A
(ከኢትዮጵያ ፈዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የተሰጠ መግለጫ)

የኢህአዴግ አገዛዝ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሕገመንገሥቱና በተለያዩ ሕጎችም የተደነገጉትን እና በተለያዩ ወቅቶች ቃል የገባቸውን ሰብአዊና ዴሞክራሲዊ መብቶች አከባበርና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታን ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ፤
በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር በርካታና እጅግ ውስብስብ የሆኑ ችግሮች አጋጥመውናል፡፡ ለእነዚህ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በሰላማዊ አግባብ ወቅታዊ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ሰላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሰላማዊ አግባብ ሲጠይቁና ሲታገሉ የቆዩ ቢሆንም፤
ከኢህአዴግ ሰሚ ጆሮ ስለተነፈጉ ችግሮቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱና ይበልጥ እየተወሳሰቡ መጥተው፤ ሀገራችንን በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ከተዋት ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሀገራችን በአሁኑ ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተዳደር ስር በኮማንድ ፖስት አማካይነት ሁኔታዎችን ሀይል በመጠቀም ለማረጋጋት በሚሞከርበት እጅግ ፈታኝ ወቅት ላይ እንገኛለን።

ይህም መላውን ህዝባችንን በከፍተኛ ከታጠቀ ሰራዊት ተፅዕኖ ስር ተሸማቅቆ እንዲኖር ያስገደደው አዋጅ አሁንም ለተጨማሪ 4 ወራት መራዘሙ ፤
የመብት ጥያቄ አንስቶ ከፍተኛ መስዋዕት የከፈለውን ህዝብ ቁጣና ምሬት የሚያባብስ እርምጃ እንጂ፤ ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ አይሆንም! ስለሆነም መድረክ አጥብቆ ይቃወመዋል።
****

ሀገራችን ለዚህ ችግር የተዳረገችበት ምክንያት የኢህአዴግ አገዛዝ ለሕዝባችን ሰላማዊ የመብት ጥያቄዎች በሕጋዊ አግባብ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ፋንታ በኃይል ለማፈን መንቀሳቀሱና መድረክና ሌሎችም ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤
የፖለቲካ ምህዳሩን በመዝጋት ኢህአዴግ የፈጠራቸውን ችግሮች በትክክል ነቅሶ በማውጣት ተጨባጭ መፍትሔ ሊያስገኝ የሚያስችል ድርድር ለማካሄድ ለብዙ ዓመታት ሲያቀርቡ ለቆዩት ጥያቄዎች ኢህአዴግ አዎንታዊ ምላሽ ነፍጎ በመቆየቱ ነው፡፡
ከዚህም በላይ ለችግሮቹ መባባስና ይበልጥ መወሳሰብ ዋነኛው ምክንያት፤ ኢህአዴግ የፖለቲካ ምህዳሩን ድርድር ጥያቄዎች በሰበብ አስባቡ ወደ ጎን እየገፋ “የጋራ ም/ቤት ማቋቋም ፤
የምክክር መድረክ ማመቻቸት ወዘተ” እያለ፤ ለማስመሰልና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብቻ ለሚጠቀማቸው መድረኮች ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱ እንደሆነ መድረክ ከተገነዘበው ቆይቷል፡፡ ከዚህም የተነሳ መድረክ ከነሐሴ 2001 ዓ ም ጀምሮ እስከ አሁን ባለው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር በመደራደር ከሁሉ አስቀድሞ የሀገራችንን ተጨባጭ የፖለቲካ ምህዳር ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ውጤታማ ድርድር በማካሄድ ተጨባጭ መፍትሔዎችን ለማስገኘት ሲጠይቅ ቢቆይም፤
ኢህአዴግ ግን በሀገራችን ወቅታዊና ነባራዊ ተጨባጭ የፖለቲካ ችግሮች ላይ በማያተኩሩና ተጨባጭ መፍትሔም በማያሰገኙ ጉዳዮች ላይ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ያህል ከአንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በፈጠረው “የጋራ ም/ቤት እየተወያየሁ ነኝ” እያለ ካለአንዳች ተጨባጭ ውጤት እስከ አሁን ቆይቶአል፡፡ በእነዚህ በከንቱ በባከኑት ጊዜያት የሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ከድጡ ወደ ማጡ እየወረደ በአሁኑ ወቅት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ
አድርሶን ይገኛል፡፡
***

ኢህአዴግ ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ችግሮች ውስጥ ሀገራችንን ካስገባት በኋላ፤
በቅርቡ (ጥር 3 ቀን 2009 ዓ ም) ለሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጻፈው ደብዳቤ ባስተላለፈው ጥሪም፤ በሃገራችን ለተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ መፍትሄው ከመድረክና ሌሎች ሀቀኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መደራደር እንጂ አሁን እንዳደረገው “ለሚደረገው ውይይት ቅድመ-ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችል የምክክር መድረክ …” አዘጋጀሁ በማለት የፕሮፖጋንዳ ስራ ለመስራት ጊዜ ማባከን አልነበረበትም። ሆኖም መድረክ በተጠቀሰው ደብዳቤ ለጥር 10 , 2009 ዓ. ም በተሰጠው ቀጠሮ በስብሰባው ላይ ሊገኝ የቻለው በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ በደብዳቤው ከተጠቀሱት ጉዳዮች የተለየና ተራ ውይይትና ምክክር እየተባለ የሚታለፍ አለመሆኑን በመገንዘብ፤
ሀገራችንንና ሕዝቦቻችንን እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የከተቱትን የፖለቲካ ምህዳር ችግሮች ነቅሶ በማውጣት መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ድርድር በአስቸኳይ ማካሄድ አሰፈላጊ መሆኑን ለኢህአዴግ በማስገንዘብ፤ ስብሰባው “ምክክርና ውይይት” ከሚባል አካሄድ ወጥቶ፤ ወደ ሁነኛ የድርድር አካሄድ ተሸጋግሮ፤ ውጤታማ የሁለትዮሽ ድርድር ማካሄድ እንዲቻል ጥረት ለማድረግ ነበር፡፡ በዚህም ውጤታማ የድርድር አካሄድ ኢህአዴግ በእውን የሚያምንበት ከሆነ፤
በሂደቱ ላይ ህዝባችን ሙሉ በሙሉ እምነት እንዲኖረው የሚያስችሉ የመተማመኛ እርምጃዎች (Confidence Building Measures) እንዲወስድ ለመጠየቅም ነበር ጥሪውን የተቀበለው፡፡ እነዚህኑ ጥያቄዎች በስብሰባው የመጀመሪው ዕለት ለኢህአዴግ በማስገንዘብያነት አቅርበናል ፤
በቀጣዮቹ የውይይት ቀናት ላይም ይህንኑ ስናስገነዝብ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
***
ኢህአዴግ በአስቸኳይ እንዲወስድ ካስገነዘባቸው የመተማመኛ እርምጃዎች ውስጥ፤
በዚሁ ድርድር ላይ በግምባር ቀደምትነት ሊሳተፉ የሚገባቸው የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ዶ /ር_መረራ ጉዲናን ጨምሮ፤
በሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ላይ እያሉ የታሰሩብን የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራር አባላት በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ያቀረብነው ጥያቄ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ይገኙባቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ከኢህአዴግ ጋር ስብሰባ ከተጀመረ ወዲህ ከሁለት ወራት በላይ የቆየን ቢሆንም፤ የጠየቅናቸው የመተማመኛ እርምጃዎች እስከ አሁንም ተግባራዊ አለመደረጋቸው በግንኙነቱ ላይ ተስፋ እንዳይኖር
አድርጓል ፡፡
***
ከዚህም በላይ ካለፉት ውጤታማና ውጤት አልባ ከኢህአዴግ ጋር ድርድሮች ተመኩሮአችን በመነሳት፤
ድርድሩ ተጨባጭ ውጤት ሊያስገኝ በሚያስችል ሁኔታ የሁለትዮሽ እንዲሆንና በገለልተኛ አደራዳሪዎች እንዲመራ ያቀረብነው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም፡፡ ይልቁንም በተግባር ሲታይ አካሄዱ ከላይ በተጠቀሰው ደብዳቤ እንደተመለከተው ሁሉ፤
የ22 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች “የጋራ የውይይት መድረክ” ሆኖ እንዲቀጥል የማድረግ አላማ እንዳለ ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልፈጀብንም ፡፡

ምክንያቱም በመድረክ እምነት የ22 የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዑካን የየፓርቲዎቻቸው አጀንዳዎችና አቋሞችን ይዘው ተራ በተራ የሚጨቃጨቁበት ስብሰባ ወይም ጉባኤ ከመሆን አያልፍምና ነው፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ ቢበዛ የምክክር ወይም የውይይት
ስብሰባ እንደሆነ እንጂ የድርድር ስብሰባ ሊሆን አይችልም፡፡
ስለዚህ ይህ አካሄድ ከተለመደው የድርድር አካሄድ የወጣ ብቻ ሳይሆን ውጤታማ አይሆንም በማለት ያቀረብነውንም ሃሳብ ኢህአዴግ መቀበል አልፈለገም፡፡
***

መድረክ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ እንደመሆኑ እና በፖለቲካ ምህዳሩ መዘጋት ምክንያት ከፍተኛ በደል በራሱ ፤
በመሪዎቹና በአባላቱ ላይ እየደረሰ እንደመሆኑ ፤
ከሌሎች መሰል ፓርቲዎች ጋር ወይም ለብቻቸው፤
የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎቹና ኢህአዴግ በጋራ በሚስማሙባቸው አጀንዳዎች ላይ፤
ከቀሩት ፓርቲዎች ጋርም በጋራ ስብሰባ ላይ እየተወያየ፤
ከኢህአዴግ ጋር የሁለትዮሽ ድርድር የማካሄድ፤
መሪ ወይም ተቀዳሚ ሚና እንዲኖረው ባቀረብነው አካሄድ ላይም ኢህአዴግ መስማማት አልፈለገም፡፡

በዚህ ስምምነት ላይ መድረስ ሳይቻል ከቀረ በኋላም፤ መድረክ በርካታ እራሱ በቀጥታ ከኢህአዴግ ጋር መደራደር ያለባቸው አስቸኳይና አንገብጋቢ ጉዳዮች
እንደሚኖራቸው በሁለትዮሽ ለመደራደር ያቀረበው አማራጭ ሃሳብም አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም፡፡

ይህ የኢህአዴግ አቋም ድርድሩ በሁለትዮሽ
በአስቸኳይ ተካሂዶ ችግሮችን በተጨባጭ ለመፍታት ውጤታማ እንዳይሆን የሚያደርግ ስለሆነ፤
ሲጀመርም ኢህአዴግ የድርድር አጀንዳ እንዳልነበረው
ዳግመኛ ማረጋገጫ ነው።
***

ስለሆነም በዚህ ትክክለኛ የድርድር ባሕሪይ በሌለውና ቀደም ሲል ኢህአዴግና አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሥርተው ከቆዩት “የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት” ከሚባለው አካል ውይይት ጋር በሚመሳሰልና
ውጤታማ ሊሆን በማይችል፤
የ22 ፓርቲዎች ውይይት ሂደት ውስጥ መቀጠል
ተገቢ ሆኖ ስላላገኘነው፤
ከላይ የተጠቀሰውን የሁለትዮሽ የድርድር አማራጭ
ለኢህአዴግ አቅርበን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡

በመሆኑም መድረክ ባቀረባቸውና ፈጣንና ተጨባጭ ውጤቶችን ሊያስገኝ በሚችለው የሁለትዮሽ ድርድር በኢህአዴግና በመድረክ መካከል በአስቸኳይ
እንዲጀመር፤ በኢህአዴግ በኩል ፈቃደኛነቱ በአስቸኳይ እንዲገልፅ አጥብቀን
እንጠይቃለን፡፡

ድል ለሰላማዊ፤ ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ትግላችን!!

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት
መድረክ

መጋቢት 22 , 2009 ዓ ም
አዲስ አበባ