(ዘ-ሐበሻ) “የበጋ መብረቅ” እየተባሉ የሚወደሱት ጀግናው ሌተናንት ጄኔራል ጃገማ ኬሎ በ96ኛ ዓመታቸው አረፉ::

ከሕይወት ታሪካቸው ለመረዳት እንደተቻለው ሌ/ጀ/ጃገማ ኬሎ የተወለዱት በጥር 20 ቀን 1913 ዓ.ም ነው:: ለቤተሰባቸው የመጨረሻ ልጅ ቢሆኑም ከሁሉም ጎበዝ ብርቱ ነበሩና አባታቸው የቤተሰቡ አለቃ አደረጓቸው:: አባታቸው ጃገማ ገና ሳይወለዱ ለወላጅ እናታቸው ‹‹ልጃችንን ስሙን ጃጋማ ብየዋለሁ›› በማለት ነበር ጃገማ ብለው የጠሯቸው:: “ጃገማ” የአባታቸው የፈረስ ስም ሲሆን በኦሮምኛ ሀይለኛ ማለት ነው:: ሌ/ጀ/ ጃገማ እስኪወለዱ ድረስ የፈረሳቸውን ስም የሚሰጡት ሁነኛ ልጅ አላገኙም ነበር::

የኢጣሊያ ጦር የአድዋ ላይ ሽንፈቱን ሊወጣ ጦሩን እጅግ አግዝፎ ከ40 ዓመት ዝግጅት በኋላ በ1928 በድጋሚ ሀገራችንን ወርሮ ህዝብ ሲፈጅ ሀገሩን ሊታደግ ሁሉም በየፊናው ሲራወጥ በ15 ዓመት ዕድሜ የአባታቸውን ጀብድ ሊደግሙ በዱር ዘምተው ጠላትን አርበድብደዋል። በዚህም “የበጋ መብረቅ” የሚል የጀግና መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል::

ሌ/ጀኔራል ጃገማ ኬሎ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ከነበሩት ሌ/ጀኔራሎች መካከል በህይወት የሚገኙት ብቸኛው ጀኔራል ሲሆኑ አንድ ወንድና አምስት ሴት ልጆች፣ አምስት የልጅ ልጆችና አራት የልጅ ልጅ ልጆችን እንዳፈሩ ስለሳቸው የተጻፉ ታሪኮች ያስረዳሉ::