ሰማያዊ እና መኢአድ አብሮ ለመስራት የትብብር ሰነድ ተፈራረሙ።
ስለትብብሩ አጭር ማብራሪያ ቀርቧል

አብሮ የመሥራት አስፈላጊነቱ በምን ይገለፃል?
1. የሁለቱ ፓርቲዎች አብሮ የመሥራት አስፈላጊነት
1.1. ሁለቱም ፓርቲዎች በሰላማዊ ትግል የኢህአዴግን አገዛዝ አስወግደው በኢትዮጵያ ከቃል በዘለለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገንባት ዜጐችን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ግምት ውስጥ በማስገባት፣
1.2. ለሰላማዊ ትግሉ ፈር ቀዳጅ የሆነው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በአባላቱ ላየ እጅግ የበዛ እስር፣ እንግልት፣ ስደትም ሆነ ግድያ ቢደርስበትም እስከ አሁን ከህዝባዊ አላማው አለማፈግፈጉን በሚገባ በማጤን፣
1.3. ከተቋቋመ አጭር ጊዜ የሆነው የሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ የህዝብን አጀንዳ አንግበው የኢህአዴግን አምባገነናዊ አገዛዝ ፊት ለፊት በመጋፈጥ እጅግ አመርቂና አኩሪ ገድል ያስመዘገቡ ወጣቶችን ያሰባሰበ ፓርቲ መሆኑን በሚገባ በመረዳት፣
በጥቅሉ ሁለቱ ፓርቲዎች ወደ አንድ ቢመጡ የሰላማዊ ትግሉን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ያደርሱታል ከሚል መደምደሚያ በመነሳት ነው፡፡

2. መኢአድና ሰማያዊ አብረው በጋራ ቢሰሩ የሚያገኙት ጥቅም ምንድነው?
2.1. በህዝብ ዘንድ የነበረው ተቀባይነታቸው ሙሉ በሙሉ ይጨምራል፤
2.2. የሰው ሃይል ጥንካሬያቸው ይጨምራል፣
2.3. የገንዘብ አቅማቸው ይዳብራል፣
2.4. የንብረትና ቁሳቁስ ሀብታቸው ያድጋል፣
2.5. ህዝብን በማስተባበር ለሰላማዊ ትግሉ መጠናከር አንድ እርምጃ ወደ ፊት በመጓዝ ወደ ውህደት የሚያደርጉትን ጉዞ ያጠናክራል፣
2.6. ስትራቴጂን፣ እውቀትን፣ ስልትን ከተናጠላዊ አጠቃቀም ወደ ጋራ አጠቃቀም ለማቀናጀት ይችላሉ፣
2.7. የየፓርቲዎችን ደጋፊዎች ወደ አንድነት ማስባሰብ ይችላሉ፣
2.8. ከደጋፊ የሚገኝ ቁሳዊ ምራላዊና ሥነ-ልቦናዊ እገዛ ይጠናከራል፣
2.9. የየፓርቲዎቹ ተናጠላዊ አስተዳደራዊ ተግባር ይማከላል፡፡ በተናጠል የሚያወጡት ወጪም ይቀንሳል፣
2.10. ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ የሚለውና እስከ አሁን ምላሽ ያላገኘው የህዝብ ጥያቄ መልስ ያገኛል፣
2.11. በፓርቲዎች ላይ ያለው ህዝባዊ አመኔታ ይበልጥ ይጨምራል፣
2.12. ከፍተኛ አቅም በመፍጠር የተጠናከረ ድርጅታዊ ሥራ ይሠራሉ፣
2.13. በሁለቱም ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ ምሁራን ወደ አንድ ስለሚሰባሰቡ ከእስከ አሁኑ የተሻለ ጥራት ያለው አመራር ይሰፍናል፣
2.14. ሁለቱም ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር በሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ ውይይትና ክርክር ጠንካራ ተገዳዳሪ ይሆናሉ፣
2.15. በፖለቲካው፣ ኢኮኖሚውና ማኅበራዊ ዘርፍ ዙሪያ ነጥሮ የሚወጣ አታጋይ ፕሮግራም ማዘጋጀት ይችላሉ፣
2.16. በሀገር ቤትም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኙ ደጋፊዎች ዘንድ ቅቡልነታቸው ከእስከ አሁኑ በበለጠ ያድጋል፣
2.17. በምርጫ ወቅት ኢህአዴግን ሊገዳደር የሚችሉ ጡንቻቸው የፈረጠመ አማራጭ ተፎካካሪ ሊሆኑ ይችላሉ፣
3. ይህ የአሁኑ አብሮ የመሥራት ስምምነት እንደእስከ ዛሬዎቹ ስለመፍረሱ ምን ዋስትና አለ?
ይህ የስምምነት ሰነድ ለፊርማ የደረሰው ከሁለቱም ፓርቲዎች በተወከሉ አመቻች ኮሚቴዎች ጥልቅና ዝርዝር ጥናትን በመንተራስ ነው፡፡ በመሆኑም አመቻች ኮሚቴው በጥናቱ፡-
3.1. የሁለቱን ፓርቲዎች ተክለ ሰውነት በጥልቅ ፈትሿል፣
3.2. የሁለቱን ፓርቲዎች አደረጃጀትም በጥልቅ አጥንቷል፣
3.3. የሁለቱን ፓርቲዎች የገንዘብና የሎጂስቲክስ አቅም በጥናቱ ዳሷል፣
3.4. የሁለቱን ፓርቲዎች ህዝባዊ ተቀባይነትም ሆነ ዲፕሎማቲካዊ ግንኙነት በጥናቱ አካትቷል፣
3.5. ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች ከየት እስከ የት እንደሆኑ እና በነማን በኩል ሊከሰቱ እንደሚችሉ ዝርዝር መረጃ አሰባስቧል፣
3.6. የሁለቱን ፓርቲዎች ደንብና ፕሮግራም ፈትሿል፣
እነዚህንና ሌሎች በርካታ ጥናቶችን በዝርዝር ካጠናቀቀ በኋላ ጥንቃቄ በተሞላበት አካሄድ እያስተሳሰረ፤ ሁለቱ ፓርቲዎች፡-
ሀ) ከሚያለያያቸው ይልቅ የሚቃራርባቸው ነገር ሚዛን ስለሚደፋ፣
ለ) አብሮ የመሥራት ሂደቱ በስሜት ላይ ተመስርቶ በጥድፊያ የተከናወነ ሳይሆን እውነታን ተመርኩዞና ጥልቅ ጥናትና ፍተሻን አካትቶ የተሠራ በመሆኑ፣
ሐ) ሊያጋጥሙ ይችላሉ ብሎ በዝርዝር ላወጣቸው ተግዳሮቶችም ቀድሞ የመፍትሄ አቅጣጫ በማመላከቱና ሌሎች ዝርዝር ሁኔታዎችን ባካተተ መልኩ የተከናወነ ስለሆነ
መ) ከዛሬ ጀምሮ እያስተሳሰረ የሚሄደው ግለሰቦችን ሳይሆን የፓርቲዎችን ሲስተም በመሆኑ፣
ይህ ስምምነት ይበልጥ ተጠናክሮ ወደ ውህደት ያመራል እንጂ እንዲሁ በቀላሉ በፍፁም የሚፈርስ ስላለመሆኑ አረጋግጣለሁ፡፡
4. ይህ ከሆነ አብሮ የመሥራት ስምምነቱ ወደ ፊት ወደ የት ያመራል?
4.1. በጥናታችን እንደተዳሰሰው የአመቻች ኮሚቴው ጥናት ጥቃቅን እንከኖችን ሳይቀር ፈትሾ ያለፈ በመሆኑ፣
4.2. ከዚህ የስምምነት ሰነድ ፊርማ ሥነ-ሥርዓት በኋላም ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ሥራዎችን እየሠሩ በተግባር እየተፈታተሹና እየተጠናኑ ስለሚሄዱ፣
4.3. ይህ አብሮ መሥራትም በአባላት መካከል ያለውን መቀራረብ ይበልጥ እያጐለበተው ስለሚሄድ፣
4.4. በዚህ ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸውም ሁለቱም ፓርቲዎች በጥንቃቄና ይበልጥ በመተዋወቅ ላይ የተመሠረተ ከፖለቲካ ጓድነት እስከ ወንድማዊ መተሳሰብ እየዘለቁ ስለሚሄዱ ጥንቅቄ በተመላበት መጠናናት ሁለቱም ፓርቲዎች ተዋህደው አንድ ጡንቻው የፈረጠመ ብቁ ተፎካካሪ ህብረ-ብሄር ፓርቲ ይሆናሉ የሚል አመኔታ ኮሚቴው አለው፡፡

አቶ አዳነ ጥላሁን
የመኢአድ ዋና ፀሐፊ
እና
የአመቻች ኮሚቴ ሰብሳቢ