April 6, 2017


ታይቶ የማይታወቅ ጠላት፤


የኢትዮጵያውያን የነፃነት ትግል “ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” ሆኖ፥ ሕዝቧ ለነፃነት ሲታገል፥ አገሪቱ በዓለም ታሪክ ታይቶ ከማይታወቅ ጠላት ላይ ወደቀች። ወያኔዎችን የማያውቅ ቃሌ የተጋነነ ይመስላል። ግን የየትኛው አገር መሪ ነው እንደ ወያኔዎች የአገሩ ጠላት የሆነ? ሕዝባቸውን የፈጁ መሪዎች እንደነበሩ የማይካድ ነው፤ ግን እነሱ ያጠፉት አገራቸውንና ሕዝባቸውን በመጥላት ሳይሆን፥ ለሀገራቸው ያላቸውን የተሳሳተ ራእይ በሥራ ላይ ለማዋል ሲሞክሩ ነው። የወያኔዎች ራእይ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን የደርግ ራእይ “ትግራይ ትቅደም” በሚል ራእይ መለወጥ ነው። ለዚህ ራእይ ዘጠናውን ሚሊዮን ሕዝብ ስድስት ሚሊዮንን ሕዝብን እንዲያገለግል፥ መስፈሪያውንም የትግራይ መስፋፊያ እያደረጉ ነው። “ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ?” የሚላቸውን ሰው ጤናው እስኪጓደል ያሠቃዩታል። ይኸን ድርሰት በምጽፍበት በአሁኑ ሰዓት እንኳን የወያኔ የፖለቲካ እስረኞች ወህኒ ቤቶችን አስጨንቀውታል። መታሰር ብቻ ሳይሆን፥ ራሳቸውን እስኪስቱ ድረስ ይሰቃያሉ፤ ይሰቀላሉ።

የመለስ ዜናዊና የሙሶሉኒ አነሣሥና ዓላማ አንድ ናቸው። የሙሶሊኒ ራእይ የሮማን የጥንት ክብር ለማስመለስ ሲሆን፥ ለማበልጸግ ደግሞ አፍሪካ ውስጥ ያልተያዘ አገር ፈልጎ የቅኝ ግዛት ወረራውን አካሄደ። የመለስ ዜናዊ ራእይ የአክሱምን ክብር ማስመለስ ሲሆን፥ ትግርኛ የማይናገሩ ኢትዮጵያውያንን ባዳዎች አድርጎ የሰፈሩበትን የኢትዮጵያ ምድር ላቀደው የትግራይ እድገትና ብልጽግና መጠቀሚያ አደረገው። አክሱም የኢትዮጵያ መንግሥት ከተማ አለመሆኗን ሲያስረዳን፥ “ሐውልቶቿ ምናችሁ ናቸው” አለን። ቀይ ባሕር ዳር ላይ የተፈጠረችውንና አራት የባሕር ወደብ የነበራትን ኢትዮጵያ ጠላቶቿ በሄዱበት መንገድ ሄዶ፥ ወደብ አልባ አደረጋት። መርከቦቿን ቸረቸራቸው ወይም በነፃ ለሌላ ቸራቸው።
የወያኔን ልዩ ጠላትነት ያነሣሁት፥ ለድርሰቴ መግቢያ እንዲሆነኝ እንጂ፥ ራሱ መለስ ዜናዊ (ነፍሱን ይማራትና) የነገረንን፥ ጋዜጠኞችና የዓይን ምስክሮች ያሰሙትን፥ የወያኔዎች ሰነድ የያዘውን ለመድገም አይደለም። ብዕሬን ያነሣሁት፥ “ምን ይሻለናል?” ለሚለው ጥያቄ የመሰለኝን መልስ ለመጻፍና መሆን የሚገባውን ለማስታወስ ነው።
ሰላማዊ ትግል፤

ሕዝቡ ነፃነትን ለማግኘት “ሰላማዊ ትግል” የሚባለውን በፓርቲ ተደራጅቶ ከሃያ አምስት ዓመት በላይ ሞከረው። ውጤቱ ወያኔዎችን ጠቀመ እንጂ ሕዝቡ የፈለገውን ነፃነትን አላገኘም። ወያኔዎችን ግን በሁለት መንገድ ጠቅሟቸዋል። አንደኛ፥ ጨቋኝ ገዢ በትጥቅ ትግል ካልሆነ እንደማይወገድ ስለሚያውቁ (እነሱ ያደረጉት ይኸንን ነው) “ሰላማዊ ትግል” የሚባል አጉል ተስፋ ለሕዝብ ሰጥተው ታጥቆ እንዳይቋቋማቸው አደረጉት። ያንንም ቢሆን፥ “መሣሪያ አታንሡ እንጂ የፈለጋችሁን መናገር ትችላላችሁ” ካሉ በኋላ ወንጀላቸው ሲነገር የሚያሠጋቸው መሆኑን ሲያዩ እሱንም ከለከሉ።
ሁለተኛው ጥቅማቸው፥ ሰላማዊ ትግሉ የሕዝብ ድምፅ የሚሆኑትን አሳቢዎች ከሕዝብ ማህል ፈልፍሎ አደባባይ አወጣላቸው፤ ለቃቅመው አሰሯቸው። ከመታፈን ያመለጡትን፥ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” እያሉ ከሀገር እንዲሰደዱ አደረጓቸው። ሰላማዊ ትግል መሸንገያ መሆኑ በይፋ ወጣ።

አማራጩ ትግል፤

ከዚህ በኋላ “በሰላማዊ ትግል ነፃነት ይገኛል” ማለት የችግር ወይም ራስን መደለል፥ ራስን በከንቱ ለሞት ማቅረብ ይሆናል። ስለዚህ፥ ምሥጢሩን የተረዱት መሣሪያ አንሥተዋል። እንኳን ነቃችሁ እላቸዋለሁ። ሆኖም ያለሥጋት አይደለም። ወያኔን በትጥቅ ትግል በየሚፋለሙ መካከል አለመግባባት ይታያል። አለመግባባቱ ካልቆመ፥ ድል አድራጊው (ያውም ሳይዋጋ) ወያኔ ይሆናል።
ድል ሁለት ዓይነት ነው፤ በሂደት ላይ የሚገኝ እና የመጨረሻው ድል። በሂደት ላይ የሚገኘው ድል ውጊያ በተደረገ ቍጥር የወያኔ ሰልፍ ሲመታ ነው። “በእንዲህ ያለ ቀን፥ እንዲህ ያለ ቦታ ላይ ከወያኔ ባንዳዎች ጋር በተደረገው ጦርነት ይኸን ያህል ባንዳ ተገደለ፥ ይኸን ያህል ቈሰለ” ከተባል በሂደት ድል ተገኝቷል።የመጨረሻው ድል ወያኔ ተንኮታኵቶ ሲወድቅ ነው። እስቲ በትጥቅ ትግል ላይ ያላችሁትን አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ ድል ስትነሡ ድሉ ለማን እንደሚሆን የወሰናችሁ ይመስለኛል። ለማን እንዲሆን ነው የወሰናችሁት?

አለመግባባት የሚጀምረው የድሉ ባለቤት ማን እንደሚሆን ባለመስማማት ምክንያት መሆኑ ግልጽ ነው። አንዱ ቡድን “ድሉ የኛ ነው” ካለ፥ ድሉ ወደ ወያኔ ድል ይቀየራል። ድሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ፋሺስቶች ሲሸነፉ ንጉሠ ነገሥቱ ባይመጡ ኖሮ፥ ወይም “ድሉ የኛ ነው” የሚሉ ወገኖች ቢኖሩ፥ በድል አድራጊዎቹ አርበኞች መካከል ችግር ይፈጠር፥ ኢትዮጵያም ከባሰ አደጋ ላይ ትወድቅ ነበር። በድል ባለቤትነት አንጣላ። የድሉ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሆን አምናችሁ በየሃይማኖት መጽሐፋችሁ ተማምላችሁ ታገሉ። መሐላው ከነፃነት ቀን በኋላ ታጋይ ሁሉ ምንም ዓይነት መንግሥታዊ ሥልጣን አለመያዝን ይጨምራል–ታግሎ ድሉን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስረክቦ፥ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተባርኮ፥ የግል ሥራ መያዝ ወይም ጡረታ መግባት።

ድሉን ለሕዝብ ማስረከብ ባህላችን እንጂ አዲስ ሐሳብ አይደለም። አንድ ማስረጃ ከክቡር ጀኔራል ጃገማ ኬሎ ታሪክ ላምጣ፤
ጃገማ አባ ዳማ ጀልዱ ሲደርስ አስራ ሶስት የጣሊያ ወታደሮችን፣ አምስት መቶ ከተለያየ አካባቢ የመጡ ባንዳዎችን በምርኮኝነት ይዞ ወደ ጊንጪ ተመለሰ። ብዙም ሳይቆይ አርበኞችና የአገር ሽማግሌዎች ተሰብስበው መከሩና ጃጌ ጃገማን «አምስት ዓመታት ሙሉ መርተህ፣ ተዋግተህ ለድል አብቅተኸናልና እንድንሾምህ ፍቀድልን» አሉት። «የለም አልፈልግም፤ የምፈልገው ሆኗል፤ ሥራዬ በስሜ ከተጠራ ይበቃኛልብሎ አሻፈረኝ አለ። [ፍቅረ ማርቆስ ደስታ፤ ጃገማ ኬሎ፥ የበጋው መብረቅ (የሕይወት ታሪክ)፥ አዲስ አበባ፥ 2002 ዓ ም፥ ገጽ 94.]

አርበኞችና የአገር ሽማግሌዎች ለጀኔራሉ ያሉት፥ “ለድል አብቅተኸናል” ነው እንጂ “ድል ነሥተሃል” አላሏቸውም። ድሉን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማድረግ ምጽዋት አይደለም። ሕዝብ እንዳለ ጦርነት አይወጣም እንጂ፥ ስንቅ በማቀበል፥ በመጸለይ፥ በውስጥ አርበኝነት በተቻለው መጠን ይሳተፋል።

በአሁኑ ትግል አለመግባባት የተፈጠረው የአማራው ተጋድሎ ማንነቱንና ጡንቻውን በተግባር ማሳየት ሲጀምር ነው። የሚባለው፥ “አማራው በኢትዮጵያዊነት እንጂ በዘር ተደራጅቶ መዝመት አይገባውም” ነው። እዚህ ላይ ያልተብራራ ነገር አለ። በነገድ፥ በጎሳ፥ ተደራጅቶ የፖለቲካ ፓርቲ መሆንና በነገዱ፥ በጎሳው ላይ በጠላትነት የተነሣበትን ኃይል ለመቋቋም በጎሳ፥ በነገድ፥ በአካባቢ መደራጀት እንደ ሰማይና እንደ ምድር የተለያዩ ናቸው። በጎሳና በነገድ ሲደራጁ የምንቃወማቸው፥ “ከኢትዮጵያ ምድር ላይ ድርሻችንን እንውሰድ” ሲሉ ነው እንጂ፥ ተለይተው ሲጠቁ ራሳቸውን ለማዳን ሲደራጁ አይደለም። ሚኒሶታ እኖር በነበረበት ጊዜ የሚሲሲፒ ወንዝ ሞልቶ የሚኒሶታን ሕዝብ እንደሚያሠጋው ሲታወቅ የአገሬው ሕዝብ ከአደጋው ለማምለጥ ቀደም ብሎ ሲተባበር አይቻለሁ። ጥፋቱ ባይተባበሩ ነበር እንጂ፥ መተባበራቸው አድኗቸዋል፤ አስመስግኗቸዋልም። ወያኔዎች፥ አማራውንና የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ለመምታት መወሰናቸውንና ውሳኔያቸውን በሥራ ላይ እያዋሉት መሆኑን አልደበቁም። ታዲያ ይኼ አደጋ ከሚሲሲፒ ውኻ ሙላት የከፋ አይደለምን? የኦርቶዶክሱ ሃይማኖት ለጥፋት ሲዳረግ ኦርቶዶክሳውያን ቀድመው ካልተነሡ፥ እስላሞቹ፥ ጴንጤዎቹ፥ ካቶሊኮቹ በቅድሚያ ሊነሡለት ነው?

የጎንደር ሕዝብ ሲጠቃ፥ ጎንደሬው ዝም ብሎ፥ የኢሉባቦር ሕዝብ ገሥግሦ መጥቶ ሊያድነው ነው?

ትክክሉ ትግል ሁሉም በተመቸው መንገድ ድልን ለኢትዮጵያ ለማበርከት መዝመት ነው። አማራው በተለየ በያዘው መንገድ ትግሉን ለማፋፋም ልዩ ጥሪ አለበት። በአባቶቹ አስተባባሪነት የተገነባችና ጠላትን የመከተች ኢትዮጵያ ስትፈርስ እያየ፥ “ወይ ጉድ” ብሎ አያርፍም። ሃይማኖቱ የመለስ ዜናዊ ጅሃድ ታውጆባታል፤ እስክትጠፋ አይጠብቅም። ለሀገርና ለሃይማኖት መታገል ለአማራ ልጆች አዲስ ነገር አይደለም። ለራሱና ለሃይማኖቱ ቢታገል፥ የድሉ ተጠቃሚው መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።
የትግራይ ሕዝብና ብዙው የደቡብ ሕዝብ ኦርቶዶክስ መሆኑን አንርሳ። ከትግሉ ለመሳተፍ ዕድል ካገኘ ሳይውል ሳያድር ይሳተፋል። የአማራው ሕዝብ ትግል ለዲሞክራሲ እስከሆነ ድረስ፥ ክርስቲያኑ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፥ ጥቅሙ የገባው ሁሉ ይረዳል። ግን ለኢትዮጵያ ተቈርቋሪነት ብዛት ያለው ታላቁ ሕዝብ አማራው ነው። “አማራው በሚያስገኘው ድል እኔም ተጠቃሚ ነኝ” የሚል ሁሉ ይረዳል። ደሙ በአማራ ደም ስር ውስጥ የማይፈስ ኢትዮጵያዊ የለም። በደም ስሩ የአማራ ደም የማይፈስበት ኢትዮጵያዊ የለም።የአማራ የደም ስሙ ኢትዮጵያዊነት ነው። የዘሩ ስሙ ኢትዮጵያዊነት ነው። የጎሳው ስሙ ኢትዮጵያዊነት ነው። ኦርቶዶክሱ በአምላኩ ተማምኖ፥ ቈርጦ ከተነሣ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን እርዳታም ባያገኝ ወያኔን ለማባረር የራሱ አቅም ይበቃዋል። የሚያቅማማውንና በወያኔ ከፋፋይነት ጥቅም ያገኘ የመሰለውን መለማመጥ አያስፈልግም፤ ጥቅሙን ሲያይ አውቆ ይመጣል። ትግሉ ተጀምሯል፤ ዕርፍ ይዞ ወደኋላ አይታይም። በዓለም ዙሪያ የተበተንክ አማራ በዚህ ትግል ሚናህ ምን እንደሆነ ዕወቅና ጥሩኝ ሳትል ያለፈላጊ ተገኝበት።

የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳ።