April 5, 2017

የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን የማሳደዱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል:ሦስት የሰማያዊ ፓርቲ የአማራ ክልል አመራሮች ማዕከላዊ ታሰሩ!!!(በሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የህዝብ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴ) የሰማያዊ ፓርቲ የአማራ ክልል አመራሮችን እያሳደዱ ማሰሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል።በአሳለፍነው ሳምንት ብቻ ሦሥት አመራሮች
*አቶ አዳነ አለሙ የወንበርማ ወረዳ የፓርቲው ሰብሣቢና የ2007 ዓ.ም ምርጫ የክልል ም/ቤት ተወዳዳሪ
*አቶ አዱኛ ካሳው የም/ጎጃም ዞን አስተባባሪ ኮሚቴ አባል
*አቶ ይስማው ዳኘው የእሥቴ ወረዳ የፓርቲው ሰብሳቢና የ2009 ዓ.ም ምርጫ የህ/ተ/ም/ቤት ተወዳዳሪ በማዕከላዊ ታሥረዋል።
1.አዱኛ ካሳው፡-ተወልዶ ያደገው ደቡብ ጎንደር አስቴ ሲሆን ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ይህንን አስከፊ ስርዓት ለመለወጥ በቆራጥነት ታገሏል፡፡በተደጋጋሚ ጊዜ ታስሯል፣ተደብደቧል እንዲሁም ከስራው ተፈነቅሏል፡፡በ2002 ዓ.ም የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ)ን ወክሎ በእስቴ ወረዳ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳዳሪ የነበረ ሲሆን ምርጫ ቦርድ የመኢአድን አመራርነት ቦታ ለህገ ወጦች ሲሰጥ በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ መታገሉን ቀጠለ፡፡ይህ አይበገሬነትና ቆራጥነት ያሳሰበው ኢህአዴግ ይኖርበት ከነበረው ባህር ዳር ከተማ አፍኖ በማምጣት በማዕከላዊ ለእስር ዳርጎታል፡፡
2.አዳነ አለሙ፡- በአንድ ዓመት ውስጥ ከ3 ጊዜ በላይ ታሰሯል፡፡በ2008 ዓ.ም ህዳር ወር ላይ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሽብር ክስ ተመስርቶበት ከ7 ወራት በላይ በግፍ እስር ላይ ቆይቶ ምንም ማስረጃ ስላልተገኘበት በነፃ ተሰናበተ፡፡በነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም በክልሉ ተከስቶ የነበረውን የህዝብ ተቃውሞ ተከትሎ በምዕ/ጎጃም ዞን በወንበርማ ወረዳ ሽንዲ ከተማ ተቃውሞውን አስተባብረሃል በሚል ታስሮ ህዝቡ ፖሊስ ጣቢያ ድረስ በመሄድ ሊያስፈታው ችሏል፡፡ይህንን ሲቃይና መከራ ተቋቁሞ ለህዝብ ነፃነት የሚታገለው አዳነ ለስራ ጉዳይ ከሚኖርበት አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በመሄዱ አምጡት በሚል ባለቤቱ አና መነኩሴ እናቱ ለእስር ተዳርገዋል፡፡በመጨረሻም ከስራ ቦታው ይዘው በማዕከላዊ አስረውታል፡፡
3.ይስማው ወንድሙ፡በደቡብ ጎንደር ዞን አስቴ ወረዳ የሰማያዊ ፓርቲ የወረዳው ሰብሳቢ ነው፡፡በ2007 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ለክልል ምክር ቤት ተወዳዳሪ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በማዕከላዊ በግፍ እስር ላይ ይገኛል፡፡እነዚህ ሰላማዊ ታጋዮች ከተያዙ ጀምሮ በቤተሰቦቻቸውና በጠበቃ እዳይጎበኙ የተከለከሉ ሲሆን ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸውና ጨለማ ቤት ታስረው እንደሚገኙ የማዕከላዊ ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡

ቆንጅት ስጦታው