Tue, 04/04/2017

ገዥው ፓርቲ ግንቦት 2007 ዓ.ም. በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ መቶ በመቶ ድልን ተጐናፅፌያለሁ ብሎ አውጆ መስከረም 2008 ዓ.ም. መንግሥት ቢመሰርትም ጥቂት ወራትን እንኳን በሰላም ማስተዳደር አቅቶት ሀገሪቱ በተቃውሞ መታመስ ጀመረች፡፡
ይህ ሥጋት ያደረባቸው በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንም ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ይገኝ እንደሆን በሚል፤ ገዥውን ፓርቲና ህዝባዊ መሠረት አላቸው ብለው የመረጧቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ አንድ ጠረጴዛ በማቅረብ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄዎች መፍትሄ እንድንፈልግ ጠይቀዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲም በሰላማዊ መንገድ የሚታገል ድርጅት በመሆኑና የህዝብን ጥያቄ ከሚያስመልሱ መንገዶች አንዱ ድርድር ነው ብሎ ስለሚያምን፤ እናደራድር ላሉ አካላት ቀና ምላሽ በመስጠት ይፋዊ ጥሪ እየጠበቀ ባለበት ሰዓት ጥር 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ከኢህአዴግ የድርድር ጥያቄ ቀረበለት፡፡ ኢህአዴግ የድርድሩን ሀሳብ እናደራድር ብለው ከጠየቁ አካላት በመንጠቅ እንደራደር ብሎ መጠየቁ ቢገርመንም ጥሪው ከየትም ይምጣ ከየት ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እስካመጣ ድረስ መሳተፍ አለብን ብለን በማመን በቅድመ ድርድር ሂደቱ ላይ በንቃት ስንሳተፍ ቆይተናል፡፡
ያለፉትን ሁለት ወራት በቅድመ ድርድሩ ሂደት ላይ የቆየን ሲሆን፤ በመጋቢት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በነበረው ውይይት ላይ አደራዳሪ ማን ይሁን? በሚለው ነጥብ ዙሪያ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ከመጣነው 21 (ሃያ አንድ) ፓርቲዎች ውስጥ ሃያችን ድርድሩ በነፃ አደራዳሪ እንዲመራ ስንጠይቅ አንድ ፓርቲ ብቻ ከኢህአዴግ ጋር ተደራዳሪ ፓርቲዎች በዙር ድርድሩን እንዲመሩት የሚል ሃሳብ አቅርቧል፡፡
ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ ያደራድር በሚለው ነጥብ መግባባት ላይ ለመድረስ መጋቢት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ባደረግነው ስብሰባ ኢህአዴግ ከአቋሙ እንደማይነቃነቅ ይፋ አድርጓል፡፡ አንድ ገዥ ፓርቲ ነፃ አደራዳሪ የምትለውን ትንሽ ጥያቄ መልሶ መደራደር

ካልቻለ፤ ለሌሎች ትልልቅ ህዝባዊ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል ብሎ ፓርቲያችን አያምንም፡፡
ሰማያዊ ፓርቲም የቀረበለትን የድርድር ጥያቄ ሲቀበል ከኢህአዴግ ባህርይ በመነሣት ገዥው ፓርቲ ድርድሩን ለፖለቲካ ትርፍ ሊጠቀምበት እንደሚመክር ከመነሻው በግምገማችን ላይ ያስቀመጥን ቢሆንም፤ ድርድሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ችግሮች የመፍትሄ ሀሳቦች የማቅረቢያ መድረክ እንደሚሆንና ሀገርና ህዝብ ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ የሚወጡበት እድል ለመፍጠር የሚረዳ ይሆናል ብለን በማሠብ ነበር፡፡
ፓርቲያችን ቅድመ ድርድሩን በህዝብ የታመነ እንዲሆን እና ለውጥ እንዲያመጣ ገዥው ፓርቲ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞችን በመፍታት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳት እና ለድርድሩ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ወገኖችን በማሳተፍ መልካም እርምጃዎችን እንዲወስድ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ምንም ዓይነት የለውጥ ምልክቶች ካለማሳየቱም በተጨማሪ ዜጐቻችንን እና አባሎቻችንን በሰላም ከሚኖሩበት ቦታ እያፈነ መውሰዱን አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ ሆኖም ቢሆን ተስፋ አድርጐበት የነበረው ይህ ድርድር በኢህአዴግ ግትር አቋም ወደ ሌላ የፓርቲዎች መድረክ ስብሰባ ወርዷል፡፡ በመሆኑም ፓርቲያችን ከዚህ በኋላ ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ በማይመራው ቅድመ ድርድር ሂደቶች ላይ እንደማይሳተፍ ለኢትዮጵያ ህዝብ እያሣወቅን፤ በማንኛውም ጊዜ ገዥው ፓርቲ ሀገራችን ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ተረድቶ የአቋም ለውጥ ካመጣ ፓርቲያችን ሁሌም ለውጥ ለሚያመጣ ድርድር ዝግጁ መሆኑን እንገልፃለን፡፡
መጋቢት 21 ቀን 2009 ዓ.ም.