March 30, 2017

የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት የወለዳቸው ተስፋዎችና ስጋቶች

አዲስ ከድሬዳዋ

(ይህ ፅሑፍ የተፃፈው ከሳምንት በፊት ነበር፤ የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮትን በመደገፍ፡፡ ፅሑፉን ለሪፖርተር ልኬው ነበር፤ ባለፈው እሁድ ሳያወጡት ሲቀሩ፣ በመሃል ግን በእንቅስቃሴው አማራ ክልልም ስለተቀላቀለ ፅሁፉ ባይወጣ ይሻላል ብዬ አስቀርቼዋለሁ፤ ሆኖም ድካሜ ከንቱ ከሚቀር በሚል እዚህ አውጥቼዋለሁ፡፡

(ትንሽ ረዘም የሚል ፅሑፍ))————-

አወዳይ ከጥቂት አመታት በፊት በሐሮማያ ወረዳ ስር ያለች አንዲት ትንሽ ቀበሌ ነበረች፡፡ አሁን ከተማዋ ከሐረርጌ ከተሞች ምናልባት ከጭሮ (አሰበ) ቀጥሎ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ነች፡፡ ከተማዋ ለሀገሪቱ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር አመታዊ ገቢ የሚያስገኝላት የጫት ቢዝነስ ማዕከል ነች፡፡ የጫት ቢዝነስ ተዋናዮቹን የአውሮፕላን ባለቤት እስከማድረግ የሚደርስ ትልቅ ቢዝነስ ነው፡፡ ሌሎቹ የቢዝነሱ ተዋናዮችም እንደየደረጃቸውና ሚናቸው ተጠቃሚ ናቸው፡፡ አሁን የአወዳይ ከተማ በእሷ ደረጃ ካሉ ሌሎች የሐገራችን ከተሞች ሁሉ የበለጠ በርካታ ሚሊየነሮች የሚኖሩባት ከተማ ነች፡፡ የአወዳይ ሚሊየነሮችና ሌሎችም የመካከለኛ ገቢ ባለቤቶች በእነሱ ደረጃ እንዳለ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የኢንተርፕርነርሺፕ ክህሎታቸው ውስን ነውና ገንዘባቸውን ቅንጡ መኖሪያ ቤት በመገንባት፣ መኪና በመግዛት፣ ወይም ባለ3 ወይም 4 ፎቅ ህንፃ በመገንባት እና በመሳሰሉት የተለመዱ ዘርፎች ላይ ነው የሚያዉሉት፡፡ በነገራችን ላይ ከአወዳይ ባሻገር እስከምዕራብ ሐረርጌ ድረስ ያሉ የተወሰኑ ወረዳዎች በጫት ወጪ ንግድ ተሳታፊ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባና አካባቢዋን የጫት ገበያንም ቀላል በማይባል ደረጃ የተቆጣጠረው ሐረርጌ ነው፤ . . . ሐረርጌ ከጫት ባሻገር የሀገሪቱ ምርጥ የሚባለው ቡና አምራች አካባቢም ነው፡፡

ግን ሌላ ተቃራኒ ሐቅም አለ፤ ሐረርጌ ከሌሎቹ የኦሮሚያ አካባቢዎች በላይ የምግብ ዋስትና ችግር ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ከፍተኛ የመሬት ጥበት ያለበት አካባቢ ነው፡፡ በዚህም መሬትም ስራም የሌላቸው ወጣቶች የሞሉበት አካባቢ ነው፡፡ እነኚህን ተቃራኒ እውነታዎች ማስታረቅ የመንግስት ሐላፊነት ነበር፤ በተለይ ግራ ዘመም የሆነው ኢህአዴግ በዚህ ጉዳይ ላይ “ቀኝ ዘመሞች ቢሆኑ የማያደርጉትን” እርምጃ መውሰድ ነበረበት፤ ግን አልወሰደም፡፡ አወዳይ ላይ በተወሰኑ ሰዎች እጅ ብዙ ሚሊዮን ብር አለ፤ ይሄ ብር ግን ለብዙሀኑ የሐረርጌ ምንዱባን የስራ እድልን ሊፈጥር በሚችልበት ሁኔታ አይደለም ኢንቨስት እየተደረገ ያለው፡፡

እዚህ ጋ ነው የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት የዘገዬ ቢሆንም አስፈላጊነቱ የሚታዬን፡፡ ብዙም የኢንተርፕርነርሺፕ ክህሎት የሌላቸው ሚሊየነር አርሶ አደሮችና ከተማ ቀመሶች ከለመዱት ዘርፍ ዉጪ ለብዙ ሺዎች የስራ ዕድልን ሊፈጥሩ በሚችሉ እና ዘመን ተሸጋሪ በሆኑ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች መሰማራት የሚችሉት ሐሳብ የሚያመነጭላቸውና የሚያስተባብራቸው ካለ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኦሮሚያ እየሔደበት ያለው አቅጣጫ ሌሎች ክልሎችም ሊማሩበት የሚገባ ይመስለኛል፡፡
የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት መቀጣጠልን ተከትሎ ብዙ ድምፆች እየተሰሙ ነው፤ አብዛኞቹ ድምፆች የተስፋና የማበረታቻ ናቸው፡፡ ጥቂት የስጋትና የትችት ድምፆችም አሉ፡፡ ከስጋት አንጻር እየተነሱ ያሉ ድምፆች የኢኮኖሚ አብዮቱ ሲጀመር ምንም እሴት የማይጨምሩ የማዕድን ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች መሬት ነጠቃና የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የፑሚስ ግብዓት በፋብሪካው በራሳቸው መሆኑ ቀርቶ በተደራጁ የኦሮሚያ ወጣቶች እንዲቀርብ መደረጉ ላይ የተመሰረቱ ናቸው (የታሰሩት ሳይፈቱ፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች እንደዚህ ሳይሆኑ፣ እንደዚያ ሳይሆኑ፣ . . . የሚሉና ከኢኮኖሚ አብዮቱ ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን አጀንዳዎች እዚህ ጋ አናይም)፡፡

መሬት የተነጠቀባቸው ሰዎች ህገመንግስታዊ መብታችን ተጣሰ እያሉ ሲሆን አቅም ያላቸው ባለሃብቶች አቅምና ቴክኖሎጂው በሌላቸው ወጣቶች ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውን መንግስት እንዲያበረታታላቸው መጠበቃቸው ትክክል አይመስለኝም፡፡ ባይሆን ውሳኔው ድንገተኛ ነውና የመዘጋጃ ጊዜ እንዲሰጣቸው ፤ ወይም የስራ ዘርፍ ሲቀይሩ አስፈላጊው ማበረታቻና እንደሁኔታው ካሳም እንዲታሰብላቸው ቢጠይቁ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡
በዚህ ረገድ ኢህአዴግ ማህበራዊ መሰረቶቼ ናቸው የሚላቸውን አርሶአደሮችን፣ የከተማ ንዑስ አምራቾችንና ላብአደሮችን የረሳ በሚያስመስል ሁኔታ በ”ማህበራዊ መሰረቶቹ ላይ” አንዳንዴ የቀኝ ሃይሎች እንኳ የማያደርጉትን ጫና ሲፈጥርባቸው ይስተዋላል፡፡ እዚህ ግባ በማይባል ካሳ አርሶአደሮች እና የከተማ ነዋሪዎች ከይዞታቸው እየተፈናቀሉ መሬታቸው ለባለሃብቶች ይሰጥባቸዋል፡፡ 30 ወይም 100 የከተማ ወይም የገጠር ነዋሪዎች ተፈናቅለው መሬቱን ያገኘው “ኢንቨስተር” ፎቅ ገንብቶ ቢሮዎችን በማከራየት ወይም የሸክላ አፈር ቆፍሮ በመሸጥ የራሱን ኑሮ ሲቀይር፣ በስራ እድል ፈጠራ ወይም በኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ግን የሚጫወተው ሚና ሳይኖር የቆዬ ቢሆንም ቡራኬውን ያገኘው ግን ከ”ግራ ዘመሙ” ኢህአዴግ ነበር፤ ማህበራዊ መሰረታቸውን መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ላይ ያደረጉ በርካታ ምዕራባውያንም ሆኑ ወደብልጽግና እየተንደረደሩ ያሉት ምስራቃውያን ፓርቲዎች እንኳ በዚህ ደረጃ አቅም የሌላቸው የመሬት/ ቤት ባለይዞታዎችን ሲጫኑ አይታይም፡፡

አእላፍ ምንዱባን ከመሀል ከተማ እየተፈናቀሉ በእነሱ ቦታ ላይ “ኢንቨስተሮች” ህንፃ ገንብተው እንዲያከራዩ ከመፍቀድ የመሬት ባለቤቶች በማህበር ተደራጅተው ባንክም ብድር አመቻችቶላቸው ህንፃውን እንዲገነቡ ቢደረግ እውነተኛ ህዝባዊ ወይም ግራ ዘመም መንግሥት ያስብላል፡፡ በዚህ ረገድ ደኢህዴን ኢህአዴግ በሐዋሳ ከተማ የመሬት ባለይዞታዎች ከባንክ ብድር እየተመቻቸላቸው የሚከራዩ ቤቶችን እንዲገነቡ እና የኢንዱስትሪ ፓርክ የጠራቸው አዳዲስ ነዋሪዎች በቤት እንዳይቸገሩ የጀመረውን አቅጣጫ ማጠናከርና ድጋፉ ለትላልቅ የቢዝነስ ህንፃዎችና ሪልስቴቶች ግንባታ ጭምር ተፈፃሚ መሆን እንዲጀምር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በገጠርም እሴት በማይጨምሩ የማዕድን ዘርፎች ተሰማርተው በርካታ ምንዱባን ሊሰሩ የሚችሉትን ብቻቸውን ሲሰሩ የነበሩ “ኢንቨስተሮች” የእስከዛሬው ቡራኬ ኢህአዴግ ማህበራዊ መሰረቶቹን በመዘንጋት የተፈጠረ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንዲያውም ይሄው እርምጃ ወደከተሞችም ሊገባ እንደሚችል/ እንደሚገባ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
የግዙፎቹ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ግብዓት አቅርቦት በተመለከተ ፋብሪካዎቹ በራሳቸው ለመስራት ግሬደሮችን፣ ገልባጮችንና ሌሎችንም አስፈላጊ ግብዓቶች አሟልተው ሲሰሩ የነበሩ ከመሆናቸው አንፃር፣ ሰራተኞቻቸውም ስራውን ለረጂም ጊዜ የለመዱትና የተካኑበት ከመሆናቸው አንጻር ብዙም ደስተኛ ባይሆኑ አይገርምም፡፡ እነሱ ላይ የሚፈጠር ቅሬታ ደግሞ በቀላሉ ሚዲያዎችና አለምአቀፍ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ጆሮ ሊደርስ መቻሉን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ በንድፈሃሳብ ደረጃ የግብዓት አቅርቦቱን ወጣቶች ተደራጅተው መስራታቸው ተገቢ ቢሆንና የግብዓት መሸጫ ዋጋውም ፋብሪካዎቹ በተስማሙበት መጠን ቢሆንም አፈፃፀሙ ላይ መንጠባጠቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ፣ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ፉክክር ባለበት የሲሚንቶ ገበያ ላይ በኦሮሚያ ያሉ ፋብሪካዎችን ተወዳዳሪነት አነሰም በዛ ሊጎዳ እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህ ላለመሆኑ ዋስትና መስጠት ከተቻለ ኦህዴድ ኢህአዴግ በነደፈው አቅጣጫ በሺ የሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል፤ ፋብሪካዎቹን የጎሪጥ የሚያይም አይኖርም፡፡ ሒደቱን ግን በጥንቃቄ መከታተል እና ከፋብሪካዎቹ ማኔጅመንት ጋር ተቀራርቦ መስራት ይጠይቃል፡፡

በኦሮሞ የኢኮኖሚ አብዮት ላይ በይፋ እየተሰሙ ያሉ ስጋቶች እነኚህ ብቻ ቢሆኑም ትኩረትን የሚሹ ሌሎች ነጥቦችም ይኖራሉ፡፡
የመጀመሪያው ሐገሪቱ ወደኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን መሸጋገር ካለባት ከአንድ ኢንቨስተር እንዲመጣ የምንጠብቀውን ገንዘብ ከብዙ ሺ ነዋሪዎች በመሰብሰብ በራስ አቅም ግዙፍ ኢንቨስትመንቶችን መፍጠር ፋይዳው የስራ ዕድል ከመፍጠር ያለፈ ነውየነገዋ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጥቂቶች እጅ ስር አለመሆኑን ከወዲሁ የምናረጋግጥበትም ጭምር ነው፡፡ በሐገር አቀፍ ደረጃም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሆኖም በዚህ ረገድ ከዚህ በፊት ምንም አልተሰራም ማለት አይደለም፡፡
የዛሬ 10 ዓመት ገደማ የአክሲዮን ማህበራትን ማቋቋም አጓጊና ብዙዎችን የሳበ ቢዝነስ ሆኖ ነበር፡፡ አሁን የምናያቸው ስካይ ባስና አሊያንስ የከተማ አውቶብስ በዚህ መንገድ የተቋቋሙ ናቸው፡፡ የቅርብ ጊዜዎቹ 3 ቢራ ፋብሪካዎችም መሰረታቸው የአክሲዮን ቢዝነስ ነው፡፡ እስካሁን ከዳር ባይደርሱም የህብር ስኳርና የሐበሻ ሲሚንቶም ሌሎቹ ተጠቃሽ አክሲዮን ወለድ ቢዝነሶች ናቸው፡፡ 
መንግስት ይህንን ዘርፍ በማጠናከር በርካታ ግዙፍ ኢንቨትመንቶች እንዲፈጠሩ ማድረግ ሲገባው ዜጎች በአክሲዮን በሚቋቋሙ ቢዝነሶች ላይ አመኔታ እንዳይኖራቸው የሚያደርጉ ተደራራቢ መሰናክሎች ተፈጥረውባቸዋል፡፡ የፌደራልም ሆነ የክልል ማህበራት ማደራጃዎች በዚህ ረገድ ሲጫወቱ የነበረው ሚና ለብዙ ትችቶች የተጋለጠ ነው፡፡ መንግስት በቅርቡ በዚህ ረገድ የነበሩ ክፍተቶችን ለመድፈን የሚያስችሉ እርምጃዎችን እወስዳለሁ እያለ ሲሆን እርምጃው ማህበራትን ከመደገፍ አልፎ የሐገሪቱ ግዙፍ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች በጥቂት ግለሰቦች ሳይሆን በብዙሃን ዜጎች ባለቤትነት ስር እንዲሆኑ የማድረግ ያለማድረግ ጉዳይ ጭምር መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት የምር ለውጥ ሊያመጣ ይገባል፡፡
እስከዛሬ ኢህአዴግ ህዝባዊ መሰረቶቼ ለሚላቸው ከተሜዎች ያመቻቸላቸው በጥቃቅንና አነስተኛ መደራጀትና አሁን ደግሞ በከተማ ሴፍቲኔት መታቀፍን እንጂ ትላልቆቹ ቢዝነሶች ላይ መሰማራትን ሳይሆን መቆየቱ ያሳዝናል፡፡ ይህንን ግዙፍ ስህተቱን ሊያርም የሚችበት ዋነኛ መንገድ ነው የአክሲዮን ቢዝነስ እንዲያብብ ማድረግ፡፡ 
የኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮት የወለዳቸው ግዙፍ ኩባንያዎችም በዚህ ረገድ ከተጋረጠባቸው ስጋት ነፃ ማድረግ ከኦህዴድኢህአዴግ ይጠበቃል፡፡ የመንግስት ባለስልጣናት አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት መቅረት፣ የአክሲዮን ማህበራቱ ማኔጅመንቶች አቅምና ተዓማኒነት ደግሞ አስተማማኝ መሆን አለበት፡፡ ከኦሮሚያ ኩባንያዎች ጋር ተያይዞ ትኩረት የሚያሻው ሌላው ስጋት ደግሞ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መረጣ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ አንዳንድ ዘርፎች በገበያው ውስጥ አስቀድሞ በቂ ተዋናይ የተሰማራባቸው ናቸው፡፡ ለዚህም የሲሚንቶ ፋብሪካንና የትራንስፖርት ቢዝነስን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የቢዝነስ ዘርፎቹ በክልሉ ተወላጆች በጎ ፈቃደኛ ምሑራንና በክልሉ አመራሮች የሚደገፍ ከመሆኑ አንፃር፣ እንዲሁም ዘርፎቹ የግዙፍ ካፒታል ባለቤቶች ከመሆናቸው አንፃር ብዙም ባልተደፈሩ፣ ግን አዋጪ በሆኑ ዘርፎች ላይ መሰማራትንም ቢታስብበት መልካም ይመስለኛል፡፡

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የክልል ኢንዶውመንቶችም ሊነሳ የሚችለው ስጋት የሐገሪቱን አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ የመፍጠር ራዕይን ሊሸረሽር በሚችል መልኩ ቢዝነሶቹ ብሔር ተኮር እየሆኑ የመቋቋማቸው ጉዳይ ነው፡፡ ስጋትነቱ ከሐገሪቱ ራዕይ ባሻገር የተቋማቱንም በነፃ ፉክክር ላይ የተመሰረተ ገበያን የማስፋት ጥረትንም ሊጎዳ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ ነገ ምን አይነት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ጥረት እያደረግን ነው የሚለውን ማሰብ ከሁሉም ይጠበቃል፡፡ አንዱ ከጀመረ ግን ሌላውም መከተሉ አይቀሬ ነውና በዚህ ረገድ ኦሮሚያን መውቀስ አይቻልም፡፡
በተረፈ አሁን በመላ ሀገሪቱ እየተቋቋሙ ካሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል የ49 ፐርሰንት ድርሻቸው ልምድ ባላቸው የውጭ ባለሃብቶች የሚያዙ ግዙፍ የኢንዱስትሪ አክሲዮኖች እየተቋቋሙ በየእጃችን ያለውን ገንዘብ አክሲዮን እንድንገዛበት የማህበራት ማደራጃም ይሁን ሌላ አካል ቢሰራ የሐገሪቱ ቁጥር አንድ ባለውለታ ይሆናል፡፡ የባንግላዴሽ፣ ቻይናና ሌሎች የምስራቅ እስያ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎችን ሎቢ እያደረጉ በሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ እንዲሰማሩና 51 ፐርሰንት ድርሻቸውን ደግሞ በአክሲዮን እንዲሸጡ ማድረግ ከተቻለ በሐገራች የጨርቃጨርቅ ቢዝነስ ላይ እመርታዊ ለውጥ ማምጣት ያስችላል፡፡ በሌሎች ዘርፎችም ላይ ተመሳሳይ ስራዎን መስራት ያስፈልጋል፡፡ ህብረተሰቡ አመኔታ እንዲያድርበት ማድረግ ከተቻለ ተዓምር መስራት ይቻላል፡፡ የኦዳ አውቶብስ አክሲዮን ማህበር በ1 ቀን ብቻ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ አክሲዮን መሸጡ የሚያሳዬን ይሄንኑ ነው፡፡ ባለሃብቶችን እንጠብቅ ቢባል ኖሮ ይሄን ያህል ካፒታል ያለው ኢንቨስተር በቀላሉ የሚገኝ አልነበረም፡፡