10/20/2016
በአብርሃም ቀጄላ
ዋሽንግተን ዲሲ

በኦሮምኛ ግእዝ ፊደላትን ስለመጠቀም ተገቢነት

ለዚህ ጽሑፍ ማክንያት የሆነኝ በመምህር ልዑለቃል አካሉ ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች አንዱ የሆነው ኦሮምኛ ቋንቋ መጻፍ ያለበት በግእዝ ፊደል ወይስ በላቲን ፊደል? (ከኢትዮጵያዊ ማንነት አንጻር ለውይይት መነሻእንዲሆን የቀረበ) በሚል ርእስ የቀረበው  ጽሁፍ  ነው።

የግእዝ ፊደላት እንዲተው ሆነ የላቲን ፊደላት መጠቀም  አመጣጡ፣ አነሳሱና መቼቱንና ከነአወሳሰኑ በዝርዝር ከማየታችን በፊት እስኪ በዚያን ጊዜ የነበረውን ተጭባጭና ነባራዊ ሁኔታ ለሙሉ ግናዛቤ ይረዳን ዘንድ አስቀድመን እንመላከት።  የ1984 ዓ/ም የክልሎች አዋጅ ከመውጣቱ ጥቂት ዓመታት ቀደም ሲል በ1981 ዓ/ም/1982 ዓ/ም/  1983 ዓ/ም  በዓለም አቀፍ ደረጃ  በተፈጠረው የሶሽያሊስት ካምፕ በተለይም የሶቤት ሶሻሊስት ሪፕብሊክ መበተን ውጤት በኢትዮጵያም የሶሻሊስት መንግሥት ነኝ ይል የነበረውን የደርግ መንግሥት  ሳላዳከመው በተቃራኒው በካፒታሊስት እና አረብ አገሮች የሚረዱት የተገንጣይ ሻቢያና ሌሎች መሰሎች ከመጠናከራቸውም  በተጭማሪ 1ኛ/ ኢትዮጵያን እንደ አንድ  አገር እንዳትቀጥል  ወይም ለማፍረስ፣ ኢትዮጵያዊነትን ለማዳከም  መጀመሪያ አገሪቱን በብሔር  በብሔር ልዩነት አስታኮ ዝላቂም ሆነ ጊዜያዊ ቅራኔ መፍጠር፤ 2ኛ/ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች  መንግሥት  የነበረውን ደርግን የአንድ ብሔረሰብእ የአማራ ብቻ መንግሥት አስመስሎ  በዚውም  አማራን ማስጠላት፣ ከሌሎች ብሔረ ሰቦችም ጋር  ማጣላት ብሎም ማማታት፤ 3ኛ/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሕዝቦች አብሮነት ወግ አጥባቂ  ስለሆነች እሁንም በተጓዳኝ ሂደት አብሮ ማዳከም  የሚለውን ፍልስፍናቸውን  ያርምዱ ነበር።  በዚህም መሠረት  ወደፊት የእነሱን የመገንጠል  ሀሳብ የሚደግፍና የሚያራምድ ፣በዚያውም እግር መንገዱም ያለውን መንግሥት ለማዳከምና ለማሸነፍ የሚረዳና የሚግዝ  እንደ ኦ.ነ.ግ እና አቦ ኢስላሚያ የመሳሰሉትን  ላይ ላዩን በጸረ ደርግ  ተቃዋሚነት በማስመሰል ሽፋን ጸረ ኢትዮጵያዊነትና የመገንጠል ሀሳብ እንዲያራምዱ አድርገው ነበር።  እንዲያውም ወደ በስተኋላው 1983/84 ዓ/ም ለኢትዮጵያውይን የ100 ዓመት የቤት  ሥራና ጣጣ ሰጥተናቸዋል በማለት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ  በአደባባይ እንደ ዘበቱ በይፋ ይታወቃል።

ይህ ከላይ የተጠቀሰው ተገንጣይ የመፍጠሩና የማገዙ ሁኔታበወያኔ በኩል ከ1982 ዓ/ም ጀምሮ ማለትም ኢ ህ አ ዴ ግ ተመሥርቶ ኅብረ ብሄራዊ ቅርጥ በመያዙ ምክንያት አለዝቦት እንዲያውም እስከነጭራሹ ትቶት  እንደነበረ  በልጽ ታይቷል።

የደርግ መንግሥት ገና በሥልጣን  ላይ  ሳለና ከመውደቁ ቀደም ሲል በሻቢያ የጦር አዝማችነት እና የጦር  ጠቅላይ መሪነት  የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባርና የአቦኢስላሚያ በኢትዮጵያዊነት ያምናሉ ኢትዮጵያዊነትን ይጠብቃሉ ያከራሉ የሚላቸውን ብሔር ብሔረ ሰቦች በጅምላ  ይልቁንም አማራን እንዲሁም ክርስቲያን የሆነውን  ኦሮሞ ጨምሮ በምዕራብ  በኩል በአሶሳ፣ በምስራቅ በኩል በወምበራ አውራጃዎች ሲገድልና  ቤተ ክርስቲያን መስጊድ ሲያቃጥል  እንደ ነበር የታሪክ ሀቅ ነው።

ኢ ህ ዴ  ግ  አዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት  ማለትም ከግንቦት 12 ቀን 1983  ጅምሮና በኋላም ለተወሰኑ ወራቶች በጊዜው  ማንኛውም የመንግሥት  መዋቅር  ወታደራዊም እንዲሁም ማንኛውም የሲቪል  ድርጅቶችና መስሪያቤቶች የልማት ድርጅቶች በተለይም የፖለቲካ ነክ ሕዝባዊ ድርጅቶችና ማኅበራት ሁሉ ፍርክስክሳቸው  የወጣ ከመሆኑም  በስተቀር ሕገወጥ ዘረፋና  ወንጀል ሥጋትና ፍርሀት  የነገሰ በመሆኑ  እነ ደራሲ ማሞ ውድነህና ሌሎችም  የአገር ሽማግሌዎች  በየቤተ ክርስቲያኑ  በተለይም በአዲስ አበባ  ውስጥ ትልቁና  ጥናታዊው የካ ሚካኤል  ምህላ አስይዘው  ሕዝቡን  እግዚኦ  የሚያሰኙበት ጊዜ ነበር።

እንግዲህ  ይህ እንዲ እየሆነ ሳለ የደርግ መንግሥት በመውደቁና  ወያኔም አዲስ አበባ ሲገባ የሻቢያ በርካታ  የጦር የጸጥታ ደህንነት ካድሬዎች ኢትዮጵያን የመበታተን አላማቸውን  እንዳነገቡ ሲገቡ።  ሻቢያዎች የሚረዱትና ኢትዮጵያን የመገንጠል አላማ ያስያዙት እና ያስታጠቁት ኦነግም አብሮ ገብቷል። በዚህ ህግ ሥርአት መንግሥት በሌለበት  ጊዜ ከወር በኋላ ሰኔ 24 ቀን 1983 ዓ/ም ህግ ቢኖርም  ያልተጠናከረበት  የትኛው ማንኛው ገዥና አስተዳዳሪ  መሆኑ በወጉ ባልተለየበት ጊዜና ሻዕቢያ በራሱ መንግሥታዊነት ለኢትዮጵያ  መስሪያቤቶች  መሾም መሻር እና በአዲስ አበባና  በመላው ኢትዮጵያ  ማሰር መሰወር የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ደብዛውን ማጥፋት፣ የተለያዩ የኢትዮጵያን ሀብትና ንብረት በጨለማ በመጫን ከወንጅ ከመተሀራ  ስኳር ፋብሪካዎች ከደብረ ብርሃን  ብርድልብስ ፋብሪካ  ሙሉ ጭነት የተጫኑ ተሳቢ መኪናዎች ከነጭነታቸው መውሰድ ብርቅእና ድንቅ የኢትዮጵያ ታሪክ ቅርሶችን እንደ ራስ አሉላ ጎራዴ የመሰለትን  ወደ ኤርትራ ማጋዝ ሲያካሂድ በበኩሉ  ኦ ነ ግ ከጫፍ ጫፍ  ከዳር እስከ ዳር  ዘረኝነትን ጠባብነትንና ጥላቻን በመንዛት በተለያዩ አካባቢዎች  የ150 ኪሎ ሜትር በማይሞላ ጎዳና  ለምሳሌ  ከሻሼመኔ ዘዋይ  አዲስ አበባ ከ10 ኬላዎች በላይ በማቆም ሕዝቡ ላይ መከራ የወረደበት በራሱ ሠራዊት የተለያዩ ኢትዮጵያዊነትን የሚምኑ  የሌሎች ብሄራትን እና የኦሮሞ ክርስቲያኖችንም ጭምሮ በስፋት ይገድልና ያፈናቅል የነበረበት ጊዜ መሆኑ ያታወቃል።

ለዚህም በ1983 ዓ/ም ሐምሌ 19 ቀን ከሀረር ድሬድዋ የቁልቢ ገብርኤልን አክብሮ  ተመላሽ ከ300 አውቶብስ በላይ ተሳፋሪ  መታገትና  መንገላታት  በከፊልም መቀማት  መዘረፍ ማካሄዱ ይታወቃል።  በድሬድዋ  የተለያዩ ለዘመናት  በድሬ ልዩ መፈቃቀር  አብረው የኖሩ የኦሮሞ፣ የሱማሌ፣  የአማራ፣ የጉራጌ፣  የአደሬ፣  ጉረቤታሞች፣ በኦነግ ዘረኛ ቅስቀሳ ምክንያት የደረሰባቸው መከራ ይታወሳል።

በዚህ ጊዜ በአገራችን ቀደም ሲል የተደረጉ የሕዝብ መብት አፈናዎች ጭቆናዎች  የነበሩ  የኢኮኖሚ  ድቀት የመሰሉት  ሁሉ ለዘመናት  ተጠራቅመው በፈጠሩት  ግንፈላ ቁጣ ስሜታዊነት ግብታዊነት  ማዕበል በተጨማሪ  የፓለቲካ  ግለትና ትኩሳት የፈጠራቸው ተጻራሪ ልዩነቶች ማለትም ለአብነት ያህል፦

  • ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት
  • የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዘር በቋንቋ በባህል በስነ ልቡና በመልክ በተክለ ሰውነት አቋም ፈጽሞ አይመሳሰሉም አይገናኙም
  • ኢትዮጵያ የ 100 ዓመታት ታሪክ ብቻ ነው ያላት
  • ኢትዮጵያ በታሪኳ አንድም ጦርነት አሸንፋ አታውቅም
  • የባንዲራ ጉዳይ
  • የወደቦች በላመብትነት ጉዳይ በተለይ የአሰብ ወደብ ይዞታና መብትነት በአጠቃላይ ሕዝቡ በሙሉ እና በይብልጥም በተለይ ምሁራንን  ግራ አጋብተውና አደናብረው የነበረበት ወቅት ሲሆን በሌላ በኩል አዲስ የወጡ የተፈጠሩ ፍልስፋናዎች የፖለቲካ አመለካከቶች የመገንጠል ጥያቄዎች ያልተለመዱ ያማይታወቁ በመሆናቸው ያለአግባብ ተነጣጥለው ከነባራዊ ተጨባጭ መርህና ሕግ ውጭ ፈጽሞ በሚያሳፍር አይነት ወርዶና ዘግጦ የጎጃም ፈለገ ዮርዳኖስ ( አባይ ወንዝ) አማራ ከሌላው አማራ  ነጻ አውጭ በደቡብም እንዲሁ ከአናሳ ብሄረሰቦች ውስጥም የተወሰኑ ቤተ ዘመዶች ጎሳዎች ነጻ አውጭ ተብለው የመገነጣጠል አባዜ ናኝቶ የነበረበት አደገኛና አጥፊ ጊዜ እንደ ነበር የታየነው።

እንደገናም ለሀገሪቱ አዲስ የሆነውን  የዲሞክራሲ መብት ትርጉም በማዛባት ፒያሳ መሀል ሜዳ ላይ መጸዳዳት የዲሞክራሲ መብቴ ነው የሚባልበት ጊዜ፣ መንገዱን ጎዳናውን ሁሉ ሱቅ ደርድሮ መተላለፊያ ማሳጣት የሰባአዊና ዲሞክራሳዊ መብቴ ነው የሚባልበት ጊዜ የሚያሰኝ ፣ ባላተገባ ጉዳይና ነገር ሁሉ መጮኽና ሥራ መፍታት ወዘተ የዲሞክራሲ መብቴ ነው የሚያስብልበት  ስርዓት የለሽ የፖለቲካ እብደትና ስካር በሀገሪቱ ሙሉ የነገሰበት ጊዜ ነበር። ማንኛውም  የመንደር የመንደር ቀማኛ  ወሮበላ ማንኛውንም ሀብታም  ከበርቴ የተመደበበትን ብር መጠን እንዲያስገባ በቁራጭ ጽሁፍ የሚያዝበት ጊዜ  ነበር።

መንገዱ ሁሉ በሽፍታና በቀማኛ ተሞልቶ ከአዲስ አበባ የተወሰኑ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ለመጓዝ በጭንቅና በአጀብ የሚኬድ የነበረበት ጊዜ  ነበር። በድሬደዋ በሶዶ በመሳሰሉት በጠቅላላው ሀገሪቱ የተለያዩ በርካታ ቦታዎች የተነሱ ግጭቶችና በተለይ ኦነግ በሀረር በአሩሲ በጠቅላላው ሀገሪቱ  የሚደርገው የጀምላ ጭፍጨፋ በአጥጋቢ ደረጃ  ለመቆጣጠር አቅም ያልዳበረበትና  ያልጠነከረበት ወቅትና ጊዜ ከመሆኑም በላይ ባማንኛውም የኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ ውስጥና  የሀገር መከላከል ትግል ጊዜያት ሁሉ እንደዚህ እንደ 1983 ዓ/ም እስከ ግንቦት 1985 ዓ/ም  ድረስ እንደ ነበረውና  እንደ ታየው  የኢትዮጵያ አገር መበታተን እና ሥጋት ፍራቻ ፈጽሞ መያዣ መጨበጫ  ያልነበረው ጊዜ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። ከስኔው 1983 ዓ/ም ሰኔ 24 ኮንፈረንስ ከተመሰረተው የሽግግር መንግሥት ቻርተር  በማስለጠቅ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ  አዋጅ ቁጥር 7 /1984 ዓ/ም ታኅሣስ  ቋንቋ ላይ የተመሰረተ የክልሎች መንግስታት መመሥረቻ አዋጅ በመውጣቱና ይህንኑ በስራ ላይ ለማዋል በሚደረገው ሂደት ላይ ከአዋጁ ቀደም ሲል ከሰኔው 1983 ዓ/ም ቻርተር መነሻ በተቋቋመው የሀድያ ና የጉራጌ ተደማጭ ምሁር የነበሩት  ክቡር የተከበሩ ደክተር ኃይሌ ወልደ ሚካኤል በጊዜው የክልል የክልል ሰባት የሀድያ የከምባታ  የጉራጌ እና የም የቋንቋዎች መገልገያ ፊደል የግእዝ ፊደል እንዲሆን፣ እንዲሁም ከየቋንቋውቹ በተጓዳኝ  የትምህርት መስጫ ቋንቋው የሀገሪቱ የመግባባያ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን  ታግለው  ጥገኛ  ኋላቀር በመባል እየተሰደቡም እየተዋረዱም ችለው ታግሰው በማስወሰናቸው እስከ አሁንም የጉራጌ ሕዝብ  የሀገሪቱ ማዕከላዊ ቋንቋ በሆነው  ይገለገላል። ትልቅ ማስተዋልና ብልህነት ስለ ፈጸሙ  በሕዝቡ እንደ ተመሰገኑ ይኖራሉ።

የሀድያ እና ካምባታን  በተመለከተ በጊዜው የተወካዮች ምክር ቤት  የነበሩት የሽግግር መንግሥት የትምህርት ምኒስቴር ምክትል ምኒስቴር የነበሩት  ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ የኢሕዴግ ቀንደኛ መሪ አባልና ትምህርት ምንስቴር ዋና ተቀዳሜ ምንስቴር የሆኑት  ጉደኛዋ ወይዘሮ ገነት ዘውዴን[1] ጫና በመገመት ዝምታን  በርጠዋል።   በተጫማሪም የካማባታም በተመለከተ አቶተስፋዬ ሀብሳ የተባሉት የሽግግር መንግሥት ዋና ጸሀፊ እንደ ዚሁ ዝምታን መርጠዋል። ሁኖም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ቅጭብለው የሰቀሉትን ቁመው ማውረድ  ያቅታል እንደ ተባለው ታግለው እንዳቃታቸው  አሁንም አለ። ሌላው የክልሉ ምሁር ፕሮፌሰር ላጲሶ ድሌቦ በጊዜው በመቃወማቸው ተሰድበውና ጥገኛ ተብለው እስከ አሁንም መድረክና ፊት ተነስቷቸው ይገኛሉ። ሌሎች በዚያን ጊዜና በበስተኋላው ጀምሮ በየም ፣ በዶርዜ ፣በጋሞጎፋ ብሄሮችም የቋንቋቸው ፊደል በግእዝ ፊደል እንዲሆንላቸው በቋንቋቸውም  በተጎዳኝ  የአገሪቱ የሁሉም የመግባባቢያ ቋንቋ የትምህርት መገልገያ መስጫ ቋንቋ እንዲሆንላቸው እስከ ዛሬና አሁንም በፈደዴሬሽን ምክር ቤት በጠቅላይ ጽ/ቤት እየታገሉ ያሉ መሆናቸው ሲታወቅ  አንዳንዶቹ  ቢቼግራቸው በፌድራል ፍርድ ቤቶች  ክስ መሰርተው እየታገሉ ይገኛሉ።  ከዚህም በስተቀር በሀገሪቱ ውስጥ በሁሉ ትላልቅ ና ትናናንሽ  ከተሞች በአዳማ (ናዝሬት) ወዘተ ከዛን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ  በተደጋጋሚ ሕዝባዊ ጥያቄና ሰልፍ እያቀረቡ አሉ።  ከዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው  በሀገሪቱ የሁሉ መግባባያ ቋንቋ በሚጠቀሙ ክክልሎች  ማለትም፦

  1. በአዲስ አበባ ክክል
  2. በድሬደዋ ክክልል
  3. በጉራጌ ክልል
  4. በቤንሻንጉል ክልል
  5. አምስትኛ በአፋር ክክል የትምህርት ቢሮዎች የተዘጋጁ የትምህርት መጻሕፍት ዋጋ 2 ብር ባቻ የሆነ፤ ለምሳሌ የአራተኛ ክፍል ሳይንስ መጽሀፍ በሌሎች ክክል ( በላቲን ፊደል በሚጠቀሙ ) እስከ 150ብር  የሚሸጥ ብርቅ ነገር እንደሆነ ይታወቃል።

እንግዲህ እንደዚህ ከዚህ እንዳየነው  የነገሮች ማያዣ መጨበጫ ጠፍቶ መላቅጡ በጠፋበት አስሸጋሪ ወቅት ላይ የአዋጅ ቁጥር ሰባትን መሠረት አድርጎ የዘውግ ክልሎቹ በቋንቋቸው ለመገልገል ሲጀምሩ አስቀድሞ በአገሪቱ ሁሉ ሲያገለግል የነበረውን  የግእዝ ፊደል  በምልአትና በተብራራ ገላጭነቱ፦

1ኛ)  በ1967 ዓ/ም ከ15 በላይ በሆኑ በተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች እና ቋንቋ የመሬት አዋጅን ፈትፍቶና ቁልጭ አድርጎ የገለጸ፣

2ኛ) የኢትዮጵያን የመሠረተ ትምህርት ከ25 በላይ ብሄርና ብሔረ ሰቦች ቋንቋዎች በጥራት ይሰጥበት የነበረ፣

3ኛ) የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ሪፕብሊክ መንግሥት ሕገመንግሥት በበርካታ በአብዛኛው ከ45 በላይ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ቋንቋ  የተገለጠበት፣

4ኛ) « የበሪሳ » ታላቁ የኦሮምኛ ጋዜጣ በየእለቱ ለዘመናት በበርካታ ቁጥሮች ሲሰራጭበት የነበረ፣

5ኛ) በ16ኛው ወይም በ17ኛ ክፍለዘመን የቅዱስ ቁርዓን የተጻፈበት፣

6ኛ) በ18ኛ መቶ ክፍለዘመን ከዛሬ 200 ዓመታት በፊት የኦሮምኛ መጽሐፍ ቅዱስ የታተመበት ፣

7ኛ) በርካታ የክርስትና መዝሙራት የተጻፉበት፣

8ኛ) በርካታ የእስልምና ዝክሮች መንዙማዎች የተጻፉበት ፊደል ነው።

በእነዚህና በመሳሰሉት  ብዙዎች ሁሉ ተፈትሾና ተፈትና ብቃቱ የተመሰከረለት ሁኖ ስላለና በተጨማሪም በተላያዩ አገራዊና  ዓለማዊ  በከፍተኛ ደረጃ የቋንቋ ምሁራንና  የቋንቋ ሳይንቲስቶች  በተደረጉ ጥናቶች የግእዝ ፊደል  ያለድርቦሽ ወይም ያለጥንድ  ደባል ፊደል ወይንም  ያለመንታ ፊደል  በነጠላው ድምጽ  ባለቤትነት  በሚገባ የሚያገለግል  ጥናታዊ ፊደል መሆኑ ተረጋግጧል።

በሌላ መበኩልም በህትመት ጎንዮሽ ጉዳይም በላቲን ፊደል ተጠቅሞ ሲታታተም 300 ገጾች የሚፈጅ መጽሐፍ  በግእዝ ፊደል ሲታተም 100 ገጽ ብቻ እንደ ሚፈጅ በናሙና ንጽጽርጥናቶች በተጨባጭ  የመጻሕፍቶቹን  ህትመቶች አቅረበው አሰይተዋል።

1ኛ/ በመሰረቱ ከነበሩን ጠላቶች ሁሉ በላይ የሕዝቦችን እና የአገራችን ጠላት በሆነው ሻብያ በዋናነት በተጨማሪም

በምስራቅ  በቀድሞው ትልቋን  ሱማልያን በእርሷ አቀንቃኞች የሚደገፍና የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦ ነ ግ) ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች፤

2ኛ/ ሻቢያ በሚረዳውና የሱማሌ መንግሥት ታላቋን ሱማሌ ለመፍጠር ከኢትዮጵያ ምስራቅ ግዛት ሕዝቦችንና አገራችንን ቆርጦና ገንጥሎ ለመውሰድ ፈጥሮት በሚደግፈው የኦጋዴን ነጻ አውጭ የተባለው ድርጅት፤ በነገራችን ላይ   የዚህ ድርጅት መሪዎች የሶማልያ ዜግነት ያላቸውና  የሲያድ ባሬ መንግሥት ከፍተኛ ወታደራዊና የሲብል ባለሥልጣኖች ምስራቅ ኢትዮጵያን እስከ ናዝሬት (አዳማ) ድረስ ለመውሰድና  ከሱማሌ ለመደረብ የሚንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው።

3ኛ/ በሻቢያና በኦጋዴን ነጻ አውጭ እንዲሁም በሶማልያ መንግሥት ይረዳ የነበረው በምስራቅ ደጋ ክልል አካባባቢ ሲንቀሳቀስ የነበረው አቦ ኢስላምያ(ጃራ) የተባለ ወግ አክራሪ ድርጅት አማካኝነትና አባሪ ተባባሪ  በመሆን በነዙት ጸረ-አገራዊነት እና ጸረ አብሮነት  ጥቂት የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በወሰዱት የጥላቻ አቋም ግእዝ ፊደል በላቲን ፊደል እንዲለወጥ ሁኗል።   ይህም ሲሆን፦

  • በጊዜው የኦነግ አመራሮች አንድ ሁለት ግለሰቦች በነበረው የግእዝ ፊደል እንዲቀጥል ያቀረቡ ሲሆን ምንም ተደማጭነት ያላገኙ መሆኑ በጊዜው ይወሳ ነበር።
  • በሌላ በኩል ነበር ታዋቂ ተደማጭ  የሆኑና ምራቅ የዋጡ የኦረሞ ተወላጆች እነ ጃጋማ ኪሎ፣ ዋቆ ጉቶና፣ የመቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ (የሶዶ ጅዳ ድርጅት መስራች) የኢትዮጵያ ትምህርት ካሪኩሌም ውስጥ የነበሩ የኦሮሞ ምሁራን የበሬሳ ዋና አዘጋጅ የነበሩ አቶ ኢብራሂም ከሜጫና ቱለማ  ነባር አንጋፋ አባላት በግልጽ በህብረትም በተናጠልም ተቃውሞ በማቅረባቸው እነዚህንና ከፊሎቹን የኢ ሠ ፓ  አባላትና  የኢሠፓ ንክኪዎች ናቸው ያረጁ ያፈጁ ናቸው በማለት ሲያጣጥሏቸው ነበር።  በነገራችን ላይ አንዳችውም እንኳን  የኢሠፓ አባል ያላሆኑና  የደርግ ደጋፊ እንኳን  ያልነበሩ መሆናቸው የተረጋገጠ ሀቅ ነበር።  እኝህመቶ አለቃ ግርማ (በኋላ ፕሬዝዳንት) ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በዚህ ዘመን አመጣሽ የፖለቲካ ጣጣ ውስጥ ማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ተቃዋሚንም ጨምሮ ላማንሳት የሚፈራቸውን መዘዝ ጎታችና ሳቢ የሆኑ አይነኬ ጉዳዮችን  በመቃወም ውሳኔና ፍትህ በመስጠት  ከማንም ግለሰብ ወይም ቡድን በላይ የሚደነቁና የሚመሰገኑ ናቸው።  ለማሳያ ያህል 1ኛ  ባልረጋና ባስፈሪው ዘመን በተለይ በ1983 ዓ/ም- ግንቦት 1995 ዓ/ም ባለው ጊዜ ላይ ካላይ በዚህ ጽሁፍ በተደነገገው አይነት  ለኢትዮጵያዊ ቋንቋ ያላቲን ፊደል መጠቀም ፈጽሞ እንደማይገባ  ተቃውሟቸውንና ምክራቸውን አሰምተዋል።  2ኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (ኢ/ኦ/ቤ/ክ) ፓትርያርክ የነበሩት  አቡነ መርቆሬዎስ ኢሕዴግ በገባ ጊዜ በ1983 ዓ/ም ከሀገር ተሳድደው ወጥተው በምትካቸው፣ በኅይወት እያሉ ፓትርያርክ ስለተሾመባቸው በዘመናት ሲያወዛግብ ቆይቶ በኋላም ተሻሚው አቡነ ጳውሎስ ስለሞቱ የቀድሞው ፓትርያርክ  በመንፈሳዊ ሕጉ መሠረት ከስደት መጥተው በመንበራቸው እንዲቀመጡ የወሰኑ ፍጹም ፍትሀዊና ቅን ፈራጅ ናቸው። 3ኛ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ አሁን በቅርቡ በኦሮምኛ ባሳተመችው  የቅዳሴ  መጻሐፍ ምርቃት ላይ ከግእዝ ፊደል በተጨማሪ  የባእድ የላቲን ፊደል መጠቀሟ ትክክል እንዳልሆነ  መታረም የሚገ።ባው ጉዳይ መሆኑን  በአደባባይ ወቅሰዋል፣ ገስጸዋል።

እስቲ ወደ ርእሰ ነጥባችን  እንመለስና የ ኦ ህ ዴ ድ ን አቋም ስንመለከት፤ በበኩሉ በኢ ህ አ ዴ ግ ውስጥ ያለው የኦሮሞ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት  በጊዜው በኦነግና በአቦ ኢስላምያ በተረጨበት  የድርጅቱ አባሎች የኦሮሞ  ዝርያ አይደለም፤ የኦሮሞ ተወላጆችም አይደሉም፤  ስማቸውን ለውጠው  የኦረሞ  ስም ያደረጉ ትግሬዎችና ወዘተ ናቸው። ኦሮሞን አይወክሉም፤  የደርግ ወታደሮች የወያኔ ምርኮኞች ናቸው በማለት የድርጅቱን አባላት  በሙሉ በየግል ስማቸውን በመጥቀስ  ባደረጉት መርዝኛ እና  አጥፊ ቅስቀሳና የስም መበከል ሳቢያ እምብዛም ተደማጭነት የሌለው ነበር።  ሁኖም አንዳኖዶች እንደ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ያሉ  ወ ዘተ የተቃውሞ ድምጽ አሰምተው የነበረ ቢሆንም አድማጭ ሰሚ አላጋኙም።  የኦሮሞ ሕዝቦች ዲሞክራሳዊ ድርጅት በጊዜው ህልውናውን  ጠብቆ ለማቆየትና የወደፊት ሕዝባዊ አላማውን ላማሳወቅ  ሌት ተቀን ደፋ ቀና የሚልበት አደገኛ ወሳኝ እና ቀውጢ ጊዜ በመሆኑ እና የሻቢያን ግፊት በኢሕአዴግ  ውስጥ  ያሉ የሻቢያ ሰርጎ ገብ ብድንን ቁጣ መፍራትና የራሱንም ያልጠነከረ አቋም በማገናዘብ  ከግምት ውስጥ በማካተት  የጊዜውን ተጨባጭ ሁኔም በማጤን እርጋታን እና ማድፈጥን እንደ ታክቲክ  በመጠቀም ቁጥብ የዝምታ አቋም ወስዷል።የኢ ህ ዲ ግ የውስጥ ስውር  ያሻቢያ  ብድን ዋና  ተጠሪ የነበረው ተስፋዬ ገብረ አብ የተባለው የእፎይታ እና የማለዳ  የኢ ህ ዴ ን  የኢ ህ ዲ ግ መጽሔቶች አዘጋጅ  ዋና የበላይ ተቆጣጣሪ እና ኃላፊ ሹም  ከፍተኛውን  ሚና እንደ ተጫወተ ይታወቃል፤ዛሬም  በሻቢያ ተጠሪነቱ  የኢትዮጵያን ብተና ቀጥሎበታል።

ኦ ህ ዴ ድ በዚያን ጊዜ የነበረውን አቅም ብንመለከት በ1984 ዓ/ም እና በ1985 ዓ/ም የተመሰረተበትን 3ኛ እና 4ኛ ዓመት ለማክበር  መስቀል አደባባይ በጠራው ጥሪና በአካሄደው በዓል ሊያሰልፍ የቻለው ሕዝብ  በጣም ጥቂት እና የድርጅቱን የተለየ ዩኒፎርም የለበሱ ከ60 የማይበልጡ  ቋንቋቸው ኦሮምኝ ጭፈራቸው ጉራጌኛ የሆነ ምንአልባት በአዲስ አበባ  ደቡቡ ግርጌ ያሉ የጌጃ አካባቢ ሰዎች ብቻ ነበሩ።  በአንጻሩ ግን የእርሱን ተፃራሪ ኦ ነ ግ ን ብንመለከት  አገሪቱ ካላት 19 የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ ምንስቴር መስሪያ ቤቶች ከ12 በላይ የያዘ የህብረተ ሰቡን ስስ ስሜት በመጫር የዘር ጥላቻን በመስበክ  የኦ ነ ግ  መርዛማ አስተሳሰብ ጎኖ መሠረት በሌለው ከንቱ ድጋፍ ያበጠበት ጊዜ ነበር።

በዚህም በጊዜው የክልል 4 ፓሬዝዳንት አቶ ሐሰን የተባለውና የኦ ነ ግ  ወኪል የነበረው ቀንደኛው  ዶክተር  ዓለሙ ገምታ በበላይ ኃላፊነት  እንዲሁም  በኢትዮጵያ ታሪክ ከሁሉ በላይ በኢትዮጵያ ጠላትነቷ ዮዲት ጉዲት የተባለችው በጊዜው የትምህርት ምንስቴር 1 ተቀዳሚ ምንስቴር  / ገነት ዘውዴ በበላይ አስፈጻሚነት  የግእዝ ፊደል ተትቶ በላቱን ፊደል እንዲተካ  አድርገዋል።

በርካታ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ  የተደረጉ ጥናቶች አሁንም ዛሬ በግእዝ ፊደል መጠቀም  ቀላላና ለሕዝብ ሳይኮሎጅካል ማኅበራዊና ብሔራዊ ማግባባት እንደ ዚሁም ለመጭው ትውልድ አብሮነት  ተወዳዳሪና መተካያ  አማራጭ የሌለው መፍትሔ  መሆኑንና ይሄው እንዲፈጸም  በበርካታ መረጃዎች እያስደገፉ በማስረዳት ላይ ይገኛሉ።

አሁን ላይ ሆነን በዛሬ መስታዎት ያንን የጨለማ ጊዜ ስናየው እንዴት  የሚያሳፍር  ሁኔታ ውስጥ ማለፋችንን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል።

እናም ዛሬ በሆደ- ሰፊነት አርቆ በማሰብ  እና በማስተዋል ቅንነት በተሞላበት  መንገድ ልብ ገዝቶ ምራቅን ዋጥ አድርጎ  በረጋ ሁኔታዎችን ለማረም  ለማስተካከል  አገራዊ ብሄራዊ  መግባብት ለመፍጠር የሚቻልበት የተደላደለ እርግጠኛ ጊዜው  አሁን  ነው። ያኔ  ቀረ ፣ ያኔ ነበር የሚል የሰነፍ ነገር  ከቶ አይሰራም። ዛሬ ጊዜው ነው፤ አሁን ጊዜው ነው፤የረፈደ ነገር የለም።

ኢ ህ ዲ ግ ከ1987 ዓ/ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከሞላ ጎደል በርካታ ነገሮችን በማረም በማስተካከል  በማደስ አሁን ካለንበት ደረጃ ደርሷል። ለአፍታ  እስቲ አንዳንዶችን ወሳኝ የሆኑትን  ብቻ ለይተን  እንመልከት።

  • ኢትዮጵያ በታሪኳ አንድም ጦርነት አሸነፋ አታውቅም ወያኔ ብቻ ነው ጦርነት አሸንፎ የሚያውቀው በተባለበት ሁኔታ ራሱን ከስህተት አርሞ በ1988 ዓ/ም የአድዋ ጦርነት 100ኛ ዓመት በብሔራዊና በዓለም ደረጃ  ተከበረ።
  • ባንዲራ___________ነው ምንም አይደል እንዳልተባለ አሁን ራሱን ታርሞ በየዐመቱ ይዘከራል የባንዲራ ቀን ይከበራል።
  • የአባት አርበኞች የአሮጌ ኢትዮጵያ አስሳሰብ  ተሸካሚዎዎች ናቸው ተብለው ባለውለተኛነታቸው ለአገር የአፈሰሱት  ደማቸውና የከሰከሱት አጥንታቸው እንዳልተነቀፈ ዛሬ ትርሞ የአባት  አርበኞች  ቀን በልዩና በተሻለ ክብር ይከበራል።
  • 80(ሰማንያ) የማይሞሉ ግለሰቦች ዩኒፎርም አልብሶ የሚኒልክ ሃውልት ይፍረስ እንዳልተባለ  ዛሬ የጀግኖቻችን  ሃውልት  ይታደሳል አዲስም ይሰራል።
  • የኢትዮጵያ ታሪክ 100 ዓመት ብቻነው እንዳልተባለ ታርሞ 2000 ዓመተምህረት  የሚልንየም  ህዳሴ በአል በታላቅ  ድምቀት በዓለም አቀፍ ደረጃ መከበሩንና ከዚያ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የተለመደ  የተከበረ የወግ  አለባበስ የመሳሰሉት ሁሉ ባህሎቻችን መከበር  እየታየ ነው።
  • በሃይማኖትና እምነት  በእኩልነት የጥንት የቀድሞ  ነባር መከባበራችንና ወንድማማችነታችን  ባህላችን ለመመለስ ጥረት ተጀምሯል።  ለአርያነትና ለማሳያ  በስልጢ የምትገኝ  የቅድስት ማርያርያም ቤተ ክርስቲያን  በአክራሪ የስልምና እምነት ተካታዮች ተቃጥላ ሳለ የክልሉ እና የአካባቢው  የእስልምና  እምነት ተከታዮች ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን መዋጮ በማሰባሰብ  በመሳተፍ በበርካታ ሚልዮን  ብር  አሰርተዋል።  ይህም  ዓለም ሁሉ በዚህ ሽብርተኛ ጊዜ ሲታመስ  ሳለ ይሄ ፍጹም ከቶ ለዓለም የሚያስደንቅ  ትንግርት በመሆኑ  በዓለም የሰላምና የአብሮ መኖር  የክብር መዝገብ  የሚመዘገብ ተአምር ነው።  ይሄ ነው የኢትዮጵያውያንን ሕዝቦች  ነባር ባህላችንና ልምዳችን።

የኢትዮጵያ ፊደላት ለኦሮምኛ አይመጥኑም የሚባለው ሀሰት መሆኑን ለማሳየት ሁለት አይነት ሰነዶች እዚችጋ አስቀምጣለሁ፡፡ አንደኛው፣ በአጼ ምንሊክ ዘመን የኖሩት የኦሮሞው ምሁርና ወንጌላዊ የነበሩት ኦናሲሞስ ነሲብ ወደ ኦሮምኛ ከተረጎሙት መጫፈ ቁልቁሎ፣ (መጽሃፍ ቅዱስ) ሁለት ገጾች እና በኢትዮጵያ ፊደላት የተጻፈ ጥንታዊ ብራና ናቸው፡፡ እንግዲህ አንባብያን ልብ በሉ፡፡ መጫፈ ቁልቁሱ የተጻፈው የዛሬ 120 ዐመት ነው፡፡ ያኔ ሙሉ መጽሃፍ ቅዲስ በግዕዝ የኢትዮጵያ ፊደላት ሊጻፍ ከቻለ፣ ዛሬ ለምንደነው የማይቻለው? ቀና መንፈስ ከአለ ይቻላል፡፡ ለማንኛዎም ማረጋገጫዎቹ እነሆ፤-

[1] ወ/ሮ ገነት ዘውዴ በኢትዮጵያ አፍራሽነታቸው በአንደኛ ደረጃ የሚታወቁና በሕዝቡም ዮዲት ጉዲት ተብለው የሚጠሩ ከሁሉ የከፋ የኢትዮጵያ ጠላት  ከመሆናቸው በላይ የግእዝ ፊደል በላቲን ፊደል እንዲተካ ካደረጉት ሰወች አንድዋ  ግምባር መሪ ናቸው።

 

ታዲያ የአፍሪካ ብችኛ ጥንታዊ ፊደል  የሆነውን  የግእዝን  ፊደል ጉዳይ  አስተውሎ  ረጋ ብሎ ለማየት  የሰከነ ጊዜ አሁን ነው፣ አልረፈደም።

እላይ ያሰፈርኳቸውን ሰነዶች የአገኘሁት ከ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ ስለሆነ ሳላመሰግነው አላልፍም፡፡

አብርሃም  ቀጄላ (ዋሺንግተን ዲሲ)

Emaile- asiyefyared@yahoo.com