03/30/2017

የቴዎድሮስ ካሳሁን ዜና ያስነሣው ተቃውሞ

ምንጩ ምንድን ነው? ዘፈንስ ኃጢአት ነውን?

ወይ ፌስ ቡክ (መጽሐፈ ገጽ) እንዲያው ለቧልተኛውም፣ ለእብዱም፣ ለአስመሳዩም፣ ለአድር ባዩም፣ ለባለጌውም፣ ለምኑም እንደልቡ የሚፈነጭበት፣ የሚቀልድበት፣ የሚያብድበት፣ የሚባልግበት የሚያስመስልበት ዕድል ሰጥቶ መራኮቻ መቀለጃ ባያደርገን እንዴት ጥሩ ነበር! ምን ይደረግ! ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ (Social media) መባሉስ ለዚሁ አይደል? በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ባለጌም፣ አስመሳይም፣ አድርባይም፣ እብድም፣ ቧልተኛም ሁሉም አይደል እንደየ ግብሩ ሲራኮት ሲፏልል የሚውለው? ይሄም እንዲያ ነው! እዚያ የሚንጸባረቀው ሁሉ እዚህም ይንጸባረቃልአዋዋላቹህን መለየት ብቻ ነው መፍትሔው፡፡ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉና የሚታዩ ነገሮች ሁሉ በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ (Social media) ላይም መታየቱ ግድነውና ያስችለን ብቻ ነው የሚባለው፡፡ ይሄንን ሁኔታ ግን ሐሳብን ከመግለጽ ነጻነት ጋር ማያያዝ ስሕተት ነው፡፡ ምክንያቱም ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ከብልግና ጋር፣ ምንም ከማይጠቅም ከማያንፅ ቧልትና ቀልድ ጋር፣ ከአሳሳች አስመሳይነት ጋር ወዘተረፈ. የሚያገናኘው ነገር ስለሌለ፣ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት መረጃ ኖረም አልኖረ እውነት ላይና ትክክለኛነት ላይ የተመሠረተ ተፈጥሯዊ መብት ስለሆነ ነው፡፡

በጣም እኮነው የሚገርመው! ምነው እንዲያው እንዲህ ለማይረባ ነገር ምን እንበል?” ብለን ተጨንቀን የማይሆን ነገር ከምንቀበጣጥር መንገዳችን ላይ ተደርቅነው ተሰንቅረው አላሳልፍ ያሉንን ቋጥኞች ከመንገዳችን ገለል ልናደርግ በምንችልበት መላ ላይ አተኩረን ብንመክር?… ምን ያህል ዋዘኞች፣ አስመሳዮችና ቧልተኞች ብንሆን ነው ስንት የመፍትሔ ያለህ!” እያለ ጣራ ቀዶ የሚጮህ ችግር እያለብን ምንም ችግር እንደሌለበት ሕዝብ የማይረባ ሙግት ፈጥረን የምንራኮተው፣ ወርቃማ ጊዜያችንንና ገንዘባችንን የምናባክነው? እነኝህ ያሉብን ችግሮች እኮ ሌት ተቀን ያለ እንቅልፍ ብንተጋባቸው ራሱ ብዙ ሳያደክሙ የማንገላገላቸው ችግሮች እኮናቸው! በአርቲቡርቲ ወሬ የተገነባ ሀገር አለ እንዴ? አሁን እውነት የቴዎድሮስ ካሳሁን የዘፈን ጥራዝ (አልበም) ለትንሣኤ ወይም ለዳግሚያ ተንሣይ መለቀቁ መንፈሳዊ ሕይዎትን የሚያስተኃቅር ስለሆነ ነው ይሄንን ያህል የሚያስቀበጣጥረው?

ይሄንን ነው አስመሳይነት የምለው፡፡ አስመሳይነት ደግሞ ብቻውን አይመጣም ከጀርባው ደብቆ የሚይዘው ሸፍጠኛ ዓላማ አለው፡፡ ቴዎድሮስ ካሳሁን የምታውቁትን ዓይነት ሰው በመሆኑ እንደ ወያኔና ኦነግ ያሉ አደገኛ አደገኛ የጥፋት ኃይል ጠላቶች ሊኖሩት ግድ እንዳለው የምታውቁት ጉዳይ ነው፡፡ እነኝህ የጥፋት ኃይሎች ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሁሉ አሁንም በመጪው የከያኔ ቴዎድሮስ ሥራ ጥቅማቸው እንዳይነካ ከባድ ሥጋት ላይ ወድቀዋል፡፡ ይሄ ሥጋታቸው እንዳይከሰትም ከዚህ ቀደምም ሲያደርጉት እንደቆዩት ሁሉ አሁንም የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ለማንም ግልጽ ይመስለኛል፡፡ እንግዲህ ስንት ግንድ ያለባቸው ሰዎች እያሉ ይሄ ሰሞኑን ትንኝ የማጥራት ያህል በመወራጨት ከቴዎድሮስ ካሳሁን በተጻራሪ ቧልተኛውም፣ እብዱም፣ አድርባዩም ምናምንቴውም እየተራኮተ የምታዩት ከዚህ አንጻር ነው፡፡ ቀባጣሪወቹን ወያኔ ኦነግና ኢትዮጵያዊነት ጠላታቸው የሆነ ሌሎች የጥፋት ኃይሎችም የቀጠሯቸው ናቸው፡፡

ይሄ ባይሆን ኖሮ እውነቴን ነው የምላቹህ ኢትዮጵያዊነት የሚያንገበግበው፣ የሀገሩና የሕዝቡ ጉዳይ የሚገደው ዜጋ በምንም ተአምር ቢሆን በኢትዮጵያዊነት ጠላቶች፣ በጥፋት ኃይሎች ለኢትዮጵያዊነት ሲል ስንት ዋጋ፣ ስንት መሥዋዕትነት ሲከፍል በኖረና እየከፈለም ባለ ከያኔ (Artist) ላይ ምን ብየ ልማው? ምን ብየ ላጥላላው?” ብሎ ተጨንቆ በሌለው ሰብእና ተጀቡኖ ምንም በማያውቀው ጉዳይ ላይ የማይሆን ነገር እየቀበጣጠረ የጥፋት ጣቱን ለመቀሰር እንዲች ብሎ አይሞክርም ነበረ፡፡
እነዚህ በቴዲ ላይ የተነሡ ምናምንቴዎች ቴዲ የከፈለውንና እየከፈለው ያለውን ዋጋ ሳያስቡ፣ ዋጋ ሳይሰጡ በቴዲ ላይ እንዲነሡ የሚያደርጋቸው ቅጥረኝነታቸው ነው፡፡ ቅጥረኞች ባይሆኑ ኖሮ እንኳንና ምንም ባልገባቸውና በማያውቁት ነገር ላይ ትንኝ ለማጥራት የማይሆን ነገርን እነቀበጣጠሩ ቴዲን ሊያጠቁ ይቅርና ቴዲ ጎልቶ የሚታይ ችግር ቢኖርበትም እንኳ ቴዲ በትልቁ ማንነት በኢትዮጵያዊነት ላይ እየተጫወተው ካለው ጉልህና ጠቃሚ ሚና አንጻር ችግሩን አይተው እንዳላዩ በመሆን የሚደግፉት፣ የሚያበረታቱት ይሆኑ ነበር እንጅ የሆነ ያልሆነ ነገር እየቀበጣጠሩ ምክኒያታዊ በመምሰል ቴዲን ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት አያደርጉም ነበር፡፡ ቴዲ አዘውትሮ አልበሙን (የዘፈን ጥራዙን) ትንሣኤን አስታኮ የሚለቅበት ምክንያት ትንሣኤ!” የሚለው ቃል የያዘው ምሥጢርና መልእክት ስለሚመስጠው፣ የሀገሩን ትንሣኤ አጥብቆ ስለሚመኝ ነው እንጅ ሌላ ምንም አይደለም፡፡ ይሄንንም በሥራዎቹ ላይ ቃል በቃል አንጸባርቋል፡፡

ይሄንን ካልኩ በኋላ እስኪ የእነኝህን አስመሳይ ቅጥረኞች ትችት እንፈትሸው! ትችታቸው ምን ያህል ተጨባጭነት አለው? እውን እነሱ እንደሚሉትስ ዘፈን ኃጢአት ነውእንዳየኋቸው ትችታቸው ምንም ደርዝ የሌለው፣ በጥራዝ ነጠቅ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ባዶ ጩኸት ነው፡፡ ለዚህ ነው ከላይ ምንም በማያውቁት ነገር ላይ በመቀበጣጠርስል የተናገርኩት፡፡ ጥራዝ ነጠቅነታቸው ምንድን ነው? ካላቹህኝ፡፡ የጠቀሱትን የእግዚአብሔር ቃል ምንነት ወይም ትርጉም አለማወቃቸው ነው፡፡ አዎ! ቃሉ ዘፈን ኃጢአት ነው ይላል!” ሃፂአት አይደለም ያልኩት፡፡ ጥራዝ ነጠቅነታቸው ከዚህ ቃል አጠቃቀም ይጀምራል፡፡ እኔ ሃፂአት ያሉትን ቃል ብቻውን ባገኘው ኖሮ ምን ማለት እንደሆነ አላውቀውም ነበረ፡፡ ይህ ቃል አማርኛም አይደለም ግእዝም አይደለም፡፡ ሃፂአት ሳይሆን የሚባለው ኃጢአት ነው የሚባለው እሽ? “ዘፋኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም!” ይላልም ቅዱስ ቃሉ፡፡ እነ ጥራዝ ነጠቅ ዘፈንወይም ዘፋኝመባሉን ብቻ ነው ያዩት፡፡

እነ ጥራዝ ነጠቅ ሆይ! እንደዛማ እንዳንል መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን በዘፈን አመስግኑት!” ይል አይደለም ወይ? መዝ. 1493, 1504 እንዲሁም ደግሞ አምላክ እንደልቤ ያለውን ቅዱስ ዳዊትን ከእስራኤል ጎበዛዝት ጋር ሆኖ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ልብሱ እሲኪወልቅ ድረስ ዘፈነ!” ይለዋልና ነቢየ እግዚአብሔር ንጉሥ ዳዊት ይሄንን በማድረጉ ኃጢአት ሠርቷላ እንግዳው? ቃሉ ግን በፍጹም እንደዛ አይልም፡፡ ከየት አመጣቹህት እናንተ? ዳዊት በመዝፈኑ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ማግኘቱን፣ መባረኩን፣ ዳዊንትን በመዝፈኑ ያሽሟጠጡት ደግሞ መቀሰፋቸውን ነው የሚናገረው፡፡ 2ኛ ሳሙ. 6 12-23 ሌላም መጨመር ካስፈለገ መጽሐፍ ቅዱስ የሙሴ እኅት ማርያም በአስረሽ (ጠብቆ ነው የሚነበበው ከፍ አድርገሽማለት ነው ትርጉሙ) በአስረሽ ምችው ከበሮዋን እየደለቀች እንደዘፈነች ይነግረናል፡፡ ነገር ግን ቃሉ የሙሴ እኅት ነቢይቷ ማርያም ይሄንን በማድረጓ ተባረከችበት አለ እንጅ ኃጢአት ነው የሠራችው ስለዚህም ተቀሰፈች አላለም? ዘጸ. 15 20-21 ከዚህም ሌላ በልዩ ልዩ የደስታ ጊዜ በዘፈን ደስታን መግለጥ አግባብ እንደሆነ ጌታ በወንጌል ተናግሯል ሉቃ. 15 11 – 32 ላይ የጠፋው ልጅ ስለመመለሱ በምሳሌ ባስተማረው ትምህርት፡፡
እናም እነጥራዝ ነጠቅ ሆይ! ዝም ብላቹህ እየቀባጠራቹህ የሰው ስም ከማጉደፋቹህ በፊት ጠይቁ እሽ? ለነገሩ እያጠፋቹህ ያላቹህት በዓላማ ነውና እውነቱን እንድትረዱ ቢደረግም የምትታረሙ አይደላቹህም፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ መልእክትና ትምህርት ዘፈንና ዘፋኝነት ኃጢአት የሚሆነው ዝሙትና እርኩሰት ከተሰበከበት፣ ለባዕድ አምልኮና ለጣዖት ከቀረበ ብቻና ብቻ ነው እሽ? ከዚያ ውጭ ግን ስለ ሀገር ቅዱስ ዳዊት ስለኢየሩሳሌም ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ ባላስብሽ ምላሴ ከትናጋየ ትጣበቅ!” እያለ እንዳዜመው ሁሉ ስለ ቅድስት እናት ኢትዮጵያ ብታዜም ብትጨፍር ብታቅራራ ብትፎክር መሳ. 11 34 , 1ኛ ሳሙ. 18 6 ፣ ከላይ እንደጠቀስኩት ስለ እግዚአብሔር ድንቅ ሥራዎች ብትዘፍን፣ በሕግ ስላገባሀት ሚስትህ ወይም እጮኛህ ውበት ደግነት አስተዋይነትብታዜም፣ ስለ እምትወዳት እናትህ ብትዘፍን፣ ስለ ተከበረና ነውር ነቀፋ ስለሌለበት ባሕል ብትዘፍን፣ ስለማኅበራዊ ችግሮች ጉዳትና ጥቅም ብታቀነቅንና የሚያንጽ መልእክት ብታስተላልፍ፣ ስለ መልካምነት፣ ስለ መተሳሰብ፣ ሕግን ስለማይጥስ ትክክለኛ ፍቅር፣ ስለመረዳዳት፣ ስለመተባበር ስለሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ብትዘፍን እንደ ቅዱስ ዳዊትና እንደ የሙሴ እኅት ማርያም በእግዚአብሔር ዘንድ ክብር ሞገስና ዋጋ የሚያሰጥ አገልግሎት ነው እንጅ በፍጹም በፍጹም ኃጢአት     አይደለም፡፡

እንዲህ ብየ ስል ግን እነኝህ ዓይነት ዘፈኖች ኃጢአት አይደሉም አልኩ እንጅ ዘወትር ከዓመት እስከ ዓመት የምናደምጣቸው፣ የምንዘፍናቸው፣ የምናቅራራቸው፣ የምንፎክርባቸው፣ የምንደነክርባቸው ናቸው አላልኩም፡፡ ለሁሉም ነገር ሥርዓት ሥርዓት አለው፡፡ ዝም ብሎ ልጓም ገደብ የሌለው ልቅ የሆነ ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ በዚህ በያዝነው የጾም ወቅት ወቅቱ የሱባኤ፣ የሐዘን፣ የለቅሶ፣ የንስሐ፣ የምሕላ ወቅት በመሆኑ ኃጢአት አይደሉም ያልኳቹህ ዘፈኖችም ሆኑ የቸብቸቦ የወረብ መዝሙሮች ማድመጥም ሆነ ማዜም አይፈቀድም ክልክል ነው፡፡ የሚፈቀደው ጭብጨባና እልልታ የሌለባቸው የንስሐ መዝሙሮች ብቻ ናቸው፡፡ በዚህ በሱባኤ በጾም ወቅት ቅዱስ ዳዊት እስትንፋስ ያለው (ነፍስ ያለው) ፍጥረት ሁሉ እንደ ክሕሎቱ እንዲያመሰግን ከተናገረው ቃል ጋር፤ የሰው ልጅ ደግሞ በመዝ.150 ላይ አምላኩን እንዲያመሰግንባቸው የተጠቀሱት ጸናጽል፣ ከበሮ፣ መሰንቆ፣ መለከት፣ እምቢልታ እነኝህ የመዝሙር ወይም የማኅሌት መሣሪያዎች ሁሉ ግምጃ ቤት ተከተው ነው የሚቆዩት፡፡ የሚፈቀደው በገና ብቻ ነው፡፡ ሱባኤው ሲያልቅ ነው ተከተው ከሰነበቱበት የሚወጡት፡፡ ሱባኤው ሲያልቅ ግን ከዕለተ ትንሣኤ ጀምሮ ተከልክሎ የቆየው ዕልልታው፣ ጭብጨባው፣ ቸብቸቦው፣ ወረቡ፣ የመዝሙር መሣሪያዎቹ ሁሉ ይወጡና ቸብቸቦውን፣ ወረቡን፣ ዘፈኑን በማቅለጥ እግዚአብሔርን ማመስገን፤ ከላይ የጠቀስኳቸውን ኃጢአት አይደሉም!” ያልኳቹህን ዘፈኖችንም በተቀሩት የፈረንጅ የዘፈን መሣሪያዎች እያደመቅን መዝፈን መደሰት ይቻላል፡፡ ይሄነው ሥርዓቱ፡፡

ጥሬ ቃል ብቻ ከጠቀስንማ እንግዳውስ መመኘትም፣ መብልም፣ ገንዘብን መውደድም ወዘተረፈ. ኃጢአት እንደሆኑ ተጽፏልና ጽድቅን ወይም የእግዚአብሔርን መንግሥትንም አትመኝ፣ መብልንም አትብላ፣ ገንዘብ በዞረበትም አትዙራ እንግዲይው? እንዲህ ቢሆን ትክክል ይሆናል? አየ እነ ጥራዝነጠቅ! ይሄንን ያህል ብፅዕና ካላቹህ ታዲያ እዚህ ምን ትሠራላቹህ? “ለእኔ ሊሆን የሚወድ እራሱን ይጣል መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ!” ብሏልና ቅዱስ ቃሉ እንደ መናኞቹ እራሳቹህን ጥላቹህ መስቀላቹህን (መከራቹህን) ተሸክማቹህ ክርስቶስን ተከተሉ እንጅ እዚህ ምን ያስመጠምጣቹሀል ታዲያ? አስመሳይ ፈሪሳዊ ሁላ! ይሄኔ እኮ እንዲህ የምትመጻደቂና የምትፈርጂ እያንዳንድሽ የሕይዎት መዝገብሽ ቢገለጥ በስንት እርኩሰት የምትገሚና የምትከረፊ ትሆኚ ይሆናል፡፡

ሌላው የገረመኝ የእነኝህ አስመሳይ ቅጥረኞች ነገር ደግሞ ምንድን ነው መሰላቹህ፦ ችግራችን ነው ያሉት በዕለተ ትንሣኤ ወይም በዳግሚያ ተንሣይ ዘፈኑ ለምን ይወጣል? ለምን ከትንሣኤ በዓል ውጪ አይሆንም?” የሚል መሆኑ ነው፡፡ አቤት አቤት ክርስትናው እንዴት አድርጎ ጠልቆ ገብቷቸዋል ባካቹህ? ከትንሣኤ ውጭ ቢሆን ችግር የለባቸውም፡፡ ወንድም ክርስትና የበዓላት ሕይዎት ብቻ አይደለም፡፡ አንድን ነገር ኃጢአት ነው ካልከው በበዓላት ቀናት ብቻ ሳይሆን በዓል ባልሆነ በማንኛውም ቀንም መቸም ቢሆን ልትርቀው፣ ከማድረግ ልትቆጠብ ነው የሚገባህ እንጅ በዓል ነው በዓል አይደለም ልትል አትችልም! ክርስትና ማለት ይሄ ነው እሽሌላኛው ገጣሚ ነኝ ባይ የሚናገረውን የማያውቅ ንክ ደግሞ ተነሣና ቴዲን ለተቃወመው መልስ ሰጠሁ ብሎ ነገር  አላበለሻሸም መሰላቹህ! ጽሑፉን አስረዝሜባቹሀለሁና ከተናገረው አንዷን ብቻ ልጥቀስ፦ ቴዲእንደ ሜሮን ለረከሰው ሥጋችን መድኃኒት የሚሆን ጥበብን የተቸረ፣ እንደናርዶስ ለሚገለማው ስብእናችን ማርከሻ ጠረን የሚሆን፣ እንደ ዮርዳኖስ ጠበል ለሚከፋፈል መክፈልት በሽታችን ድኅነት (መዳኛ) የሆነ ነው!” ብሎ አረፈው፡፡ ይሄንን ሁሉ ካለ በኋላ ቴዲ ክርስቶስ ነው አለማለቱ ገርሞኛል፡፡ ይሄንን አቅለ ቀላል ገለባ ከቃሉ እንደታዘባቹህት ሲበዛ ግብዝ ብቻ አይደለም ደንቆሮና መናፍቅም ነው፡፡ እንዴት እንደ ሜሮን ለረከሰው ሥጋችን” ይላል? ሜሮን የትና መቸስ ነው የረከሰ ነው የተባለው? እንዴት እንደ ናርዶስ ለሚገለማው ስብእናችንይላልናርዶስ የትና መቸስ ነው ይገለማል የተባለው? እንዴት እንደ ዮርዳኖስ ጠበል ለሚከፋፈል መክፈልት በሽታችን” ይላል! የዮርዳኖስ ጠበል የተከፋፈሉ ወንዞች አንድነት የሚፈጥሩበት ወንዝ እንደመሆኑ መንፈሳዊ ምሳሌነቱ
የአንድነት እንጅ የት ቦታ ነው የመለያየት የመከፋፈል ምሳሌ ሆኖ የተነገረውአንባብያን ሆይ! ሜሮን ማለት ምን መሰላቹህ? ከከርቤ የሚወጣ የሚቀመም መዓዛው የሚመርክ የሚመስጥ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውል ሽቱ ነው፡፡ ናርዶስም ናርዶስ ከተባለ ተክል የሚወጣ የሚቀመም መዓዛው እጅግ የሚማርክ የሚመስጥ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውል ሽቱ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት ለአገልግሎት ከመብቃታቸው በፊት ተባርከው ለአገልግሎት የሚበቁት በእነኝህ የተቀደሱ ሽቱዎች ተረጭተው ከተቀደሱ ከከበሩ በኋላ ነው፡፡ እነኝህን የከበሩ የተቀደሱ የቤተክርስቲያን ሀብቶችን ነው እንግዲህ ይሄ ጭንጋፍ እንደ ሜሮን የረከሰ፣ እንደ ናርዶስ የሚገለማእያለ የመጥፎ ነገር ምሳሌ ሊያደርጋቸው የጣረው፡፡ ይሄ ጤነኝነት ነውከያኔ (Artist) ቴዎድሮስ ካሳሁን መፍራት መሸሽና መጠንቀቅ ያለበት እንደዚህ ዓይነቱን ጋኔን የሚጋልበውን ግብዝና አቅለ ቀላሉን ነው፡፡ ቴዲ እነኝህ ዓይነቶችን የአጋንንት ፈረሶች እህ ብለህ ከሰማሀቸው በውዳሴ ከንቱ አንተነትህን አስረስተው ልክ አምላክ እንደሆንክ እንዲሰማህ ሊያደርጉህ ሁሉ ይችላሉና በዚህም ነፍስህንም ሥጋህንም በማርከስ ውድቀት ላይ ሊጥሉህ ይችላሉና እጅግ ተጠንቀቃቸው፡፡ ከአጠገብህ አታድርሳቸው፡፡

ለማንኛውም፣ ለቅጥረኛውም፣ ለአስመሳዩም፣ ለአድርባዩም፣ ለንኩም ለምኑም ልቡና ይስጥልና! ሌላ ምን እንላለንቴዲሻም ያበርታሽ! በተነቀፍሽ ቁጥር አንድጊዜ በመጽሔት ሌላጊዜ ይሄው አሁንም በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ እንዲህ እያስለፈለፍሽኝ ያልረባ ሥራ ቀላቅለሽ ላግኝሽና ዋ!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.co