በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ሰሙነ ሕማማት ማለት የሕማሞት ሰሞን ማለት ነው፡፡ ጌታ አዳምንና የአዳምን ልጆች ለማዳን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ 33 ዓመት ከሦስት ወር ከኃጢአት በስተቀር ሰው የሚሆነውን ሁሉ ሆኖ በምድር ተመላልሶ ካስተማረ በኋላ እራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ሠውቶ እኛን በዳዮቹን ክሶ የመጣበትን የማዳን ሥራውን በፈጸመባት የመጨረሻ ሳምንት (ሰሙንባሉ ሰባት ቀናት የተቀበላቸው እጅግ አሰቃቂ ጸዋትወ መከራዎችን የሚገልጥ ቃል ነው በግእዙ ሰሙነ ሕማማት በአማርኛው የሕማሞች ሰሞን ወይም ሳምንት የሚለው ቃል፡፡ ይህ ሰሞን ከዕለተ ሆሣዕና እሑድ ሦስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ያሉ ቀናትን ያጠቃልላል፡፡

በአጋጣሚ ሆኖ ዘንድሮ በሰሙነ ሕማማት የግዝት በዓል አልዋለም፡፡ አልፎ አልፎ እንዲህ የግዝት በዓል የማይውልበት ሰሙነ ሕማማት ያጋጥማል፡፡ በአብዛኛው ጊዜ ግን በሰሙነ ሕማማት በተለይም ስግደት በታዘዘባቸው ከሰኞ እስከ ዓርብ ባሉ ቀናት በአንደኛው ቀን ላይ የግዝት በዓል ይውላል፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ በዚያ ቀን ይሰገዳልየለም አይሰገድም!” የሚል ውዝግብ በየአብያተክርስቲያኑ ይነሣል፡፡ ይሰገዳል!” የሚሉቱ ወገኖች የፍትሐ ነገሥቱን ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን ጨርሶ በመርሳትና ባለመረዳትም ከጌታ በዓል የሚበልጥ በዓል የለምመንፈሳዊ ተግባርን የሚከለክል ሕግ የለም!” በማለት ባሸነፉበት ደብር ወይም ቤተክርስቲያን ተሰግዶ ሲውል፤ የለም አይሰገድም!” የሚሉቱ ወገኖች ባሸነፉበት ደብር ወይም ቤተክርስቲያን ደግሞ የፍትሐ ነገሥት ድንጋጌዎችን (አንቀጽ 15 እና 19) በመጥቀስ በግዝት በዓላት መስገድ ክልክል እንደሆነ በማስረዳት ስግደቱን የበዓል ስግደት የሚያዘውን አንገት በማዘንበል ብቻ በማድረግ የተቀረውን የጾምና የጸሎት ሥርዓት በመፈጸም ያሳልፋሉ፡፡
ወደፊት ቅድስት ቤተክርስቲያን እንዲህ እንደዛሬው በአላውያን ገዥዎች ተቀፍድዳ ከተያዘችበት ተፈትታ፣ ሥራውን ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ፣ የቤተክርስቲያንን ጥቅም የሚያስቀድም ሲኖዶስና የሊቃውንት ጉባኤ ሲኖራት ቁርጥ ያለ ውሳኔ ልትሰጥባቸው ከሚገቡ ጥቂት የማይባሉ ጉዳዮች አንዱ ይህ ጉዳይ ነው፡፡  ለመሆኑ ግን ስግደት በበዓላት ቀን የሚከለከለው ለምንድን ነውየግዝት በዓላት የተባሉት አምስት ቀናትስ ከሌሎቹ ተለይተው እንዴት ሊመረጡ ቻሉየሚሉትን ጥያቄዎች አስቀድመን መመለስ ይኖርብናል፡፡ ውዝግቡ ለእነኝህ ሁለት ጥያቄዎች በቂ መልስ ለመስጠት ካለመቻል ይመነጫል፡፡ ለእነኝህ ሁለት ጥያቄዎች በቂ መልስ መስጠት ቢቻል ኖሮ የይሰገዳል አይሰገድም ውዝግብ ከቶውንም የሚነሣ ጥያቄ ባልሆነ ነበር፡፡ እስኪ ወደ ጥያቄዎቹ እናምራ፦
ለመሆኑ ስግደት በበዓላት ቀናት የሚከለከለው ለምንድን ነውበነገራችን ላይ ይህ ክልከላ ክርስቶስ በወንጌሉ ላይ ማቴ. 16 ፤ 24-28, ሉቃ. 9 ፤ 23 ላይ እኔን መከተል የሚወድ ራሱን ይጣል ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ!” ባለው ቃል መሠረት ራሳቸውን ጥለው መስቀላቸውን (መከራንተሸክመው ክርስቶስን የተከተሉትን፣ መከራ በመቀበል ክርስቶስ ትቶልን የሔደውን ፈለግና ምሳሌነት 1ኛ ጴጥ. 2 ፤ 21 በመከተል ክርስቶስን የመሰሉትን ሐዋርያው ጳውሎስም ስለ ክርስቶስ ሲሉ ሰውነታቸውን መከራ እንድትቀበል ማድረጋቸውን በገላ. 5 ፤ 24 ላይ የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉት!” በማለት ያደነቃቸውን የእምነት አርበኞችን ማለትም መናንያንን አይመለከትም፡፡
መናንያን በምነና ሕይዎት ውስጥ እንዲያደርጓቸው የታዘዟቸውን የተጋድሎ ተግባራት ወይም ትሩፋት ከአቅም በላይ የሆነ ከባድ ሕመም ካላጋጠማቸውና በእርጅና ምክንያት ካልደከሙ በስተቀር እስከ ዕለተ ሞታቸው ወይም እረፍታቸው ድረስ በዓል ምን ሳይሉ ያለማቋረጥ እንዲያደርጉ ስለታዘዙና በበዓለ ሐምሳውም ሳይቀር ስለሚፈጽሙ ይህ የግዝት ክልከላ ስግደትንም ሆነ ሌላ በበዓል የሚከለከልን ተግባር የምነና ትሩፋቱ ያደረገን መናኝ አይመለከትም፡፡ ግዝቱ የሚመለከተው ሕጋውያንን ወይም ከምነና ውጭ ያለነውን ብቻ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ስግደትን በግዝት በዓላትና በዐበይት በዓላት የከለከለችበት ምክንያት በአጭሩ ሲመለስ ለእግዚአብሔር ቸርነት ምሕረት ጸጋ ስጦታ ብልጫ ለመስጠት ነው፡፡ ቸርነትህ፣ ምሕረትህ፣ ይቅርታህ፣ ጸጋህ ያድነናል እንጅ እኛስ ምንም የጽድቅ ሥራ ብንሠራ ጽድቃችን እንደመርገም ጨርቅ ነውና ጽድቃችን አያድነንም!” በሚለው ትሑት መሠረታዊ አስተምህሮ ምክንያት ቸርነቱን፣ ምሕረቱን፣ ጸጋውን ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ ቸርነቱን ምሕረቱን ጸጋውን በልዩ ሁኔታ ለማክበር ለማድነቅ ለማሰብ፣ ለቸርነቱ ለምሕረቱ ለጸጋው ብልጫ ለመስጠት ሲባል ነው ስግደት መልካምና መንፈሳዊ ተግባር ሆኖ እያለ ቤተክርስቲያን በሌሎች በዓል ባልሆኑት ቀናት ከዓመት እስከ ዓመት በርትተን እንድንሰግድ ያዘዘችውን ስግደት በበዓል ቀናት እንዳናደርግ የከለከለችው፡፡ ገብቷቹሀል አይደልወደ ሁለተኛው ጥያቄ ስናልፍ፦ የግዝት በዓላት የተባሉት አምስት ቀናት ማለትም 129 የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት የሚታሰብበት ዕለት፡፡ 221የአምላክ እናት የቅድስት ድንግል ማርያም እረፍት የሚታሰብበት ዕለት፡፡ 312 የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከአምላክ እየተላከ የሰው ልጆችን ከመከራ ከፈተና የሚታደግበት የሚያድንበትና በአምላኩ ፊት ተንበርክኮ ለፍጥረተ ዓለሙ ምሕረትን የሚለምንበት ዕለት፡፡ እና ሁለቱ ሰንበታት ማለትም እግዚአብሔር ከዓሥርቱ ትዕዛዛቱ አንዱ አድርጎ እንድናከብራት ሥራ እንዳንሠራባት የተናገረላት ቅዳሜ ዘፍ. 20 ፤ 8-11እና ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ ከሞት የተነሣባት እሑድ ማቴ. 28 ፤ 1- 6 ናቸው አምስቱ የግዝት በዓላት የሚባሉት፡፡ 

ጥያቄው እነኝህ በዓላት ከሌሎቹ በዓላት ተለይተው እንዴት ሊመረጡ ቻሉየሚለው ነው፡፡ በርካቶች ሰዎች አባቶችና መምሕራንን ጨምሮ እንዴት ግን የሥላሴ በዓል እያለ፣ የመድኃኔዓለም በዓል እያለ፣ የአማኑኤል በዓል እያለ … እነሱ ቀርተው የእመቤታችንና የቅዱስ ሚካኤል በዓላት የግዝት በዓላት ተደርገው ሊደነገጉ ቻሉ?” ሲሉ የሠለስቱ ምዕትን ምርጫ ትክክለኛነት ሲጠራጠሩ ይስተዋላሉ፡፡ በእግዚአብሔር መንፈስቅዱስ የተቀኙት የቤተክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት የደነገጉት ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ ሊቃውንት እነኝህን በዓላት የታመመን መጠየቂያ፣ የተጣላን ማስታረቂያ፣ የታሰረን መጎብኛ፣ ድሆችን ማጽናኛ፣ ለጋብቻ ሽምግልና መላኪያና ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮችን መፈጸሚያ፣ ወደ እግዚአብሔር ቤት በመሔድ ቃሉን የምሰማባቸው የምንጸልይባቸው እንጂ ሥራ የማይሠራባቸው የዕረፍት ቀናት አድርገው የመረጡበትና የደነገጉበት ምክንያት እግዚአብሔርን በምልዓት ለማክበር ለማመስገን ለማምለክ ሲባል ነው፡፡

እኒህ ሊቃውንት ከወላዲተ አምላክና ከቅዱስ ሚካኤል በዓላት ይልቅ የሥላሴ ወይም የመድኃኔዓለም በዓላት እንደሚበልጡ ጠፍቷቸው አይደለም እነዚያን ትተው እነዚህን የግዝት በዓላት ያደረጉት፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን በምልዓት ለማክበር ለማምለክ ለማመስገን ነው እንጅ፡፡ ይሄም ምን ማለት ነውእግዚአብሔርን ያለ እሱነቱን፣ ህልውናውን፣ ቸርነቱን፣ ጸጋውን፣ ምሕረቱን የገለጸባቸው ነገሮች ማሰብ አይቻልም፡፡ እግዚአብሔር እግዚአብሔር እንደሆነ እንድናውቀውና እንድናመልከው ያደረገን ቸርነቱ ነው፣ ምሕረቱ ነው፣ ማዳኑ ነው፣ ጸጋው ነው፣ ኃያልነቱ ነው፡፡ ያለእነዚህ ባሕርያቱና ድርጊቶቹ እግዚአብሔርን ማወቅና አውቆም ማምለክ አይቻልም፡፡

ስለዚህም እግዚአብሔርን ማወቅና ማምለክ ማለት እነኝህን ነገሮች ማሰብ፣ መዘከር፣ ማክበር፣ ከፍ ከፍ ማድረግ ማለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት 318ቱ ሊቃውንት ቤተክርስቲያን እግዚአብሔርን በምልዓት እንድታከብር ለማድረግ ሲሉ 1ከእግዚአብሔር በዓላት አንዱን ያውም ሰውና እግዚአብሔር አንድ የሆኑበትን የድኅነት መሠረት የተጣለበትን 2ከሰማያውያን በዓላት የዋነኛውን የመላዕክት አለቃን የቅዱስ ሚካኤልን 3ከምድራውያን በዓላት ደግሞ የዋነኛዋን መልዕልተ ፈጣሪ መትሕተ ፈጣሪ የሆነችዋን የወላዲተ አምላክን በዓላት በመምረጥና ከሁለቱ ሰንበቶች ጋር በመጨመር ከራሱ ከባለቤቱ፣ ከሰማያውያኑና ከምድራውያኑ ቸርነቱ፣ ምሕረቱ፣ ጸጋው፣ ኃይሉ የተገለጸባቸውንና እግዚአብሔርን ያወቅንባቸውን ኩነቶች፣ ድንቅ ሥራዎቹን በመዘከር፣ በማሰብ፣ በማክበር፣ በማመስገን እግዚአብሔር በምልዓት እንዲመለክ አደረጉ ደነገጉ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም እነኝህ የግዝት በዓላት ከሌሎቹ በዓላት ተለይተው የተመረጡት እግዚአብሔርን በምልዓት፣ በስፍሐትና በጥልቀት ለማምለክ ሲባል ነው ማለት ነው፡፡ ግልጽ ነው? 318ቱ ሊቃውንት እንዲህ ቀላል መስለዋቹሀልእኛ ስላልገባን ካልሆነ በስተቀር እነሱ የተሳሳቱትና በስሕተት የደነገጉት አንዳችም ነገር የለምሰብሳቢያቸው እግዚአብሔር መንፈስቅዱስ ነውና፡፡ አሁን ወደዚህ ሁሉ ሐተታ ወደከተተን ጥያቄ መልስ እንመለስ፡፡ ጥያቄው ምን ነበር? “በሰሙነ ሕማማት የግዝት በዓል ሲውል ይሰገዳል ወይስ አይሰገድም?” የሚለው ነው፡፡ ልብ ብላቹህት ከሆነ የዚህን ጥያቄ መልስ ከሁለቱ ጥያቄዎች የመጀመሪያውን ጥያቄ በመለስንበት ጊዜ መልሰነዋል፡፡ መልሱም ስግደት በበዓላት ቀን የተከለከለበት ምክንያት እኛ ምን የጽድቅ ሥራ ብንሠራ ጽድቃችን እንደ መርገም ጨርቅ በመሆኑና ይህ ሥራችን ብቻውን ሊያድነን የማይችል በመሆኑ እርኩሰታችንን፣ በደላችንን፣ መተላለፋችንን ሳያስብ ለሚያድነን ቸርነቱ፣ ምሕረቱ፣ ይቅርታው፣ ጸጋው ብልጫ ለመስጠት፣ ለማሰብ፣ ለማክበር፣ ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ ለማመስገን ሲባል ነውና በበዓላት ቀናት ስግደት የተከለከለው የግዝት በዓል በሰሙነ ሕማማት ከሰኞ እስከ ሐሙስም ዋለ ዓርብ የስቅለት ቀን አይሰገድም፡፡ በአንገታችን ብቻ እያዘነበልን አስተብርኮም ሆነ ሙሉ ስግደት ሳናደርግ፡፡ እጹብ ድንቅ የሆነች ቸርነቱን፣ ምሕረቱን፣ ጸጋውን፣ ማዳኑን በማድነቅ፣ በማክበር፣ በማመስገን፣ ከፍ ከፍ በማድረግ ዕለቱን ከስግደት ውጪ ያሉ ሌሎች የጾም የጸሎት ሥርዓቶችን እየፈጸምን እናሳልፋለን እንጅ ስግደት አይሰገድም፡፡

እንዲያው እንኳን የስግደት ፍቅሩ፣ በስግደት ለእግዚአብሔር የመገዛቱ፣ በስግደት እግዚአብሔርን የማምለኩ፣ የማመስገኑ፣ የማክበሩ ፍቅር አደረብን እንጅ ሌሎች ከበዓላት ውጭ የሆኑ በርካታ ቀናት አሉና በእነኛ ቀናት አብዝተን በመስገድ መንፈሳዊ ፍላጎታችንንና ግዴታችንን ማሟላት እንችላለንና በዓመት አንድ ቀን እየመጣን ቀናኢና ለስግደት ፅሙድ በመምሰል በዚህች ዕለት ካልሰገድኩና ካላሰገድኩማ ሞቸ እገኛለሁ!” ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ ከላይ የገለጽኩትን በዓላት የተደነገጉበትን መሠረታዊ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ፣ ሐሳብና ሥርዓትም መጣስ መተላለፍ ነውና ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ አንድ መረሳት የሌለበት ጉዳይ ቢኖር ስግደት በዓል ባልሆነ ቀን በጾም ወቅትም ሆነ ከጾም ውጪ የሚደረግና ይሄንንም የማድረግ ግዴታ እንዳለብን ብዙዎቻችን አንገነዘብም፡፡ ስግደት በተለይም ከጾምና ከጸሎት አይለይም፡፡

የድንግል ልጅ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ያለ ደዌ ያለ ሕማም ሰሙነ ሕማማቱን በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በደስታና በሰላም ያድርሰን አሜን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለ ወላዲቱ ድንግል ወለ መስቀሉ ክቡር አሜን ወአሜንአይኩን ለይኩን!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com