Wednesday, 05 April 2017 12:30
 በይርጋ አበበ

ከ2008 ዓም ህዳር ወር ጀምሮ ለተከታታይ የሰላም መደፍረስ የገጠመው የኢትዮጵያ ምድር ለበርካታ ዜጎች ህልፈት እና በቃፍ ላይ ላለው የአገሪቱ ኢኮኖሚ መድቀቅም ምክንያት ሲሆን ለገዥው ፓርቲ ኢህአዴግም ሆነ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ተሳትፎ ባላቸው ምሁራንና ፖለቲከኞች ራስ ምታት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህ ችግር ተባብሶም አገሪቱ ወደከፋ እልቂት ሳታመራ ችግሩ በጊዜ መፍትሔ እንዲያገኝ የአገሪቱ ገዥ ፓርቲ ለ21 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጉዳዩ ላይ ድርድርና ውይይት እንዲያደርጉ ጥያቄ አቀረበ። ጥር 3 ቀን 2009 ዓም ለፖለቲካ ፓርቲዎች በተጻፈ ደብዳቤ የተገለጸውም ይኸው ጉዳይ እንደሆነ ደብዳቤው ይገልጻል።

በኢህአዴግ ጥሪ የቀረበላቸው ፓርቲዎቹም ሊካሄድ ስለታሰበው ድርድር የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት መርሆች ላይ ለሰባት ጊዜያት (መድረክ እና መአሕድ ለስድስት ጊዜ ብቻ ነው የተሳተፉት) ውይይት ካደረጉ በኋላ በተለይ “ድርድሩን ሶስተኛ ወገን ይምራው” በሚለው ነጥብ መስማማት ባለመቻላቸው ከመድረክና ከመአሕድ በተጨማሪ ስድስት ፓርቲዎች ራሳቸውን ከድርድሩ ውጭ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ገዥው ፓርቲ በበኩሉ “ድርድሩ በዙር እየተመራ ቢካሄድ ጉዳቱ ምን ላይ ነው?” ሲል ይጠይቅና “አደራዳሪ የምትሉትን ቅድመ ዝግጅት ርሱት ይህን ማድረግ ካልቻላችሁ ግን ጉዟችን እዚህ ላይ ሊቆም ይገባል” ሲል አቋሙን በግልጽ አስቀምጧል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚያደርጉት ድርድር አንዳች ለውጥ አገኛለሁ ብሎ ተስፋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም በሁለቱ ወገኖች አለመግባባት ድርድሩ ሳንካ ተፈጥሮበታል። ለመሆኑ ሁለቱ ወገኖች በዚህ አቋማቸው ከቀጠሉ በአገሪቱ የተፈጠረው ችግር ወዴት ሊያመራ ይችላል ስንል የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያወጧቸውን መግለጫዎችና አመራሮችን ጠይቀን ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረከ (መድረክ) መጋቢት 22 ቀን 2009 ዓም ባወጣው መግለጫ “የኢህአዴግ አገዛዝ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሕገ መንግሥቱና በተለያዩ ህጎችም የተደነገጉትን እና በተለያዩ ወቅቶች ቃል የገባቸውን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አከባበርና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታን ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ፤ በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር በርካታና እጅግ ውስብስብ የሆኑ ችግሮች አጋጥመውናል። ለእነዚህ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በሰላማዊ አግባብ ወቅታዊ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ሰላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሰላማዊ አግባብ ሲጠይቁና ሲታገሉ የቆዩ ቢሆንም፤ ከኢህአዴግ ሰሚ ጆሮ ስለተነፈጉ ችግሮቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱና ይበልጥ እየተወሳሰቡ መጥተው፤ ሀገራችንን በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ከተዋት ይገኛሉ። በዚህም ምክንያት ሀገራችን በአሁኑ ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተዳደር ስር በኮማንድ ፖስት አማካይነት ሁኔታዎችን ሃይል በመጠቀም ለማረጋጋት በሚሞከርበት እጅግ ፈታኝ ወቅት ላይ እንገኛለን” በማለት በአገሪቱ የተከሰተውን ችግር ምክንያት ነው ብሎ ያመነበትን አስቀምጧል።

መድረክ በመግለጫው አያይዞም “የኢህአዴግ አገዛዝ ለሕዝባችን ሰላማዊ የመብት ጥያቄዎች በሕጋዊ አግባብ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ፈንታ በኃይል ለማፈን መንቀሳቀሱና መድረክና ሌሎችም ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምህዳሩን በመዝጋት ኢህአዴግ የፈጠራቸውን ችግሮች በትክክል ነቅሶ በማውጣት ተጨባጭ መፍትሄ ሊያስገኝ የሚያስችል ድርድር ለማካሄድ ለብዙ ዓመታት ሲያቀርቡ ለቆዩት ጥያቄዎች ኢህአዴግ አዎንታዊ ምላሽ ነፍጎ በመቆየቱ ችግሩን እንዲባባስ አድርጎታል” ሲል ይገልጻል። መድረክ ሀቀኛ ተቃዋሚ ሲል የሚገልጸው በምን መመዘኛ ነው ተብለው የተጠየቁት የመድረኩ ኃላፊዎች “በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል በመሆኑን ከኢህአዴግ ጋር የጥቅም ተጋሪ ያልሆኑትን ነው” ሲሉ መልሰዋል።

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር በቅድመ ሁኔታ ባለመስማማት ራሱን ያገለለው ሌላው ፓርቲ ሰማያዊ ነው። ፓርቲው “በነጻና ገለልተኛ አደራዳሪ ያልተመራ ድርድር ለህዝብ ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ አያመጣም” ሲል ያወጣውና ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ “ኢህአዴግ በግንቦት 2007 ዓም በተካሄደው ምርጫ መቶ በመቶ ድል ተጎናጽፌያለሁ ብሎ አውጆ መስከረም 2008 ዓም መንግስት ቢመሰርትም ጥቂት ወራትን እንኳን በሰላም ማስተዳደር አቅቶት ሀገሪቱ በተቃውሞ መታመስ ጀመረች” ሲል የችግሩን መነሻ ይገልጻል። ሰማያዊ ፓርቲ ከድርድሩ መውጣቱን በገለጸበት መግለጫው “አንድ ገዥ ፓርቲ ነጻ አደራዳሪ የምትለውን ትንሽ ጥያቄ መልሶ መደራደር ካልቻለ ለሌሎች ትልልቅ ህዝባዊ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል ብሎ ፓርቲያችን አያምንም። በመሆኑም ፓርቲያችን ከዚህ በኋላ ነጻና ገለልተኛ አደራዳሪ በማይመራው ቅድመ ድርድር ሂደቶች ላይ እንደማይሳተፍ ለኢትዮጵያ ህዝብ እናሳውቃለን” ብሏል። “ሆኖም ገዥው ፓርቲ ኢትዮጵያ ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ተረድቶ የአቋም ለውጥ ካመጣ ፓርቲያችን ሁሌም ለውጥ ለሚያመጣ ድርድር ዝግጁ መሆኑን እንገልጻለን” ሲል አቋሙን ግልጽ አድርጓል። ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር አጠር ያለ ቃለ ምልልስ ያደረጉት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ “እዚህ ውሳኔ ላይ (ከቅድመ ድርድሩ መውጣትን) የደረስነው በስራ አስፈጻሚው ሙሉ ድምጽ ነው” ብለዋል።

“ለሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ችግሮች ትክክለኛ መፍትሔ ለማስገኘት ኢህአዴግ ከሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውጤታማ የሆነ ድርድር ሊያካሂድ ይገባል” በሚል ርዕሰ መግለጫ ያወጣም መድረክ “መድረክ ከነሐሴ 2001 ዓ.ም ጀምሮ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ከሁሉ አስቀድሞ የሀገራችን ተጨባጭ የፖለቲካ ምህዳር ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ውጤታማ ድርድር በማካሄድ ተጨባጭ መፍትሄዎችን ለማስገኘት ሲጠይቅ ቢቆይም፤ ኢህአዴግ ግን በሀገራችን ወቅታዊና ነባራዊ ተጨባጭ የፖለቲካ ችግሮች ላይ በማያተኩሩና ተጨባጭ መፍትሄም በማያስገኙ ጉዳዮች ላይ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ያህል ከአንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በፈጠረው “የጋራ ም/ቤት እየተወያየሁ ነኝ” እያለ ካላአንዳች ተጨባጭ ውጤት እስከ አሁን ቆይቷል። በእነዚህ በከንቱ በባከኑት ጊዜያት የሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ከድጡ ወደ ማጡ እየወረደ በአሁኑ ወቅት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አድርሶን ይገኛል” ብሏል። ፓርቲው አያይዞም “ኢህአዴግ በጠራው የድርድር ቅድመ ዝግጅት ላይ የመተማመኛ እርምጃዎች ኢህአዴግ መውሰድ እንዳለበት” አስታውቆ እንደነበር ገልጿል። መድረክ ያስቀመጠው የመተማመኛ እርምጃ “በዚሁ ድርድር ላይ በግምባር ቀደምትነት ሊሳተፉ የሚገባቸው የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ፤ በሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ላይ እያሉ የታሰሩብን የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራር አባላት በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ይገኙባቸዋል” የሚሉ እንደነበር ገልጾ “ሆኖም ግን ከኢህአዴግ ጋር ስብሰባ ከተጀመረ ወዲህ ከሁለት ወራት በላይ የቆየን ቢሆንም፤ የጠየቅናቸው የመተማመኛ እርምጃዎች እስከ አሁንም ተግባራዊ አለመደረጋቸው በግንኙነቱ ላይ ተስፋ እንዳይኖረን አድርጓል” ብሏል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለቀጣዮቹ አራት ወራት መራዘሙን የተቃወመው መድረክ ምክንያቱን ሲያስቀምጥም “መላውን ህዝባችንን በከፍተኛ የታጠቀ ሰራዊት ተፅዕኖ ስር ተሸማቅቆ እንዲኖር ያስገደደው አዋጅ አሁንም ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙ፤ የመብት ጥያቄ አንስቶ ከፍተኛ መስዋዕት የከፈለውን ህዝብ ቁጣና ምሬት የሚያባብስ እርምጃ እንጂ ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ አይሆንም!” በማለት ነው። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በበኩላቸው “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም በአገሪቱ ያሉ ቸግሮች ከኢህአዴግ አቅም በላይ መሆናቸውን ማሳያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ድርድሩን የገጠመው ሌላ ፈተና

ኢህአዴግ የጠራው የድርድር ሀሳብ ተቃውሞ የገጠመው ከአደራዳሪ ነጻና ገለልተኛ መሆን ብቻ አይደለም። መድረክ ድርድሩ የ22 ፓርቲዎች ስብሰባ ሳይሆን የሁለትዮሽ ወይም ሀሳባቸው ተቀራራቢ የሆኑ ፓርቲዎች በመሪ ተደራዳሪ እንዲደራደሩ የሚል ነው። እንደ መድረክ አቋም የፖለቲካ ድርድር በ22 ፓርቲዎች መካሄዱ “ጉንጭ አልፋ ክርክር” ከመሆን አይዘልም። ይህን አቋሙን በመግለጫ ሲያስታወቅም “መድረክ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ እንደመሆኑ እና በፖለቲካ ምህዳሩ መዘጋት ምክንያት ከፍተኛ በደል በራሱ፤ በመሪዎቹና በአባላቱ ላይ እየደረሰ እንደመሆኑ፤ ከሌሎች መሰል ፓርቲዎች ጋር ወይም ለብቻው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎቹና ኢህአዴግ በጋራ በሚስማሙባቸው አጀንዳዎች ላይ ከቀሩት ፓርቲዎች ጋርም በጋራ ስብሰባ ላይ እየተወያየ፤ ከኢህአዴግ ጋር የሁለትዮሽ ድርድር የማካሄድ መሪ ወይም ተቀዳሚ ሚና እንዲኖረው ባቀረብነው አካሄድ ላይም ኢህአዴግ መስማመት አልፈለገም። በዚህ ስምምነት ላይ መድረስ ሳይቻል ከቀረ በኋላም መድረክ በርካታ ራሱ በቀጥታ ከኢህአዴግ ጋር መደራደር ያለባቸው አስቸኳይና አንገብጋቢ ጉዳዮች እንደመኖራቸው በሁለትዮሽ ለመደራደር ያቀረበው አማራጭ ሃሳብም አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም። ይህ የኢህአዴግ አቋም ድርድሩ በሁለትዮሽ በአስቸኳይ ተካሂዶ ችግሮችን በተጨባጭ ለመፍታት ውጤታማ እንዳይሆን የሚያደርግ ስለሆነ ሲጀምርም ኢህአዴግ የድርድር አጀንዳ እንዳልነበረው ዳግመኛ ማረጋገጫ ነው” በማለት አሰታውቋል።

መድረክ በመግለጫው አክሎም “በዚህ ትክክለኛ የድርድር ባህሪይ በሌለውና ቀደም ሲል ኢህአዴግና አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች መስርተው ከቆዩት “የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት” ከሚባው አካል ውይይት ጋር በሚመሳሰልና ውጤታማ ሊሆን በማይችል የ22 ፓርቲዎች ውይይት ሂደት ውስጥ መቀጠል ተገቢ ሆኖ ስላላገኘነው ከላይ የተጠቀሰውን የሁለትዮሽ የድርድር አማራጭ ለኢህአዴግ አቅርበን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን። በመሆኑም መድረክ ባቀረባቸውና ፈጣንና ተጨባጭ ውጤቶችን ሊያስገኝ የሚችለው የሁለትዮሽ ድርድር በኢህአዴግና በመድረክ መካከል በአስቸኳይ እንዲጀመር በኢህአዴግ በኩል ፈቃደኛነቱ በአስቸኳይ እንዲገልፅ አጥብቀን እንጠይቃለን” ሲል አቋሙን ግልጽ አድርጓል።

ሌሎች ፓርቲዎችስ ምን አሉ?

ኢህአዴግ ድርድሩ ሊካሄድ የሚገባው በነጻና ገለልተኛ አደራዳሪ ሳይሆን ራሳችን ተደራዳረዎቹ በዙር እናደራድር ሲል በድርድሩ ኢህአዴግን ወክለው የቀረቡት አቶ አሰመላሽ ወልደስላሴ እና አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተናግረዋል።

መድረክና ሰማያዊ ቀደም ብለው አቋማቸውን ያሳወቁ ሲሆን የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአሕድ)ም የሁለቱን ፓርቲዎች ዱካ ተከትሎ ያለ አደራዳሪ መደራደር አልፈልግም ሲል አቋሙን ገልጿል። ኢዴፓ፣ መኢአድ፣ ኢብአፓ፣ ኢራፓ እና መኢዴፓ “ያለ አደራዳሪ መደራደር አንፈልግም ሆኖም ከድርድሩ መውጣታቸንንም ሆነ በድርድሩ መቀላችንን የምናሳውቀው በፓርቲያችን ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ መሰረት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በአቶ አየለ ጫሜሶ የሚመራው ቅንጅት፣ አንድነት፣ መኢብን፣ የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ እና ሌሎች ፓርቲዎች ድርድሩን በዙር እየተመሩ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድርድር ቅድመ ዝግጅት ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓም የሚቀጥል ይሆናል። በዚያ እለትም ሰማያዊ መድረክ እና መአሕድ የማይሳተፉ መሆኑን ከአሁኑ አሰታውቀዋል። ድርድሩ ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችልም ወደፊት የምናየው ይሆናል።

ስንደቅ