April 4, 2017

ኢሳት (መጋቢት 25 2009)

አባ ገብረየሱስ የዋልድባ ገዳሙ ለልማት መነካት የለበትም በማለት ሲያሰሙ የቆዩትን ተቃትሞ ተከትሎ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ክትትል ሲደረግባቸው ቆይቶ ከሁለት ወር በፊት ታፍነው መወሰዳቸውን መዘገባቸው ይታወሳል።

ከአንድ ወር በላይ የገቡበት ያልታወቀው አባ ገብረየሱስ ከቀናት በፊት ወደ ማዕከላዊ የምርመራ እስር ቤት መግባታቸው መረጃ እንደደረሰባቸው የዋልድባን እንታደግ ማህበር አባላት የሆኑት አቶ ሳምሶን ታፈሰና አቶ ዳምጠው አየለ ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃልምልልስ አስረድተዋል።

ገዳሙ በልማት ስም መነካት የለበትም በማለት ለአመታት ተቃውሞን ሲያሰሙ የነበሩት መነኩሴ በቁጥጥር ስር በዋሉ ጊዜ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የማህበሩ አባላት አክለው ገልጸዋል።

አባ ገብረየሱስ፣ ገዳሙ መነካት የለበትም ያሉትን አቋም በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ለኢሳት እንዲሁም ለአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው ፕሮግራም ቃለመጠየቆችን ሲሰጡ መቆየታቸው ይታወሳል።

የዋልድባን ገዳም መነኩሴ በጸጥታ ሃይሎች ሲደረግባቸው ከነበረ ክትትል ለማምለጥ ራሳቸውን ለአምስት አመት ያህል ተሰውረው መቆየታቸውም ተመልክቷል።

የዋልድባን እንታደግ ማህበር መነኩሴው በማዕከላዊ የምርመራ እስር ቤት ቆይታቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸምባቸው የሚል ስጋት እንዳደረበት ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ የእምነት ተከታዮች መነኩሴ ለህዝብ እና ለሃይማኖቱ ጥቅም መከበር የከፈሉትን መስዋዕትነት ግምት ውስጥ በመክተት ከጎናቸው እንዲቆምና አጋርነቱን በተለያዩ መልክ እንዲገለጽ የማህበሩ አባላት ጥሪን አቅርበዋል።

የስኳር ኮርፖሬሽን በዋልድባ ገዳም አካባቢ የስኳር ፋብሪካን ለመገንባት በያዘው እቅድ ገዳሙ በልማቱ ስራ እንደሚነካ ለገዳሙ አሳውቆ እንደነበር ይታወሳል። ይህንኑ መረጃ ተከትሎ አባ ገብረየሱስ ለዘመናት የቆየው ገዳም በምንም ሁኔታ ሊነካ አይገባም በማለት በአደባባይ ለመታት ሲያስተጋቡ ቆይተዋል።የአባ ገረየሱስ መታሰርን ተከትሎም 39 መነኮሳት ተመሳሳይ ተቃውሞን ስታካሄዱ ነበር ተብለው በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

By ሳተናው