቸውንም ሆነ የዓመት ልብሳቸውን የሚሸፍኑት በእንስሳት እርባታ አማካኝነት ነው። ይህ የአርብቶ አደር ቁጥር በ2006 .ም በተካሄደ ጥናት 15 ቢሊዮን ብር ለአጠቃላይ የአገሪቱ ገቢ ያስመዘገበ ሲሆን፤ ይህም ከግብርናው ዘርፍ አጠቃላይ 38 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል። አገሪቱ ከአፍሪካ በእንስሳት ብዛት ቀዳሚ ስትሆን ወደ ውጭ ከምትልከው ሸቀጥ ውስጥም ከቡና ቀጥሎ የቆዳና ሌጦ ተከታዩን ደረጃ ይይዛል።

የአርብቶ አደሩ ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚ ይህን ያህል አስተዋፅኦ እያበረከተ የዘርፉ ቀጥተኛ ባለቤቶች (አርብቶ አደሩ) ለምን ተጠቃሚ አልሆኑም? የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ይነሳል። የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በተመለከተ በ1987 .ም የፀደቀውና አሁንም ድረስ በስራ ላይ ያለው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በአንቀፅ 40 ቁጥር 5 ላይ “የኢትዮጵያ ዘላኖች ለግጦሽም ሆነ ለእርሻ የሚጠቀሙበት መሬት በነፃ የማግኘት፣ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብት አላቸው” ሲል ለአርብቶ አደሩ ተዋንያን ሕጋዊ እውቅና እና ከለላ ሲሰጥ ይታያል። ሕገ መንግሥቱ ከተጠቀሰው አንቀጽ በተጨማሪ ዝርዝሩን በሕግ የሚወስን እንደሆነም ይገልፃል። ሆኖም የአርብቶ አደሩ ኑሮ ካለመሻሻሉም በላይ በየጊዜው እየከፋና እየተወሳሰበ ሂዷል። በተለይም በአገሪቱ በተደጋጋሚ እየተከሰተ በሚገኘው ድርቅ የመጀመሪያ ተጠቂ የሆነው ይህ ዘርፍ ነው። ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ለሚለው መልስ ለመስጠት ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ የተባለ የጥናትና ምርምር ማዕከል ሰሞኑን በጉዳዩ ዙርያ ያስጠናውን ጥናት ይፋ አድርጎ ነበር። የጥናቱ ውጤትም ለዘርፉ ችግር ዋናው ምክንያት የፖሊሲ ችግር ነው ሲል ያስቀምጣል። እኛም የጥናቱን ዝርዝር ከዚህ በታች ለአንባቢያን በሚመች መልኩ አቅርበነዋል።

                                                                            ውለታው የተዘነጋው የአርብቶ አደሩ ዘርፍ ጠቀሜታ

የአርብቶ አደሩ ዘርፍ ከስያሜው ጀምሮ አለመግባባቶች የሚስተዋሉበት ዘርፍ ነው። በ1987 ዓም የጸደቀውን የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ጨምሮ በርካታ ምሁራንና አብዛኛው የአገሬው ህዝበ አርብቶ አደሩን “ዘላን” ሲል ይጠራዋል። ከዚህ ቀደም ባሉት ዘመናት ደግሞ “የከብት ጭራ ተከታይ” የሚል መጠሪያም እንደነበረው ቀለም ቀመስ አርብቶ አደሮች ይናገራሉ። አርብቶ አደር ወይም በእንግሊዝኛው (Pastoralist) ቀደም ሲል ይጠራበት ከነበረው “ዘላን” (Nomad) እንዲቀየር የተደረገው አሉታዊ ትርጓሜ ያለው ቃል በመሆኑ እንደሆነ ምሁራን ተናግረዋል። ከቃሉ ጀምሮ እስከ ምርት ሂደቱ (Process) ለውዝግብ ክፍት የሆነው ዘርፍ በአገሪቱ ኢኮኖሚና ማህበራዊ የሚጫወተውን ሚና በተመለከተ ዶክተር ታፈሰ መስፍን መተኪያ ሲገልጹ “በ2006 .ም በኤስኦስ ሳህል አማካኝነት በተካሄደ ጥናት የአርብቶ አደሩ ዘርፍ በዓመት እስከ 15 ቢሊዮን ብር ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ መረጃው ያመለክታል። ይህም እንደ ኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስቴር መረጃ 16 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን ጂዲፒ ይሸፍን ነበር። 12 ሚሊዮን የአገሪቱ ዜጎችም በአርብቶ አደር ስራ ተሰማርተው ይገኛሉ” በማለት ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ወተት አቀናባሪዎች ዋና ስራ አስኪያጅና የአርብቶ አደሮች ፎረም ኢትዮጵያ ምክትል የቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ታፈሰ በጥናታቸው አያይዘውም “pastoral areas contribute significantly to the national economy, but this is no quantified and well understood by policy makers as there is no statistical data gathered by central statistical agency on the direct and indirect values of pastoralists” ወይም በአቻ የአማርኛ ትርጉሙ  “የአርብቶ አደሩ ዘርፍ ለአገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም ዘርፉ የሚሰጠው ሚና ግን በፖሊሲ አውጭዎች ውለታው ሊቆጠርለትና ከግንዛቤ ሊገባለት ካለመቻሉም በላይ በማዕላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ የአርብቶ አደሩ ዘርፍ በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋነት የሚሰጠውን ጥቅም የሚያሳይ አኃዛዊ መረጃ አልተዘጋጀለትም” ብለዋል።

ዶክተር ታፈሰ በጥናታቸው አያይዘውም “የአርብቶ አደር ስራ በኢትዮጵያ ያለው ዘዴ ውስብስበ ሰፊ እና ለኢኮኖሚና ለማህበራዊ ለውጥ ተለምዷዊነት ያለው ቢሆንም በፖሊሲ አውጭዎች ላይ ዘርፉ በልማት ያለው ከፍተኛ ሚና የሰጡት ግንዛቤ አነስተኛ ነው። አርብቶ አደሮቹንም ኋላ ቀር እና ለለውጥ ያልተዘጋጁ ሲሉ ይገልጿቸዋል” በማለት ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት ዘርፉ መንግስት ልዩ ትኩረት በሚሰጥባቸው የኢኮኖሚና የልማት ፕሮግራሞች ተጽእኖ እያረፈበት መሆኑን የሚገልጹት ዶከተር ታፈሰ፤ የአርብቶ አደሩን የግጦሽ መሬት ለሌላ ገልግሎት እንዲውል ማድረግና በከተሞች መስፋፋት አርብቶ አደሩ ወደ ዳር እየተገፋ እንዲሄድ መደረጉ ፈተና መሆኑን ተናግረዋል። ዶክተር ታፈሰ በጥናታቸው በህገ መንግስቱ አንቀጽ 40 ቁጥር አምስት የተቀመጠው የአርብቶ አደሮች (ህገ መንግስቱ ዘላኖች ነው የሚለው) መብት በአሁኑ ሰዓት መሬት ላይ እየተተገበረ አለመሆኑን አመልክተዋል። በተለይም ከግጦሽ መሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸው የተጠበቀላቸው አለመሆኑን ነው የገለጹት።

                                                                           አርብቶ አደሩን የዘነጋው አገር አቀፍ (ወጥ) ፖሊሲ?

ጥናቱ በሚቀርብበት ወቅት ከታደሙ ምሁራን ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አንዱ አገር አቀፍ ተመሳሳይ (ወጥ) ፖሊሲ መከተል ሌሎች ዘርፎችን እንደጎዳው ሁሉ አርብቶ አደሩንም ተጋላጭ እንዳደረገው ተነስቷል። ለአብነት ያህልም በኦሮሚያ ክልል ቦረና አካባቢ የሚገኙ አርብቶ አደሮች በሶማሌና አፋር ክልል ከሚገኙ አቻዎቻቸው ጋር ተመሳሳይ ፖሊሲ መከተል ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን ያነሱት የጥናቱ ተሳታፊ ምሁራን “የአካባቢዎቹ መልክዓ ምድርና የተፈጥሮ ሀብት የሚለያይ ሲሆን የእንስሳቱ ዝርያም የተለያየ ነው። ታዲያ በምን መመዘኛ ነው ተመሳሳይ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ (Land use policy) መተግበር ያስፈለገው?” ሲሉ ተናገረዋል።  

ጥናቱን ያዘጋጁት ዶክተር ታፈሰ መስፍንም የተነሳውን ሀሳብ ተገቢነት በጥናታቸው መመልከታቸውን ገልጸው ከፖሊሲ ተመሳሳይነት በተጨማሪም የአርብቶ አደርን በተመለከተ በፌዴራል፣ በክልል እና በዞን ደረጃ የተዘረጋው የመንግስት መዋቅር በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ ያልተዘረጋ በመሆኑ አርብቶ አደሩ ጠንካራ ክትትልና የምክር አገልግሎት እንዳያገኝ አድርጎታል ብለዋል። የአገሪቱ ህግ አስፈጻሚዎችና ፖሊሲ አውጭዎችም ጉዳዩን ትኩረት ሊሰጡበት እንደሚገባ ማሳሳቢያቸውንና መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

                                                                                          የአርብቶ አደሩ ዋና ዋና ፈተናዎች

ድርቅና የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት እንደ ሌሎች የግብርና ዘርፎች ሁሉ አርብቶ አደሩንም የሚያጠቁት ሲሆን አርብቶ አደሩ ላይ ግን በተለይም ጡንቻቸውን ያበረቱበታል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በግጦሽ መሬት እና በእንስሳት መጠጥ ውሃ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ የሚያሳድሩ በመሆኑ ነው። ከድርቅና አየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖዎች በተለየ አርብቶ አደሩ ላይ ቁጣቸውን ከሚያሳረፉ ተጽእኖ ፈጣሪዎች መካከል የከተሞች መስፋፋት፣ የእርሻ መሬት ማስፈለጉ እና የመሰረተ ልማት ችግሮች በዋናነት የሚጠቀሱ ችግሮች መሆናቸውን የዶክተር ታፈሰ ጥናት አመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የጋራ (ማህበረሰቡ የሚጠቀምባቸው) የግጦሽና የሰብል ምርት ማካሄጃ መሬቶችን በግል ባለሀብት ለኢንቨስትመንት እንዲሆኑ በመንግስት መወሰኑ አርብቶ አደሩን እየተፈታተኑ ካሉ ችግሮች መካከል ቀዳሚው ነው።

የህዝብ ቁጥር መጨመር ለምሳሌ ከ1994 እስከ 2007 ዓም ድረስ ባሉት 13 ዓመታት ብቻ የአፋር ህዝብ 33 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ የሶማሌ ህዝብ ደግሞ 39 በመቶ እድገት አሳይቷል። ይህ ደግሞ ችግሩን እንዲባባስ የሚያደረገው ይሆናል። ምክንያቱም በተፈጥሮ አየር መዛባት የመጠጥ ውሃና የእንስሳት መኖ ሲቀንስ በኢንቨስትመንት ምክንያት የእንሰሳት መዋያ ቦታዎች መጠን ሲያንስ እና ቀደም ሲል ያልታረሱ መሬቶች ጭምር ለእርሻ አገልገሎት እንዲውሉ ሲደረግ የዘርፉን ምርታማነት የሚቀንሱት ሲሆን በአንጻሩ የህዝብ ቁጥሩ ግን ከመቀነስ ይልቅ የሚጨምርበት ሂደት እንዳለ በጥናቱ ተመልክቷል። ይህ መሆኑ ደግሞ አገሪቱም ሆነች የዘርፉ ተዋነያን (አርብቶ አደሮቹ) ሊያገኙት ከሚገባቸው ጥቅም ሳያገኙ እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል ማለት ነው።

የጥናት አቅራቢው ለጠቀሷቸው ችግሮች አርብቶ አደሩ የአቅሙን ያህል ለመከላከል ሙከራ ማድረጉን የጠቀሱ ሲሆን በተለይም የግጦሽ መሬት በሚጠፋበት ወቅት የሚግጡ እንስሳትን (Grazers) ወደ ገበያ በማውጣት በምትኩ እንደ ግመል ያሉ ቀንጣቢ (Browsers) እንስሳትን ለማላመድ ሙከራ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በእንስሳቱ በመንጋ ውስጥ የወንዶችን ቁጥር በመቀነስ የመኖ እጠረትን ለመቅረፍ ሙከራ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ይህን የአርብቶ አደሩን የግል ተነሳሽነትና ጥረት ፖሊሲ አውጭዎችና የአገሪቱ ህግ አስፈጻሚዎች ሊደግፉት እንደሚገባ ጥናት አቅራቢው ጥቆማቸውን ሰጥተዋል።

                                                                                            የውሃ ብዛት ጥራትና አርብቶ አደሩ የሚሸፍነው የአገሪቱ መሬት

አብዛኛው የአገሪቱ ቆላማ ክፍል በተለይም አፋርና ሶማሌ ክልሎች ሙሉ በሙሉ የአርብቶ አደር አካባቢዎች መሆናቸው ይታወቃል። በኦሮሚያ ክልልም 353 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ከሚሸፍነው የክልሉ ቆዳ ስፋት ውስጥ 152 ሺህ 70 ስኩዌር ኪሎ ሜትሩ ወይም የደቡብ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችን የሚሸፍነው የኦሮሚያ ከልል መሬት አርብቶ አደር የሚኖርበት ነው። 25 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ከሚሸፍነው የጋምቤላ ክልልም ቢሆን ከ17 ሺህ በላይ የሚሆነው በአርብቶ አደር የተያዘ ነው። የተጠቀሱትን ክልሎች እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ዙሪያ ጨምሮ በአጠቃላይ በሰባት የአገሪቱ ክልሎች 624 ሺህ 850 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬት የአርበቶ አደር ቀጠናዎች እንደሆኑ የዶክተር ታፈሰ ጥናት ያመለክታል።

በእነዚህ አካባቢዎች ደግሞ ስድስት ትላላቅ የአገሪቱ ወንዞች የሚፈሱ በመሆኑም የውሃ ክምችቱ አሳሳቢ እንዳልሆነ የገለጹት ዶክተር ታፈሰ መስፍን፤ “ሆኖም ወንዞቹ ከደጋው ክፍል ተነስተው ወደ ቆላማው አካባቢ የሚፈሱ የውሃዎቹ ጥራት ግን ጥሩ አይደለምሲሉ ተናግረዋል። የውሃዎቹ ጥራት ጥሩ ባለመሆኑም በእንስሳቱ ጤና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የድርቅ ጉዳት በአርብቶ አደሩ ላይ

ከአገሪቱ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 49 በመቶ የሚሆነውን መሬት የሚይዘው የአርብቶ አደር ዘርፍ ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት በአርብቶ አደሩም ሆነ በአጠቃላይ አገሪቱ ላይ ሊከሰት የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው። በዚህ ዓመት እና ባለፈው ዓመት ብቻ በተጠቀሱት የአርብቶ አደር አካባቢዎች በደረሰው ድርቅ የተጎጂዎች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን የሞቱ እንስሳትም የዚያኑ ያሀል እንደነበር ከፌዴራል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የተገኘ መረጃ አመልክቷል። ድርቅ በሚደርስ ሰዓት ያን ያህል አደጋ የሚደርስ ከሆነ ለአርብቶ አደሩ ዘላቂ መፍትሔ የተቀመጠው ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ መሰረታዊ መልስ የሚሻ ይሆናል።

አንድ አርብቶ አደር በአንድ ወቅት ድርቅ ምክንያት ከሚያረባቸው የቁም እንስሳቱ መካከል የተወሰኑት ቢሞቱበት እነዚያን ለመተካት በትንሹ ከአራት እስከ ሰባት ዓመታት ሊወስድበት ይችላል። ኑሮውን በእንስሳቱ ጤንነትና ህይወት ላይ ብቻ የመሰረተው አርብቶ አደር የሚደርስበት ጉዳት ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ መሆኑን መንግስትም ሆነ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች የሚገልጹት ሀቅ ነው። ይህንን ጉዳት ለመቀነስ ደግሞ የምሁራን ጥናትና የፖሊሲ አውጭዎች ተግባብቶና ተቀራርቦ መስራት አስፈላጊ መሆኑን የዶክተር ታፈሰ መስፍን ጥናት አመልክቷል።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በደረሰው የድርቅ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመታደግም እንስሳትን በማረድ በተንቀሳቃሽ ቄራ (mobile slaughtering) ዜጎችን በመመገብ እንደሆነ ዶክተር ታፈሰ በጥናታቸው ገልጸዋል።

ስንደቅ