Posted on April 2, 2017

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስተር ደሳለኝ ሃይለማሪያም በፓርላማ ላይ ኤርትራን እስከመቸ ነው የምንታገሳት ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ በቅርቡ ኢትዮጲያ በኤርትራ ላይ የፖሊሲለውጥ እንደምታደርግ መጠቆማቸውን አዋዜ ራዲዮ ሪፖርተር ጋዜጣን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። “ላለፉት 15 አመታት በኤርትራ ላይ የተከተልነው የተመጣጣኝ ፖሊሲእንዳልሰራና አሁን ግን አዲስ ፖሊሲ በቅርቡ ይፋ አድርገን ወደ ተግባር እንገባለን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስተር ሓይለማሪያም ደሳለኝ ለምክር ቤት ተወካዮች በመልስና ጥያቄአስተጋብተዋል።

በሻእቢያና በወያኔ ድርጂቶች ዲሞክራሲያዊ ባልሆነ አመራር እና በወታደራዊ ሃይል ወደ ስልጣን የመጡት ሻእቢያና ወያኔ የኢትዮጲያን ሕዝብና የኤርትራን ሕዝብ ከመለያየታቸው ባሻገር በአመራሮች አለመግባባት ምክኒያት ሁለቱንም ህዝቦች ወደ ትርጉም የለሽ ጦርነት በመክተት ከሁለቱም ወገን ከ120 000 ሕዝብ ማለቁ የአጭር ጊዜ ታሪካዊ ስህተት ነው።

እነዚህ የጠላት መሳሪያ ሆነው ኢትዮጲያን በሚያዳክሙ የአረብ ጠላቶች ተፈጥረውና አድገው ወደ ስልጣን የመጡ አመራሮች ዲሞክራሲያዊ ስርአት መስርተው በአንድነት ለመኖር የሚችሉበትን ወርቃማ እድል እርስ በርሳቸው ከመናናቃቸውና ካለመተማመናቸው የተንሳ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን ከአንድነት ይልቅ ደግሞ መለያየትን የመረጡ መሪዎች ናቸው።

እነዚህ የህዝባቸውን ተጠቃሚነት ሳይሆን በዘርና በስልጣን ላይ ያተኮሩት መሪዎች ወያኔዎች ለራሳቸው የረጅም ጊዜ እቅድ ኤርትራን በፍጥነት በማስገንጠል የኢትዮጲያን ሃብት ያለተቀናቃኝ በመዝረፍ ታላቅዋን ትግራይን በኢኮኖሚ አሳድገው ለመገንጠል አልመው ሲንቀሳቀሱ ሻእቢያዎች ደግሞ የፈጣሪያቸውን የግብፁ የጀማል አብደል ናስርን እቅድ ለመፈፀም ከኢትዮጲያ መገንጠልን መርጠው ተገነጠሉ።

ምንም እንኳን ወያኔና ሻእቢያ አፈጣጠራቸው ትግራይና ኤርትራ የሚባሉ ሁለት ትግርኛ አገሮችን ለመገንጠልና ለመመስረት የተደራጁ ሃይሎች ቢሆኑም ከድል በኋላ በነበረው ሃይል ሚዛን በመሳሪያ ሲያስብ የነበረው ሻእቢያና በረጅም እርቀት ሻእቢያን ካስገነጠለ በኋላ በኢትዮጲያ ሃብት ትግራይን በኢኮኖሚ፤ በወታደራዊ ሃይል እና በቆዳ ስፋት ታላቅዋን ትግራይን ካሳደገ በኋላ ለመገንጠል በረጅሙ ያነጣጠረው ወያኔ በተንኮል ሻእቢያን አሸንፎታል። ይህን ተንኮል ዘግይተው የተረዱት ሻእቢያዎች በአገራቸው ላይ የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ ኪሳራ ለመቀልበስ በደንበር ሰበብ የመጀመሪያው ጦርነት እንደ ተቀጣጠለ አለም ምስክር ነው።

እነዚህ የጥፋት ሃይሎች በዘረኛነት የተሳከሩ ለዲሞክራሲ ሰላምና ለሕዝብ ጥቅም ያልቆሙ መሪዎች ስለነበሩ በእልኸንነት፤ ሼርና ተንኮል ምክኒያት ወደ ትርጉም የሌሽ ጦርነት በመግባት አንዱ አንዱን ለማጥፋት ሁሌም በተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ የተነሳ የምዕራብ ትግራይ የፖለቲካ ባለስልጣናት የሁለቱም ወገን (የኢትዮጲያና የኤርትራ) ተወላጅ የሆኑት እንደ እነ ስብሃት ነጋ፤ ጀኔራል ሳሞራ፤ እነ መለስ ዜናዊ፤ እነ በረከት ስምኦን፤እና ሌሎችም የሕውሐት ባለስልጣና ከበርሃ የትግል ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ስም የሚያወጡት ፖሊሲ ዋና አላማ የወደፊቷን የታቅዋን ትግራይን ጥቅም ማእከል ያደረገ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ከኢትዮ-ኤርራ ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ያተኮረው ትግራይ እስከምትለማ ድረስ (የማትድን ወይንም የማትሞት) ኤርትራን መፍጠር ነበር። በተቻለ መጠን ኤርትራ በኢኮኖሚና በወታደራዊ ሃይል ከወያኔ የተሻለች ሃገር እንዳትሆን አድርጎ በማቆየት ለወደፊቷ ትግራይ ቢቻል በአጋርነት ካልሆነ ግን በወታደራዊ ሃይል ወያኔን የማትፈታተን ደካማ ኤርትራን መፍጠር ነበር። ያለፈው ( ያለጦርነት ያለሰላም) ፖሊሲ ውስጠ ዋና አላማ በወያኔ የበላይነት የምትፈጠር (የትግራይ ትግሪኝት) አገር ለመመስረት በማቀድ የተቀረፀ ፖሊሲ ነበር።

እነዚህ የምእራብ ትግራይ የፖለቲካ ባለስልጣናት ቡድን ከትጥቅ ትግል ጀምረው ለኢትዮጲያዊነት በማድላት በኤርትራ ላይ ጠንካራ አቋም ያላቸውን የትግራይ ልጆች እነ ስብሃት ነጋ አስጨርሰዋል። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ወያኔ ከሁለት የተከፈለው በነስብሃት ነጋ አፍቃረ-ኤርትራ እና በነ ጀነራል ፃድቃን በኤርትራ ላይ ባላቸው ፖሊሲ እና አመለካከት የኢትዮጲያን ጥቅም በማስቀደማቸው ምክኒያት ነበር ከስልጣናቸው የተባረሩትና ወያኔ ከሁለት የተከፈለው። በወያኔ-ኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ ከበርሃ ጀምሮ የኤርትራ ጉዳይ ሲነሳ ሁሌም አሸናፊው የነስብሃት ነጋ ቡድን ነው። ነገር ግን የእነ ስብሃትን ፖሊሲ በኢትዮጲያ ላይ ስለሚኖረው የወደፊት አደጋ አስቀድመው ያስጠነቀቁት እና ከስልጣናቸው የተባረሩት የነ ጀነራል ፃድቃን ቡድን ማስጠንቀቂያ አሁን ራሳቸውን እነስብሃት ነጋን እና የወያኔን መሪዎች ህልውና ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ፖሊሲ መሆኑ ታምኖበታል። አሁን የወያኔ ማእከላዊ አገዛዝ እና የወደፊት ታላቋ ትግራይ አደጋ ያለው እነ ስብሃት ነጋ የትም አይደርስም ሲሉት የነበረው ሻእቢያ ቀድመን ካላጠፋነው እነርሱ (ሻእቢያ) እኛን (ወያኔን) የሚያጠፋ ሃይል ሻእቢያ መሆኑን አረጋግጠዋል። ለኢትዮጲያ የአዲሱ ፖሊሲ ለውጥ መነሻው ይኽ ፖለቲካዊ ክስተት ነው።

የወያኔ አገዛዝ በውስጥና በውጭ ከባድ ተግዳሮት ገጥሞታል። በሃገር ውስጥ ወያኔ ከዚህ በኋላ ወርቅም እንኳን ቢያነጥፍ በአማራውና በኦሮሞው ተቀባይነትን አያገኙም።በውጭ ደግሞ የኤርትራ ጂኦ-ፖለቲካዊ አጋር ግብጽና ሌሎች አረብ ሐገራት ኤርትራን በወታደራዊና በኢኮኖሚ የልብ ልብ እየሰጧት ነው። የወያኔ መሪዎች ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። በሰሜን ከኤርትራ ጋር በምሽግ ለጦርነት ተፋጠዋል። በደቡብ ትግራይ የወያኔ ተስፋፊዎች የአማራውን መሬት በጉልበት ወደ ትግራይ በማካለል የአማራን መሬት እያረሱ በሰላም እንደማይኖሩ በደንብ ገብቷቸዋል። በመሃል ሃገር እነሱ በፈጠሩት የዘረኝነት ፖለቲካ በተያያዘ የጥላቻ ሃውልት እየሰሩ ከአማራ ጋር ሲያጋጩት የነበረው የኦሮሞ ሕዝብ አሁን ነቅተውባቸዋል። የወያኔ አገዛዝ አንገሽግሿቸዋል። በዚህ አጣብቂኝ ውስብስብ የውስጥና የውጭ ውጥረት ተራ በተራ የወያኔ መሪዎች መውጫቸውን ለመፈልግ በመሯሯጥ እና አዲስ ፖሊሲ በመቅረጽ ላይ ይገኛሉ።

በወያኔ አመራር የፖሊሲ ቀራጮች መመዘኛ በአሁኑ ሰአት ለወደፊቷ ታላቋ ትግራይ እጅግ በጣም አስጊ ጠላት ነው ብላ የምትፈርጀው እስከ አፍንጫው የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የሻእቢያን ጦር ነው። ምንም እንኳን ይህ መንገድ እነ ስብሃት ነጋን ደስ ባያሰኝም አሁን ግን ኤርትራን ለመታደግ ምንም ምርጫ አይኖራቸውም። ቀጣዩ ስጋታቸው የአማራን የብሄር ድርጅት ንቅናቄ ሲሆን ይህን ንቅናቄ ለማዳከም በከፍተኛ ወጭ ተሰማርተዋል። በሶስተኛ ደረጃ የኦሮሞን ህዝብ በሙስናና በስልጣን በመደለል በስልጣን ላይ ለመቆየት አጥብቀው በመፍጨርጨር ላይ ናቸው።

ስለዚህ የጠቅላይ ሚኒስተር ደሳለኝ በኤርትራ ላይ የሚወጣው አዲሱ የፖሊሲ ለውጥ (የጦርነት እቅድ) ለመላው ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ታስቦ ሳይሆን የወደፊቷን ታላቅዋን ትግራይ ሲመሰርቱ እንቅፋት የሚሆንባቸውን ጠላት በአንደኛ ደረጃ ለማስወገድ የታሰበ ፖሊሲ ነው። የወያኔ መሪዎች በኢትዮጲያ ሰራዊት የሳእቢያን ወታደራዊ ሃይል ካዳከሙ በኋላ በወያኔ ተዛዝ የሚንቀሳቀስ የኤርትራ መንግስትን በመመስረት ለትግራይ ትግርኝት ፈር ቀዳጅ መንግስት ለማስቀመጥ የታሰበ የጦርነት ፖሊሲ እንደሚሆን ይገመታል። የወያኔ መንግስት አዲሱ ፖሊሲ በሃገር ውስጥ የተፈጠረበትን ፖለቲካዊ ቀውስ በውስጣዊ ስሌት የወደፊቷን ታላቅዋን ትግራይን ተጠቃሚ የሚያደርግ አቅጣጫ ቀያሪ ጦርነት በመክፈት በኢትዮጲያ ህዝብ ደም ለመነገድ ያሰቡ ይመስላል። ነገር ግን ይህ መሰሪና ጦረኛ ፖሊሲ ራሱን የቻለ ሌላ ተጎታች ተግዳሮት አለበት።

በመጀመርያ ኤርትራ በተሰጣት ጊዜ መሰረት ላለፉት 15 አመትት በወታደራዊ መሳሪያ ራሷን አጎልብታለች፤ በግብፅና በኢትዮጲያ ያለው የአባይ ግድብ የውሃ አጠቃቀም ምክኒያት ግብጽ ኢትዮጲያን ለማዳከም ማንኛውንም አይነት እርዳታ ለኤርትራ ታበረክታለች። አሁን ደግሞ ግብፅና ኤርትራ በቀይ ባህር ላይ የጋራ ኮማንድ ፖስት ስምምነት አድርገዋል ስለዚህ በተዛዋሪ ሳይሆን በቀጥታ ከኤርትራ ጎን ግብጽ ልትሰለፍ ትችላለች። ከዚህ በተጨማሪ አሁን በአማራ መሬት ስጦታ የኢትዮጵያ አጋር የሆነችው ሱዳን በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ የግብጽና የአረቦች አገልጋይ ከመሆን አያመልጡም። ሶማሊ ላንድ በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ በግብጽ ክንድ ውስጥ መውደቋ አይቀርም። የእርስ በርስ ጦርነት መፈንጫ የሆነው ደቡብ ሱዳን የግብጽ የጦር አውሮፕላን ማእከል ሆኗል። እነዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ተግዳሮቶች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ የወያኔ መሪዎች ከኢትዮጲያ ህልውና ይልቅ በራሳቸው የፖለቲካ ስልጣን ላይ ያተኮሩ ከመሆናቸው የተነሳ ይህን ሁሉ ውጫዊ ውጥረት ለማብረድ እና በጋራ ጠላትን ለመመከት የውስጥ ልዩነትን በማስወገድ እና አገር አቀፍ ፖለቲካዊ እርቅ በማድረግ እና ሰላም በመፍጠር ለሃገር የሚቆረቆሩ መሪዎች አይደሉም። እነዚህ በቁምከሊቢያ፤ ከሶሪያና ከኢራቅ መማር ያልቻሉ አሁንም የኢትዮጲያን ሕዝብ በጠበንጃ እያስፈራሩ ለመግዛት ራሳቸውን ያዘጋጁ መሪዎች ናቸው።

የኢትዮጲያ የክልል ፖለቲካና የፌደራል እስከ መገንጠል ፖሊሲ፤ የክልል ተስፋፊነት እና የደንበር ጦርነቶች የኢትዮጲያ ህዝብ እርስ በራሱ እየተጋደል ይገኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የወያኔ መሪዎችና ፖሊሲያቸው ሌላው የኢትዮጲያ ሕዝብ እንዳያምናቸው ሆነዋል። አሁንም አብዛኛው ኢትዮጲያዊ በአሁኑ የወያኔ አመራሮች የትግራይ ክልል ከኢትዮጲያ ጋር በአንድነት ለመቀጠሏና ላለመቀጠሏ ምንም ዋስትና የላቸውም። ለታላቋ የወያኔ ትግራይ የወደፊት እቅድ አሁን ነብሱን አሳልፎ የሚሰጥ የትኛው የኢትዮጲያ ሰራዊት ነው? የሰራዊቱ አካል የሆኑት የኢትዮጲያ ህዝቦች ፌስ ቡክ እንዳታይ፤ እሳት ቲቪ እንዳታይ፤ ራዲዮ እንዳትሰማ፤ በህብረት እንዳትሰበሰቡ በሚል ማርሻል ህግ የሚያስተዳድርን የወያኔ መንግስት እና ሲመቸው ህገ መንግስት ጠቅሶ ለመገንጠል የተዘጋጀን የማይታመን የወያኔን ድርጅት አምኖ ፊት ለፊት እየተዋጋ የሚሞት ሕዝብ ማን ነው? ማንናውንም ያገባኛል የሚሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች አስወግዶ ራሱ ጠፍጥፎ የፈጠራቸውን ድርጂቶች እየሰበሰበ አይናጭሁን ጨፍኑ እና ሌላ 25 አመት ላሞኛችሁ ለሚል የወያኔ ፓርቲየሚያወጣው የጦርነት ፖሊሲ ለወያኔ ጥቅም የኢትዮጲያን ሕዝብ ቁጥር ለመቀነስ ካልሆነ በስተቀር ለኢትዮጲያ ብሄራዊ ጥቅም የታሰበ ፖሊሲ እንዳልሆነ ማንኛው ኢትዮጲያዊ ሊገነዘበው ይገባል።

በርግጥ ወያኔ በኢትዮጲያ ማእከላዊ መንግስት የበላይነትን ካጣና ጠቅልለው በህግ መንግስቱ አንቀጽ 39:4 መሰረት ቢገነጠሉ ብቻ ለብቻ ብድራቱን የሚበቀላቸው የሻእቢያ ወታደራዊ ሃይል ነው። ይህ ያስፈራቸው የነስብሃት ነጋ ቡድን አሁን የሚያወጡት አዲስ ፖሊሲ በቂ መሳሪያ ካልያዘው ከአማራና ኦሮሞ ይልቅ እስካፍንጫው የታጠቀውን ሻእቢያን መጀመሪያ ማስወገድ ቁጥር አንድ እቅዳቸው ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ የተገለጠ ነው።

ይህ የጦርነት እቅድ ወደ ተግባራዊነት ከተገባ ሁለት የተለያዩ ውጤቶችን ሊያስከትል ይችላል። የመጀመሪያው ወያኔ በኤርትራ ላይ ጦርነት ከጀመረ ጦርነቱን በፍጥነት መጨረስ ስትራቴጅካዊ ግዴታው ነው። ጦርነቱም ምንልባት ድንገተኛና ፈጣን ሊሆን ይችላል። የጦርነቱ መጓተት የወያኔን መንግስት በውስጥ ትልቅ ፈተና ስለሚያመጣበት እንደምንም ተሟሙተው በወያኔ አሸናፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል። የኤርትራ መሸነፍ ለጊዜውም ቢሆን ለወያኔ መንግስት ታላቅ ድልን ይሰጠዋል። ኤርትራን ካሸነፉና አሻንጉሊት መንግስት ካቋቋሙ በፍጥነት የትግራይ ትግርኝትን ፖለቲካዊ፤ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መዋቅር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይመሰርታሉ። ትግራይ ትግርኝትን ከመሰረቱ በኋላ ለወያኔ መሪዎች የመሃል አገር ፖለቲካ ምንም አያስፈራቸውም ቢችሉ በሃይል በበላይነት ይቀጥላሉ ባይችሉ ደግሞ ሃይላቸውን የሚያዞሩት የኢርትራንና የትግራይን ህዝብ አፍኖ በመያዝ እና ህገመንግስቱን በመጥቀስ ያለምንም ስጋት መገንጠል ይችላሉ።

ምንም የጦር መሳሪያ የሌለው አማራና ኦሮሞ አሁን በትግራይ ትግርኝት ላይ የሚያመጣው ምንም አይነት ተፅእኖ አይኖርም። በዚህ ላይ አማራውን ራሱ ወያኔ ይከበዋል። ለኦሮሞው ደግሞ እስካፍንጫው የታጠቀ የሶማሊያ ክልል ልዩ ሃይል ይበቃዋል። በዚህ ላይ በዜሮ የሚወጡት የአማራው ብ አዴንና የኦሮሞው ኦህደድ ናቸው። እነዚህ የትሮጃን ፈረሶች ከሃባቸው ጥቅም ይልቅ በቁጥር እጂግ አናሳ በሆኑ የህውሃት መሪዎች ስውር እቅድ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን ያልተገነዘቡ ወይንም አውቀው የህዝባቸውን ጥቅም አሳልፈው የሰጡ መሪዎች ናቸው።

ሁለተኛው ክስተት ሊሆን የሚችለው የኤርትራ መንግስት በወያኔ ከመደፍጠጥ የሚያድናቸው ሃይል አለ ወይንስ የለም የሚለው ጥያቄ በኤርትራ በኩል መልስ ሲኖረው ነው። ኤርትራ ለአዲሱ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ለውጥ የሚኖራቸው ቅድመ ዝግጂት የሚመለስ ክስተት ነው። የሻእቢያ መንግስት የሚቀጥለው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እጅግ ፈጣንና ፋታ የማይሰጥ ጦርነት እንደሆነ አስቀድመው መገንዘብ አለባቸው። ወያኔ በምንም በልኩ የተራዘመ ጦርነት እንደማያዋጣው ጠንቅቆ ያውቃል። በኤርትራ ለረጂም ቀናቶች የወያኔን ሃይል በመመከት እንኳን ከተከላከለች የወያኔ መሪዎች ታላቅ ኪሳራ ውስጥ ይገባሉ። የክልል ደንበር ጦርነቶችም ይቀጥላሉ ስለዚህ በመሃሉ ከውጭና ከውስጥ ኪሳራ የሚገጥመው የወያኔ ጦር ሊሆን እንድሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።

ምናልባት ግብጾች ለኤርትራ ሕዝብ ካላቸው ፍቅር ተነስተው ሳይሆን የወያኔን የውስጥ ችግር ተንተርሰው ኤርትራን ለማዳን በቀጥታ ጦርነት ሊሳተፉ ይችላሉ። ለግብፆች ጂኦ ፖለቲካ ጠቀሜታ የተፈጠሩት ሻእቢያዎች በወያኔ/ኢትዮጲያ ወታደራዊ ሃይል ሲጠፉ ግብጾች ቆመው የሚል ግምት የለንም። የግብፆች ከኤርትራ ጋር በቀጥታ ጦርነት መሰለፍ ምናልባት በስግብግብነት የተገነባችው መቀሌና ሌሎች ከተሞች በአረቦች ዘመናዊ የጦር አውሮፕላን ኢላማ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። እነዚህ በዘር ፖለቲካ የጦዙት የወያኔ መሪዎች ኢትዮጲያን የጎዱ መስሏቸው እነሱ ራሳቸው በቆፈሩት የዘረኛነት ጉድጓድ ቀስ በቀስ የሚሰጥሙበት ሁኔታዎችን የወያኔ መሪዎች ራሳቸው ፈጥረዋል። ከሁሉ የሚገርመኝ ግን እስካሁን የትግራይ ልሂቃን ይህን ያፈጠጠ የውስጥና የውጭ ፖለቲካዊ ውስብስብነት እያዩና እየሰሙ አንዳቸውም መሪዎቻቸውን አለመቃወማቸው ከፊት ለፊታቸው ያተጋረጠውን ወያኔ ፈጠር ችግር አለመግንዘባቸውን ወይንም ተባባሪነታቸውን ያስረዳል።

በሌላ መልኩ ምናልባት የምዕራብ ትግራይ የወያኔ መሪዎች የነስብሃት ነጋ ቡድን እንደገና የተለሳለሰ አዲስ ፖሊሲ ለመቅረፅ ያስቡ ይሆናል። ምንም እንኳን ከዚህ በፊት በበላይነት የኢትዮጲያን ብሄራዊ ጥቅም በመጉዳት ለኤርትራ የሚያደላ ፖሊሲ እየቀረጹ እስካሁን ድረስ የተጓዙ ቢሆኑም አሁንም አይናቸውን በጨው ታጥበው እንደገና በንግድና በደንበር መካለል አሳበው አሁንም ኢትዮጲያን የሚጎዳ ፖሊሲ ሊከተሉ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን እንዲህ አይነቱን ለኤርትራ የሚያደላ ፖሊሲ መከተል አሁን በአማራውና በኦሮሞው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን ስለሚያስከትል እንደ ባለፈው ዘመን በተጽእኖ የሚፈጥሩት ፖሊሲ ደግሞ በሃገር ውስጥ ተጨማሪ ተቃውሞን ሊያስነሳባቸው ይችላል። ስለዚህ አሁን ለወያኔ ሕውና እና ለወደፊቷ ሪፐብሊክ ትግራይ ሲባል ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም የቆመ በሚመስል ፖሊሲ በኢትዮጲያ ሰራዊት ሻእቢያን ሰራዊት መደምሰስ ነው።

በማጠቃለያም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ ለውጥ የኢትዮጲያን ብሔራዊ ጥቅም ማእከል ያደረገ ሳይሆን የወደፊቷን ታላቅዋን ትግራይ ተግዳሮቶች በቅድሚያ ለመመንጠር የታሰበ እንጂ የኢትዮጲያን ሕዝብ ጥቅም ታሳቢ በማድረግ አይደለም። ስለዚህ በአዲሱ የኤርትራ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድመ ዝግጂት የሻእቢያን መንግስት በወታደራዊ ሃይል በመደምሰስ የወያኔን አሻንጉሊት መንግስት በመመስረት ላይ የታቀደ ሊሆን ይችላል።

የወያኔ ድል አድራጊነት በጊዚያዊነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ በበላይነት እንዲቀጥሉ የሚረዳቸው ሲሆን በረጂም ጊዜ ደግሞ የትግራይ ትግሪኝትን ፖለቲካዊ መዋቅር በፍጥነት ለመፍጠር እና ለመደራጀት ከመጥቀሙም ባሻገር ወያኔዎች በመሃል አገር የሚፈጠረዋልገዛም ባይነት ለወደፊትይ የማያሳስባቸውና የትግራይ ትግርኝትን እቅድ ለመተግበር ያሚያስችል መሰሪ ፖሊሲ ቀርጸው ወደ ጦርነት ለመግባት የታቀደ ፖሊሲ ሊሆን ይችላል።

የወያኔ መሪዎች ከስተት ላይ ሌላ ስሕተት እየሰሩ ከመሄድ እና ለኢትዮጵያ መፈራረስ ለእርስ በርስ ጦርነት ምክኒያት ከመሆን ይልቅ ከዚህ ቀደም እንደነበሩ የኢትዮጲያ መሪዎች እንዳደረጉት ከስልጣን ይልቅ ኢትዮጲያዊነትን በማስቀደም ሀገራዊ እርቅን በማድረግ ሁሉም ብሄር ተከባብሮ የሚኖርባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጲያን ለመፍጠር የሚያስችል ፖሊሲ ብትቀርጹ ለአሁኑና ለሚመጣው ትውልድ ታሪካዊ ስራ ሰርታችሁ ማለፍ ትችሉ ነበር። ከዚህ ቀደም እንኳን ጥይት ጅራፍ አይጮኽም በላችሁ ነገር ግን ብዙ የኢትዮጲያንና የኤርትራን ህዝብ አስጨረሳችሁ አሁን ደግሞ ለአንድ ብሄር ብቻ እና ትግራይ ትግርንትን ብቻ አስባችሁ የጦርነት ፖሊሲ ብትቀርፁ ለዘልዝለም የማያባራ የጦርነት የቤት ስራን ለልጆቻችሁ እያወረሳችሁ መሆኑን ከውዲሁ እናሳስባችኋለን።

ፋሲሎ ዘ-ከንቲባ ጠምሩ    

 Source: http://welkait.com/?p=7571