አገራችን ባለፈው ዓመት ካለፈችበት ህዝባዊ ተቃውሞዎች አንፃር ኢሕአዴግ ከህጋዊ አገራዊ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ማድረግ እንደሚፈልግ መግለፁ ለብዙዎቻችን ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል ነበር።

 

ሆኖም በቅድመ ድርድር ሂደቱ ወቅት ኢሕአዴግ ያሳየው አካሄድ ሚጠቁመው ከድርጅቱ አመራር ውስጥ አንዳንዶቹ አገራችን ያለችበትን አደገኛ ሁኔታና ሂደት በአግባቡ ያላጤኑ ፥ አደጋውን አለባብሰው ማለፍ የመረጡ ፥ ብቃትና አቅም የሌላቸው ፅንፈኛ ጥቂቶች ፡ የድርድር ተስፋውን እያጨለሙት መሆኑን ነው።

ኢሕአዴግ ከደርግና ከአፄው ስርዓት ያልተማረው ዋና ቁምነገር ሁሉን ተቆጣጥሮ ፡ ሁልጊዜ እያለባበሱ ማለፍ እንደማይቻል ነው። እስከ መጨረሻው ሰጥቶ መቀበልን ያልፈለገው ደርግ ዛሬ የታሪክ አመድ ሆኗል። በፍጥነት ተሃድሶ ማድረግ ያልፈለገው የአፄው ስርዓት ዛሬ የሚገኘው በጥቂት አረጋውያን ትዝታ ውስጥ ብቻ ነው።

ኢሕአዴግና አባላቶቹ ሊያስተውሉት ሚገባው ፡ በአገሪቱ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ምልክት እንጂ መንስዔ እንዳልሆነ ነው። እሳት ላይ የተጣደ የጀበና ውሃ እሳቱ እስካለ ድረስ መፍላቱንና መንተክተኩን ይቀጥላል።

ገዢው ፓርቲ በተፈበረኩ የስራ ዕድል ቁጥሮች ፕሮፓጋንዳ ፡ በጅምላ እስራትና በ”አይደገምም” የአስገድዶ ቃልኪዳን ማስገባት ፡ ከስሩ የተቀጣጠለውን እሳት በቋሚነት ማስቆም አይችልም። እሳቱ እሳካለ ድረስ ውሃው ደጋግሞ ይገነፍላል።

ለዚህ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ግልፅ ፣ አሳታፊ ፣ ሚዛናዊና በገለልተኛ አካላት የሚመራ ድርድር ማድረግ ብቻ ነው።

ገዢው ፓርቲ ድርድሩ ያለአደራዳሪ ይደረግ ማለቱ የሚያሳየው አንዳንድ የኢሕአዴግ አመራሮች ድርድሩን እንደለመዱት ለፓለቲካ ፍጆታ ለመጠቀም ማሰባቸውን ከመሆኑም በላይ ፡ ባለፉት 25 ዓመታት የታየውን የኢሕአዴግን ‘የኔ መንገድ ብቻ’ አፍራሽና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው።

ይህ የኢሕአዴግ አንዳንድ ፅንፈኛ መሪዎች አኪያሄድ በፓለቲካ ድርጅት ያልታቀፉ ፣ ለአገር የሚያስቡ ቅንና የመደራደር ዋጋና ትርጉም የተገነዘቡ ዜጎች ኢትዮጵያ የሏትም ከሚል አስተሳሰብ የተነሳ ሲሆን ፡ ይህ አስተሳሰብ በህዝብ ላይ አመኔታን ካለመጣልና ህዝብን ከመናቅ የመነጨ ነው።

አደራዳሪ የሌለው ድርድር ማለት ዶክተር የሌለው ሆስፒታል ማለት ነው። ውጤቱ ኪሳራ ነው። አገራችን ያለችበት አደጋ የሚታያቸው አስተዋይና አርቆ አሳቢ የኢሕአዴግ መሪዎችና አባላት የራሳቸውንም ሆነ የድርጅቱን ህልውና ማስከበርና ማስቀጠል ሚችሉት ድርድሩን በገለልተኛ አደራዳሪዎች እንዲመራ በማድረግ ብቻ ነው።

ድርድሩ ከፓለቲካ ፍጆታ ያላለፈ ከሆነ ግን በሌሎች አገሮች ያየነውን የህዝብ ሰቆቃ ለመድገም ጥቂቶች የቆረጡ መሆናቸውንና ፡  በኢሕአዴግ ውስጥ ይሄው አፍራሽ አስተሳሰብ የበላይነቱን ይዞ ገዢው ፓርቲ ሌሎች ቀደምት ስርዓቶች የተጎናፀፉትን ውድቀት እየተጠባበቀ መሆኑን ያመላክታል።

ለተተኪው ትውልድ መግባባትን እናውርስ።

ፎረም 65

www.65Percent.org